Thursday, June 12, 2014

በምግብ ራሳችንን መቻላችንና ፀጉር ስንጠቃው

በጥንት ዘመን ሁሉም የአለም ህዝቦች ለፍጆታ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ በራሳቸው ስለሚያሟሉ በኢኮኖሚ ራሳቸውን የቻሉ /self sufficient/ ነበሩ፡፡ ለራሳቸው የሚሆን ልብስ፤ የጦርና የእርሻ መሳሪያ፤ የመኖሪያ ጎጆ፤ ወዘተ በራሳቸው ይሰራሉ፡፡ ከጫካ በማሰባሰብ፤ በማደን፤ በማርባትና በእርሻ የምግብ ፍላጎታቸውን ያሟላሉ፡፡ የአለም ህዝብ ቁጥር እያደገ ሲሄድ ግን ከጫካዎች የሚሰበሰበውና ከአደን የሚገኘው ምግብ እየቀነሰ ሄደ፡፡ ስለሆነም ሰዎች በምግብ ራሳቸውን ለመቻል በእርሻና በእርባታ ላይ አተኮሩ፡፡ በአሁኑ ዘመን ደግሞ በማሽን ታግዘው በብዛት የሚመረቱ ምግቦች በስፋት በመምጣታቸው ጥቂቶች የምግብ አምራቾች ብዙውን የአለም ህዝብ ይመግባሉ፡፡ ይህ በምግብ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም ምርቶች ላይ የሚታይ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ በተለይ ባደጉት ሀገራት ያሉ ሰዎች ከማምረት ይልቅ ምርቶችን የሚሸምቱበትን ገንዘብ ማግኘት ላይ ተሰማሩ፡፡ ተቀጥረውና በንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው በሚያገኙት ገንዘብ ምግብና ሌሎች ቁሶችን ገዝተው ራሳቸውን ይችላሉ፡፡ የንግድ አገልግሎትም በዛው ልክ ተስፋፋ፡፡
ያኔ በጥንት ዘመን የሕዝቦችም ሆነ የመንግስታት ጭንቅ ያልነበረው የምግብ ፍጆታን ማሟላት ግን አሁን ለሀገራት አንዱ የራስ ምታት ሆኗል፡፡ የአንድ መንግስት የስኬትና የድክመት መገለጫ ሚዛን ሆኖም ይወሰዳል፡፡ የግንቦት 20 የድል በዓል ሲከበር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ኢትዮጵያ በምግብ እህል ራሷን መቻሏን ለመንግስታቸው ስኬት አንዱ መገለጫ አድርገው ያቀረቡትም ለዚሁ ነው፡፡
የጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝን ንግግር ተከትሎ በርካታ ሃሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡ በተለይም ሁሉንም የመንግስትን ስኬቶች በማጣጣል የሚታወቁ እንደ ኢሳት ያሉ መገናኛ ብዙሃን ይህንንም በማጣጣል የቀደማቸው የለም፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በምግብ ራስን በመቻልና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ መካከል እንዲሁም በሀገር ደረጃና በቤተሰብ ደረጃ ራስን በመቻል መካከል በመላጋት በማህበራዊ ድረ ገፆች ትችታቸውን አቅርበዋል፡፡ በርግጥ ኢትዮጵያ በምግብ እህል ራሷን ችላለችን? የሚለውን ጥያቄ ኋላ የምመለስበት ሆኖ በመጀመሪያ በሁለቱ ፅንሰ ሃሳቦች መካከል ያለውን ልዩነት እንመርምር፡፡
