Wednesday, January 8, 2014

ከዲሲ ቦሌ፤ ከቦሌ 4 ኪሎ? ቅርብ ነው

በአሜሪካ ሀገር የሚኖር አንድ <<የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ም/ቤት>> ብሎ ለራሱ ትልቅ ስም የሰጠ /ምን ልበለው?/ ፓርቲ፤ ድርጅት፤ መያድ… እንዳለ መቼም በስሚ ስሚ ሳታውቁ አትቀሩም፡፡ ይሄ ነገር የተመሰረተው በሰኔ 2004 ነው፡፡ ዋና ፅ/ቤቱን ዋሽንግተን ዲሲ አድርጎ ማንኛውንም አይነት የወያኔ/ ኢህአዴግ መንግስት መጣል የሚያስችሉ እቅዶችን መንደፍና መተግበር ደግሞ አላማው ነው፡፡
ም/ቤቱ በተመሰረተ ከወር በኃላ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያ የወቅቱ ጉዳይ ‘ያሳሰባቸው’ ግለሰቦች ታዲያ ሰብሰብ አሉና <እንግዲህ መለስ ሞቷል፤ ከሱ ሌላ ደግሞ ሊያስተዳድራት የሚችል ሰውም ፓርቲም የለም፤ ያኔ በ1997 ስንፈልገው ያጣነው የዚች ሀገር እጣ ፈንታ አሁን በኛ ትከሻ ላይ መውደቁ ነው፤ ምን ይሻላል?> ሲሉ መከሩ፡፡
መጨረሻ የደረሱበት ማደማደሚያም ለዚህ ‘ለማይቀረው ታሪካዊ ሃላፊነት’ ራሳቸውን በፍጥነት ማደራጀት እንደሚገባ ነበር፡፡ ከዛም ላሉት ዋና ዋና የመንግስት ስልጣን ቦታዎች ራሳቸውን መደቡና በተጠንቀቅ ቆሙ፡፡ እንደሰማሁት ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የታጩት ዶ/ር ፍሰሃ እሸቱ ነበሩ፡፡ ከዲሲ እስከ ቦሌ፤ ከቦሌ እስከ 4 ኪሎ? ምናላት ቅርብ ነች፡፡
ከታላቁ መሪ ሞት በኃላ የተከሰተው ግን ለነሱ ያልጠበቁት ነበር፡፡ ሁሉ ነገር እንደነበረ ሆነ፡፡ ክፍት የስልጣን ቦታም አልተገኘ፡፡ አንድ ሰሞን ወዲያ ወዲህ ቢሉም ሁሉ ነገር ፍሬ አልባ ሆነባቸውና ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርገው ተውት፡፡
አሁን ደግሞ <የጠፋነው የሽግግር ም/ቤት ቻርተር ስናረቅ ነበር> እያሉ ነው፡፡ ለማንኛውም ማርቀቁ አመት ፈጀብን ያሉትን ባለ 14 ገፅ የሽግግር ግዜ ህገ መንግስት ተብዬውን አነበብኩት /enjoy አደረግኩት ብል ይሻለኛል/፡፡ አንዳንዶቹን አንቀፆች ላሳውቃችሁ፡፡ የመረጥኳቸው ይበልጥ ስላዝናኑኝ ነው፡፡
መግቢያ፤ “ይዋል ይደር እንጅ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማሸነፉና የወያኔ ፀረ ኢትዮጵያ ስርዓት መገርሰሱ አይቀሬ ነው፡፡”
(እንግዲህ አሁን <ይዋል ይደር እንጅ> ወደሚል የተስፋ ቆራጭ ንግግር ያስገባቸው አገዛዝ ከአመት በፊት <የሳምንታት እድሜ የቀረው> ሲሉት የነበረው ነው፡፡)
አንቀፅ 9፤ “የኢትዮጵያ ዋና ይፋ የስራ ቋንቋ አማርኛ ሲሆን ኦሮምኛ፤ ትግሪኛ፤ ሶማሌኛ እና እንግሊዘኛ ተደራቢ የስራ ቋንቋዎች ናቸው፡፡”
(በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አማርኛ የፌዴራል መንግስት የስራ ቋንቋ እንደሆነ ተመዝግቧል፡፡ አሁን ግን አማርኛ “ዋና” “ይፋ” የሚሉ ቅፅሎች ተጨምረውላት ሞቅ ደመቅ ብላ መምጣቷን ልብ ይሏል፡፡)
አንቀፅ 11፤ሐ፤ “እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጥምር ዜግነት የመያዝ መብቱ የተረጋገጠ ነው፡፡ የሌላ ሀገር ዜግነት በመቀበሉ ምክንያት ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን ያጣ ማንም ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱ ይከበርለታል፡፡”
(የአሜሪካ ዜግነት ይዞ በኢትዮጵያ ባለስልጣን ለመሆን ይችን አንቀፅ ማስገባት የግድ ይላላ፡፡)
አንቀፅ 17፤ “ዜጎች ለራስ ጥበቃና ለአደን የሚጠቀሙባቸው ሽጉጦችና ጠመንጃዎች ባለቤት የመሆን፤ የመግዛት እና የመሸጥ መብት አላቸው፡፡”
(ይሄ ጥሩ ይመስላል፡፡ መጀመሪያ ከሚገዙት አንዱ መሆኔ አይቀርም፡፡ የጦር መሳሪያ ንግድ የስራ እድል ሊፈጥርም ይችላል፡፡)
አንቀፅ 18፤ “ከንብረት ልውውጥ ቀረጥ ውጭ መንግስት ከግለሰቦች ደሞዝ ላይ ግብር መውሰድ አይችልም፡፡”
(ይሄም አሪፍ ነው፡፡ በተለይ ለከፍተኛ ደሞዝ ተከፋዮች፤ ከአርሶ አደሩስ?)
አንቀፅ 38፤ ለ፤ “ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆነው ግለሰብ ስራ በሚጀምርበት ጊዜ እድሜው ከ25 ማነስ የለበትም፡፡”
(የ26 አመት ወጣት ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲኖረን የሚፈቅድ በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል፡፡)
በነገራችን ላይ ከመለስ ሞት በኋላ ኪሎውን ቤተ-መንግስት ለመረከብ ሰፍ ብሎ የነበረው ምክር ቤት  <<የህዳሴ ቦንድ የሚባል ነገር በአሜሪካ መሸጡ ይቁም>> ብሎ ለአሜሪካ መንግስት አቤት ብሎ የነበረ ነው፡፡ <<የገዙትም ገንዘባቸው ይመለስላቸው>> ብሎ ነበር፡፡ ለኦባማ አስተዳደር የፃፈውን ደብዳቤ ማየት ከፈለጉ በዚህ ሊንክ ይጓዙ፡፡
Post a Comment