Wednesday, April 22, 2015

ከአይ ኤስ እኩል የማወግዛቸው …

በከበደ ካሳ
አይ ኤስ በፈፀመው ጭፍጨፋ ልቤ በሃዘን ደምቷል፣ ድርጊቱ የተፈፀመው በኢትዮጵያውያን ላይ መሆኑን ስሰማ ደግሞ ሃዘኔን ድርብ አድርጎታል፡፡ እናም ይህን አስነዋሪ ድርጊት በግሌ አወግዘዋለሁ፡፡ ፈጣሪ የሟቾችን ነፍስ በገነት ያኑርልን፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውም መፅናናትን ይስጥልን።
በየትኛውም ሁለተኛ አገር በስደት መኖር በሰላም ወጥቶ በሰላም ስለመግባት ዋስትና አይሰጥም፣ ለሰው ልጅ በማይመጥን ኢሰብዓዊ አያያዝ ስር ሊጥል እንደሚችልም በቅርብ ጊዜያት በደቡብ አፍሪካ፣ በየመን፣ በሳውዲ አረቢያና አሁን በሊቢያ በዜጎቻችን ላይ የተደረጉ ጥቃቶች ማሳያ ናቸው። ነገ በሌሎች የተሻለ ህይወት ፍለጋ ከአገራቸው በተሰደዱ ዜጎቻችን ላይ ላይደገም ምንም ዋስትና የለንም። እናም ወገኖቻችን በያሉበት አገር ከመሰል ጥፋቶች እንዲጠበቁ ፈጣሪ እንዲረዳቸው እፀልያለሁ።
ይህን ሰይጣናዊ እርምጃ በማወግዘው ልክ ታዲያ ሁለት ነገሮችንም አወግዛለሁ፡፡ አንደኛው በማህበራዊ ድረ ገፆች የአይ ኤስን ድርጊት በአብነት በማንሳት በእስልምና እና በክርስትና እምነቶች መካከል ቁርሾ ለመፍጠር የሚተጉትን ነው። አንዳንዶች በዚህ እርምጃ አስታከው ያልተገራ ምላሳቸውን በእስልምና እምነትና በእምነቱ ተከታዮች ላይ ሲያውለበልቡ አይቻለሁ።