Thursday, January 2, 2014

እኔና የተከበሩ ግርማ ሰይፉ፤ በጅግጅጋበኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የተከበሩ ግርማ ሰይፉ በ8ኛው የብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ላይ ከተሳተፉ በኋላ ምልከታቸውን በፋክት መፅሄት ላይ አስፍረዋል፡፡ እኔም ይህን ፅሁፍ በፋክት መፅሄት ላይ ያወጣሁት ለአቶ ግርማ ምላሽ ለመስጠት ሳይሆን በአንዲት ከተማ ውስጥ ከርመን ጥሬ ሃቆችን ያየንበት አግባብ ሃራምባና ቆቦ ቢሆንብኝ ነው፡፡
አቶ ግርማ ሰይፉ በፅሁፋቸው ሰፊ ትኩረት የሰጡበት ጉዳይ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ያለው የሰላም ሁኔታ ነው፡፡ በርግጥ ክልሉ ለአልሸባብ ሽብር ቡድን ካለው ቅርበት አንፃር ዝግጅቱ ያለምንም የሽብር አደጋ መጠናቀቁ ስኬት ተብሎ የሚፈረጅ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ይህ ስኬት የተመዘገበበትን አግባብ ግን አጣጥለውታል፡፡ እንደርሳቸው ለስኬቱ ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራዊት በአካባቢው መስፈሩ (በሳቸው አገላለፅ በህዝቡ ቁጥር ልክ)፤ ባጃጆች እንዳይነቃነቁ መታገዳቸውና በየሆቴሉና በየመንገዱ ፍተሻ መብዛቱ ናቸው፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ያለኝን ግላዊ እይታ ከማቅረቤ በፊት ግን የሃቅ ግድፈቶችን ማስረዳት ተገቢ ይሆናል፡፡ የመጀመሪያው የሰራዊቱ ብዛት ነው፡፡ እኔም ከዚህ በዓል በፊት ወደ ከተማዋ ለአራት ግዜ ስመላለስ ይህን ያህል የሰራዊት ብዛት አላየሁም፡፡ በዚህ በዓል ላይ በሰራዊቱ አይነትና ብዛት ላይ ግልፅ ጭማሪ ታይቷል፡፡ ይህ ጭማሪ ግን አቶ ግርማ እንዳሉት በህዝቡ ቀርቶ በተሳታፊ እንግዶች ልክ የሚገለፅ አይደለም ብቻ ሳይሆን ክልሉ ካለው የደህንነት ስጋት አንፃር እዚህ ግባ የማይባል ነው፡፡
ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ባገኘሁት መረጃ መሰረት በዚህ በዓል ላይ ለመሳተፍ ከ7ሺ በላይ እንግዶች ወደ ጅግጅጋ ከተማ ገብተዋል፡፡ የሰራዊቱ ብዛት መረጃ ባይኖረኝም ማንም በበዓሉ ላይ የተሳተፈ እንደሚረዳው ግን የተሳታፊዎችን 1በመቶ እንኳን ሊሆን የሚችል አይደለም፡፡ ባጃጅ ታክሲዎች እንዳይንቀሳቀሱ ታግደዋል ያሉትም ቢሆን ከእውነት የራቀ ለሀሰት የቀረበ እይታ ነው፡፡ ደፍሬ ሀሰት ነው ያላልኩት ባጃጆቹ በዋናው አስፋልት ላይ እንዳይንቀሳቀሱ መታገዳቸው ሃቅ ስለሆነ ነው፡፡ ከዋናው አስፋልት ውጭ ባሉ መስመሮች ላይ ግን የተለመደው ስምሪት ነበራቸው፡፡
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ታዲያ አቶ ግርማ የሰራዊቱን ቁጥር በ50ና በ60 እጥፍ ለማባዛት፤ በአንድ መስመር ላይ ያለን የትራፊክ እንቅስቃሴ መቋረጥ የመላ ከተማይቱ አስመስለው ለማቅረብና በሆቴሎችና እንግዶች ባረፉባቸው ቦታዎች ያለን የደህንነት ፍተሻ “በየመንገዱ” ወደሚል ፅንፍ ለመውሰድ ምን አነሳሳቸው?
