Tuesday, August 4, 2015

ሲፈርድልን ገለልተኛ፤ ሲፈርድብን…
ምንጮች እንደዘገቡት ዛሬ (12/12/2013) የዋለው የፍርድ ቤት ችሎት በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ባሉ ግለሰቦች ላይ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አስሩ ጥፋተኛ አይደሉም (የቀረበባቸው የአቃቢ ህግ ማስረጃ ጥፋተኛ የሚያሰኛቸው አይደለም) ሲባሉ 19 ያክሉ ደግሞ በተጠረጠሩበት ወንጀል የቀረበባቸው የአቃቢ ህግ ማስረጃ ጥፋተኛ መሆናቸውን በበቂ ሁኔታ የሚያሳይ በመሆኑ እንዲከላከሉ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል፡፡ ይህን ዜና የአክራሪ ሃይሉ ገፆች <<ሰበር ዜና>> በሚል እየተቀባበሉት ነው፡፡ እኔን የገረመኝ ግን አዘጋገባቸው ነው፡፡ (በምስሉ ላይ ስክሪን ሾት የተደረገውን ያገናዝቡ።)

"በኢትዬጲያ ሙስሊሞች ላይ መንግስት የጥፋተኘነት ውሳኔ አስተላለፈ" አሉ፡፡

ግን ለመሆኑ በምን አይነት ስሌት ነው እነዚህ ተጠርጣሪዎች ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጋር አንድና ያው የሆኑት፡፡ ማንን እንደሚወክሉ አናውቅም እንዴ? እኔ ነኝ ያለ (የአሸብር በላይን ሙዚቃ ማለቴ አይደለም) እስኪ በእነዚህ ሙስሊሞች ላይ የተወሰነ ውሳኔ በመላው የኢትዮጵያ መስሊሞች ላይ የተወሰነ ውሳኔ መሆኑን በሎጂክ ያስረዳኝ፡፡

Wednesday, April 22, 2015

ከአይ ኤስ እኩል የማወግዛቸው …

በከበደ ካሳ
አይ ኤስ በፈፀመው ጭፍጨፋ ልቤ በሃዘን ደምቷል፣ ድርጊቱ የተፈፀመው በኢትዮጵያውያን ላይ መሆኑን ስሰማ ደግሞ ሃዘኔን ድርብ አድርጎታል፡፡ እናም ይህን አስነዋሪ ድርጊት በግሌ አወግዘዋለሁ፡፡ ፈጣሪ የሟቾችን ነፍስ በገነት ያኑርልን፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውም መፅናናትን ይስጥልን።
በየትኛውም ሁለተኛ አገር በስደት መኖር በሰላም ወጥቶ በሰላም ስለመግባት ዋስትና አይሰጥም፣ ለሰው ልጅ በማይመጥን ኢሰብዓዊ አያያዝ ስር ሊጥል እንደሚችልም በቅርብ ጊዜያት በደቡብ አፍሪካ፣ በየመን፣ በሳውዲ አረቢያና አሁን በሊቢያ በዜጎቻችን ላይ የተደረጉ ጥቃቶች ማሳያ ናቸው። ነገ በሌሎች የተሻለ ህይወት ፍለጋ ከአገራቸው በተሰደዱ ዜጎቻችን ላይ ላይደገም ምንም ዋስትና የለንም። እናም ወገኖቻችን በያሉበት አገር ከመሰል ጥፋቶች እንዲጠበቁ ፈጣሪ እንዲረዳቸው እፀልያለሁ።
ይህን ሰይጣናዊ እርምጃ በማወግዘው ልክ ታዲያ ሁለት ነገሮችንም አወግዛለሁ፡፡ አንደኛው በማህበራዊ ድረ ገፆች የአይ ኤስን ድርጊት በአብነት በማንሳት በእስልምና እና በክርስትና እምነቶች መካከል ቁርሾ ለመፍጠር የሚተጉትን ነው። አንዳንዶች በዚህ እርምጃ አስታከው ያልተገራ ምላሳቸውን በእስልምና እምነትና በእምነቱ ተከታዮች ላይ ሲያውለበልቡ አይቻለሁ።

