Monday, February 3, 2014

መክሸፍ እንደ ጎንደሩ ሰልፍ

Gonder 1
Gonder 2
Gonder 3
እውነቴን ነው የምላችሁ፤ አትሳደቡ፡፡ ልክ ስትሳደቡ የምረዳው ነገር ቢኖር እውነት ከናንተ ጋር እንዳልሆነች ነው፡፡ አሁን ትናንትና ጎንደር ከተማ ውስጥ የተካሄደው የሰማያዊ ፓርቲ የተቃውሞ ሰልፍ ምን ያህል ሰው እንደወጣበት በፎቶ ወይም በቪዲዮ አሳዩኝ ስላልኩ ይህ ሁሉ ስድብ ሊወርድብኝ ይገባል አንዴ? ስድባችሁ ያስረዳኝ ስትፅፉ የነበረው የውሸት መሆኑን ነው፡፡ ለነገሩ አይደንቀኝም፤ ምክንያቱም እውነት ተናግራችሁ ስለማታውቁ፡፡
ቆይ ያን ሁሉ የፅሁፍ መልዕክት በፌስቡክ ስትለቁልን፤ /ህዝቡ እየጎረፈ ነው፤ ከተማዋ በሞንታርቦ ተደበላለቀች፤  አደባባዮች ተጨናነቁ…/ ምስል ያጠራችሁ ሰልፉ ፌስቡክ ላይ ካልሆነ /ወይም በኔ አገላለፅ ኢንተርኔት ካፌ ውስጥ ካልሆነ/ በስተቀር እንዴት የተቀረፀ ነገር ይጠፋዋል?
እስኪ ሁለት ንፅፅሮችን ላሳያችሁ፡፡
Wondem Mequanent---- እንዲህ አለ፡፡
<<ሉዓላዊነታችንን አናስደፍርም!!
አባቶቻችን ያስረከቡንን መሬት አሳልፈን አንሰጥም፣ ወያኔ አምባገነን ነው፣ ወያኔ ሌባ ነው፣ 23 አመት ተቀለደብን፣ በሉዓላዊነት ቀልድ የለም የሚሉ መፈክሮች እየተሰሙ ነው። ዳር ቆሞ ሲያይ የነበረው ሰው እየተቀላቀለ ነው :: ወደ 60ሺ ሕዝብ ወቷል>>
 Lemi Sime Demie------ ደግሞ እንዲህ አለ፡፡
<<እስካሁን የጎንደሩን ሰልፍ በሚመለከት ሁለት ነገሮች ፈገግ አሰኝቶኛል፡፡ አንደኛው በፓርቲው ደጋፊ የተሰጠ ሲሆን እንዲህም ይላል፡
“ህዝቡ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትን "ስንፈልጋቹህ አገኘናቹህ" እያላቸው ነው” …
ሁለተኛው ከአንድ አስተያየት ሰጭ የተሰጠ ‘comment’ ነው፡፡ እንዲህም ይላል፡፡
I AM AT GONDER AND ALL WHAT I C IS 22 KIDS PLAYING FOOTBALL @ MESKEL SQUARE’ lol>>
እነዚህ ሁለት ሰዎች በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ውግንናቸው ለማን እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ግን የግል አመለካከታቸውን ትተን ባስቀመጡት አሃዝ ላይ እንነጋገር፡፡ ለወንዱሙ መኳንንት የሰልፈኛው ቁጥር 60ሺ ነው፤ ለለሚ ሲሚ ደሚ ደግሞ /በአስተያየት የደረሰው/ የሰልፈኞቹ ቁጥር 22 ነው፡፡
በሁለቱ ቁጥሮች መካከል ያለው ልዩነት የትየለሌ ነው፡፡ ግን ማጋነን ሊኖረው ይችላል ብለን እናስብና ቁጥሮቹን ወደ ማደራደር እንግባ፡፡ ለምሳሌ ወንድሙን <አይ ግዴለም አጉሊ መነፅር አድርጎ ይሆናል> እንበልና ቁጥሩን ወደ 50ሺ ዝቅ እናድርግለት፡፡ ለለሚ ደግሞ <እሱን ተውት ሆዳም ካድሬ ሆኖ ነው> እንበልና ቁጥሩን ወደ 100 ከፍ እናድርግለት፡፡ ከዚህ በኋላ ከሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ አስተባባሪዎችና ልሳናቸው ሆኖ ከዋለው ኢካዴፍ ያገኘናቸውን ምስሎች እንመልከት፡፡
ጎንደር 1 በሚለው ምስል ላይ ያሉትን ሰዎች መቁጠር ጀምሬያለሁ፡፡ 80 ናቸው፡፡ ‘ሆዳም ካድሬ’ ላለመባል ብዬ ዳር ላይ የሚታዩትን ጥቁርና ነጭ ድንጋዮችም እንደሰው ነው የቆጠርኳቸው፡፡
ጎንደር 2 በሚለው ምስል ላይ ያሉት ደግሞ ከዛም ያነሱ መሆናቸው አያጠራጥርም፡፡ ለመተቸት ቢሆን ኖሮ <እዚህ ላይ የሚታዩት ከሞላ ጎደል በሙሉ እድሜያቸው ለአቅም ፖለቲካ ሰልፍ ያልደረሱ ህፃናት ናቸው> የሚል ክርክር ማንሳት እችል ነበር፡፡ ይቅር ትቼዋለሁ፡፡
ጎንደር 3 በሚለው ምስል ላይ የሚታዩት ሰዎች ቁጥር 15 ያክል ነው፡፡ ግን መሃል ላይ ያለችው ሴት ድፍረቷና ሰንደቅ አሰቃቀሏ ስላስደነቀኝ የ100 ደጋፊ ግምት ሰጥቻታለሁ፡፡ በመሆኑም ይህ አሃዝ ወደ 115 ከፍ ብሏል፡፡

