Sunday, July 20, 2014

የሰንደቅ አላማችን ፖለቲካ


የግንቦት 7 አሸባሪ ቡድን ዋና ፀሃፊ የነበረው አንዳርጋቸው ፅጌ በኢትዮጵያ የደህንነት ሃይሎች ቁጥጥር ስር መዋሉ በአገር ውስጥም በውጭም ያሉ ደጋፊዎቹን ሲበዛ አበሳጭቷቸዋል፡፡ ይህ በኢትዮጵያ ሕግ በተደጋጋሚ ወንጀለኛ ተብሎ የተፈረደበትና በፓርላማውም ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀ ድርጅት አመራር ልክ እንደ ነፃነት ታጋይ ተቆጥሮ አንዳርጋቸው ይፈታ እየተባለለት በአንዳንድ የውጭ አገር ከተሞችም ሰልፍ እየተወጣለት ነው፡፡ በስዊዘርላንድ ከተማ በተካሄደው ሰልፍ ላይ ታዲያ ሰልፈኞቹ የትግራይ ብሔራዊ ክልል ሰንደቅ አላማን ሲያቃጥሉ ተስተውለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ የቡድኑ ደጋፊዎችም ይህንኑ ድርጊት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ በመደገፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ፅሁፌ ጋር በቀጥታ ስለማይገናኙ ሌሎቹን የድጋፍ አይነቶች ወደጎን ልበልና ላነሳው ወደፈለግሁት አቢይ ነጥብ ልግባ፡፡

የቀድሞ የአረና አባል የነበረውና አሁን ደግሞ የአንድነት ፓርቲ አባል የሆነው አስራት አብርሃም በዉጭ ያሉት እነዚህ የግንቦት 7 አባልና ደጋፊዎች ባንዲራ የማቃጠላቸውን ተገቢነት በፌስቡክ ገፁ ላይ አስፍሯል፡፡ ለዚህም ምክንያት ያደረገው ባንዲራው የትግራይ ሕዝቦች ሳይሆን የህወሃት ነው የሚል ነው፡፡ ቃል በቃል ያለው ይህንን ነው፡፡

“ሰሞኑን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሰልፍ ላይ የህወሀትን ባንዴራ በማቃጠላቸው ምክንያት አንዳንድ የህወሀት ካድሬዎችየትግራይ ህዝብ ባንዴራ አቃጠሉትእያሉ ህዝቡን ያልሆነ ስሜት ውስጥ ለመክተት እየጣሩ ነው። ለመሆኑ የህወሀት እንጂ የትግራይ ህዝብ የሚባል ባንድራ አለ እንዴ? ሲጀመር ይሄ ባንዴራ የኮሚኒዝም ርዕዮተ ዓለም እንዲወክል ሆኖ ነው የተቀረፀው፤ በምንም ዓይነት ከትግራይ ህዝብ ባሕልና ታሪክ ጋር የሚያገናኘው ነገር ያለ አይመስለኝም። ለወደፊት በሚኖረው ፌደራል ስርዓት ውስጥ የትግራይ ህዝብ በራሱ ምርጫ የሚውለበለብ የክልሉ ባንደራ ሊኖረው ይችል ይሆናል እንጂ ይሄ የትግራይ ህዝብ የሚወክል ባንዴራ አይደለም። በግርግር ህወሀትና የትግራይ ህዝብ ማምታታት ይቅር! አንድን ህዝብ እንደ ህዝብ የሚያጥላሉቱን ለይተን መቃወም እንችላለን፤ ህወሀት ሲነካ በትግራይ ህዝብ ስም ለመከላከል መሞከር ግን ፍትሀዊ አይደለም!”

