Monday, January 19, 2015

የዲያስፖራ ፖለቲካ

በውጭ አገር ያለው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ዲያስፖራ /እዚች ቅርብ ኬንያ በሽግግር ላይ ያሉትም ሳይቀሩ/ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዳሻው ማሽከርከር እንደሚፈልግና እያደረገው እንደሆነም ከአሁን በፊት ሁለት ተጨባጭ ማስረጃዎችን አቅርቤያለሁ፡፡
አንደኛ ከወራት በፊት ግርማ ካሳ የተባለ የአንድነት ፓርቲ ደጋፊ ‹‹አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ /አንድነት/ እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ ካልተዋሃዱ ሽራፊ ዶላር አንልክም›› ማለቱን በተጨባጭ ማስረጃ  አቅርቤላችኋለሁ፡፡
ከዛም ወዲህም የሰሜን አሜሪካ የአንድነት ድጋፍ ማህበር ሰብሳቢ አቶ ግርማይ ግዛው ለአንድነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ለኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው የላከውን ደብዳቤ አስነብቤያችኋለሁ፡፡ ይሄ ሰው ኢንጂነር ሃላፊነታቸው እንዲለቁና ለአዳዲስ አመራሮች እንዲያስረክቡ ትዕዛዝ ያስተላለፈበት የደብዳቤው አንቀፅ እንዲህ ይላል።


“I plead with you for the sake of your legacy and honor as well as for UDJP, step down now and with dignity, honor and the love of the country, please transfer your leadership for a new breed of leaders. You have many unchartered opportunities such as to be a member of the council of elders and advice and mentor many young leaders for years to come like Dr. Hailu Araya”
በግርድፉ ሲተረጎም፤ 
ለክብርዎትና ለዝናዎ እንዲሁም ለፓርቲው ሲሉ ዛሬ ነገ ሳይሉ ከመንበርዎ ይውረዱና ሃላፊነትዎን ለወጣቶች አስተላልፉ፡፡ ከፈለጉ ልክ እንደ / ሃይሉ ሻውል የአዛውንቶች /ቤት አባል ሆነው ወጣቶችን መምከርና መግራት ይችላሉ፡፡እንደማለት ነው፡፡
አሁን ሶስተኛ ማስረጃዬን አቀርባለሁ፡፡ እንደሚታወቀው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አንድነት ፓርቲ ፕሬዝዳንቱ የነበሩትን ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራውን አንስቶ አፈንግጦ የከረመውን በላይ ፍቃዱን ሾሟል፡፡ ኢ/ር ግዛቸው ስልጣኑን የለቀቁት በራሳቸው ፈቃድ እንደሆነም ሲነገር ነበር፡፡ ኢ/ሩ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅም ይህንኑ ቢደግሙትም አንደምታው የሚያሳየው ግን ሳይወዱ በግድ መልቀቃቸውን ነው፡፡ ያም ሆኖ የፅሁፌ ትኩረት ስላልሆነ ወደ ሶስተኛው ማስረጃዬ ልግባ፡፡
