Sunday, July 20, 2014

ታማኝ ሎሌ/በፈድሉ ጀማል/
በሀገራችን ለረጅም ጊዜ ስር ሰዶ የቆየው የፈውዳል ስርዓት እያስከተለ የነበረው ጭቆናና በደል ከጊዜ ወደ ጊዜ አስከፊነቱ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ መላው የሀገራችን ህዝቦች የስርዓቱን መውደቅ በመሻት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። በስርዓቱ ላይ የማያሻሙ ግልፅ ጥያቄዎችን በማንሳትም የስርአቱን ኢ-ፍትሃዊነት በአደባባይ እልፍ ሆነው በመውጣት መስክረዋል፡፡ ያኔ ያነሷቸው ሶስት ቁልፍ የፖለቲካ ጥያቄዎች የብሔር እኩልነት፣ የመሬት ባለቤትነትና የመንግስት ስልጣን ጥያቄዎች ናቸው። “መሬት ላራሹ” የሚለው መፈክር ከፍ ብሎ የተስተጋባበት ነበር፤ ዘመኑ፡፡ እነዚህን ህዝባዊ ጥያቄዎች በማንገብ በ1960ዎቹ አርሶ አደሮች፤ ተማሪዎች፤ እምነት ተከታዮች፤ ወዘተ… የከፈሉት መስዋዕትነት ከማናችንም አዕምሮ የማይጠፋ ትውስታ ነው። ምንም እንኳን የማታ ማታ ትግሉን ፍሬ አልባ የሚያደርግ ሌላ አምባገነን ስርዓት ቢተካም።
በህዝባዊ አብዮት ወታደራዊው መንግስት ወደ ስልጣን ከወጣበት ማግስት ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ዴሞክሲያዊና ሰብዓዊ መብት የሚረግጡ፤ የፖለቲካ ስልጣን ባለቤትነትንም የሚነፍጉ አዋጆችንና ክልከላዎችን ቢደነግግም የመሬት ላራሹ ጥያቄን በመቀበሉ ለአጭር ግዜም ቢሆን ተቀባይነትን ማግኘት ችሎ ነበር፡፡ ይህም የመሬት ስሪት ባለቤትነት መብት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሚጫወተውን የላቀ ሚና ያሳየ ነው፡፡
ደርግ ጊዜ ለመግዛትና የህዝቡንም ይሁንታ ለማግኘት የመሬት ጥያቄን ይመልስ እንጂ ከተፈጠረበት ዘውዳዊ አገዛዝ ተቆራርጦ የህዝቦችን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞች የማስከበር ተፈጥሯዊ ባህሪ እንደሌለው በማመን በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች በህቡዕ እና በግልፅ፤ በገጠርና በከተማ ትግላቸውን የጀመሩት ገና በጥዋቱ ነበር፡፡ እነዚህን የ60ዎቹን ጥያቄዎች አንግበው ከታገሉትና ካታገሉት ድርጅቶች መካከል በፅናት እስከመጨረሻው በመዝለቅ ለስኬት የበቃው ኢሕአዴግ ብቻ ነው፡፡
የፊውዳሉ የመሬት ይዞታና ኋላ የተከተለውም የምርት ነፃ ተጠቃሚ ያለመሆን ችግሮች በህዝቡ ትግል ተወግደው አርሶ አደሩ የመሬት ባለቤት ብቻ ሳይሆን የምርቱም ብቸኛ ባለቤት የሆነበት ስርዓት የሰፈነው ከ1983 በኋላ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የቃል ኪዳናቸው ሰነድ በሆነው ህገ መንግስት  አንቀፅ 40 ላይ “መሬት የማይሸጥና የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው" የሚል አረፍተ ነገር በማስፈር መሬት በቀጥታም ይሁን በእጅ አዙር ዳግም በመሬት ከበርቴዎች መዳፍ እንዳይወድቅ አፅንተዋል፡፡ ኢሕአዴግም መሬት የሚሸጠው በመቃብሬ ላይ ነው በማለት መሬትን እንደ ሸቀጥ ለመሸመት ሲቋምጡ የነበሩ ሃይሎችን ተስፋ አጨልሞባቸዋል፡፡ ከውጭም ከውስጥም የነበሩበትን ጫናዎች ተቋቁሞ ባለፉት 23 አመታት በአንድ በኩል የውሳኔውን ትክክለኛነት ባስመዘገባቸው ለውጦች ሲያረጋግጥ በሌላ በኩል ለሚመራው ህዝብና ለመሰረታዊ አቋሞቹ ያለውን ታማኝነት በተግባር አስመስሯል፡፡
አርሶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደሩ አሁን መሬቱን በባለቤትነት መንፈስ በመንከባከቡና የምርታማነት ማሻሻያ ዘዴዎችን በመጠቀሙ ከመሬቱ የሚያገኘው ጥቅም እያደገ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡ አሁን አርሶ አደሩ የሚያነሳቸው ጥያቄዎችም ማጠንጠኛቸው ተጠቃሚነቱን ይበልጥ ማሳደግ ላይ ነው፡፡ መሬቴን ለየትኛው ሰብል ላውለው? እንዴት አድርጌ ልጠቀመው? ምን ግብዓትስ ልጠቀም የሚሉት በርግጥም የአርሶ አደሩ የዘወትር ጥያቄዎች ናቸው። መንግስት ግብዓቶችን፤ ቴክኖሎጂና ሙያዊ ድጋፍ እንዲያቀርብለትም በየመድረኮቹ ሁሉ ይጠይቃል፡፡ የመንግስት ትኩረትም እነዚህን ተገቢነት ያላቸውን ጥያቄዎች መመለስ ላይ ነው።
ራሳቸውን ከዘመኑ ጋር ማዘመን ያልቻሉት የሀገራችን ተቃዋሚዎች ግን ዛሬም ላይ ሆነው የመሬት መሸጥ አለበት እንጉርጉሯቸውን በመደጋገም ከ40 አመት በፊት ያከተመለትን የመሬት ከበርቴ አሮጌ ስርዓት አዲስ የኒዮ ሊበራል ቀሚስ አልብሰው ይሰብኩናል፡፡ እውነትም መሬት በሱ መቃብር ላይ ካልሆን እንደማይሸጥ የተረዱት የአንድነት አመራሮች ታዲያ ሰሞኑን መሬትን በመሸጥ የሰፊውን ህዝብ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ስንል ኢሕአዴግን እንቀብረዋለን በማለት ሲደነፉ ተስተውለዋል፡፡
መሬትን መሸጥ እንዴት የኢትዮጵያን ሕዝብ ተጠቃሚ ሊያደርግ እንደሚችል ማስረዳት የተሳናቸው የአንድነት አመራሮች በዚህ ንግግራቸው ውግንናቸው ከሰፊው ህዝብ ሳይሆን ከጥቂት ከበርቴዎች መሆኑንና ዛሬም ለምዕራባውያን ጌቶቻቸው ፍላጎት መፈፀም ደከመን ሰለቸን የማይሉ ታማኝ ሎሌ መሆናቸውን ዳግም አረጋግጠዋል፡፡
በኢትዮጵያ መሬትን ለመውረር የሚያስችል ምንም አይነት የህግም ሆነ የአሰራር ክፍተት እንደሌለ ይልቁንም መሬት በመንግስትና በህዝብ የጋራ ሀብትነት መቆየቱ በጋራ ለመልማት ምቹ እድል እንደሚፈጥር እየታወቀ ተቃዋሚዎቻችን ነጋ ጠባ “መሬታችንን ለአረብ ሸጣችሁ” እያሉ ይወቅሱናል፡፡ ይህን ባሉበት አፋቸው መልሰው መሬት እንዲሸጥ ካልፈቀዳችሁ “እንቀብራችኋለን” ሲሉ ይዝቱብናል፡፡
<<መሬት መሸጥ መለወጥ አለበት>> የሚለው የአንድነት መግለጫ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ጥያቄ ያለመሆኑን ለመረዳት በሀገራችን የቅርብ ግዜ ታሪክ ውስጥ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችና ከፊል አርሶ አደሮች ይህንን ጥያቄ ካለማንሳታቸው በላይ ማረጋገጫ ሊኖር አይችልም፡፡ በርግጥም መሬት የመሸጥ ህዝባዊ ጥያቄ ባይኖርም መሬት የመግዛት የንዑሳን ፍላጎት መኖሩ የማይካድ ጉዳይ ነው፡፡ ለምዕራባዊያን መንግስታትና ለቆሙለት የባለሀብት መደብም ይህ ፖሊሲያችን እንደማይመቻቸው ግልፅ ነው፡፡ ያም ሆኖ የቆምንለት ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ የምዕራቡ አለም ባለሀብት እንዳልሆነ፤ ማህበራዊ መሰረታችንም ሰፊው አርሶ አደር እንጂ ጥቂቱ ከበርቴ እንዳልሆነ ስለምናውቅ እኛስ በአቋማችን ፀንተን በቃላችን እንኖራለን፡፡
Post a Comment