Monday, September 1, 2014

ይህን ከምሰማስ እንኳን ወጣሁ

ትናንት አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ /አንድነት/ 6 አመት የምስረታ በዓሉን አክብሯል፡፡ እኔም በበዓሉ ላይ ተገኝቼ ነበር፡፡ / ግዛቸው አንድ በጣም ረጅምና አንድ መካከለኛ በድምሩ ሁለት ንግግሮች ካደረጉ፤ ሌሎችም በተመሳሳይ ግጥሞችን ካቀረቡ፤ ዳቦ ከተቆረሰ፤ ወዘተ በኋላ ሰዓቱ እየገፋ ሲሄድ ሌላ ጉዳይ ነበረኝና ወጣሁ፡፡
ታዲያ ከወጣሁ በኋላ የፓርቲው ኤዲቶሪያል ቦርድ አባል የሆኑት አቶ አስራት ጣሴም ንግግር አድርገው ነበር አሉ፡፡ እናም ከፓርቲው በጡረታ እየተገለሉ ያሉትን / ሃይሉ አርዓያን በሚያወድሰው ንግግራቸው እንዲህ አሉ፡፡
አባይን ከደፈረው {መለስ} ይልቅ ኮሎኔል መንግሥቱን የደፈረው / ኃይሉ አርአያ የሚደነቅና ታላቅ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ 
ህም፤ መቼም ከቆየን ብዙ እንሰማለን፡፡ ይች ንግግራቸው ሁሌም ስትገርመኝ እንደምትኖር አስባለሁ፡፡ ለጊዜው ግን መገረሜን ትቼ አቶ አስራት ጣሴ በሞቅታ /በመጠጥ ሳይሆን በጭብጨባ/ የተነሳ እየጨፈለቁ ያለፏቸውን እውነታዎች ላንሳ፡፡
አንደኛ፤ አቶ አስራት ጣሴን አይናቸው አላይ፤ ጆሯቸው አልሰማ፤ ጭንቅላታቸው አላመዛዝን፤ ህሊናቸው አልታመን፤ ሁለመናቸው አልታዘዝ ካላላቸው በስተቀር መንግስቱን ከመለስ ዜናዊ በላይ የደፈረው የለም፡፡ አዎ እርግጥ ነው፤ / ሃይሉ አርዓያ ያኔ የደርግ ሸንጎ አባል እያሉ እንዲህ ብለዋል፡፡ /ከንግግሮቹ መካከል ጠንከር ጠንከር የሚሉትን መርጬ ነው ያቀረብኩላችሁ/
ከመድረኩ የሚታየው አንድ ችግር አለ፤ ጓድ ፕሬዝዳንት ከእርስዎ፡፡ይሄ መድረክ ነፃ መድረክ ነው፡፡ ይሄ ሸንጎ ከፍተኛ የስልጣን አካል ነው፡፡ ከበላዩ የወከለው ህዝብ ካልሆነ በስተቀር የለውም የበላይ፤ ባለሙሉ ስልጣን ነው፡፡ በፈለገው ጉዳይ የፈለገውን ጉዳይ አንስቶ ሊወያይና ሊወስን ይችላልከሚለው ነገር እየተነሳን ይሄ መድረክነፃነው ይላል፡፡ ጥሩ፡፡ ባንድ በኩል ደግሞየገጠመንን ችግር መፍትሄ እንፈልግ በነፃ መድረክ በነፃ ውይይትበሚባልበት ጊዜ ደግሞ አንዳንድ ሃሳቦች ሲቀርቡ ደግሞ እስኪ ይሄ ይዘቱ ምንድን ነው? ጉድለት ካለው ደግሞ ጉድለቱ ታይቶ ውድቅ የሚሆን ከሆነ ውድቅ ይሆናል፡፡ ከመድረኩ ግን ሊኮነን አይገባውም በቅድሚያ፡፡ ይሄማ ነፃ መድረክ አይደለም ማለት ነው፡፡
ነፃ መድረክ ከሆነ በነፃ መነጋገር አለብን ማለት ነው፤ አለበለዚያየለም በዚህ አቅጣጫ ነው፤ ይሄ ነው መፍትሄያችንና በዚህ ነው መሄድ ያለብንተብሎ ከተነገረን ደግሞ ቁርጡን እናውቀዋለን፡፡ ይሄንን ለማመን አስቸግሮናል፡፡ አሁን የምንነጋገረው እውነት እየተደማመጥን ነው ወይ? ህዝብና መንግስት እኔ ደጋግሜ የምለው ነው ፕሬዝዳንት፤ ማንኛውም መድረክ ሆድና ጀርባ ሆኗል፡፡ብለዋል፡፡ ይህንንም ታሪክ ከትቦላቸዋል፡፡