ኢ/ር ግዛቸው ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ ባደረጉት በዚህ የመጀመሪያ ቃለ መጠይቃቸው ይሄን የዲያስፖራ ጣልቃ ገብነት ደጋግመው ገልፀውታል፡፡ እርሳቸው ከስልጣን የለቀቅሁበት ዋናው ምክንያት ተቋማዊ አሰራሮችንና የፓርቲውን ሕገ ደንብ በጣሰ መልኩ በቡድን ተፅዕኖ ነው ብለዋል፡፡ ይህን ተፅዕኖ ከአገር ውስጥ የሚመነጭና ከውጭ የሚመጣ ሲሉ ከፍለውታል፡፡ የውጭውን ተፅዕኖ ሲያብራሩም፤
“የአንድነት የድጋፍ ሰጪ ማህበራት በውጪ አገር አሉ፡ እነሱ በእኔ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አድርገዋል፡፡ ኢ- ተቋማዊ፤ ኢ- ደንባዊ በሆነ መንገድ” ብለዋል፡፡
የተፅዕኖውን መገለጫ ሲያብራሩም እንዲህ ነው ያሉት፡፡
“አንድነትን እንደ ኤጀንት የመጠቀም ፍላጎት አላቸው፡፡ በገንዘብ ይረዱናል፤ በዚያ ምክንያት የማዘዝ፤ የአንጋሽነት ሚና ለመጫወት ይሞክራሉ፡፡ ይህንን ደግሞ እኔ አልቀበልም፡፡ እነሱ የፓርቲው ደጋፊ ናቸው እንጂ የወሳኝነት ቦታ ይዘው፤ ግዛቸው ይውጣ፤ እገሌ ይምጣ ሊሉ የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር አይቸልም፡፡ እናም በየሚዲያውና ማህበራዊ ድረ ገፆች ከፍተኛ ዘመቻ ነው ያካሄዱት”
ኢ/ር ግዛቸው እንደሚሉት አንድነት የራሱ የፓርቲ አደረጃጀት አለው፡፡ ፕሬዝዳንቱን የሚያወርደውም ሆነ የሚያወጣው ይሄው አደረጃጀት መሆን አለበት፡፡ በውጭ ያለው አባል ግን ከድጋፍ መስጠት ዘሎ ከስልጣን ልቀቅ የሚል ደብዳቤ ይፅፋል፤ ፒቲሽን ያስፈርማል፤ የገንዘብ ማዕቀብ ያደርጋል ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡
ኢንጂነሩ ከስልጣናቸው ለመልቀቃቸው የሰማያዊ ፓርቲ እጅ እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ያነሳሳቸው ደግሞ አንድነት ፓርቲ በምርጫ 2002 ዋዜማ ያጋጠመው መከፋፈል ነው፡፡ ማንም የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሁኔታ በቅርበት የሚከታተል ፖለቲከኛ እንደሚያስታውሰው በወቅቱ በፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም የተመራ አንድ ቡድን ከእናት ፓርቲው ራሱን ገንጥሎ በመውጣት <<መርህ ይከበር>>፤ <<ዝም አንልም>> የሚሉ ስሞችን ይዞ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡
ይህ ቡድን የፅ/ቤትና ንብረት ይገባኛል ጥያቄ አንስቶ በፕሮፌሰር መስፍን እየተመራ ባምቢስ አካባቢ የነበረውን የአንድነት ፓርቲ ቢሮ በመውረሩ የተነሳ ግጭት ተፈጥሯል፤ የሰው ደምም ፈስሷል፡፡ /ማየት ለፈለገ የቪዲዮ ማስረጃ ማቅረብ እችላለሁ/ እናም ኢንጂነሩ የሚሉት ያኔ ያባረርኳቸው አሁን አባረውኛል ነው፡፡ የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ አይደል የሚባለው፡፡ እርሳቸው ያሉትን እጠቅሳለሁ፡፡
“ይሄ ነገር ሰፋ ባለ መንገድ የታቀደበት ነው ብየ አምናለሁ፡፡ በምርጫ 2002 ዋዜማ አንድነት ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ነበር፤ በተወሰኑ ቡድኖች፡፡ አሁን ሰዎቹ ሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ በምርጫ ዋዜማ አሁንም እንዲህ አይነቱ ፕሮጀክት የተደገመ ይመስለኛል፡፡ ይሄ የእኔ የግል አስተያየት ነው፡፡”