ይህ ግለሰብ ያመነበትን ካሰፈረ በኋላ ብዙዎች ተቃውሟቸውን ገልፀውለታል፡፡ አብዛኞቹም ያጠነጠኑት በግለሰቡ እምነት ላይ ነው፡፡ ይሁንና ይህ የአስራት አብርሃም አስተያየት ከግለሰቡ ተነጥሎ ከኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ጋር ተሳስሮ መታየት አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ ለዚህም ምክንያቶቼን አንድ ሁለት ብዬ በዝርዝር አቀርባለሁ፡፡

ከዛ በፊት ግን ስለሰንደቅ አላማው እኔ ያለኝን አረዳድ ላቅርብ፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት ስለ ሰንደቅ አላማ በሚያትትበት አንቀፅ 3 ንዑስ አንቀፅ 3 ላይ የፌዴራሉ አባሎች {ክልሎች} የራሳቸው ሰንደቅ አላማና አርማ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ዝርዝሩን በየራሳቸው ምክር ቤት ይወስናሉ፡፡ ይላል፡፡ የትግራይ ብሔራዊ ክልል ሕገ መንግስት ደግሞ “የትግራይ ብሔራዊ ክልል የራሱ አርማ ያለው ሰንደቅ አላማ ይኖረዋል” ይላል፡፡ በዚሁ መሰረት ክልሉ በህግ የተወሰነ ሰንደቅ አላማ አውጥቶ በመጠቀም ላይ ይገኛል፡፡

ሆኖም ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት ይህ አይነትሰንደቅ አላማን ህልውና የመካድ አመለካከት ከግለሰቦች እምነት አልፎ የፓርቲዎችም እምነት ከመሆን የደረሰ፤ ከትግራይ ክልል ባንዲራም ከፍ ብሎ በኢፌዴሪ ሰንቅ አላማም ላይ የሚሰነዘር የአመለካከት ዝንፈት ነው፡፡ በርግጥ ችግሩ በሰንደቅ አላማ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለሕገ መንግስት ካለ የአልገዛም ባይነት መንፈስ ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ነው፡፡

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ

ፍኖተ ነፃነት በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የሚታተም ጋዜጣ ነው፡፡ በመስከረም ወር 2004 የፓርቲው አፈ ቀላጤ በሆነው በዚህ ጋዜጣ ላይ ጋኖች አለቁና ምንቸቶች ጋን ሆኑ በሚል ርዕስ የወጣ ፅሁፍ እንዲህ ይላል፡፡    

“ቀደምት አያቶቻችንና አባቶቻችን ትንቢት የመቅሰምና የመተርጐም ብቃትና ችሎታ ስለነበራቸው፣ ነቢያት የተነበዩትን ሁሉ በተግባር አውለውታል፡፡ በመሆኑም በቀድሞው ሰንደቅ ዓላማችን ላይ የነበረውንና በዚህ መንግሥት ከቦታው ተነስቶ ብቃትና ትርጉም በሌለው ኢትዮጵያን በማይወክል ምስል የተተካውን የአንበሳ ዓርማ የመሲሁን የኢየሱስን ወደ ምድር መውረድ ኢትዮጵያን ወክሎ መምጣት በመገንዘብና በመንደፍ የተባለውን ዓርማ ከሰንደቅ ዓላማው ላይ እንዲታይና እንዲኖር አደረጉ፡፡”

“ይሁን እንጂ፣ የእግዚአብሔርን አምላካዊነትና ጠባቂነት አምና ለተቀበለችው ጥንታዊት የአዳም መገኛ ምድረ ኤዶም ወይም ምድረ ገነት ለተባለችው ለኢትዮጵያ የተሰጣትን በረከት ምንነቱንና ምሥጢሩን ሳይረዳ፣ ይህ መንግሥት የአንበሳውን ዓርማ አንስቶ ትርጉም በሌለው ዓርማ መተካቱ ታሪክ የማይረሳው ከፍተኛ ስህተት ነው፡፡”