ከዛ በፊት ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩትን መጥቀስ ተገቢ ይሆናል፡፡ “ዛሬ አርሶ አደርና አርብቶ አደር ህዝባችን ባደረገው እንቅስቃሴ ግንቦት 20/1983 ስንጀምር በዋና ዋና ምርቶች 50 ሚሊዮን ኩንታል ያመርት ከነበረበትና በሀገር አቀፍ ደረጃ በምግብ ራስን መቻል ቀርቶ የተመፅዋችነት ደረጃው ጣሪያ ከደረሰበት ተነስተን ደረጃ በደረጃ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በሁለት አስርት አመታት ውስጥ 250 ሚሊዮን ኩንታል በማምረት በሀገር አቀፍ ደረጃ በምግብ ራሳችንን ችለናል፡፡ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ፕሮግራሞችን ቀርፀን በመተግበር ላይ በመሆናችን የዛሬ ሶስት አመት የአፍሪካ ቀንድን የመታው በ60 አመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ትልቅ ድርቅ በተከሰተበት ወቅት እንኳን ያላንዳች መሰናክል ልንቋቋም ችለናል፡፡”
በምግብ እህል ራስን መቻል ማለት ለህልውና ሲባል ከሌላ ሶስተኛ ወገን ድጋፍም ሆነ የምግብ እርዳታ ያለመፈለግ ማለት ነው፡፡ በአንድ ሀገር ውስጥ የሚመረተው ምርት መጠን ለሀገሪቱ ዜጎች የሚያስፈልገውን ያህል ሆኖ ሲገኝና ይህም ዘላቂነት ያለው መሆኑ ሲረጋገጥ አንድ ሀገር በምግብ ራሷን ችላለች ይባላል፡፡ ራስን መቻል ከምግብ ባለፈ ባሉት የኢኮኖሚ እድገት መገለጫዎችም ሊተረጎም ይችላል፡፡ ይህም አንድ ሀገር ከሌላ ማንኛውም ሀገር ወይም ድርጅት ምንም ድጋፍ ወይም እርዳታ ያለመፈለግ ደረጃ መድረሷን የሚያመላክት ነው፡፡ ጫፍ የረገጠው የዚህ አይነት በኢኮኖሚ ራስን መቻል ‘አውታርኪ’ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ከሌላ ሀገር ጋር ምንም አይነት የንግድ ግንኙነት ያለማድረግንም ያካትታል፡፡ ይሄ ከሞላ ጎደል ምናባዊ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
በሌላ በኩል በአለም የምግብና እርሻ ድርጅት /FAO/ ትርጓሜ መሰረት የምግብ ዋስትና ተረጋገጠ የሚባለው በአንድ ሀገር ያሉ ሁሉም ዜጎች ሁልጊዜ ንቁና ጤናማ ሆነው ለመቆየት የሚያስችላቸው በቂ፤ ንፁህና የተመጣጠነ የምግብ አማራጭ ለማግኘት የሚችሉበት የኢኮኖሚ አቅምና አቅርቦት ሲኖራቸው ነው፡፡ ስለዚህ የምግብ ዋስትና አንደምታው የራስን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የውስጥ ፍጆታን ከማሟላትም የዘለለ ነው፡፡ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ማለት የምርት መውደቅና የአለም አቀፍ ገበያ አሉታዊ ተፅዕኖ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንኳን ለዜጎች በቂ የምግብ ምርት ሳያስተጓጉል የሚያቀርብ የምርት፤ የግብይትና የመጠባበቂያ ክምችት ስርዓት የመዘርጋት አቅምን የተመለከተ ነው፡፡ … ይህ ደግሞ በእርሻ መሬት ላይ ከሚደረግ ርብርብ ባሻገር የዜጎችን ገቢ መጨመርን፤ የውጭ ምንዛሬ ክምችትን ማሳደግንና የክምችትና ስርጭት መሰረተ ልማትን ማስፋፋትን ይጠይቃል፡፡ (Household Food Security: Concepts and Definitions, pdf.)