ኢንጂነሩ ለእሳቸው ስልጣን መልቀቅ ምክንያቶች ውስጣዊና ውጫዊ ተፅዕኖዎች አሉ ቢሉም ውስጣዊ ተፅዕኖውም ቢሆን ምንጩ ከውጭ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡
“አገር ውስጥ ያለው ከውጪው ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ትልቁ ችግራቸው ግንኙነታቸው ተቋማዊ ሳይሆን ግለሰባዊ ነው፡፡ እንደዚሁም ቡድናዊ ነው፡፡ የዚያ ነፀብራቅ አገር ውስጥ አለ፡፡ ከእነሱ ጋር የሚገናኙ፤ ፓርቲውን ተቋማዊ ባልሆነ መንገድ ለመምራት የመሞከር ነገር አለ፡፡”
የአንድነት ፓርቲ የቀድሞ ሊቀመንበርን ማዕከል አድርጌ ከላይ እንዳብራራሁት በውጭ ያለው ተቃዋሚ አገር ውስጥ ላሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዶላር ሲልክ አብሮ ፅንፈኛ አመለካከቱን ይልካል፡፡ ያሻውን መሾም፤ ያሻውን መሻር ይፈልጋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹም አሜን ብለው ይቀበላሉ፤ እንቢ ካሉ ደግሞ ዶላሩ ታንቆ ይያዝባቸዋል፡፡ ከውጭ በህገ ወጥ መንገድ በሚያገኙት ገንዘብ ላይ የተንጠለጠሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ታዲያ ይሄኔ ጉሮሯቸው ይታነቅና መንፈራገጥ ይጀምራሉ፡፡ ትንሽ ቢንገራገጩም ቆይተው የተላከላቸውን ትዕዛዝ ይተገብራሉ፡፡ ‹‹እምቢ›› ብሎ ‹‹እሺ›› ለማለት አይነተኛ ምሳሌ አንድነት ፓርቲ ነው፡፡ ከጅምሩ ‹‹አሜን›› ብሎ ትዕዛዙንም ዶላሩንም ለመቀበል ምሳሌ የሚሆነው ደግሞ ሰማያዊ ፓርቲ ነው፡፡
ፅሁፌን የምጨርሰው በአጠቃላይ ለተቃዋሚ ፓርቲ አባሎች በተለይ ደግሞ ለአንድነቶች ሰዋዊ ምክሬን በመለገስ ነው፡፡ አሉን የምትሏቸው ፓርቲዎቻችሁ የፅንፈኛ ዲያስፖራ አሻንጉሊት ሆነዋል፡፡ መሪያችን የምትሏቸውንም የመምረጥና የማውረድ መብት በእጃችሁ አይደለም፡፡ በተደጋጋሚ በማስረጃ አስደግፌ ዲያስፖራው በርቀት መቆጣጠሪያ መሳሪያ ሊዘውራችሁ ይፈልጋል ያልኩትን ብትቀበሉት ይሻላችሁ ይመስለኛል፡፡
ለነገሩ በተለይ አንድነቶች ከመቀበል የተሻለ ምርጫ ያላችሁ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም አለቃችሁ ‹‹ተፅዕኖው ከስልጣኔ አስነስቶኛል›› ሲል ‹‹ተፅዕኖ የለም›› ማለት ኮተታም ተቃዋሚ ካድሬ /ኮተካ/ ያስብላችኋል፡፡ /ዱሮስ ምን ነበርን ብላችሁ እንደማትጠይቁኝ ተስፋ አደርጋለሁ/
በተጨማሪም ኢንጂነሩን ዋሽቷል ወይም ተሳስቷል እንዳትሉ ሌላ ቅርቃር ውስጥ የገባችሁ ይመስለኛል፡፡ እንደምታውቁት ባለፈው አምስት አመራሮች ካፈነገጡ በኋላ ኢንጂነር ግዛቸው መንበሩን ሲያደላድል ከአገር ውስጥ እስከ ውጪ በተዘረጋው የሶሻል ሚዲያ መረባችሁ ‹‹ስልጣን ላይ ሙጭጭ አለ›› እያላችሁ ጥላሸት ስትቀቡት ነበር፡፡ አሁን ስልጣኑን ሲለቅ ደግሞ ‹‹እንዲህ ነው ጀግና አመራር እያላችሁ›› በጥላሸቱ ላይ ቀለም ቀባችሁት፡፡ አሁን ደግሞ ‹‹የውጭ ጣልቃ ገብነት ከስልጣኔ አስነሳኝ፤ እዚህ ያለው ብሔራዊ ም/ቤት፤ ጠቅላላ ጉባዔ፤ የአባላት ጉባዔ፤ ወዘተ… የይስሙላ ነው›› ሲላችሁ ሌላ ጥላሸት ልትቀቡት አትችሉም፡፡ በመገለባበጥ ሃትሪክ እንስራ ካላላችሁ በስተቀር፡፡
እናም አላችኋለሁ፤ ራሳችሁን ሁኑ፡፡
Post a Comment