/ይቅርታ አሁን በዛው በሰልፉ ላይ ተሳታፊ ከነበረ የፓርቲው አባል/ደጋፊ በደረሰኝ አስተያየት መሰረት ይህች ሴት ፎቶውን የተነሳችው ጎንደር ሳይሆን አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ ነገር ግን ጎንደር ላይ ቅስቀሳው ‘መጧጧፉን’ ለማሳየት ብለው ፎቶውን ተጠቅመውበታል፡፡ እኔንም አሳስተውኛል፡፡ በመሆኑም 115 የሚለው ቁጥር በ0 እንዲጣፋልኝ እጠይቃለሁ፡፡/
ሁለት የቁጥር ግምቶችን አየን፤ ሶስት የፎቶ ማስረጃዎችንም አየን፡፡ ታዲያ የሰው ብዛት  እውነት ከማ ጋር መሆኗን ነው የሚያሳየው? ማንም አይን ያለው መፍረድ እንሚችለው ብዛቱ 60ሺ ሳይሆን ጥቂት መቶዎች ብቻ ቢሆን ነው፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ፤ የጎንደሩ ሰልፍ ከሽፏል፡፡
መክሸፍ ግን ምንም አይደለም፡፡ አሁን ከሸፈ ማለት ሁልግዜ ይከሽፋል ማለትም አይደለም፡፡ ለምሳሌ ወደ ድንበሩ በጣም ጠጋ ቢሉ /ሰልፉን ቋራ፤ አርማጭሆ…ላይ ቢያደርጉት/ የተሻለ የሰው ብዛት ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ይሄን ግን ግምት እንጂ ምክር አድርጋችሁ እንዳትወስዱብኝ፡፡ ከመክሸፉ በላይ የሚያሳስበው ግን ውሸቱ ነው፡፡ ለምን ይዋሻል?
ልብ በሉ፤ የምሞግታችሁ በራሳችሁ ካሜራ በተነሳ ፎቶ፤ በራሳችሁ ሚዲያ በተዘገበ ሪፖርት ነው፡፡ በኢቲቪ ካሜሬ ነው እንዳትሉ ብዬ ማለት ነው፡፡ ትናንት እንደተናገርኩት እዚህ አዲስ አበባ መጥታችሁ ልታቀነባብሩት ካልሆነ በስተቀር እስካሁን በፌስቡክ  ያገኘኋቸው ፎቶዎቻችሁ እነኚህ ብቻ ናቸው፡፡ ሌላ ካላችሁ አውጡትና እንነጋገርበት፡፡
በርግጥ ከሰልፉ አስተባባሪዎች አንዱ <<በምስልና በቪዲዮ መረጃዎችን በጊዜ መልቀቅ ባለመቻላችን አስቀድሜ ይቅርታ . . . በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ ስንመለስ በበቂ ሁኔታ እናሰራጫለን! ለጊዜዉ ግን ጎንደር ከገባን አንስቶ በተከሰተው የኔትዎርክ ችግር እንደልብ ማህበራዊ ድረገፆችን መጠቀም አልቻልንም!>> ብሏል፡፡ እነዚህን ፎቶዎች የለጠፋችሁት ታዲያ በኔት ወርክ ካልሆነ በምን ወርክ ነው? ለማንኛውም እንዳትጠፋ፤ እንጠብቅሃለን፡፡
ግን የጎንደርን ህዝብ ምን ነካው? እኔ ስከማውቀው ድረስ የጎንደር ሰው እንግዳ አክባሪ ነው፡፡ ከተለያየ ሀገር የሚጎርፍለነትን ቱሪስት በጨዋ ባህሉ አክብሮ፤ አስደስቶ ነው እንግዶቹን የሚመልሰው፡፡ ምነዋ ታዲያ ለአቶ ይልቃል ጌትነት እንዲህ ጨከነባቸው? እሳቸውም እኮ ከአሜሪካ የስራ ጉብኝታቸው ነበር ተንደርድረው ጎንደር የገቡት፡፡
ደሞ እኮ የጎንደር ህዝብ ደስተኛና ጭፈራ የሚወድ ነው፡፡ እንዲያ ሙዚቃ በሞንታርቦ ሲለቀቅለት ነሸጥ አድርጎት ያልወጣው ምን ነክቶት ነው? ግድ የላችሁም ሰማያዊ ፓርቲ የጎንደር ህዝብን ያሳዘነበት የሆነ ነገር አለ፡፡
Post a Comment