Wednesday, February 12, 2014

መስራታችሁን ካላቆማችሁ ማውራታችንን አናቆምም- ግብፅ
ትናንት ማለትም ጥር 04/2006 የመንግስት ኮሚዩንኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ባዘጋጀው አንድ አውደ ጥናት ላይ ተሳትፌ ነበር፡፡ የመገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ምሁራን ተሳትፈዋል፡፡ የመነጋገሪያ አጀንዳችን ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፡፡ በዚህ ዝግጅት ሁለት ጥናታዊ ፅሁፎች የቀረቡ ሲሆን ግድቡን በተመለከቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የውይይቱን ይዘት በመገናኛ ብዙሃን እንደተከታተላችሁትና ቀሪውን ደግሞ ሰሞኑን በሚወጡ ጋዜጦች እንደሚዘገብ ተስፋ በማድረግ የእኔን ቀልብ ወደሳበው አንድ ጉዳይ ልምጣ፡፡


እንደምታስታዉሱት ከዚህ እለት ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ የውሃ፤ መስኖና ኢነርጂ  ሚኒስትር አቶ አለማየሁ ተገኑ እና የግብፅ የመስኖ ሚኒስትር ሞሃመድ አብዱል ሙታሊብ በአዲስ አበባ ውይይት አድርገው ነበር፡፡ ስለዚህ ውይይት ውጤት የኛው ሚኒስትር አቶ አለማየሁ ተገኑ ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡ እርሳቸው እንዳሉት ውይይቱ ያለስምምነት ነው የተቋጨው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ግብፅ ከአሁን በፊት አቅርባቸው የነበሩና በኢትዮጵያና በሱዳን ተቀባይነት ያላገኙትን ሀሳቦች {መተማመን የመገንባት መርህና የግድቡን ተፅዕኖ የሚያጠና ሌላ አለም አቀፍ ኮሚቴ ማቋቋም} አሁንም ዳግም ይዛ በመምጣቷ ነው፡፡


በአባይ ተፋሰስ ሀገራት መካከል መተማመንን የመፍጠር ጉዳይ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት ጉዳይ በመሆኑ ኢትዮጵያ በዚህ ላይ የመነጋገር የተናጠል መብት እንደሌላትና ጉዳዩን በተመለከተ የተፋሰሱ ሀገራት አስቀድመው በናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት /CFA/ ላይ የተወያዩበት በመሆኑ ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ ላይ እንደማትደራደር አቋሟን ግልፅ አድርጋለች፡፡ የባለሙያዎች ኮሚቴ የማቋቋም ጉዳይም በባለፈው ውይይት ተቀባይነት ያላገኘና ሃላፊነቱም ከባለፈው ኮሚቴ ያልተለየና ግልፀኝነት የጎደለው በመሆኑ ኢትዮጵያ እንደምትቃወመው ሚኒስትሩ ለአቻቸው አስረድተዋል፡፡


አቶ አለማየሁ እንደተናገሩት በአንፃሩ ግብፅ በውይይቱ ሂደት ላይ እንቅፋት መሆኗን እንድትተው ማሳሰቢያ ተሰጥቷታል፡፡ በጥቅሉ ሲታይ ለግብፅ የተሰጡት ማሳሰቢያዎች ጉዳዩ የሶስትዮሽ ስለሆነ ወደጋራ ውይይቱ ተመለሺ፤ ውይይቱን የማደናቀፍ ስራ አትስሪና መሪዎቿም የተሳሳተ መረጃ ለመገናኛ ብዙሃን አትስጡ የሚሉ ናቸው፡፡


የግብፅ ልዑካን ግን በነዚህ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ፍላጎት አላሳየም፡፡ ይልቁንም <<አለም አቀፍ የባለሙያዎች ኮሚቴ መቋቋም የለበትም ካላችሁ ግንባታውን አቁሙትና ጥናቱ በብሄራዊ ኮሚቴም ቢሆን ይካሄድ፡፡ ካልሆነ ግን እናንተ ስራችሁን እየሰራችሁ እኛን ለመገናኛ ብዙሃን አትናገሩ አትበሉን>> የሚል ምላሽ ነው የሰጡት፡፡