ስለሆነም በምግብ ራስን መቻል የትልቁ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ግብ አንድ ቀዳሚ አካል ተደርጎ መታየት ያለበት እንጂ በራሱ የእድገት ጫፍ አይደለም፡፡ በምግብ እህል ራስን መቻል የመጨረሻ ግብ ሊሆን እንደማይችልና እንደማይገባ ታንዛኒያ ምስክር ነች፡፡ ታንዛኒያ በዱሮ ታሪኳ እንደ ብዙዎቹ የአለም ሀገራት በምግብ እህል ራሷን የቻለች ነበረች፡፡ ከ1973 - 1975 ባጋጠሟት ሁለት ድርቆች ግን ታሪኳ ተቀይሮ የዜጎቿን ህይወት ለመታደግ ስትል ማሽላ ከውጭ በገፍ ለማስገባት ተገደደች፡፡ ከዚህ በኋላ ‘ኪሊሞ ቻ ኩፋ ና ኩፖና’ ወይም በአማርኛው ‘እርሻ የህልውና ጉዳይ ነው’ የሚል ፕሮጀክት ነድፋ በመተግበሯ በምግብ እህል ራሷን ከመቻል ባለፈ ማሽላን ወደ ውጭም መላክ ጀመረች፡፡ ነገር ግን በ1970ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ የተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ ከድርቅ ጋር ተዳምሮ ዜጎቿ ከ1981 እስከ 1984 ምግብ የሚገዙበት ኩፖን ለማግኘት ረጅም ሰልፎችን እንዲሰለፉ አስገደዳቸው፡፡ ከ1985 ጀምሮ ደግሞ እንደገና ማንሰራራት ጀመረች፡፡ በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ያለፈችው ታንዛኒያ እስካሁን የምግብ ዋስትናዋን አላረጋገጠችም፡፡
ኔፓል እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ኢኮኖሚዋ በእርሻ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ 65 ከመቶ ህዝቧም በዚሁ ይተዳደራል፡፡ ግብርናው ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርቷ ውስጥ ከ35 በመቶ የማያንሰውን ይይዛል፡፡ የእርሻ ምርት መጠኑ ከአንዱ ግዛት አንዱ ቢለያይም እንደ ሀገር ሲታይ ግን ከፍላጎቷ በላይ የምግብ እህል ስለምታመርት በሀገር ደረጃ በምግብ ራሷን ችላለች ትባላለች፡፡ ከግማሽ የሚበልጡት ግዛቶቿ ግን የምግብ ምርት እጥረት አለባቸው፡፡ ስለሆነም የምግብ ዋስትናዋን ገና አላረጋገጠችም፡፡
አቶ ኃይለማርያም በንግግራቸው በምግብ ራስን መቻልንና የምግብ ዋስትና ማረጋገጥን ለያይተው ነው ያቀረቡት፡፡ ኢትዮጵያ በምግብ ሰብል ምርት ራሷን የቻለች ሲሆን የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ በትክክለኛው መንገድ ላይ ትገኛለች ነው ያሉት፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለቱን ለያይተው ማስቀመጣቸው ተገቢ መሆኑንና በአንፃሩ በምግብ ራስን መቻልንና የምግብ ዋስትና ማረጋገጥን እንዳሻ እየለዋወጡ መከራከሪያ ማድረግ ስህተት መሆኑን ነው፡፡ በዚህ ብዥታ ውስጥ ሆኖ የሚቀጥል ሙግትም ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ነው የሚሆነው፡፡ ‘ሁሉም ዜጋ በግለሰብ ደረጃ በምግብ ራሱን ችሏል’ እንደተባለ በማስመሰል የሃሰት መረጃ ማሰራጨትም በዚሁ ማዕቀፍ የሚታይ ነው፡፡ በፋይዳው ከተመዘነ በቤተሰብ/ግለሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋጥ የሚቀርበው እንደውም ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ እንጂ በምግብ ራስን ለመቻል አይደለም፡፡ ሆኖም የሰማይ ያህል ርቋት የነበረውን በሀገር ደረጃ በምግብ ራስን መቻል ማሳካት የቻለችው ኢትዮጵያ በዚህ አካሄዷ በቤተሰብ ብሎም በግለሰብ ደረጃ የምግብ ፍጆታዋን ማሳካትም የሚሳናት አይደለችም፡፡