አንድነት ፓርቲ በጋዜጣው ላይ ባወጣው ፅሁፍ በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት የተደነገገውን ሰንደቅ አላማ እንደማይቀበል ግልፅ አድርጓል፡፡ አንድነት በዚህ ደረጃ ለኢፌዴሪ ሰንደቅ አላማ ተቃውሞውን የገለፀ ፓርቲ ሆኖ ሳለ አባሎቹ ለአገሪቱ ባንዲራ ክብር ይሰጣሉ ብሎ መጠበቅ ዘበት ነው፡፡ የክልሎችን ሰንደቅ አላማ ይቀበላሉ ብሎ መጠበቅም ሞኝነት ነው፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ

ሰማያዊ ፓርቲ ከአንድ አመት ቀደም ብሎ ከ1997ቱ የተቃውሞ ሰልፍ ወዲህ የመጀመሪያው የተባለለትን ሰልፍ አካሂዶ ነበር፡፡ በዚህ ሰልፍ ላይ ታዲያ አንድ አነጋጋሪ ድርጊት ተፈፀመ፡፡ ድርጊቱ የተፈፀመው ፒያሳ ከሚገኘው አፍሪካ ወርቅ ቤት ፊት ለፊት ነው፡፡ ከግንፍሌ እየገነፈለ የመጣው ሰልፈኛ ቁልቁል ሲንደረደር ከወደ መርካቶ የመጣው የድጋፍ ሃይል ወደ ላይ እየተመመ ነበር፡፡ ከመርካቶ አቅጣጫ አራት ወጣቶች የኢፌዲሪ ሰንደቅ አላማን ወደጎን ዘርግተው ይዘው መጡ፡፡ ወደ ዋናው ሰልፍ ሊቀላቀሉ በግምት 100 ሜትር ሲቀራቸው የሰልፉ አስተባባሪዎች ወደነሱ ሲሮጡ መጡና አንደኛው ይህን ባንዲራ ለምን ይዛችሁ መጣችሁ? የኛ እንዳልሆነ አታውቁም?” እያለ በቁጣ ደነፋባቸው፡፡ በመካከላቸውም በተፈጠረ ግጭት ሰንደቅ አላማ የያዙ ተሰላፊዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡

በወቅቱ ሰንደቅ አላማዋ እርስ በርስ በተካሄደ መጓተትና ትንቅንቅ ተረጋግጣና ተጎሳቁላ ስለነበር በኢቲቪ ዜናውን የተመለከቱ ኢትዮጵያውያን ተግባሩን አውግዘውታል፡፡ ያኔ የሰማያዊ ፓርቲ አባሎች ምላሽ የነበረው ታዲያ ይሄ የኢሕአዴግ እንጂ የእኛ ባንዲራ አይደለም የሚል ነበር፡፡

አክራሪው የእስልምና ሃይል

በኢፌዴሪ ሰንደቅ አላማ ላይ ከተፈፀሙ አፀያፊ የቅርብ ጊዜ ተግባሮች ከብዙዎች ትውስታው የማይጠፋው ራሱን ድምፃችን ይሰማ’ በሚል የሚጠራው አክራሪና ፅንፈኛ ሃይል የፈፀመው ነው፡፡ ይህ ሃይል የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን የመብት ጥያቄዎች ለራሱ ፖለቲካዊ ግቦች ማስፈፀሚያነት ለመጠቀም ባደረገው እንቅስቃሴ እምነታችሁ ተነካ በሚል ያደናገራቸውን ወጣቶች አደባባይ ማስወጣት ችሎ ነበር፡፡ ከአመት በፊት በዚሁ በአዲስ አበባ በፈጠረው ሁከት ላይ እጅግ የተጎሳቆለችና የተበጣጠሰች ሰንደቅ አላማን በማውለብለብ ለሰንደቅ አላማ ያለውን ጥላቻ በግላጭ አሳይቷል፡፡

