Tuesday, August 4, 2015

ሲፈርድልን ገለልተኛ፤ ሲፈርድብን…
ምንጮች እንደዘገቡት ዛሬ (12/12/2013) የዋለው የፍርድ ቤት ችሎት በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ባሉ ግለሰቦች ላይ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አስሩ ጥፋተኛ አይደሉም (የቀረበባቸው የአቃቢ ህግ ማስረጃ ጥፋተኛ የሚያሰኛቸው አይደለም) ሲባሉ 19 ያክሉ ደግሞ በተጠረጠሩበት ወንጀል የቀረበባቸው የአቃቢ ህግ ማስረጃ ጥፋተኛ መሆናቸውን በበቂ ሁኔታ የሚያሳይ በመሆኑ እንዲከላከሉ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል፡፡ ይህን ዜና የአክራሪ ሃይሉ ገፆች <<ሰበር ዜና>> በሚል እየተቀባበሉት ነው፡፡ እኔን የገረመኝ ግን አዘጋገባቸው ነው፡፡ (በምስሉ ላይ ስክሪን ሾት የተደረገውን ያገናዝቡ።)

"በኢትዬጲያ ሙስሊሞች ላይ መንግስት የጥፋተኘነት ውሳኔ አስተላለፈ" አሉ፡፡

ግን ለመሆኑ በምን አይነት ስሌት ነው እነዚህ ተጠርጣሪዎች ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጋር አንድና ያው የሆኑት፡፡ ማንን እንደሚወክሉ አናውቅም እንዴ? እኔ ነኝ ያለ (የአሸብር በላይን ሙዚቃ ማለቴ አይደለም) እስኪ በእነዚህ ሙስሊሞች ላይ የተወሰነ ውሳኔ በመላው የኢትዮጵያ መስሊሞች ላይ የተወሰነ ውሳኔ መሆኑን በሎጂክ ያስረዳኝ፡፡


እስኪ ተመልከቱ ፍርድ ቤቱ የተወሰኑትን ጥፋተኛ ሲል የተወሰኑትን በነፃ አሰናብቷል፡፡ የታሰሩት የመላው ሙስሊሞች ተወካዮች ናቸው ካሉ ታዲያ ለምንድን ነው <<መንግስት የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን በነፃ አሰናበተ>> ብለው የማይዘግቡት? ነው ወይስ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የሚወከሉት ጥፋተኛ ተብሎ በተበየነበት እንጅ ነፃ ናችሁ በተባሉት አይደለም? እንደኔ ሁለቱም ራሳቸውን እንጅ ሰላም ወዳዱን ኢትዮጵያዊ ሙስሊም አይወክሉም፡፡

ሌላው ጉዳይ ይህን አይነት ውሳኔ ለማስተላለፍ ህገ መንግስታዊ ሃላፊነት የተሰጠው አስፈፃሚው (Executive) ሳይሆን ህግ ተርጓሚው (Judicial) ነው፡፡ ታዲያ "መንግስት የጥፋተኘነት ውሳኔ አስተላለፈ" ማለትን ምን አመጣው? እንደገባኝ ፍርዱን የሰጠው አስፈፃሚው ነው እያሉን ነው፡፡

ግን ይበልጥ ግራ የሚያጋባው በዚሁ ዘገባ ላይ "በዕድሜ የገፉት አባቶች / ከማል ገለቱ፣ … (የተዘረዘሩት ስሞች 10 ናቸው) በነፃ ፍርድ ቤቱ እንዲሰናበቱ መወሰኑ ተዘግቧል" የሚል አረፍተ ነገርም ቀላቅለዋል፡፡ ይሄ ደግሞ የሚያሳየው በነፃ ያሰናበታቸው ፍርድ ቤቱ መሆኑን ነው፡፡

እንዴ! አስፈፃሚው (መንግስት) እና ህግ ተርጓሚው (ፍርድ ቤት) መዝገቡን ተከፋፍለው ነበር እንዴ ሲመረምሩ የነበሩት? ነው ወይስ በነፃ መሰናበት ሲሆን የፍርድ ቤት፤ ጥፋተኛ ሲኮን ደግሞ የመንግስት ፍርድ ነው ተብሎ አስቀድሞ ተፈርጇል?