አሁን በርግጥ ኢትዮጵያ በምግብ እህል ራሷን ችላለችን? ወደሚለው ጥያቄ ልመለስ፡፡ በምግብ ራስን መቻል በቀላል የሂሳብ ስሌት ሀገራዊ የምግብ እህል ምርት መጠንን ለሀገሪቱ ዜጎች ቁጥር በማካፈል ነው የሚሰላው፡፡ ጉዳዩን ይበልጥ ሳይንሳዊና አስተማማኝ ለማድረግ ሌሎች የመለኪያ መንገዶችን መጠቀምም ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ዋና ዋና የምግብ እህሎች የሚይዙት የካሎሪ መጠን ይተመንና አንድ ግለሰብ በሚያስፈልገው የካሎሪ መጠን የአንድ ሀገር ዜጎች ቁጥር ተባዝቶ ይካፈሉታል፡፡  በመጀመሪያው ስሌት መሰረት አሁን ኢትዮጵያ የምታመርተው 250 ሚሊዮን ኩንታል / 25ቢሊዮን ኪ.ግራም/ እህል ለ84 ሚሊዮን ዜጎቿ ቢካፈል በነፍስ ወከፍ 298 ኪ.ግራም ይደርሳቸዋል፡፡  ይህ ለ12 ወራት ሲካፈል ከ24 ኪ.ግራም በላይ ነው፡፡ በማደግ ላይ ያለች ሀገር ደግሞ በምግብ ራሷን ችላለች ለማለት በግለሰብ ደረጃ በወር 15 ኪ.ግራም የምግብ እህል ማቅረብ ነው የሚያስፈልጋት፡፡ በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ችላለች ማለት ሳይንሳዊና በመረጃ የተደገፈ ነው፡፡ ይህንን መገዳደር የሚቻለው አንድም ሌላ ሳይንሳዊ ትንታኔ በማቅረብ አሊያም የሚቀርቡትን አሃዞች ወድቅ የሚያደርግ ሌላ ተጨባጭ መረጃ በማቅረብ ብቻ ነው፡፡ ካልሆነ ፀጉር ስንጠቃና ይዘትን ማንሻፈፍ የግንቦት 20 ፍሬዎችን ሊደብቃቸው አይችልም፡፡
በምግብና እርሻ እንዲሁም በኢኮኖሚ ምሁራን ዘንድ አከራካሪ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል አንዱ በምግብ እህል ራስን መቻል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደ ወሳኝ ዘዴ መወሰድ ይገባዋል ወይ? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ‘መወሰድ ይገባዋል’ የሚሉት ወገኖች ‘የምግብ ፍላጎቴን ገዝቼ አሟላለሁ’ ብሎ በገበያ ላይ መተማመን አያዋጣም ይላሉ፡፡ ለዚህም በምግብ ምርቶች ዋጋ ላይ የሚያጋጥሙ መዋዠቆችን፤ በአቅርቦት ሂደት የሚያጋጥሙ መሰናክሎችንና የአለም ኢኮኖሚ አለመረጋጋትን በመከራከሪያነት ያነሳሉ፡፡ በተቃራኒው በኩል ያሉ ወገኖች ደግሞ ‘በምግብ ራሴን በመቻል የምግብ ዋስትናዬን አረጋግጣለሁ’ ማለት እጅግ ውድና አንድን ሀገር ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ነው ይላሉ፡፡ ከዚህ ይልቅ የሀገርን አንፃራዊ ፀጋ /comparative advantage/ ግምት ውስጥ ያስገባ የምርት ስርዓትን በመከተል የመግዛት አቅምን ማሳደግና እጥረት ያለበትን ከሌሎች በመግዛት ማሟላት ተመራጭ ነው ይላሉ፡፡
