Sunday, March 9, 2014

ብልጡ አልጀዚራ ኢቲቪን ሸወደው/ይህ ጽሑፍ  በሳምንታዊው ሰንደቅ ጋዜጣና በሆር አፌየርስ ድረ ገፅ ለንባብ የበቃ ነው/

በኳታር መንግስት ሃብት የተቋቋመውና ስነ አፈጣጠሩ ሲጠናም የምዕራቡን አለምና የእስራኤል ሚዲያን የአረብ ሀገራት ጉዳይ አዘጋገብ ለመገዳደር የተፈጠረው የአልጀዚራ ቴሌቪዥን ጣቢያ ስትራግል ኦቨር ናይል በሚል ርዕስ አንድ ዘጋቢ ፊልም አዘጋጅቶ ነበር። ጣቢያው ይህን ፊልም በቴሌቪዥኑ ያስተላለፈው ሲሆን በድረ ገፁ ላይ ስለጫነውም በርካቶች ተመልክተውታል።

የዘጋቢ ፊልሙ ይዘት በናይል ወንዝ የተነሳ በላይኛውና በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት መካከል ስለነገሰ ውጥረት ሲሆን ትኩረት ያደረገው ደግሞ ከላይኛው ተፋሰስ ኢትዮጵያ ላይ፤ ከታችኛው ተፋሰስ ደግሞ ግብፅ ላይ ነው። ይህን ፊልም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከሞላ ጎደል እንደወረደ በሚባል ደረጃ ወደ አማርኛ ተርጉሞ አቅርቦታል። ‘ጠብቁን’ የሚል ማስታወቂያ መሰራቱና ፊልሙ በተደጋጋሚ መታየቱ የአባይ ፍጥጫ ከሚለው ጩኸታም ርዕሱ ጋር ተዳምሮ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እንደተከታተሉት ለመገመት አይከብድም።

ይህን ዘጋቢ ፊልም የተከታተሉ የምቀርባቸውን ሰዎች ስለ ዘገባው ያላቸውን አስተያየት ጠይቄያቸው ነበር። የሚበዙቱ እንዳደነቁት ነግረውኛል። ሁሉም ለማለት በሚቻልበት ደረጃ በምስል አጠቃቀሙ፤ በትረካው ፍሰትና በታሪክ አወቃቀሩ በጥቅሉ በአቀራረብ ደረጃ ምርጥ የሚባል ዘጋቢ ፊልም እንደሆነ ይስማማሉ። እኔም በዚህ ረገድ ልዩነት የለኝም። ሆኖም አንዳንድ ያሳሰቡኝን ጥያቄዎች ሳነሳ የጠየቅኋቸውም እንደኔው ግር ይላቸዋል አለያም እውነትክን ነው፤ ከኢትዮጵያ ጥቅምና አቋም ጋር ይጋጫልይሉኛል።