በመዲናችን አዲስ አበባም ሆነ ሌሎች ከተሞች እንዲህ ያሉ ትልልቅ ስብሰባዎች ሲኖሩ የመንገዶች መዘጋትና ለውጥ መደረግ አዲስ አይደለም፡፡ ከተለመደው የተለየ የደህንነትና የጥበቃ ሰራዊት ስምሪት መደረጉንም ተላምደንዋል፡፡ ስብሰባው በዲፕሎማሲ ስራችን ካለው ፋይዳ አንፃር እንመዝነው ካልሆነ በቀር እንጅ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ በመዲናችን ሲካሄድ በተለይ በትራንስፖርት ላይ ያለው አሉታዊ አስተዋፆ የሚናቅ አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከቤተ መንግስት ሲወጡ እግር ጥሎን ከተገጣጠምን ለረጅም ደቂቃዎች ባለንበት እንድንቆም እንታዘዛለን፡፡ አልሸባብ በኬንያ ላይ የፈፀመውን የሽብር ተግባር ኢትዮጵያም ላይ ለመድገም መዛቱንና የደህንነት መስሪያ ቤታችንም ምልክቶች መታየታቸውን ካረጋገጠ ወዲህ የጥንቃቄ ደረጃውም ከፍ ማለቱን አቶ ግርማ ሰይፉ ይቅሩና ማንም የኔ ቢጤ የሚታዘበው ነው፡፡
በመዲናችን ያለው ሁኔታ እንዲህ በሆነበት ለአመታት የአልሸባብና ኦብነግ መናኸሪያ በነበረው የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ነገሮች ሁሉ አማን በአማን ይሆናሉ ብሎ መገመት ይከብዳል፡፡ ለዚህ የሚመጥን ጥንቃቄ ያለማድረግም ክልሉ በኦብነግ የሽብር ቡድን ተደጋጋሚ ጥቃት የደረሰበት መሆኑንና የውጭ ሀገር ዜጎች ጭምር በጅምላ መጨፍጨፋቸውን መዘንጋት ነው፡፡ ለኛ ብቻ ሳይሆን ለአለምም የስጋት ምንጭ የሆነው አልሸባብ ከሚፈለፈልባት ሱማሊያ ጎረቤት በሆነው ክልላችን የውጭ ሀገር መሪዎችን፤ አምባሳደሮችን፤ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችንና ራሳቸውን አቶ ግርማን ጨምሮ ሌሎችም የፖለቲካ አመራሮች የተሳተፉበትን የ10ሺዎች በዓል የሚመጥን ጥበቃ ያለማድረግ ከእንዝህላልነት ውጭ ምን ትርጓሜ ሊሰጠው ይችላል?
