Tuesday, July 1, 2014

የመን የኢንተርፖል አባል ነች

የመን የኢንተርፖል አባል ነች እንዴ?  ግጥም አርጋ::
ኢትዮጵያስ አባል ነች? በደንብ እንጂ:: እንደውም እነ ግርማይ ገብረሚካኤልን /የአስካሉካን ትሬዲንግ ዋና ስራ አስኪያጅ / አንከባክቦ ያስረከባት ኢንተርፖል አይደል እንዴ?
እና የመን የግንቦት 7ን ዛቻ ፈርታ ካልፈታችው በስተቀር የግንቦት 7 ዋና ፀሃፊ የአንዳርጋቸው ፅጌ  እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?
ህወሃት በኦፕሬሽን መቀሌ በመቀሌ እስር ቤት የነበሩ ታጋዮችን ለማስፈታት የፈፀመችውን ገድል የግንቦት 7 ጦር ሰራዊት በሰንዓ ካልደገመው በቀር ፍፁም ብርሃነ እና ጃዋር መሃመድ እንዳሉት ጊዜው ለአሸባሪዎች እየጨለመባቸው ይመስላል፡፡
ለነገሩ ግንቦት 7 እንዲህ አይነት ኦፕሬሽን የመፈፀም አቅሙም ፍላጎቱም እንደሌለው መግለጫው ያሳያል፡፡ አህያውን ፈርቶ እንዲሉ የመን ላሰረችው እሱ እገድላለሁ እያለ የሚያስፈራራው የኢትዮጵያን ሹማምንት ነው፡፡

"በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አካል፣ መንፈስ እና ሕይወት ላይ ለሚደርሰው ጥቃት ሁሉ በማንኛውም መንገድ በማንኛውም ቦታ የምንበቀል መሆኑንና ብዙ የወያኔ ሹማምንት ዋጋ የሚከፍሉበት እንደሚሆን እንዲያውቁት እናስጠነቅቃለን።"
በማንኛውም መንገድ በማናቸውም ቦታ ይሄኔ ነው መፍራት፡፡ ማነህ ረዳት፤ ጫፍ ላይ ወራጅ አለ፡፡
ግን ግንቦት 7 እንዳለው ሰውያቸው በየመን ምድር አንድም ወንጀል ያልፈፀመ ከሆነ የየመን መንግስት ለምን ያለ እዳው የሰው ሰው አስሮ ይቀልባል? ለእነሱ መልካም የሚሆነው ከሁለቱ መንገዶች አንዱን ተጠቅመው አንዳርጋቸውን ለኢትዮጵያ መንግስት አሳልፎ መስጠት ነው፡፡ አንድም በቀጥታ አሊያም በተዘዋዋሪ በኢንተርፖል በኩል፡፡
አንዳርጋቸው እንደሚታወቀው በሀገራችን ፍርድ ቤት በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሶ በሌለበት የእድሜ ልክ እስራት ተወስኖበታል፡፡ ኢንተርፖል የሚያድነው ደግሞ በሽብርተኝነት፤ በአደንዛዥ እፅ ዝውውር፤ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፤ በሙስና፤ በዘር ማጥፋት ወንጀል፤ ወዘተ የሚፈለጉ ወንጀለኞችን ነው፡፡
በርግጥ ኢንተርፖል ከሀገራት የውስጥ ፖለቲካ ገለልተኝነቱን ለማረጋገጥ ሲል ራሱን የሚያቅብባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ይህን ጉዳይ በየትኛው መነፅር ሊያየው እንደሚችል ህግ አዋቂዎች ሃሳብ ስጡበት፡፡
እኔ ግን ግንቦት 7 መወራጨቱን ትቶ እንደልማዱ ግብፅን ደጅ ቢጠና የሚሻለው ይመስለኛል፡፡ ችግሩ ደግሞ አዲሱ የግብፅ ፕሬዝዳንት አል ሲ ሲ ከእንግዲህ ወዲያ በኢትዮጵያ ውስጥ ጉዳይ ሴራ ላለመሸረብ ለእኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ቃል መግባታቸው ነው፡፡
ማን ሊሰማኝ እንጂ እንደኔ እንደኔ ግን ግንቦት 7 ያለው ብቸኛ አማራጭ ኤርትራን ከጎረቤትሽ ጋር አማልጅኝ ማለት ብቻ ነው፡፡ ይሄ ሳይሻል አይቀርም፡፡ ኢሳያስ አፈወርቂ ለዚህ ካልሆኑትማ ምን ሊያደርጉለት ነው? አንዳርጋቸው እኮ ለእሳቸው ያልሆነው የለም፡፡ ታዲያ ከእነዛ ከየመን ጋር ከሚያነታርኳቸው ደሴቶች አንዷን እጅ መንሻ ቢያደርጉለት ምን ያንሰዋል?
ቆይ ግን አንድ ሃሳብ ልጨምር፡፡ ግንቦት 7 ባወጣው መግለጫ እንዲህ ብሏል፡፡
"በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አካል፣ መንፈስና ሕይወት ላይ የሚደርሰው ማንኛውም ጥቃት ለነፃነታቸው ለመሰዋት ዝግጁ የሚሆኑ እልፍ አዕላፍ ታጋዮችን እንደሚፈጥር ጥርጥር የለንም።"
ታዲያ የአንድ ጓዳቸው መታሰር እንዲህ እልፍ አዕላፍ የሚያደርጋቸው ከሆነ ለምን ብርሃኑ ነጋንስ ልከውልን አናስርላቸውም? ያኔ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ውሳኔ በርግጥም ተግባራዊ ይሆናል፤ እነሱም ሁለት እጥፍ እልፍ አዕላፍ ሰራዊት ይኖራቸዋል:: win win solution ማለት ይሄ አይደል?
በመጨረሻ እዚህ ሶሻል ሚዲያ ላይ ያላችሁ የግንቦት 7 የንቅናቄው አባላትና ደጋፊዎች በአማርኛና በእንግሊዘኛ ቦይኮት የመን /Boycott Yemen/፤ ፍሪ አንዳርጋቸው /Free Andargachew/፤ ሼም ኦን የመን /Shame on Yemen/ እያላችሁ የቋንቋ ኔት ወርክ አታጨናንቁ፡፡ የየመን ብሄራዊ ቋንቋ አረብኛ ነው፡፡ ለመጀመር ያክል ‘ቦይኮት የመን’ በአረብኛ ‘مقاطعة الجمهورية اليمنية መሆኑን ሳሳውቃችሁ ፅናቱን እንዲሰጣችሁ ከመመኘት ጋር ነው፡፡ እናንተ ደግሞ አንዳርጋቸው የመን ሰንዓ ላይ ትራንዚት ሲያደርግ የተያዘው ከየት ወደየት ሲበር እንደሆን አፈላልጋችሁ፤ ንገሩን ባካችሁ፡፡

Take it easy, am not as such serious.
Post a Comment