እዚህ ላይ የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅትን /OECD/ ምልከታን ማከል ተገቢ ነው፡፡ ይህ ተቋም በምግብ ራስን መቻል በምግብ ዋስትናን ለማረገገጥ ብቸኛ መፍትሄ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ብሎ ያምናል፡፡ አንዲት ሀገር በውስጧ በምታመርተው ላይ ብቻ ጥገኛ ከሆነች በአንድ ወቅት ድርቅ ቢያጋጥማት ወይም የተፈጥሮ አደጋ ቢከሰትባት የምግብ እህል ዋጋ እጅግ ይንርና ዜጎቿ ገዝተው እንኳን መመገብ ይቸገራሉ ነው መነሻው፡፡ በመሆኑም እንደ ድርጅቱ ምክር ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ በተጓዳኝ የድህነት ቅነሳ ፕሮግራሞችን መንደፍ፤ የመንግስትና የግል ኢንቨስትመንትን ማሳደግ፤ የገቢ ንግድን ማሳለጥና የአደጋ ግዜ መጠባበቂያ ክምችትን ማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያስችላሉ፡፡
ነባራዊ አለም አቀፍ ሁኔታው እንደሚያሳየው በቀድሞ ዘመናት ሰፊ ተቀባይነት የነበረው በምግብ ራስን መቻል የምግብ ዋስትናን ለማረገገጥ ዋነኛ ስልት ነው የሚለው አመለካከት እየደበዘዘ ሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚን ማሳደግ የተሻለ ነው የሚለው አማራጭ እየገነነ መጥቷል፡፡ ያም ሆኖ አሁንም ቢሆን አንዲት ሀገር ወደ ውጭ የምትልከው የእርሻ ምርት መጠን ከውጭ ከምታስገባው ምርት መብለጥ አለበት የሚለው ብዙዎቹ የሚስማሙበት ነው፡፡ አሁን አለማዊ ሁኔታዎች ከመቼውም ግዜ በበለጠ ፍጥነት እየተቀያየሩ ነው፡፡ የጥቂት ሀገራት ኢኮኖሚ መቃወስ አለምን ቀውስ ውስጥ ሲከት እያየን ነው፤ ማህበራዊ አለመረጋጋቶችና ግጭቶች አለምን በሁሉም ጫፎች እየናጧት ነው፤ ሽብርተኝነትና አክራሪነት ሌላው የሀገራት ፈተና ነው፡፡ በነዚህ ሁሉ ችግሮች መካከል ሆኖ የአለም የምግብና እርሻ ድርጅት /FAO/ የሚለውን ‘በቂ፤ ንፁህና የተመጣጠነ ምግብ’ ለማሟላት በሌሎች ሀገሮች ላይ ጥገኛ መሆን አደጋ ያስከትላል፡፡ ለዚህም ነው አሁን አሁን የዘርፉ ሳይንቲስቶች በገጠር ብቻ ሳይሆን በከተሞችም፤ በሰፊ መሬት ላይ ብቻ ሳይሆን በጠባብም፤ በመሬት ላይ ብቻ ሳይሆን ጣሪያ ላይም ማምረት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን እያስተዋወቁ ያሉት፡፡
ሌላው መዘለል የሌለበት ነጥብ መንግስታት በአመታዊ እቅዳቸው ውስጥ በምግብ ራስን የመቻል ምጣኔያቸውን /food self sufficiency rate/ ለማሳደግ ግብ ማስቀመጣቸው ነው፡፡ ይህም የምግብ ብክነትን መቀነስና ከምግብ በኋላ ትራፊን ዳግም ጥቅም ላይ ማዋልን /recycling/ ጭምር ያካትታል፡፡ ለአብነት ጃፓን ከ2000 እስከ 2010 ባሉት አመታት በምግብ ራስን የመቻል ምጣኔዋን በ1998 ከነበረበት 40 በመቶ ወደ 45 በመቶ ለማሳደግ አቅዳ ተንቀሳቅሳለች፡፡ ይሁንና ጥረቷ ምንም ውጤት አላስገኘላትም፡፡ ለዚህም ሀገሪቱ በተደጋጋሚ የሚያጋጥማት ርዕደ መሬትና በተፈጥሯዊ ምክንያቶች የተነሳ የምርት መቀነስ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ያለፉትን ጉድለቶች ሁሉ በመድፈን በ2020 ምጣኔውን ወደ 50 በመቶ ለማሳደግ አቅዳለች፡፡
ከላይ ካሉት አለም አቀፋዊ የክርክር መነሻዎች ተነስቶ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ መገምገም ይቻላል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ በሁሉም መነሻዎች ላይ በምግብ ራስን መቻል በበጎ ጎኑ እንጂ በጉዳት የሚታይ አይደለም፡፡ በምግብ ራስን መቻል እንደ ስጋት የሚታየው ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ብቸኛ ስልት ተደርጎ ሲወሰድ ነው፡፡ ይህን ስልት