በኔ የግል አመለካከት አቶ ግርማ ወደዚህ የብዜትና የማስፋት ጨዋታ የገቡት የክልሉ ፀጥታ ባለቤት ህዝቡ ሳይሆን ሰራዊቱ ብቻ እንደሆነና ይህም ዘላቂነት እንደሌለው ለማስገንዘብ ነው፡፡ እርሳቸው እንደገለፁት <<የዘላቂነቱ ጉዳይ>> ወደፊት አብረን የምናየው ቢሆንም የባለቤትነት ጉዳይ ላይ ግን አሁንም ለአስተያየት የሚከብድ አይደለም፡፡
የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልልን ሰላም በማስፈን ረገድ ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት የመከላከያ ሰራዊቱና የክልሉ ልዩ ሃይል ናቸው፡፡ የትም ቢሆን ፀጥታንና ደህንነትም የማረጋገጥ ተልዕኮን የሚሸከመው የታጠቀው ሃይል ነው፡፡ ይህ ሃይል ሃላፊነቱን ሲወጣ ግን ህዝቡን ከጎኑ ማሰለፍ ካልቻለና በተቃራኒው ህዝቡን ካገለለ ስኬታማ ሊሆን አይችልም፡፡ ይልቁንም ለፀረ ሰላም ሃይሉ ምሽግ ነው የሚያበጅለት፡፡ የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል አሁን ለደረሰበት የሰላም ደረጃ የህዝቡ ሚና በዚህ ማዕቀፍ የሚታይ ነው፡፡ በሰራዊቱ የፀረ ኦብነግና አልሸባብ እንቅስቃሴ ላይ ህዝቡ እምነት ባይኖረውና አሻራውን ባያሳርፍበትማ ይህ በዓል ብቻ ሳይሆን የእለት እንቅስቃሴውም እንዳለፉት አመታት በተኩስ ድምፅ የታጀበ በሆነ ነበር፡፡ ስለዚህ የሰላሙ ባለቤት ሰራዊቱና ህብረተሰቡ ነው፡፡
ካልተሳሳትኩ በስተቀር የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ በበዓሉ በሰላም መጠናቀቅ ደስተኛ አይመስሉኝም፡፡ ምክንያቱሞ ኢሕአዴጋዊ አይደሉማ፡፡ በፅሁፋቸው ላይ “ኢሕአዴጋዊ አንባቢዎቼ ደስ ይላቸው ዘንድ ከዝግጅቱ ዋና ስኬት ልጀምር፡፡ የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ለአልሸባብ ታጣቂዎች ካለው ቅርበት አንፃር ቡድኑ አንድ ክስተት በመፍጥር ለስሙ የሚመጥን የሽብር ተግባር መፈፅም ያለመቻሉም ሆነ ያለመሞከሩ ለኢትዮጵያ መንግስትና ለክልሉ መስተዳድር ስኬት ነው” ብለዋል፡፡ ወደፅሁፋቸው ማገባደጃም በፓናል ውይይቱ ላይ አስተያየት ስለሰጠች አንዲት ከባህር ዳር ዩንቨርስቲ የመጣች ተማሪ ያነሱና <<ሀገሩ ተኩስ በተኩስ ነው ተብላ ካልመጣች በስተቀር አሁን ጅግጅጋ ያየችው እንዲህ የሚያስፈነድቅ አለመሆኑን የሚነግራት መኖር ነበረበት>> ብለዋል፡፡
እነኝህ ንግግሮቻቸው <<አቶ ግርማ የሚደሰቱት ወይም የሚፈነድቁት ምን ቢሆን ነበር?>> የሚል ጥያቄ አጫሩብኝ፡፡ እንዴ፤ በጅግጅጋ ሰላም መሆን ለመደሰት እኮ የግድ ጅግጅጋን ወክሎ ፓርላማ መግባትን አይጠይቅም፡፡ ጠበብ እናርገው ካልንም እርሳቸው በተመረጡበት መርካቶ ውስጥም ሱማሌያውያን አሉ፡፡ እኔ እንደማስበው ደግሞ እርሳቸው ወደ ጅግጅጋ የተጓዙት በአሉን በሰላም አክብረው በሰላም ወደቤታቸው ለመመለስ እንጅ አደጋ ደርሶባቸው ገዥውን ፓርቲና መንግስትን በእንዝህላልነት ለማስወቀስ አይደለም፡፡ ታዲያ ቢያንስ ይህ አላማቸው በመሳካቱ ምናለ አብረን ብንደሰት?
