Thursday, December 19, 2013

የነብርን ጅራት አይዙም፤ ከያዙም…ልክ የዛሬ ሳምንት <<ሲፈርድልን ገለልተኛ ሲፈርድብን፤ …>> በሚል ርዕስ አንድ ብጣቂ ፅሁፍ እዚሁ ግድግዳዬ ላይ ለጥፌ ነበር፡፡ የፅሁፉ አላማ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሃይማኖት አክራሪነትና በሽብር ድርጊት ተጠርጥረው በህግ ጥላ ስር ባሉ ሰዎች ላይ ያስተላለፈውን ውሳኔ ያጥላሉ ሰዎችን ፍርደ ገምድልነት ማጋለጥ ነበር፡፡ ፅሁፉን ያላያችሁ ካላችሁ አሁንም በዚህ አድራሻየግል ብሎጌ ውስጥ ብትገቡ ታገኙታላችሁ፡፡
በዚህ ፅሁፍ ውስጥ ታዲያ አንድ አረፍተ ነገር ሰፍሮ ይገኛል፡፡ እንዲህ የሚል፡፡ <<ለነገሩ ዩንቨርስቲ እያለንም <A> ስናገኝ <A> አገኘሁ <F> ስናገኝ ደግሞ መምህሩ <F> ሰጠኝ እያልን አይደል እዚህ የደረስነው፡፡ >>
ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው ይሄ <<ኤፍ ሰጠኝ>> የሚለው አነጋገር ሁልግዜ ስህተት የማይሆንባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ቢያንስ እኔን በተመለከተ በርግጠኝነት ስህተት አይደለም፡፡
በፎቶው ላይ እንደምታዩት በደቡብ ዩንቨርስቲ /የአሁኑ ሐዋሳ ዩንቨርስቲ/ የውጭ ቋንቋና ስነ ፅሁፍ ትምህርት ክፍል 4ኛ አመት ተማሪ ሳለሁ የመጀመሪያው መንፈቅ አመት የውጤት ሪፖርቴ የሚያሳየው ከወሰድኳቸው 7 ኮርሶች ውጤት ውስጥ ስድስቱ <ኤ> ሲሆኑ አንዱ ደግሞ <ኤፍ> እንደሆነ ነው፡፡
እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ስድስቱን ኤዎች እኔው ራሴ ነኝ ያገኘኋቸው፡፡ አንዷን ኤፍ ግን መምህሬ ራሱ ነው የሰጠኝ፡፡ ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ፀጉሩ በጥላቻ ፖለቲካ የተዘፈቀ የቅንጅት ካድሬ፤ የአንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት /መያድ/ ከፍተኛ አመራርና የደቡብ ዩንቨርስቲ ገስት ሌክቸረር፡፡
ወቅቱ /1998/ ብዙዎች በመንጋ አሰተሳሰብ እየተነዱ ከነሱ እምነት ያፈነገጡትን ሁሉ በእጃቸው ባለ ሃይል ተጠቅመው /ከኢሕአዴግ የተቀበሉት ሃይል ቢሆንም እንኳን/ የሚቀጠቅጡበት ነበር፡፡ እናም ይሄ በሃላፊነት ላይ ሃላፊነት የተደራረበለት ‘ብርቱ ሰው’ በእኔ በምስኪኑ ተማሪ ላይ ጠንካራ ጡጫውን አሳረፈብኝ፡፡ ግዜ ያገዘው ቅል አይደል የሚባለው፡፡