መለስ ዜናዊ ግን ከንግግርም በላይ ነው፡፡ መለስ በወሬ ሳይሆን በተግባር "አንድ ጥይትና አንድ ሰው እስኪቀር …" ያለውን መንግስቱን አገር ጥሎ እንዲበር አድርጎታል፡፡ አስራት ጣሴ እንደሚያውቁት ኮሌኔላቸው መንግስቱ በአፍሪካ ወደር የሌለው ሰራዊት ገንብቶ ነበር፡፡ ይህ ሰራዊት የተበተነው በዶ/ ሃይሉ ሸንጎው ነፃነት የለውም ንግግር ሳይሆን በጦር ስትራቴጂስቱ መለስ ዜናዊ በሚመራው ሰራዊት ነው፡፡ ይህንንም ታሪክ ከትቦታል፡፡ አለምም መስክሮለታል፡፡
አቶ አስራት ጣሴ ታዲያ አንዱን ታሪክ ጥለው ሌላውን ቢያነሱ ማን ይሰማቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አልሰማህም፤ መስሚያዬ ጥጥ ነው ነው የሚላቸው፡፡
ሁለተኛ፤ እንደ አቶ አስራ ንግግርና እሳቸው ባይሉትም ማንም እንደሚያውቀው አባይ ተደፍሯል፡፡ የደፈረው ደግሞ መለስ ዜናዊ ነው፡፡ እራሳቸው አቶ አስራት ጣሴ ግን ከአሁን በፊት በአንድ መድረክ ላይ ‹‹አባይን የደፈሩት ጃንሆይ ናቸው›› ብለው ነበር፡፡ /ይችን ንግግራቸውን ከኢቲቪ አርካይቭ ማግኘት ይቻላል/ ያኔ ታዲያ እኔ ‹‹ጃንሆይማ አባይን አልደፈሩም›› ብዬ ልከራከራቸው አሰብኩና ‹‹ማን ያውቃል፤ ከእኔ እሳቸው ለጃንሆይ ይቀርባሉ፤ ምናአልባት ጃንሆይ በህልሜ አባይን ደፈርኳት›› ሲሉ ሰምተው ይሆናል ብዬ ዝም አልኩ፡፡
አሁን ግን ምነው በተከራከርኳቸው ብዬ ተፀፀትኩ፡፡ ያኔ ‹‹ተው ህልም እንዳይሆን›› ብዬ መሳሳታቸውን ብነግራቸው ኖሮ አሁን ደግመው አይሳሳቱም ነበር፡፡ ‹‹ምነው እናቴ፤ እንቁላል ስሰርቅ በቀጣሽኝ›› አይደል ያለው ልጁ፡፡
ሶስተኛ፤ አባይን ለመገደብ መነሳት /መድፈር/ አስቸጋሪ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ አቶ አስራት ጣሴ በዚህ ንግግራቸው አንድነቶች ‹‹ለኢትዮጵያ አንድነት የታገለ›› እያሉ የሚያንቆለጳጵሱትን መንግስቱ ኃይለማርያምን አባይን ከመድፈርም የበለጠ የማይደፈር፤ ለመተቸት /እንደ / ሃይሉ አርዓያም ለስለስ ብሎም ቢሆን እንኳን/ የማይቻል አምባገነን እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡ በዚህ በክፉ ቀን ተጨማሪ ወዳጅ እንዳያስኮበልልብዎ ልብ ቢሉ ይሻልዎታል፡፡ ደግነቱ እነሱም ነገር ዘወር አድርገው ማየት አይችሉም፡፡
የትናንቱ በአል አንድነት እንደ አክርማ በሁለት በተሰነጠቀበት ማግስት የተከበረ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ ከበዓል በፊት ተሃድሶ ይቅደምጀግኖቻችንን አሳስሮ በዓል ብሎ ነገር የለም ያሉት የአፈንጋጭ ቡድኑ አባላት በዚህ በዓል ላይ አልተገኙም፡፡ እንደውም ፓርቲው ለአንዳንዶቹ በአመራርነት ላበረከቱት አስተዋፆ የምስክር ወረቀት አዘጋጅቶላቸው ነበር፡፡ የሚቀበል ጠፋ እንጂ፡፡
አቶ ግርማ ሰይፉመድረክ መሪው ልክ እንደማያውቅ ሆኖ ይጣራል፡፡ የሚነሳ የለም፡፡ ተወካይ ይላል፡፡ ወፍ የለም፡፡ አቶ ተክሌ በቀለ እያለ ይቀጥላል፤ ማንም የለም፡፡ ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ ሲል አቤት ቅብል ወረቀቷን፡፡ አቶ አበበ አካሉ አቤት …. እንዲህ ነበር ውሏችን፡፡
አንድነቶች ለማንኛውም እንኳን 6ኛውን ዓመት የልደት በዓላችሁን ለማክበር አበቃችሁ እላለሁ፡፡ በዝግጅታችሁ በመታደሜ ደስ ብሎኛል፡፡