ከበዓሉ ዝግጅቶች ሁሉ አቶ ግርማን የማረኳቸው የፓናል ውይይቶቹ ናቸው፡፡ ሌላውንማ <<ጭፈራና ዳንኪራ>> ሲሉ ገልፀውታል፡፡ እርሳቸው እንዳሉትም ከየዩንቨርስቲ ተወክለው የመጡ ተማሪዎች በውይይቶቹ በነፃነት የፈለጉትን ይናገሩ ነበር፡፡ አንደኛዋ የጅግጅጋን የሰላም ሁኔታ አድንቃ ብታስከፋቸውም ሌሎቹንስ “{ንግግራቸው} ነፃነታቸውን ስለሚያሳይ ሊበረታታ ይገባዋል” ሲል አሞካሽተዋል፡፡ ተማሪዎቹ በብሄር ከፋፍላችሁ ገነጣጠላችሁን፤ ያለፈ ታሪክ አታንሱብን፤ ትምህርት ጥራት ወደቀ፤ ወዘተ የሚሉ አስተያየቶችን በድፍረት ተናግረዋል፡፡ ይሄን ያዳመጡ ታዲያ በሻይ ሰዓት ስለሁኔታው የየራሳቸውን ትንታኔ ሰጥተዋል፡፡ አንዳንዶች ሾልከው የገቡ መሆን አለባቸው ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ ዩንቨርስቲዎቹ በደንብ የማያዉቋቸውን ተማሪዎች ነው የላኩት ብለዋል፡፡ አፈጉባዔ አባዱላ ገመዳ ግን እነዚህ ተማሪዎች የዲሞክራሲያችን ውጤቶች ናቸው፤ ይህ አይነት ልምድም በሁሉም መድረኮች መዳበር አለበት ሲሉ በመድረኩ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ሔኖክ ረታ የተባሉ ፀሃፊም በታህሳስ 09/ 2006 ሪፖርተር እትም <<የዚህ ትውልድ መነቃቃት የተንፀባረቀበት>> ሲሉ መድረኩን ገልፀውታል፡፡
ከፓናሎቹ ጋር የተያያዘ ገጠመኜን ላውጋችሁና ፅሁፌን ላጠናቅ፡፡ ጥናታዊ ፅሁፎቻቸውን ካቀረቡት ምሁራን መካከል አንዱ ሴንተር ፎር ደቨሎፕመንት ስተዲስ የተባለው ቲንክ ታንክ ስራ አስኪያጅ ዘፋኒያ አለሙ ናቸው፡፡ ፅሁፋቸውን ባቀረቡ ምሽት አብረን እየተወያየን ሳለ በፓናሉ ላይ አቶ ግርማ ሰይፉ ተገኝተው እንደነበር ነገርኳቸው፡፡ ደነገጡ፡፡
“ምነው?” አልኳቸው፡፡
“ታድያ ምነው ሳይናገሩ ዝም ብለው ወጡ?” አሉኝ፡፡ የፌዴራል ስርዓቱና ህገመንግስታዊ ድንጋጌዎች ላይ ተማሪዎች ሳይቀሩ ነፃ ውይይት ባደረጉበት በዚህ መድረክ አቶ ግርማ የሚሰማቸውን ሊናገሩበት፤ የፓርቲያቸውን አቋም ሊያስተዋውቁበት ሲገባ ዝም ማለታቸው በርግጥም ያስገርማል፡፡
“እሳቸው የሚናገሩበት ሌላ መድረክ አላቸው” አልኳቸው፡፡ ፋክትን አስቤ ነበር፡፡ እንዳልኩትም ተናገሩ፡፡
በነገራችን ላይ አቶ ግርማ እኝህን ጥናታዊ ፅሁፍ አቅራቢ “የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ስርዓት ብዝሃነትን አያስተናግድም ብለው በድፍረት ተናገሩ” ሲሉ ፋክት ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ ወቅሰዋቸዋል፡፡ አቶ ዘፋንያ ግን ትችቱን እንዳነበቡት፤ ነገር ግን እሳቸው በዚህ መልኩ እንዳላስቀመጡት አረጋግጠውልኛል፡፡
Post a Comment