ማሳሰቢያውን የግብፁ ሚኒስትር ሊያጣምሙት ቢሞክሩም ዋና ይዘቱ ለመገናኛ ብዙሃን ምንም አትበሉ ሳይሆን የሀሰት መረጃ እየሰጣችሁ ህዝባችሁንም ሆነ የእኛን ህዝብ አታወናብዱ ነው፡፡  ግብፆች ህዝባቸውን በየመገናኛ ብዙሃኖች ለማወናበድ መሞከራቸው የተለመደ ሆኗል፡፡ እኝሁ ሚኒስትር ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት እንኳን ምን እንዳስወሩ ይታወሳል፡፡ <<ወደ ኢትዮጵያ የምሄደው በኢትዮጵያው ሚኒስትር አለማየሁ ተገኑ ጥያቄ ቀርቦልኝ ነው>> ብለው በዴይሊ ኒዊስ ኢጂፕት ዜና አሰርተው ነበር፡፡ 


እውነታው ግን ይህ ሳይሆን ሞሃመድ አብዱል ሙታሊብ የመጡት ራሳቸው ጥያቄ አቅርበው ነው፡፡ አቶ አለማየሁ ተገኑ እንደገለፁት ግብፅ በካርቱሙ ውይይት ሁለተኛ በውይይቱ አልሳተፍም ካለች በኃላ ኢትዮጵያ ምንም ጥሪ አላቀረበችም፡፡  
“የመስኖ ሚኒስትሩ ስልክ ደውሎ ከናንተ ጋር መወያየት አፍልጋለሁ፤ ልምጣ አለኝ፡፡ መምጣት ትችላለህ አልኩት” ነው ያሉት አቶ አለማየሁ ተገኑ፡፡ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ይህንኑ አረጋግጧል፡፡
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃዚም ኤል ቢብላዊ በመሃል /ጃንዋሪ 9/2014/ ብቅ ብለው <<ድርድር በአንድ ጀንበር የሚያልቅ አይደለም፤ እንቀጥልበታለን>> ብለው ነበር ለጋዜጠኞች፡፡ ይህን ተከትሎ በራሳቸው ጥያቄ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የመስኖ ሚኒስትሩ ይህን ‘የተጠየቅሁ’ ዜና ያሰራጩበት ምክንያት ህዝብን ከማታለል ውጭ ምን ሊሆን ይችላል፡፡


አቶ አለማየሁ ተገኑ ስለውይይቱ የሰጡንን ማብራሪያ ሲያጠቃልሉ እንዲህ ብለውን ነበር፡፡  
“በቃ ይሄው ነው፡፡ ለሶስት ሰዓት ያክል ተወያየን፡፡ በመጨረሻም ምሳ ተገባብዘን ተለያየን፡፡ ወደ ድርድሩ ተመለሱ ብለናቸው ነበር፤ ምላሽ ግን አልሰጡንም፡፡ ከሄዱ በኋላ የሚሉትን ደግሞ አብረን እንሰማለን፡፡”
እኔም ሰውየው ካይሮ እንደደረሱ ምን እንደሚሉ ለመስማት እየተጠባበቅሁ ነበር፡፡ ሰውየው መስራታችሁን ካላቆማችሁ ማውራታችንን አናቆምም ስላሉ የሆነ ወሬ እንደሚኖራቸው በመገመት አይኖቼ ድረ ገፆቻቸው ላይ እንደተተከሉ ነው የዋሉት፡፡ አብዱል ሙታሊብ ካይሮ እንደደረሱ በቀጥታ የተላተሙት ከቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ነው፡፡ በዚሁ በታላቁ የህዳሴ ግድባችን የተነሳ፡፡


የመስኖ ሚኒስትሩ ትናንት ምሽት በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው እንደተናገሩት ከሆነ የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመት ዳቮትሉ ኢትዮጵያን ከጎበኙ በኋላ በህዳሴው ግድብ ግንባታ የሚያግዙ ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ቃል ገብተዋል፡፡ “ይሄ ጉዳይ ግብፅን የማይወዱ በአንድ ጎራ የተሰለፉበት ሆኗል” ሲሉ ለህዝባቸው መናገራቸውን ወርልድ ቡለቲን ዘግቧል፡፡