ነገርን ነገር ያነሳዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ልክ ጴጥሮስ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንዳደረገው ብርቱካን ሚደቅሳም የከረመ በሽታዋ አገርሽቶባት “ከእስር ያስፈታኝ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ነው” በማለት የኢትዮጵያን ህዝብና መንግስት ለሶስተኛ ግዜ የካደችበትን ዜና ዘገባ ሰርቼ ነበር፡፡ በራሷ የምስክርነት ቃል ላይ የተመሰረተውን ይህን ዜና በመስራቴ ብቻ አንድ የፌስቡክ ጓደኛዬ <<ብርቱካን ያንተ መጫወቻ ትሁን፤ አንተማ ምን ታደርግ፤ ግዜ ያገዘው ቅል ድንጋይ ይሰብራል>> ሲል ወቀሰኝ፡፡ እኔማ እርሷ ያለችውን ደገምኩት እንጅ ምን አደረኩ ብለህ ነው፡፡ ይልቁንስ ግዜ ስታገኙ ምን እንደምታደርጉ ገና በጠዋቱ ያሳያችሁን እናንተ ናችሁ እንጅ፡፡
ወደ ዋናው ጉዳዬ ልመልሳችሁ፡፡ ያንን ‘መምህሬን’ በሃዋሳ ከተማ አሞራ ገደል ከሚባለው አካባቢ በፍቅር ሃይቅ ዳር ከተገነባው የሚያምር ቪላ ቢሮው ድረስ እየተመላለስኩ <<እባክህ እጅህ ከብዶኛል፤ ከትከሻዬ ላይ አንሳልኝ>> ብለውም ሊለመነኝ ፈፅሞ አልፈቀደም፡፡ በየቀኑ ቢሮው ብመላለስም በየቀኑ <<አላውቅልህም፤ ሂድና እዛው ዲፓርትመንት ሄድ፤ ፋካሊት ዲን ከምትሏቸው ጋር ተነጋገር>> ብሎ ይመልሰኛል፡፡
ሄድና ዲን ተብዬዎቹ ደግሞ <<እኔ ምን አገባኝ፤ ከራሱ ኤፍ ከሰጠህ መምህር ጋር ተነጋገር እንጅ>> ይሉኛል፡፡ እንዲህ እያሉ እንደ ፔንዱለም ከምስራቅ የሃዋሳ ጫፍ ወደ ምዕራብ ጫፍ ሲያመላልሱኝ ቀኑ ነግቶ ይመሻል፡፡ ለአምስት ወራት ያክል በግምት በደርሶ መልስ 15 ኪሎ ሜትር የሚሆን መንገድ በእግሬ ተመላለስኩ፡፡ ደግነቱ ሃዋሳ የቆንጆ ሀገር ነች፤ ወገብና ዳሌ እያየሁ መንገዱን ፉት እለዋለሁ እንጅ እንደነሱ ተንኮል ቢሆን ኖሮ መሃል ፒያሳ ላይ ሩሄን ስቼ እወድቅ ነበር፡፡
ይህን ጉዳይ ባስታወስኩት ቁጥር አዕምሮዬን የሚፈትነኝ አንድ ጥያቄ አለ፡፡ <<ይሄ ሰው አሸናፊነቱን በፀጋ ተቀብዬ ከእግሩ ስር ወድቄለት ሳለሁ እንኳን አልፋታህ ያለኝ ምን ታይቶት ነው?>> የሚል ጥያቄ፡፡ አንዳንድ ግዜ አይ፤ የነብርን ጅራት አይዙም፤ ከያዙም አይለቁም ብሎ ነው እልና ራሴን በነብር ቆዳ ጠቅልዬ እንቆራጠጣለሁ፡፡ ደግነቱ እሱ አጠገቤ የለም፡፡
ይህ ሰው አሁን የት እንዳለ አላውቅም፡፡ ግብረ አበሩ የነበረ ተማሪ ግን አሁን ጭምተኛ የፌስቡክ ጓደኛዬ ነው፡፡ ይመችህ ብዬዋለሁ፡፡ ካለፈው ስህተታቸው የማይማሩ፤ በአፍ ጢሙ የተደፋውን ቅንጅት አቧራ እየጠረጉ መልሰው ሊጭኑብኝ የሚሹ አድሮ ቃሪያ የሆኑ አንድ ሺ ያክል የፌስ ቡክ ጓደኞች ግን አሉኝ፡፡ ከጠቅላላ ጓደኞቼ አንድ አራተኛውን እንደሚይዙ እገምታለሁ፡፡
አሁን እላችኋለሁ፡፡ የኔ ትከሻ እንደዛን ግዜው ልፍስፍስ እንዳልሆነ፤ የናንተም ጡጫ እንደዛን ግዜው እንደማይበረታ ታውቃላችሁ፡፡ ማስፈራራቱንና መሳደቡን ትታችሁ በስልጡን መንገድ እንነጋገር፡፡
ማስታወሻ፤ ይህች ፅሁፌ መታሰቢያነቷ ለቀድሞው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና ለአሁኑ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ለአቶ አያሌው ጎበዜ ትሁን፡፡ ለምን እንደሆነ እኔና እርሳቸው እናውቃለን፡፡
Post a Comment