እንዲህ ነው እንግዲህ በፍርድ ስርዓቱ ላይ ያለን እምነት፡፡ ሲፈርድልን 'ገለልተኛ ፍርድ ቤት' የሚል ተቀጥላ እናበጅለታለን፤ ሲፈርድብን ደግሞ 'በተፅዕኖ ስር የወደቀው' እንለዋለን፡፡ እኔ የምለው ለምን ቢያንስ አቋም ይዘን አንደግፈውም ወይም አንቃወመውም?

ለነገሩ ዩንቨርስቲ እያለንም <A> ስናገኝ <A> አገኘሁ <F> ስናገኝ ደግሞ መምህሩ <F> ሰጠኝ እያልን አይደል እዚህ የደረስነው፡፡

እንደው ዝም ብዬ ቀለም እጨርሳለሁ እንጅ እነዚህ አክራሪዎች የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ላለመቀበል ዳር ዳር ማለት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ባለፈው ህዳር 23 እንኳን ለኮሚቴዎቻችን በነፃ ከመሰናበት ያነሰ ፍትህ ተቀባይነት የለውም ብለው ለጥፈው ነበር፡፡ እኔም ይህን ዳር ዳርታቸውን አይቼ እንዲህ ስል ምላሽ ወዲያወኑ ሰጥቼ ነበር፡፡

<<አንዳንዶቻችሁለኮሚቴዎቻችን በነፃ ከመሰናበት ያነሰ ፍትህ ተቀባይነት የለውም፡፡እያላችሁ በፍትህ ስርዓቱ ላይ ለምን ጣልቃ ትገባላችሁ?

እንግዲህ ዳኞች ማንም ስለጮኸ ተገዥነታቸውን ከህግና ከህሊናቸው ባለፈ ለሶስተኛ ሃይል የሚሰጡ ከሆነ ይሄኛውስ በዳኞች ላይ ተፅዕኖ አይፈጥርምን?

ደሞ ጫና መፍጠራችሁ ካልቀረለኮሚቴዎቻችን በይቅርታና በካሳ ከመሰናበት ያነሰ ፍትህ ተቀባይነት የለውም፡፡ብትሉ አይሻልም?>>

ይህን ከቅንነት የመነጨ ምክር በመለገሴ የተረፈኝ ግን ያው የተለመደ ስድብና ማስፈራሪያቸው ነው፡፡ ልቦና ይስጣችሁ ከማለት ውጭ ምን እላለሁ፡፡

ለማንኛውም አሁን በሁለቱም በኩል (ነፃ በተባሉትም ሆነ እንዲከላከሉ በተወሰነባቸው ላይ) ያለው የፍርድ ቤት ክርክር የመጀመሪያ እንጅ የመጨረሻ አይደለም፡፡ ጥፋተኛ የተባሉት ለጥር 22 የመከላከያ ምስክራቸውን እንዲያቀርቡ ችሎቱ ወስኗል፡፡ ነፃ በተባሉት ላይ ደግሞ ምን አልባትም አቃቤ ህግ ይግባኝ ሊጠይቅ ይችላል፡፡

በወንጀል ድርጊቱ እጃቸው ሳይኖር በጥርጣሬ የተያዙ ወይም በማያውቁት ወጥመድ አክራሪው ሃይል ለሽብር ተግባሩ ያጠማዳቸው ወገኖቻችን ነፃነታቸውን እንዲቀዳጁ እመኛለሁ፡፡ ኧረ እንደውም አንድ ንፁህ ዜጋ ባልሰራው ወንጀል ከሚታሰር አስር ወንጀለኞች በነፃ ቢለቀቁ ይሻላል የሚሉትን ወገኖችን ሃሳብ እጋራለሁ፡፡ ሊያሸብሩን የሞከሩት ግን የእጃቸውን ማግኘት አለባቸው፡፡
Post a Comment