የሚከተሉ ሀገሮች የእህል ገቢ ንግድን /import/ ከፍተኛ ታሪፍ በመጣልና በሌሎች መንገዶች እንዲቀጭጭ ያደርጉታል፡፡ ይህን ግዜ ነው በምግብ ራስን የመቻል ስልት በዘላቂው የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ላይ ስጋት ይደቅናል የሚባለው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህን የሚፈቅድ አሰራር የለም፡፡ ምርት ከውጭ እንዳይገባ የሚከለክል ወይም አሉታዊ ጫና የሚፈጥር የተለየ ታሪፍ አልተጣለበትም፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ እንደ የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት /OECD/ ያሉ አለም አቀፍ ተቋማት የሚመክሯቸውን ሌሎች እርምጃዎች በመውሰድ ላይ ነች፡፡ የምግብ ዋስትና ስትራቴጂና የምርት ተኮር ሴፍቲኔት መርሃ ግብርን እንደ ሰፈራ ካሉ ሌሎች የድህነት ቅነሳ ፕሮግራሞች ጋር በማስተሳሰር በመተግበሯ ተጨባጭ ለውጥ በማስመዝገብ ላይ ነች፡፡ ሀገራዊ ኢንቨስትመንቱም በመንግስትም ሆነ በግሉ ዘርፍ ከመቼውም ግዜ በተሻለ ፍጥነት እያደገ ነው፡፡ ከቅርብ ግዜ ጀምሮ ደግሞ ሀገሪቱ ቀዳሚ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ከሆኑ ሀገራት ተርታ በመሰለፍ ላይ ነች፡፡ የገቢ ንግድን ለማሳለጥ ቁልፍ ሚና ባለው የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ላይ ትገኛለች፡፡ ድንገተኛ አደጋን በመከላከልና መቋቋም ረገድም መጠባበቂያ እህል በማስቀመጥ፤ ምግብና እርዳታን በቅልጥፍና በማሰራጨትና አስቀድሞ መጠንቀቅና ማስጠንቀቅ ላይ የተሻለ አቅም ገንብታለች፡፡ በድምሩ ከታየም ሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚያው እድገት በማስመዝገብ ረገድ በስኬት ላይ ያለች ሀገር ነች፡፡
ሌላው በምግብ ራስን የመቻል ስልትን ጥርጣሬ ውስጥ የሚከተው ጉዳይ ሀገራት ያላቸውን አንፃራዊ ፀጋ /comparative advantage/ ትተው በምግብ ማምረት ላይ ከተጠመዱ ሃብታቸውን ያላግባብ ያባክናሉ የሚለው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ይህ አይነቱ ስጋት እንዲኖር ነባራዊ ሁኔታውም አይፈቅድም፡፡ ሀገሪቱ ግብርናን ዋነኛ የኢኮኖም መሰረት አድርጋ የያዘችው አንፃራዊ አቅሟ ያለውም እዚሁ ላይ ስለሆነ ነው፡፡ ዘርፉ ጉልበትና መሬትን በስፋት ተጠቅሞ በአነስተኛ ካፒታል የሚለማ ስለሆነ ነው የተመረጠው፡፡ ስለሆነም የሚያስከትለው የሃብት ብክነት የለም፡፡ በጥቅሉ ሲታይ በኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገው ጥረት ብቸኛ ስልት ተደርጎ ያልተወሰደ ይልቁንም ከሌሎች የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ ስልቶች ጋር ተጣምሮ እየተተገበረ ያለ ነው፡፡ ከሁለቱም ተከራካሪ ወገኖች ያሉትን መልካም ነጥቦች የተቀመረ /eclectic/ አቅጣጫ እየተከተለች ነው፡፡ የነዚህ ድምር የሚያሳየው በኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻል የተደረገው ርብርብ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ የመመራቱን ግልፅ ስዕል ነው፡፡
Post a Comment