Monday, December 30, 2013

ኢንጅነር ግዛቸው የአንድነት ሊቀመንበር ሆኑ

በአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የፌስቡክ ገፅ ላይ <<ከአባላትና ደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ ግፊትና ተማጽኖ በመቅረቡ ኢንጂነር ግዛቸው ድርጅቱን በሊቀመንበርነት ለመምራት እራሳቸዉን እጩ አድርገዉ አቀረቡ።>> የምትል ዘገባ አየሁ፡፡
በኋላም በምርጫው ያሸነፉት እኝሁ እንደ ልደቱ ምርጫ ሲያልፍ ጠፍተው ምርጫ ሲቃረብ ነው ድጋሚ የመጡትለፓርቲ ስራ ግዜ የላቸውምወዘተ በሚል የሚታሙት / ግዛቸው ሽፈራው ናቸው፡፡ እኔ ግን የውሸት ኢንጂነር ሳይሆኑ እውነተኛው ኢንጅነር በመሆናቸው ብቻ አደንቃቸዋለሁ፡፡ ግልባጭ ለይልቃል ጌትነት ፅፌያለሁ፡፡
ይህች የምርጫ ሂደት ምን አስታወሰችኝ መሰላችሁ? ካልተሳሳትኩ ግዜው 2002 ይመስለኛል፡፡የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ በአይቤክስ ሆቴል ጠቅላላ ጉባዔውን እያካሄደ ነበር፡፡ በዛውም የፕሬዝዳንት ምርጫ ያደርግ ነበር፡፡
ያኔ ታዲያ በጠና ታምመው የነበሩትና የእለት ተዕለት የፓርቲውን ስራ እንኳን ለመፈፀም ያልቻሉት የወቅቱ ፕሬዝዳንት / ሃይሉ ሻውል "ራሴን ከምርጫ ውድድር አግልያለሁ" አሉ፡፡ በዚህ ግዜ 20ዎቹና 30ዎቹ መካከል ያሉ ብዙ ወጣቶች ኢንጂነሩ ጫማ ላይ ወደቁ፡፡ እርሳቸውም የወጣቶቹን ልመና ተቀበሉ፤ ፕሬዝዳንትም ሆኑ፡፡ እስካሁንም ባይሰሩበትም ስልጣናቸው በእጃቸው ነው፡፡
እኔ ታዲያ እነዚህ ተስፋ ያላቸው ወጣቶች አንድ እድሜያቸው የገፋ፤ ጤናቸው የታወከ አመራር በቃኝ ሲሉ ለሳቸውም ለፓርቲውም ጤንነት ሲባል ሊቀበሏቸው ሲገባ እንዲህ ከመሬት የሚነጠፉት ምን ነክቷቸው ነው? አልኩ፡፡ ለራሴ ነው ታዲያ፡፡ ምንም እንኳን ይህም ዜና ሊሆን ቢችልም ለፓርቲው ጤንነት ስል ግን በዜናዬ ላይ አላካተትኩም፡፡
ኃላ ስሰማ ታዲያ <<ነገሩ ወዲህ ነው>> አሉኝ፡፡ ያሉኝ ደግሞ ከፓርቲው ተከፍሎ የወጣው ሌላ ቡድን አባሎች ናቸው፡፡ እንደ አሜባ መበጣጠስ መቼም የተቃዋሚዎቻችን ባህሪ ነው፡፡ የዚህ ቡድን አስተባባሪ የነበረችው ስትነግረኝ (እሷም ኋላ ይቅርታ ጠይቃ ከፓርቲው ተቀላቅላለች) ወጣቶቹን ጫማ ላይ እንዲወድቁ ቀድመው ያዘጋጁት ራሳቸው / ሃይሉ ናቸው፡፡
የፓርቲውን ኦዲት ሪፓርት ስሰማ ፓርቲው ሁለት መቶ ብር ገደማ (ቁጥሩን በትክክል አሳስታውሰውም) በእዳ ተመዝግቦበታል፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ ግማሹ ከራሳቸው ከኢ/ ሃይሉ ሻውል የተበደረው ነው፡፡ ታዲያ እኝህ ሰው ቢያደራጁስ ይፈረድባቸዋል እንዴ? ያበደሩትን ሳይቀበሉማ ለምኔ ብለው፡፡ መቼም በዚህ ፅድቅ እንደማይገኝ አይጠፋቸውም፡፡
"ፓርቲው ይህን ያክል ገንዘብ ከሊቀመንበሩ መበደሩ በግለሰቡ ጫና ውስጥ አያሳድረውም ወይ?" ስል ለአንድ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ የሰጠኝ መልስ ታዲያ <እኔንም ባበደሩኝ> ብዬ እንድመኝ አደረገኝ፡፡
"ኢንጅነርን ባታውቃቸው ነው፡፡ እርሳቸው ይሄኔ ማበደራቸውንም ረስተውታል" አለኝ፡፡
የአንድነት ጠቅላላ ጉባዔ አቶ ግርማና አቶ ተክሌን የመሰሉ ጎልማሶች ለውድድር ቀርበውለት ሳለ / ግዛቸውን ያክል አዛውንት <<ካልተወዳደሩ>> ብሎ ከፍተኛ ግፊትና ተማጽኖማድረጉ በእዳ ተይዞ እንዳልሆነ ግን ተስፋ አለኝ፡፡

ለማንኛውም ለአዲሱ ሊቀመንበር ለኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው መልካም የስራ ዘመን ተመኝቻለሁ፡፡ መጪው ምርጫም እንደ ምርጫ 2002 ገና በጠዋቱ (በቁርስ ሰዓት) ምርጫው ተጭበርብሯል ብለው አውጀው ምሳ ሰዓት ላይ ይቅርታ የማይጠይቁበት እንዲሆንም ተመኝቸላቸዋለሁ፡፡
Post a Comment