Monday, January 19, 2015

የዲያስፖራ ፖለቲካ

በውጭ አገር ያለው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ዲያስፖራ /እዚች ቅርብ ኬንያ በሽግግር ላይ ያሉትም ሳይቀሩ/ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዳሻው ማሽከርከር እንደሚፈልግና እያደረገው እንደሆነም ከአሁን በፊት ሁለት ተጨባጭ ማስረጃዎችን አቅርቤያለሁ፡፡
አንደኛ ከወራት በፊት ግርማ ካሳ የተባለ የአንድነት ፓርቲ ደጋፊ ‹‹አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ /አንድነት/ እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ ካልተዋሃዱ ሽራፊ ዶላር አንልክም›› ማለቱን በተጨባጭ ማስረጃ  አቅርቤላችኋለሁ፡፡
ከዛም ወዲህም የሰሜን አሜሪካ የአንድነት ድጋፍ ማህበር ሰብሳቢ አቶ ግርማይ ግዛው ለአንድነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ለኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው የላከውን ደብዳቤ አስነብቤያችኋለሁ፡፡ ይሄ ሰው ኢንጂነር ሃላፊነታቸው እንዲለቁና ለአዳዲስ አመራሮች እንዲያስረክቡ ትዕዛዝ ያስተላለፈበት የደብዳቤው አንቀፅ እንዲህ ይላል።