በአጠቃላይ በአገራችን የሰንደቅ አላማ ጉዳይ በቀጥታ ከአገሪቱ የተቃውሞና የአክራሪነት እንቅስቃሴ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው፡፡ ለዚህም ነው በአለም ከምናያቸው የተቃውሞ ሰልፎች በተለየ መልኩ በአገራችን የተቃውሞ ሰልፎች ሲካሄዱ ባንዲራችንን የማናየው ወይም ሰልፈኞቹ በሕገ መንግስቱ ከተደነገገው ውጭ አርማ የሌለው ባንዲራ ይዘው የሚወጡት፡፡

ሌላው ጉዳይ ተቃዋሚና ፅንፈኛ ሃይሎች ስለ ሕገ መንግስቱ ያላቸው አረዳድ ነው፡፡ እነሱ ሕገ መንግስቱን ስለማይቀበሉት/ስለማያምኑበት በሕገ መንግስቱም ሆነ ከሱ በታች ባሉት ሕጎች ለመመራት እንደማይገደዱ ያስባሉ፡፡ ለምሳሌ ሰማያዊ ፓርቲ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ  
ነፃነት በሌለበት ሀገር ዜጎች ሰብዓዊ ክብራቸውን ለማስጠበቅ የሚያደርጉት ጥረት የሌሎች ሀገር መንግስታት የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት በዓለም አቀፍ ስምምነቶችም ሆነ በተለይ በሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ጥላ የሚያጠላ መሆኑን ግንዛቤ አለመወሰዱ እጅግ የሚያሳዝን ድርጊት ነው” 
በማለት ለግንቦት 7 የሽብር ቡድን ያለውን የቁርጥ ቀን አጋርነት አሳይቷል፡፡ ልብ በሉ፤ ግንቦት 7 የመንግስት ስልጣንን በሃይል ለመያዝ ጦር ሰብቆ በኤርትራ በረሃዎች የመሸገ ነው፡፡ ሕገ መንግስቱ ደግሞ በአንቀፅ 9“በዚህ ሕገመንግስት ከተደነገገው ውጭ በማናቸውም አኳኋን የመንግስት ስልጣን መያዝ የተከለከለ ነው” ይላል፡፡ በተጨማሪም የፀረ ሽብር ሕጉ በምክር ቤቱ ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀውን ግንቦት 7 ማበረታታትን ወንጀል ያደርጋል፡፡ ለሰማያዊ ፓርቲ ፖለቲከኞች ግን ሕጉን ስለሚቃወሙት እነሱን የሚገዛ አይመስላቸውም፡፡

በተመሳሳይ ሕገ መንግስቱ የኢፌዴሪ ሰንደቅ አላማ ምን እንደሚመስል ይደነግጋል፡፡ ክልሎችም የራሳቸውን እንዲሁ፡፡ ተቃዋሚዎች ግን አሁን ያለው ሰንደቅ አላማ በሚቃወሙት ሕገ መንግስት የተደነገገ በመሆኑ የሚያከብሩት ሳይሆን ኢሕአዴግና ደጋፊዎቹ ብቻ ሊያከብሩት የሚገባ ይመስላቸዋል፡፡ ህልውናቸውን ካረጋገጠላቸው ሕገ መንግስት ጀምሮ በየትኛውም ሕግ የተጠቀሱ መብቶቻቸው በተጣሱ ወይም የተጣሱ በመሰላቸው ጊዜ ደግሞ ወዲያዉኑ ተገልብጠው የሕገ መንግስት ዘብ ሆነው ይቆማሉ፡፡

በርግጥ አስራት አብርሃም ለራሱ የሰጠው ማዕረግየፖለቲካ አክቲቪስትና ደራሲ’ የሚል መሆኑ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ ካለው ሃላፊነት ጋር ሲደመር አስራት ይህን መፃፉ ሊያስገርም ይችላል፡፡ ሆኖም ግን የግለሰቡ እምነት የተቃዋሚዎቻችን እምነት መገለጫ ተደርጎ መታየት ያለበት ነው፡፡
Post a Comment