እንደተባለው ቱርክ ባለሙያዎች ትለግሰን ወይም አትለግሰን መረጃው የለኝም፡፡ ግን አንድ ነገር ማለት ይቻላል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እርሳቸው እንዳሉት የግብፅ ጠላቶችን በአንድነት ያሰለፈ መድረክ አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ ብንነሳ ግድቡ ሁሉንም ሀገራት ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ እንዲውል ነው እየሰራች ያለችው፡፡ ሱዳንም ይህንኑ በመረዳቷ ነው ድጋፏን የለገሰችው፡፡ የላይኛው ተፋሰስ ሀገሮችም የትብብር ማዕቀፉን ሲያፀድቁ ከናይል ውሃ ሁላችንም ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንሆናለን ብለው እንጂ ግብፅን ለመበቀል ብለው አይደለም፡፡


ሙታሊብ ቱርክን ሲወቅሱ ለእኛም ያላቸውን ንቀት እየገለፁ ነበር፡፡ ድረ ገፁ በእንግሊዘኛ ያሰፈረው ወደኛ ሲተረጎም እንዲህ ይነበባል፡፡

“እኔ ማለት የምፈልገው {ለቱርክ} ይህንን ነው፡፡ ቱርክ አታቱርክ ግድብን ስትገነባ ኢራቃውያንንና ሶሪያውያንን ውሃ እያስጠማች ነው፡፡ አለም አቀፍ ስምምነቶችንም ሽራለች፡፡ ላሰምርበት የምፈልገው ግብፅ እንደ ኢራቅና ሶሪያ ያለመሆኗንና ኢትዮጵያም ቱርክ ያለመሆኗን ነው፡፡”
ይሄ የፀብ አጫሪነት ንግግር ነው፡፡ ይሄ ንቀት ነው፡፡ አሽሙሩ ሲተረጎም <<ግብፅ እንደነ ኢራቅና ሶሪያ ግድቡ ሲገነባ ዝም ብላ የምታይ አቅመ ቢስ አይደለችም፤ ኢትዮጵያ ደግሞ እንደ ቱርክ አርፈሽ ተቀመጪ ከተባለች የመገንባት አቅም ያላት አይደለችም>> ማለት ነው፡፡ ሌላ ትርጉም ያለው ካለ አስተያየት ሊሰጥበት ይችላል፡፡


እርግጥ ነው፤ ቱርክ ስትገነባ ‘ሽራዋለች’ የሚባል አለም አቀፍ ስምምነት ባይኖርም /በዚህ ላይ ምሁራኖቻችን ሌላ ትንታኔ ይጨምሩበታል ብዬ እጠብቃለሁ/ የጎረቤቶቿን ጫጫታ ግን የሚሰማ ጆሮ አልነበራትም፡፡ በወቅቱ ፕሬዝዳንቷ የነበሩት ሱሌይማን ዴምረል 
“ልክ ቱርክ የነሱን ነዳጅ ይገባኛል እንደማትለው ሁሉ ኢራቅም ሆነች ሶሪያ በቱርክ ወንዝ ላይ የይገባኛል ጥያቄ ሊያነሱ አይችሉም፡፡ ይህ የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው፡፡ የፈለግነውን ማድረግ እንችላለን፡፡ የውሃ ሃብታችሁን እንጋራለን ሊሉን አይችሉም” ማለታቸው ይታወሳል፡፡
እኛ ግን ጎረቤቶቻችንን ዞር በሉ አላልንም፡፡ ናይል ለሁላችንም የሚበቃ ነው፤ ግድቡም ከተደማመጥን ሁላችንንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ነው፤ ለዚህም ተቀራርበን እንወያይ ነው ያልነው፡፡ አንዳንዴም ከመስመር እየወጣን ጭምር መተማመን እንዲሰፍን ሰርተናል፡፡ ይህ እኛን ከቱርክ፤ የህዳሴውን ግድብም ከአታቱርክ ግድብ ጋር ያለያየናል፡፡ ይህኛውን ክርክር <<ሙታሊብ ልክ ናቸው፤ እኛ ቱርክ አይደለንም፡፡ ኢትዮጵያዊ እንጂ፡፡ ግብፆች ደግሞ በደንብ ያውቁናል>> ብለን ብንዘጋው የሚሻል ይመስለኛል፡፡


እኝህ ሚኒስትር ሀገራቸው እንደገቡ በአዲስ አበባ ስለነበራቸው ቆይታም ተናግረዋል፡፡ በመካከላችን ያለውን ክፍተት ለማጥበብ ያቀረብናቸውን ሀሳቦች ሁሉ ኢትዮጵያ ውድቅ አድርጋለች ሲሉ ከስሰዋል፡፡ 