“I plead with you for the sake of your legacy and honor as well as for UDJP, step down now and with dignity, honor and the love of the country, please transfer your leadership for a new breed of leaders. You have many unchartered opportunities such as to be a member of the council of elders and advice and mentor many young leaders for years to come like Dr. Hailu Araya”
በግርድፉ ሲተረጎም፤ 
ለክብርዎትና ለዝናዎ እንዲሁም ለፓርቲው ሲሉ ዛሬ ነገ ሳይሉ ከመንበርዎ ይውረዱና ሃላፊነትዎን ለወጣቶች አስተላልፉ፡፡ ከፈለጉ ልክ እንደ / ሃይሉ ሻውል የአዛውንቶች /ቤት አባል ሆነው ወጣቶችን መምከርና መግራት ይችላሉ፡፡እንደማለት ነው፡፡
አሁን ሶስተኛ ማስረጃዬን አቀርባለሁ፡፡ እንደሚታወቀው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አንድነት ፓርቲ ፕሬዝዳንቱ የነበሩትን ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራውን አንስቶ አፈንግጦ የከረመውን በላይ ፍቃዱን ሾሟል፡፡ ኢ/ር ግዛቸው ስልጣኑን የለቀቁት በራሳቸው ፈቃድ እንደሆነም ሲነገር ነበር፡፡ ኢ/ሩ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅም ይህንኑ ቢደግሙትም አንደምታው የሚያሳየው ግን ሳይወዱ በግድ መልቀቃቸውን ነው፡፡ ያም ሆኖ የፅሁፌ ትኩረት ስላልሆነ ወደ ሶስተኛው ማስረጃዬ ልግባ፡፡
ኢ/ር ግዛቸው ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ ባደረጉት በዚህ የመጀመሪያ ቃለ መጠይቃቸው ይሄን የዲያስፖራ ጣልቃ ገብነት ደጋግመው ገልፀውታል፡፡ እርሳቸው ከስልጣን የለቀቅሁበት ዋናው ምክንያት ተቋማዊ አሰራሮችንና የፓርቲውን ሕገ ደንብ በጣሰ መልኩ በቡድን ተፅዕኖ ነው ብለዋል፡፡ ይህን ተፅዕኖ ከአገር ውስጥ የሚመነጭና ከውጭ የሚመጣ ሲሉ ከፍለውታል፡፡ የውጭውን ተፅዕኖ ሲያብራሩም፤
“የአንድነት የድጋፍ ሰጪ ማህበራት በውጪ አገር አሉ፡ እነሱ በእኔ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አድርገዋል፡፡ ኢ- ተቋማዊ፤ ኢ- ደንባዊ በሆነ መንገድ” ብለዋል፡፡
የተፅዕኖውን መገለጫ ሲያብራሩም እንዲህ ነው ያሉት፡፡
“አንድነትን እንደ ኤጀንት የመጠቀም ፍላጎት አላቸው፡፡ በገንዘብ ይረዱናል፤ በዚያ ምክንያት የማዘዝ፤ የአንጋሽነት ሚና ለመጫወት ይሞክራሉ፡፡ ይህንን ደግሞ እኔ አልቀበልም፡፡ እነሱ የፓርቲው ደጋፊ ናቸው እንጂ የወሳኝነት ቦታ ይዘው፤ ግዛቸው ይውጣ፤ እገሌ ይምጣ ሊሉ የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር አይቸልም፡፡ እናም በየሚዲያውና ማህበራዊ ድረ ገፆች ከፍተኛ ዘመቻ ነው ያካሄዱት”
ኢ/ር ግዛቸው እንደሚሉት አንድነት የራሱ የፓርቲ አደረጃጀት አለው፡፡ ፕሬዝዳንቱን የሚያወርደውም ሆነ የሚያወጣው ይሄው አደረጃጀት መሆን አለበት፡፡ በውጭ ያለው አባል ግን ከድጋፍ መስጠት ዘሎ ከስልጣን ልቀቅ የሚል ደብዳቤ ይፅፋል፤ ፒቲሽን ያስፈርማል፤ የገንዘብ ማዕቀብ ያደርጋል ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡
ኢንጂነሩ ከስልጣናቸው ለመልቀቃቸው የሰማያዊ ፓርቲ እጅ እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ያነሳሳቸው ደግሞ አንድነት ፓርቲ በምርጫ 2002 ዋዜማ ያጋጠመው መከፋፈል ነው፡፡ ማንም የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሁኔታ በቅርበት የሚከታተል ፖለቲከኛ እንደሚያስታውሰው በወቅቱ በፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም የተመራ አንድ ቡድን ከእናት ፓርቲው ራሱን ገንጥሎ በመውጣት <<መርህ ይከበር>>፤ <<ዝም አንልም>> የሚሉ ስሞችን ይዞ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡
ይህ ቡድን የፅ/ቤትና ንብረት ይገባኛል ጥያቄ አንስቶ በፕሮፌሰር መስፍን እየተመራ ባምቢስ አካባቢ የነበረውን የአንድነት ፓርቲ ቢሮ በመውረሩ የተነሳ ግጭት ተፈጥሯል፤ የሰው ደምም ፈስሷል፡፡ /ማየት ለፈለገ የቪዲዮ ማስረጃ ማቅረብ እችላለሁ/ እናም ኢንጂነሩ የሚሉት ያኔ ያባረርኳቸው አሁን አባረውኛል ነው፡፡ የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ አይደል የሚባለው፡፡ እርሳቸው ያሉትን እጠቅሳለሁ፡፡
“ይሄ ነገር ሰፋ ባለ መንገድ የታቀደበት ነው ብየ አምናለሁ፡፡ በምርጫ 2002 ዋዜማ አንድነት ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ነበር፤ በተወሰኑ ቡድኖች፡፡ አሁን ሰዎቹ ሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ በምርጫ ዋዜማ አሁንም እንዲህ አይነቱ ፕሮጀክት የተደገመ ይመስለኛል፡፡ ይሄ የእኔ የግል አስተያየት ነው፡፡”
ኢንጂነሩ ለእሳቸው ስልጣን መልቀቅ ምክንያቶች ውስጣዊና ውጫዊ ተፅዕኖዎች አሉ ቢሉም ውስጣዊ ተፅዕኖውም ቢሆን ምንጩ ከውጭ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡
“አገር ውስጥ ያለው ከውጪው ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ትልቁ ችግራቸው ግንኙነታቸው ተቋማዊ ሳይሆን ግለሰባዊ ነው፡፡ እንደዚሁም ቡድናዊ ነው፡፡ የዚያ ነፀብራቅ አገር ውስጥ አለ፡፡ ከእነሱ ጋር የሚገናኙ፤ ፓርቲውን ተቋማዊ ባልሆነ መንገድ ለመምራት የመሞከር ነገር አለ፡፡”
የአንድነት ፓርቲ የቀድሞ ሊቀመንበርን ማዕከል አድርጌ ከላይ እንዳብራራሁት በውጭ ያለው ተቃዋሚ አገር ውስጥ ላሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዶላር ሲልክ አብሮ ፅንፈኛ አመለካከቱን ይልካል፡፡ ያሻውን መሾም፤ ያሻውን መሻር ይፈልጋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹም አሜን ብለው ይቀበላሉ፤ እንቢ ካሉ ደግሞ ዶላሩ ታንቆ ይያዝባቸዋል፡፡ ከውጭ በህገ ወጥ መንገድ በሚያገኙት ገንዘብ ላይ የተንጠለጠሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ታዲያ ይሄኔ ጉሮሯቸው ይታነቅና መንፈራገጥ ይጀምራሉ፡፡ ትንሽ ቢንገራገጩም ቆይተው የተላከላቸውን ትዕዛዝ ይተገብራሉ፡፡ ‹‹እምቢ›› ብሎ ‹‹እሺ›› ለማለት አይነተኛ ምሳሌ አንድነት ፓርቲ ነው፡፡ ከጅምሩ ‹‹አሜን›› ብሎ ትዕዛዙንም ዶላሩንም ለመቀበል ምሳሌ የሚሆነው ደግሞ ሰማያዊ ፓርቲ ነው፡፡
ፅሁፌን የምጨርሰው በአጠቃላይ ለተቃዋሚ ፓርቲ አባሎች በተለይ ደግሞ ለአንድነቶች ሰዋዊ ምክሬን በመለገስ ነው፡፡ አሉን የምትሏቸው ፓርቲዎቻችሁ የፅንፈኛ ዲያስፖራ አሻንጉሊት ሆነዋል፡፡ መሪያችን የምትሏቸውንም የመምረጥና የማውረድ መብት በእጃችሁ አይደለም፡፡ በተደጋጋሚ በማስረጃ አስደግፌ ዲያስፖራው በርቀት መቆጣጠሪያ መሳሪያ ሊዘውራችሁ ይፈልጋል ያልኩትን ብትቀበሉት ይሻላችሁ ይመስለኛል፡፡
ለነገሩ በተለይ አንድነቶች ከመቀበል የተሻለ ምርጫ ያላችሁ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም አለቃችሁ ‹‹ተፅዕኖው ከስልጣኔ አስነስቶኛል›› ሲል ‹‹ተፅዕኖ የለም›› ማለት ኮተታም ተቃዋሚ ካድሬ /ኮተካ/ ያስብላችኋል፡፡ /ዱሮስ ምን ነበርን ብላችሁ እንደማትጠይቁኝ ተስፋ አደርጋለሁ/
በተጨማሪም ኢንጂነሩን ዋሽቷል ወይም ተሳስቷል እንዳትሉ ሌላ ቅርቃር ውስጥ የገባችሁ ይመስለኛል፡፡ እንደምታውቁት ባለፈው አምስት አመራሮች ካፈነገጡ በኋላ ኢንጂነር ግዛቸው መንበሩን ሲያደላድል ከአገር ውስጥ እስከ ውጪ በተዘረጋው የሶሻል ሚዲያ መረባችሁ ‹‹ስልጣን ላይ ሙጭጭ አለ›› እያላችሁ ጥላሸት ስትቀቡት ነበር፡፡ አሁን ስልጣኑን ሲለቅ ደግሞ ‹‹እንዲህ ነው ጀግና አመራር እያላችሁ›› በጥላሸቱ ላይ ቀለም ቀባችሁት፡፡ አሁን ደግሞ ‹‹የውጭ ጣልቃ ገብነት ከስልጣኔ አስነሳኝ፤ እዚህ ያለው ብሔራዊ ም/ቤት፤ ጠቅላላ ጉባዔ፤ የአባላት ጉባዔ፤ ወዘተ… የይስሙላ ነው›› ሲላችሁ ሌላ ጥላሸት ልትቀቡት አትችሉም፡፡ በመገለባበጥ ሃትሪክ እንስራ ካላላችሁ በስተቀር፡፡
እናም አላችኋለሁ፤ ራሳችሁን ሁኑ፡፡