Friday, August 15, 2014

ኢንጂነሮቹና አቶዎቹ

ሰሞኑን ዘና ከምልባቸው ነገሮች አንዱ በአንድነት አመራሮችና አባላት መካከል ያለው የቃላት ጦርነት ነው፡፡ በተለይ በኢንጅነር ዘለቀ ረዲና በአቶ ግርማ ካሳ መካከል፡፡ እንደሚታወቀው አንድነት አሁን የኢንጂነር ግዛቸዉ አንድነት እና 'የበላይ ፍቃዱዉ አንድነት በሚል ለሁለት ተከፍሏል፡፡ ተክሌ በቀለ ለጊዜውሶስተኛውን አንድነትለመመስረት የሚያስችል በቂ ድጋፍ ስለሌላቸውከሁለተኛው አንድነትጋር ተዳምረው ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው /../፡፡
እኔ እንደታየኝ ከሆነ ለፓርቲው መሰበርም ሆነ ለቃላት ጦርነቱ ዋና መነሻ /ultimate cause/ ይሄው የአመራሩ መከፋፈል ነው፡፡ በርግጥ ሰሞኑን የተከሰተ ‹‹ኢንጂነር ግዛቸው የውህደት አመቻች ኮሚቴውን አፈረሰብን›› የሚል ምክንያት እንዳለ አውቃለሁ፡፡ ይች ግን ሰበብ ቢጤ /immediate cause/ ነች፡፡
ወደ መነሻ ነጥቤ ልምጣና በሁለቱ የፓርቲው አባሎች መካከል የተደረጉ ልውውጦችን ላስነብባችሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሁለቱን ግለሰቦች ለማስተዋወቅ ያክል አቶ ዘለቀ ረዲ ማለት አሁን በአንድነት ፓርቲ ውስጥ አመራር ናቸው፡፡ ውግንናቸው ደግሞ ከኢንጂነር ግዛቸው ጋር እንደሆነ ከፅሁፎቻቸው ለመረዳት አይከብድም፡፡ የፓርቲው የአደረጃጀት ጉዳዮች ሃላፊ እስከመሆንም የደረሱ ናቸው፡፡ ባለፈው አመት እንዲሁ በፓርቲው አመራሮች መካከል በተነሳ ውዝግብ ከዚህ ወንበራቸው ተነስተው አነስ ወዳለች ወንበር ተሸጋግረዋል፡፡ በግሌ ስገመግማቸው ጥሩ ፀሃፊ ናቸው፡፡ አቶ ግርማ ካሳ ደግሞ በአሜሪካ የሚኖሩ ተራ የፓርቲው አባል ናቸው፡፡ ውግንናቸው ከበላይ ፍቃዱ ጋር ነው፡፡ እኝህን በግሌ ስገመግማቸው ደፋር ፀሃፊ ናቸው፡፡ በፈለጉት ጉዳይ ደስ እንዳላቸው ይፅፋሉ፡፡ እኒህ ሰሞኑን የተከሰሱ ጋዜጦችና መፅሄቶችምደስ ይበላቸውእያሉ ያትሙላቸው ነበር፡፡
ርዕሴ ላይ 'ኢንጂነሮቹና አቶዎቹ' ያልኩት ይህን ጊዜያዊ አሰላለፍ አይቼ ነው፡፡ ሁለቱ የፓርቲው አባላት ሰሞኑን የነበራቸውን መጎሻሸም ወደ ከፍተኛ የቃላት ጦርነት /full scale fighting/ አሸጋግረውታል፡፡ እናም በመጨረሻው ፅሁፎቻቸው እንዲህ ተባብለዋል፡፡
ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ
በእርግጥ አቶ ግርማን በጽሁፍ እንጂ በአካል አላውቃችውም፡፡ አንዳንድ በአካል የሚያውቋቸው ሰዎች ግን በእድሜ ገፋ ያደረጉ ሰው እንደሆኑ ነግረውኛል። ሆኖም ሰሞኑን እያደረጉ ያሉትን ነገር ስመለከት ግን ሌላው ቀርቶ በእድሜ ደረጃ በሰል ያሉ የሀገራችን ሰዎች ሲያደርጉ የነበረውን ሳይሆን በተቃራኒ እንደ  አላዋቂ ሰው የሚያደርገውን ሲያደርጉ ማየቴ በእጅጉ አሳዝኖኛል።
አቶ ግርማ ካሳ
የኔ እድሜ እዚህ ላይ ለምን እንደተነሳ ባይገባኝም፣ የስድሳዎቹ ትዉልድ እንዳልሆንኩ ግን ይወቁልኝ። ደርግ ሲመጣ ሕጻን ልጅ ነበርኩ።

ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ
ይቅርታ ይደረግልኝና በአንድነት መካከል የነበረው የፕሬዝዳንት ውድድሩም ከሮ እስኪበጠስ ያደረሱት እኚሁ ሰው ናቸው። እገሌን ኢንዶርስ እናደርጋለን፤ እገሌ ይበቃዋል እያሉ ውሳኔ ሰጭ ሆኑ፡፡ ነገሮችን ከእርስ በርስ ክርክር አልፎ የማህበራዊ ድህረ ገጾች ማዳመቂያ አደረጉት።
አቶ ግርማ ካሳ
እንደ አንድነት ደጋፊ አስተያየቴን ጽፊያለሁ። ይሄ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ መብቴ ነው። «አትናገሩ፣ አትጻፉ፣ አስተያየት አትስጡ» የሚል ፖለቲካ ኢሕአዴጎች አካባቢ ያለ ነው። እነ አቶ ከበደ ካሳ ተናገሩ፣ ጻፉ የተባሉትን ብቻ እንደሚጽፉና እንደሚናገሩ፣ እኛም የአንድነት አመራሮች ማንበብ የሚፈልጉትን ብቻ ጻፉ የሚሉን ከሆነ ችግር ነው።

ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ
ሰውየው በአንድ ጎን ከሚሰሙት ውጭ ግራ ቀኝ አያዩም። ከአንድ ወገን በሰሙት ብቻ ሲፈርዱ አይቻቸዋለሁ። ትክክል አይደሉም ሲባሉ እንኩዋን የተሳሳቱበት ቦታ ካለ ቆም ብሎ ከማሰብና ሥህተታቸውን ከማረም ይልቅ አለመሳሳታቸውን ለማሳመን መከረኛ ብዕራቸውን ያሾላሉ።
አቶ ግርማ ካሳ
ጠመንጃና ጡንቻ አይነሳ እንጂ ብእርስ ከሾለ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። ብእርን የሚፈሩ ደካሞች፣ በራሳቸው የማይተማመኑና የኃይል፣ የስድብና የማስፈራራት ፖለቲካን የሚያራምዱ አምባገነኖች ናቸው።

ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ
እኔ እዚህ አብሬ እየሰራሁ ያልገባኝን አሜሪካን ሀገር ሆነው አቶ ግርማ ካሳ የገባቸው ነገር በእጅጉ ግራ ያጋባል።
አቶ ግርማ ካሳ
አሜሪካ አገር ነው የምኖረው። ደግሞ አገር ቤት ከሚኖሩ ግማሽ ወይንም ሶስት አምስተኛ ኢትዮጵያዊ አያደርገኝም።
በዚህ የፌስቡክ ክርክር ላይ ኢንጂነር ዘለቀ ብዙም ደጋፊ ያገኙ አይመስሉም፡፡ ተክሌ በቀለም /የፓርቲው / /መንበር/ ለአቶ ግርማ ካሳ ወግነው ባወጡት ፅሁፍ እንዲህ ሲሉ ዝተውባቸዋል::
የአመለካከት ትግሉ ከስርአቱ ጋር ብቻ ሳይሆን ከጎናችን ካሉቱም ጋር ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ይህንንም ከተገነዘብን ቆይተናል፤ ለዉጥ የሻትነዉም ለዚህ ነዉ፡፡ የፕሬዝዳንቱ {የኢንጂነር ግዛቸው} ቃል አቀባይ ሃላፊነት ቦታን የመዉስድ ፍላጎትዎንም በግሌ አደንቃለሁ፡፡ እኛ በዚህ አመራርና ዉሳኔ አሰጣጥ ለዉጥ ስለማይመጣ የካቢኔዉ አባላት ሆነን አብረን አንሰራም አልን እንጂ ሌላ ግምገማና ጉርጎራ ዉስጥ አልገባንም፤ ለሱ እንደርስበታለን፡፡
ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ አሁን የፅሁፍ ስቱዲዮ ልገባ ስል ባወጡት ጽሁፍ ደግሞ በአቶ ተክሌ በቀለየኢንጂነሩ ቃል አቀባይ መሆን ትፈልጋለህመባላቸው ስላንገበገባቸው ይመስላልጆሮ ለባለቤቱ ባእድ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ እንግዲህ ለአቶ ተክሌይሉህን በሰማህ ገበያ ባልወጣህእያሏቸው ነው ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን አቶ ተክሌ አሁንግምገማና ጉርጎራ ውስጥ አልገባንም፤ ለሱ እንደርስበታለንቢሉም ኢንጂነር ዘለቀ ቀድመው መግባት የፈለጉ ይመስላሉ፡፡
ካፈነገጡት አመራሮች ውስጥ አንዱ የሆኑት አቶ ዳንኤል ተፈራም ለአቶ ዘለቀ ረዲም ሆኑ ሌሎች የአንድነት ሰዎች ፌስ ቡክ ላይ መሽጎ ነገር መጎንጎን አይጠቅምም፡፡ ሲሉ ዘልፈዋቸዋል፡፡  ፌስ ላይ ከሚጎነጉኑት አንዱ አቶ ግርማ ካሳ መሆናቸውን ልብ ላለ ግን 'ምነዋ የአቶ ዳንኤል ማሳሰቢያ ለተቃወሟቸው ኢንጂነር ዘለቀ ብቻ ሆነ? መጎንጎን መጎንጎን ነው፡፡' የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ ያም ሆነ ይህ በጥቅሉ ሲታይ ኢንጂነር ዘለቀ ረዲን አንዳንዶች ቢደግፏቸውም ብዙዎች ተቃውመዋቸዋል፡፡ ፅናቱን ይስጥዎት ብያለሁ፡፡
አቶ ግርማ ካሳ በዚህ ፅሁፋቸው ላይ አቶ ከበደን ለጊዜው ልተዋቸውና…” በማለት የሆነ ጊዜ እንደሚመጡብኝ በተዘዋዋሪ ዝተውብኛል፡፡ እንዳመጣብኝ እጠብቅዎታለሁ እንጂ የት እሄዳለሁ? ግን በንጉሱ ዘመን የተወለደ ሰው በደርጉ ዘመን ከተወለደ ጋር መነታረክ አይበጀውምና ቢቀርብዎት ይሻልዎታል፡፡ ይህን ምክሬን ሳይሰሙ ቀርተው ብዕርዎትን ቢያሾሉ ግን እኔም ጋር ያለው ላጲስ አይደለምናማርያምን አልምርዎትም፡፡ Lol.
በነገራችን ላይ ይህ አንድነት ቤት የተፈጠረ እሰጣ እገባ ለሰማያዊ ፓርቲ አባሎች ሰርግና ምላሽ ሆኗል ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ አንዳንዶቹም ለዚህ ያበቃን ‹‹የበሳሉ መሪያችን ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ብልህ አመራር ነው›› ብለዋል በፌስቡክ ግድግዳቸው፡፡ አቤል ኤፍሬም የተባለ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነትን የማደንቅባቸው 5 ምክንያቶች በሚል ከዘረዘራቸው ውስጥ ያልተጠና ውህደት እንደማያዋጣ ቀድመው መረዳታቸውና አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከሰማያዊ ውጭ ፓርቲ አለ ብለው ያለማመን ድፍረታቸው መሆኑን ገልጧል፡፡

በመጨረሻ  አገር ውስጥ ላላችሁ ለአንድነት ፓርቲ ተራ አባላት ባትሰሙኝም አንድ ምክር ልለግሳችሁና ላብቃ፡፡ እናንተ በዚህ ጉዳይ ጣልቃ ባትገቡ መልካም ነው፡፡ ጦርነቱ ሲበርድ ትመጣላችሁ፡፡ እስከዛው የኢፌዴሪ ፓርላማ አባላት ከመረጣቸው ህዝብ ጋር ለመመካከር እረፍት እንደወጡት እናንተም ዞር ዞር እያላችሁ የህዝቡን የልብ ትርታ ብታዳምጡ መልካም ነው እላችኋለሁ፡፡