ዴይሊ ኒውስ ኢጂፕት ድረ ገፅ ደግሞ የሚኒስትሩን የቴሌቪዥን ንግግር የዘገበው <<የግብፅ ልዑካን ቡድን አጣብቂኝ ውስጥ ያስገቡንን ችግሮች ለመፍታት ያቀረባቸውን መፍትሄዎች በሙሉ ያለበቂ ምክንያት በኢትዮጵያ ውድቅ ተደርገዋል፡፡ ይህም ውይይቱን ምክንያት አልባ ወደመሆን አድርሶታል ብለዋል>> በሚል ነው፡፡


ሙታሊብ ቀጥለውም “መፍትሄ በማያመጣ ውይይት ውስጥ የምንቀጥል ሞኞች አይደለንም፡፡ ሌሎች የምንወስዳቸው ርምጃዎች ይኖሩናል” ብለዋል፡፡ እርምጃዎቹ ምን እንደሆኑ ባያብራሩም፡፡ መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ ከማለት ውጭ ምን እንላለን፡፡ ምክንያቱም የትኛውም እርምጃ ቢሆን ግብፅን የላይኛው ተፋሰስ ሀገር፤ ኢትዮጵያን ደግሞ የታችኛው ተፋሰስ ሀገር እንደማያደርጋት የሚጠፋን ሞኞች አይደለንም፡፡


በዚህ ዘገባ ላይ በእንግሊዘኛው "Ethiopian officials say they do want to harm Egypt. But when we ask them to put that on paper they refuse," said Abdel-Muttalib. የሚል አረፍተ ነገር አለ፡፡ ይህን ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን ንግግር ልዋስና ግብፆች ካላበዱ በስተቀር እንዲህ ይላሉ ብሎ ለማመን ይከብዳል፡፡ እኔ ከድረ ገፁ የአርትዖት ስህተት የተነሳ አፍራሽ ቃል /not/ ተዘላ ይመስለኛል፡፡ they do not want to harm Egypt ለማለት አስበው ማለት ነው፡፡ ባይሆንም ቢያንስ ለመልካም ጉርብትና ሲባል እንደዛ ነው ብለን ብናስብ ሳይሻል አይቀርም፡፡


በተደጋጋሚ የሀሰት መረጃ በመስጠት የሚታወቁት የሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ካሊድ ዋሲፍም ከሰኞው ውይይት በኋላ እኔስ ለምን ይቅርብኝ በሚያስመስል መልኩ በዚህ የግብፅን ጥቅም በማያስከብር ውይይት ላይ ሀገራቸው እንደማትካፈል ማረጋገጣቸውን ካይሮ ፓስት ድረ ገፅ ላይ ተዘግቧል፡፡ ሲቀልዱ ይሁን ከምራቸው ባይረዳኝም በዚሁ ድረ ገፅ እንዲህም ብለዋል፡፡

“የህዳሴው ግድብ አለም አቀፍ ተቀባይነት /legitimacy/ የለውም፡፡ ምክንያቱም እስካሁን አንድም ሀገር ግድቡ እንዲቀጥል ማፅደቁን አላስታወቀም፡፡”
እውነቴን ነው፤ ይህን እንኳን ሲቀልዱ መሆን አለበት፡፡ ቀልድ ካልሆነ ታዲያ የትኛው ሀገር ነው አፅድቄላችኋለሁ፤ ቀጥሉ እንዲለን የምንጠብቀው? የትኛውስ ሀገር ነው ግድብ ልገነባ ነው ፍቃድ ስጡኝ ወይም በፓርላማችሁ አፅድቁልኝ ሲል የሌላ ሀገርን ደጅ የሚጠናው? ግብፅስ አስዋንን ስትገነባ የስንት ሀገሮችን ፊርማ አሰባስባ ነው?


በመጨረሻም እደግመዋለሁ፡፡ ግብፆች መስራታችሁን ካላቆማችሁ ማውራታችንን አናቆምም ብለዋል፡፡ ይሄ ለክፉ የሚሰጥ አይደለም፡፡ እኛም እንዲህ ብለን ጉዳዩን ከደቡብ ኮሪያዎች ልምድ ጋር አስተሳስረንዋል፡፡ የደቡብ ኮሪያው የኤሌክትሪክ ኩባንያ ኤል ጂ እንዲህ የምትል መለያ አለችው፡፡ We create others talk. እናንተ አውሩ፤ እኛ እንሰራለን ለማለት ነው፡፡
Post a Comment