Saturday, January 17, 2015

የሀገር ናፍቆት

እኛ /እኛ የነገሮች አካሄድ ቀድሞ የተገለጠልን/ ከአመታት በፊት ‹‹ኢሳት የሻዕቢያ ነው›› ስንል እናንተ /እናንተ የፊቱን ቀርቶ የኋላውን ለመረዳት የሚከብዳችሁ/ ‹‹ኢሳትማ የእኛ የኢትዮጵያውያን ድምፅ ነው›› አላችሁ፡፡ ለነገሩ እሱም አሰብና ምፅዋን ደገምገም እያረገ በመነካካት ስሜታችሁን ሰቅዞ ይዞላችሁ ነበር፡፡
አሁን ግን ሁሉም ነገር ግልፅ የሆነላችሁ ይመስለኛል፡፡ ሰሞኑን በኢሳት ባለቤት በግንቦት 7 እና በሻዕቢያው እንግዴ ልጅ አርበኞች ግንባር መካከል ቅልቅሉ ሲፈፀም /ሰርጉ እንኳን ቀድሞ የተበላ ነው/ ጆሯችሁን ኮርኩራችሁ አዳምጣችኋል፡፡ ግንቦት 7 እና አርበኞች ግንባርአግአዴን በሚል ስም በግላጭ ተዋህደዋል፡፡
ከእንግዲህ እንደ ኮሶ እየመረራችሁም ቢሆን የአሰብና የምፅዋ ወደብ ጉዳይ የኤርትራዊያን ጉዳይ እንጂ የኢትዮጵያውያን ጉዳይ እንዳልሆነ ሁለታችንም በአንድ ድምፅ እንናገራታለን፡፡ ልዩነታችን እኛ ‹‹የአሰብ ወደብ የግመል መጠጫ ሆኖ ቀርቷል›› ማለታችንን ስንቀጥል እናንተ ግን የአሰብ ወደብ ለኤርትራ ያለውን ፋይዳ ልትነግሩን መዳዳታችሁ የማይቀር መሆኑ ነው፡፡
ከዚሁ የሁለቱ ሃይሎች መቀላቀል ጋር በተያያዘ ሁለት የኢሳት ጋዜጠኞች ወደ ኤርትራ ዘምተዋል፡፡ የጦር ወሬ በቀጥታ ከበረሃ ሆነው ሊነገሩን ማለት ነው፡፡ ግን እስካሁን አንድምየጀግና ወሬአላደረሱንም፡፡ እንግዲህ እዛ ያለው የኢንተርኔት ሁኔታ ስላልተመቻቸው ነው ብለን እንለፈው፡፡ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ተመልሰው ኔትወርክ ሲያገኙ ይዘግቡልናል ብለን እንጠብቅ፡፡
የኔትወርክ ነገር ከተነሳ አይቀርስ፤ ፋሲል የኔአለም /አንዱ ዘማች/ በፌስቡኩ ላይ በኤርትራ ያለው ችግር የኔትወርክ ብቻ ነው ብሎናል፡፡ “I feel as if I were in Addis here. One problem observed is internet connection.”
እንዳፍህ ያድርገው፤ የኤርትራ ህዝብ ችግሩ ሁሉ ተወግዶለት በኢንተርኔት እጦት ብቻ ቢሰቃይ የእኔም ምኞት ነበር፡፡ ግን ችግሩ ሁሉን አቀፍ ነው፡፡ እናንተው ተነስታችሁ ፌስቡክ ላይ በለጣጠፋችኋቸው ፎቶዎች እንኳን የታዘብነው ከአሁኗ አስመራ ይልቅ ደርግ ጥሏት የሄደው አስመራ በውበት እንደምትበልጥ ነው፡፡ መቼም ዜጎቿ የሻዕቢያን ፈንጂና የጥይት እሩምታ ከቁብ ሳይቆጥሩ ወደ ኢትዮጵያ በሺዎች የሚጎርፉት ኢንተርኔት ፍለጋ እንዳልሆነ ልባችሁ አያጣውም፡፡
እንደሚታወቀው ኢሳት እስካሁን የኤርትራውን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ጉዳይ የሚዘግበው በእጅ አዙር ነበር፡፡ ከኤርትራ ቲቪ በመቅዳት ወይም እንደ አንዳርጋቸው ያሉ ሰዎችን በቃለ መጠይቅ መልኩ እንዲያንቆለጳጵሷቸው በማድረግ፡፡ አሁን ግን ፕሬዝዳንቱን በቀጥታ ኢንተርቪው እንደሚያደርጋቸው ይጠበቃል፡፡
ይህ አይቀሬ መሆኑን ፋሲል እንዲህ ሲል ፍንጭ ሰጥቶናል፡፡
