Friday, January 24, 2014

ኢሳት የድርጅት ሎሌ ነው- አበበ ገላው


Editor’s note: የተቃዋሚ አክቲቪስት የሆነው አበበ ገላው በግንቦት 2004 የቀድሞው ጠ/ሚኒስተር መለስ ዜናዊ የተገኙበት ስብሰባ ላይ የተቃውሞ ጩኸት ካሰማ ከወራት በኋላ፤ ከግንቦት ሰባት ድርጅት መሪ ከዶ/ር ብርሀኑ ነጋ የበለጠ ትኩረት ስቧል በሚል ከኢሳት ገለል እንዲል ተደርጎ በነበረበት ወራት በግል ያደረጋውን ንግግር የድምጽ ቅጂ፤ HornAffairs ከታማኝ ምንጮች አግኝቷል፡፡
የአበበ ገላውን ኑዛዜ የHornAffairs ብሎገር የሆነው ከበደ ካሣ እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡
**************
ይህን የ11 ደቂቃ የተቀረፀ ድምፅ ጋብዣችኋለሁ፡፡ ከየት አመጣኸው እንዳትሉኝ፡፡ ዊክ ሊክስ ወይም ስኖውደን ብቻ ናቸው እንዴ አፈትልኮ የወጣ መረጃ የሚያሰረጩት? በመረጃው ትክክለኛነት ላይ ተማምናችሁ ዝም ብላችሁ ኮምኩሙት፡፡

እንደኔ እንደኔ ሙሉውን ቅጂ ብታዳምጡት መልካም ነው፡፡ በደካማ ኢንተርኔትና በጊዜ ማጣት የተነሳ ሙሉውን ማድመጥ ካልቻላችሁ ግን ሙሉ መረጃው በዚህ ፅሁፍ ቀርቦላችኋል፡፡ ልዩነቱ ይሄኛው በፅሁፍ ሲሆን ያኛው በድምፅ መቅረቡ ነው፡፡ ታዲያ ልክ እንደ አበበ ገላው እዚህም እዚያም መዝለል እንዳይሆንባችሁ ታዲያ ሙሉ ንግግሩ በሶስት አበይት ርዕሶች ተደራጅቶላችኋል፡፡ ሲያስፈልግ ደግሞ ንግግሩ እንደወረደ በጥቅስ ምልክት ውስጥ ተቀምጧል፡፡

Wednesday, January 8, 2014

ከዲሲ ቦሌ፤ ከቦሌ 4 ኪሎ? ቅርብ ነው

በአሜሪካ ሀገር የሚኖር አንድ <<የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ም/ቤት>> ብሎ ለራሱ ትልቅ ስም የሰጠ /ምን ልበለው?/ ፓርቲ፤ ድርጅት፤ መያድ… እንዳለ መቼም በስሚ ስሚ ሳታውቁ አትቀሩም፡፡ ይሄ ነገር የተመሰረተው በሰኔ 2004 ነው፡፡ ዋና ፅ/ቤቱን ዋሽንግተን ዲሲ አድርጎ ማንኛውንም አይነት የወያኔ/ ኢህአዴግ መንግስት መጣል የሚያስችሉ እቅዶችን መንደፍና መተግበር ደግሞ አላማው ነው፡፡
ም/ቤቱ በተመሰረተ ከወር በኃላ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያ የወቅቱ ጉዳይ ‘ያሳሰባቸው’ ግለሰቦች ታዲያ ሰብሰብ አሉና <እንግዲህ መለስ ሞቷል፤ ከሱ ሌላ ደግሞ ሊያስተዳድራት የሚችል ሰውም ፓርቲም የለም፤ ያኔ በ1997 ስንፈልገው ያጣነው የዚች ሀገር እጣ ፈንታ አሁን በኛ ትከሻ ላይ መውደቁ ነው፤ ምን ይሻላል?> ሲሉ መከሩ፡፡

Thursday, January 2, 2014

እኔና የተከበሩ ግርማ ሰይፉ፤ በጅግጅጋበኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የተከበሩ ግርማ ሰይፉ በ8ኛው የብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ላይ ከተሳተፉ በኋላ ምልከታቸውን በፋክት መፅሄት ላይ አስፍረዋል፡፡ እኔም ይህን ፅሁፍ በፋክት መፅሄት ላይ ያወጣሁት ለአቶ ግርማ ምላሽ ለመስጠት ሳይሆን በአንዲት ከተማ ውስጥ ከርመን ጥሬ ሃቆችን ያየንበት አግባብ ሃራምባና ቆቦ ቢሆንብኝ ነው፡፡
አቶ ግርማ ሰይፉ በፅሁፋቸው ሰፊ ትኩረት የሰጡበት ጉዳይ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ያለው የሰላም ሁኔታ ነው፡፡ በርግጥ ክልሉ ለአልሸባብ ሽብር ቡድን ካለው ቅርበት አንፃር ዝግጅቱ ያለምንም የሽብር አደጋ መጠናቀቁ ስኬት ተብሎ የሚፈረጅ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ይህ ስኬት የተመዘገበበትን አግባብ ግን አጣጥለውታል፡፡ እንደርሳቸው ለስኬቱ ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራዊት በአካባቢው መስፈሩ (በሳቸው አገላለፅ በህዝቡ ቁጥር ልክ)፤ ባጃጆች እንዳይነቃነቁ መታገዳቸውና በየሆቴሉና በየመንገዱ ፍተሻ መብዛቱ ናቸው፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ያለኝን ግላዊ እይታ ከማቅረቤ በፊት ግን የሃቅ ግድፈቶችን ማስረዳት ተገቢ ይሆናል፡፡ የመጀመሪያው የሰራዊቱ ብዛት ነው፡፡ እኔም ከዚህ በዓል በፊት ወደ ከተማዋ ለአራት ግዜ ስመላለስ ይህን ያህል የሰራዊት ብዛት አላየሁም፡፡ በዚህ በዓል ላይ በሰራዊቱ አይነትና ብዛት ላይ ግልፅ ጭማሪ ታይቷል፡፡ ይህ ጭማሪ ግን አቶ ግርማ እንዳሉት በህዝቡ ቀርቶ በተሳታፊ እንግዶች ልክ የሚገለፅ አይደለም ብቻ ሳይሆን ክልሉ ካለው የደህንነት ስጋት አንፃር እዚህ ግባ የማይባል ነው፡፡