"Me, my colleague Mesay and some Ethiopian politicians met Isayas Afewerki of Eritrea today at a construction site in the outskirts of Asmara. During our brief discussion, he raised a number of points regarding the past, present and future relationships between Ethiopia and Eritrea. Here are some of his words I remember from the discussion. ESAT will interview him soon."
እዚህ ላይ ጥያቄው ቃለ ምልልሱ በምንኛ ይካሄዳል የሚለው ነው? በአማርኛ ወይስ በትግርኛ?
ኢሳያስ ይታነቃታል እንጂ ትምክህቱን አራግፎ አማርኛ አያወራትም፡፡ ኢሳትም ይሞታታል እንጂ ትምክህቱን አራግፎ ትግርኛ ያወራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ስለዚህ ያለው አማራጭ መሳይ መኮንን በአማርኛ ይጠይቃል፤ ኢሳያስ ደግሞ አልሰሜ መስሎ በትግርኛ ይተረጎምለታል፤ ከዛ በትግርኛ ይናገራል፤ የማይሰማው መሳይ ደግሞ አንገቱን ይነቀንቃል፤ ኢሳት ደግሞ ተርጉሞ ያስተላልፈዋል፡፡ ወይም ደግሞ ቃለ ምልልሱ በሁለት አማርኛ መናገር የሚችሉ ሰዎች መካከል የሚካሄድ ቢሆንም ቅሉ መግባቢያቸውን እንግሊዘኛ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡
መቼም የኢሳያስን አማርኛ አለመናገር ከትምክህት ጋር ሳያይዘው ፓራዶክስ እንደማይሆንባችሁ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ኢሳያስ ለቋንቋውና ለተናጋሪው ሕዝብ ካለው ንቀት የተነሳ አማርኛን አቀላጥፎ መናገር የሚችል ቢሆንም እንኳን በከንፈሩ እንዲዞር አይፈልጉም፡፡ የኢሳት ትምክህት ግን ማብራሪያም አያስፈልገውም፡፡
መቼም ሰሞኑን የፋሲልን ፖስቶች ያየና የእንግሊዘኛ ሰምና ወርቅ የሚረዳ ፌስቡከር ይሄ ጋዜጠኛ በኢትዮጵያ ናፍቆት ምን ያህል እንደተሰቃየ ለመረዳት አይከብደውም፡፡
ከላይ ያለችውን የእንግሊዘኛ አረፍተ ነገር “I feel as if I were in Addis here. One problem observed is internet connection.” እንኳን ብናያት ወርቋ ፋሲላችን አዲስ አበባ ቦሌ ካልዲሲ ኮፊ ቁጭ ብሎ ኢንተርኔት እየተጠቀመ የአዲስ አበባን ቆንጆ ቆንጆ ህንፃዎች /ልብ አርጉልኝ ቺኮች አላልኩም/ የማየት ፍላጎቱ እንዳየለበት ታሳብቃለች፡፡
ሌላም አንድ ፖስት አንብቤለታለሁ፡፡ እንዲህ ትላለች፡፡ “One note, after 7 years, I was able to see Humera, the border town of Ethiopia, and Tekeze River. It was unforgettable experience.”
ፋሲል ለሰባት አመታት ከሀገሩ ውጭ ቆይቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን በማየቱ /ለዛውም በወታደራዊ አጉሊ መነፅር/ የማይረሳ ትዝታ እንደቋጠረ ነግሮናል፡፡ ምስኪን ፋሲል! እንግዲህ ዳሩን ሲያይ እንዲህ ናፍቆት ያንገበገበው መሃሉን ቢያይ ምን ሊሆን እንደሚችል አስቡት፡፡

ቆይ ግን እድሜ ልኩን አሜሪካ ተደብቆ በሀገር ናፍቆት ከሚሰቃይ በጊዜ ሀገሩ ቢገባ አይሻለውም ትላላችሁ? በነገራችን ላይ ፋሲል የእድሜ ልክ እስር የተበየነበት በመሆኑ ቢመጣም ማረፊያው የት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ግን ቢሆንም 'ሁሉም በሀገር ያምራል' ይባል የለ፡፡