Monday, December 16, 2013

ኧረ የኤዲተር ያለህ!!ሎሚ መፅሄት ቁጥር 24 ታህሳስ 5 እትም ላይ የወጣ አንድ ፅሁፍ አነበብኩ፡፡ <ፅሁፍ> የምለው በፊደሎች ስለተገነባ ብቻ እንጅ ይህን ስም ለማግኘት የሚመጥን ሆኖ አይደለም፡፡

ፀሃፊው ፍቅሩ ባልቻ ይባላሉ፡፡ በግል ስለሳቸው የማውቀው ምንም ነገር የለኝም፤ ያነበብኩትም ይህንን ፅሁፋቸውን ብቻ ነው፡፡ ካሁን በፊት ስለመፃፋቸውም የማውቀው ነገር የለም፡፡ ብቻ ይህ ፅሁፋቸው ከደረጃ በታች ሆኖ ስላገኘሁት የመፅሄቱንም ዝና <ካለው ማለቴ ነው> የሚያበላሽ ስለሆነ ልተቻቸው ወደድኩ፡፡

የፅሁፉ ርዕስ <<የአቶ ደመቀ መመረቅ ዜና ሊሆን ይችላልን?>> ይላል፡፡

የአንድ ገፅ ፅሁፍ ነው፡፡ ስድስት አንቀፆች አሉት፡፡ በውስጡ ደግሞ ከተነሳበት ጉዳይ ጋር ምንም ትስስር የሌላቸው ሌሎች አራት አጀንዳዎችን ያነሳል፡፡ በአማካኝ እያንዳንዱ አጀንዳ በአንድ አንቀፅ ገደማ ተብራርቷል ማለት ነው፡፡ 

ፀሃፊው ስለ ኢሕአዴግ አመራሮች የትምህርት ጉዳይ ያነሱና ጥቂት እንኳን ሳይራመዱ ስለ ጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሱዳን ጉብኝት ያትታሉ፡፡ በዛው ፍጥነት ተወርውረው ወደ ሀገራቸው ይመለሱና ስለ ገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን ሙስናና ብልሹ አሰራር ያነሳሉ፡፡ እሱን ጥለው ደግሞ በኢሕአዴግ መካከል አለ ስላሉት መከፋፈል ያነሳሉ፡፡ የፅሁፉን ያለመብሰል የሚያሳየው ደግሞ ፀሃፊው እነዚህን አጀንዳዎች ለማስተሳሰር ምንም አይነት ጥረት አለማድረጋቸው ነው፡፡

ሌላው ትኩረቴን የሳበው ፅሁፉ የትየለሌ የጥያቄ ምልክቶች (?) ያሉበት መሆኑ ነው፡፡ በስድስት አንቀፆቹ ውስጥ 23 ጥያቄዎች አሉት፡፡ በአንድ አንቀፅ በአማካኝ አራት ጥያቄዎች ማለት ነው፡፡ ምን ልበላችሁ፤ ፅሁፉ የሰፈረበት ገፅ የሒሳብ ደብተር መስሏል ብል ይቀላል፡፡ ፀሃፊው በጥቅሉ <<አውቀዋለሁ፤ ልንገራችሁ>> ሳይሆን <<አላውቀውም፤ ንገሩኝ>> ነው የሚሉት፡፡ ይሄ እንግዲህ <<ይመስላል>>፤ <<ይወራል>>፤ <<ይነሳል>> እያሉ ያስቀመጧቸውን <ከእውቀት ነፃ> የሆኑ አስተያየቶች ትቼ መሆኑ ነው፡፡

ኧረ የኤዲተር ያለህ!! እንዴ ኤዲተር እኮ አንድ ፀሃፊ ፅሁፉን ይዞ ሲመጣ ስለፃፈው ነገር እውቀቱ እንዳለውና ያንን እውቀቱን በደንብ እንደገለፀው ማረጋገጥ አለበት፡፡ በአቀራረብ ላይ ያሉ ችግሮችን የማረም፤ ፅሁፉ ይበልጥ ማራኪና አዲስ ነገር የሚያስጨብጥ እንዲሆን እሴት የመጨመር ሃላፊነትም አለበት፡፡ ከፅሁፉ ይዘት ጋር የሚሄድ በሩቅ የሚጠራ ርዕስ መመረጡንም ማረጋገጥ አለበት፡፡ የግል ጋዜጣ ወይም መፅሄት አዘጋጅ ስትሆን ደግሞ ለሽያጭ የሚቀርብ ስለሆነ ውሸትም ቢሆን እንኳን አጣፍጠህ ማቅረብ ይጠበቅብሃል፡፡ እውነታው እንደዚህ ስለሆነ ነው እንጅ ውሸት መፃፍን ደግፌ አይደለም፡፡

እኔ ብሆን እኝህን ፀሃፊ ስለምትፅፉት ጉዳይ ካላወቁ መጀመሪያ ጠይቁ እንጅ ለማወቅ ብሎ የሚከፍልዎትን አንባቢ በጥያቄ አታጨናንቁ እላቸው ነበር፡፡

የዚህ ፅሁፍ ርዕስ <<የተለያዩ ጉዳዮች>> ወይም <<ልዩ ልዩ ትችቶች>> ወይም <<ከትችቶች ጥቂቶቹ>> ካልሆነም <<የትችቶች ስብስብ>> የሚል ቢሆን እኔም ይህን ትችት ባላነሳሁ፡፡ <<የአቶ ደመቀ መመረቅ ዜና ሊሆን ይችላልን?>> የሚል ምሁራዊ ጥያቄ አንስቶ ይህን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ሳይመልሱ/ሳያብራሩ ሌላ መፅሃፍ የሚወጣው አጀንዳ ማንሳት፤ እሱንም አንጠልጥሎ ሌላ ማንሳት ቢሆንብኝ እንጅ፡፡

ኤዲያ! እነ ተስፋዬ ገብረ አብ፤ አሌክስ አብርሃምን የመሰሉ ምርጥ የአማርኛ ፀሃፊዎች ባሉበት ዘመን ላይ ሆነን ይህን እናንብ? ምነው ሸዋ! እንዴ፤ ባይፃፍስ ምን አለበት? እንደኔ አርፎ ቁጭን ማንም አይወስድብንም እኮ፡፡

ወደ ፅሁፉ ዋና ጭብጥ ልመልሳችሁና በሱ ላይ ፀሃፊውን ልሞግታቸው፡፡ <<የአቶ ደመቀ መመረቅ ዜና ሊሆን ይችላልን?>> ወደሚለው ማለቴ ነው፡፡

የዜና መምረጫ መስፈርቶች በርካታ ናቸው፡፡ ወጥም አይደሉም፡፡ ይልቁንም እንደየሀገሩና የሚዲያው ባህሪ የሚወሰኑ ናቸው፡፡ ለብዙዎቹ የሚያግባቡ መለኪያዎች ግን አሉ፡፡ እነሱን ተራ በተራ ብንፈትሽ የደመቀ የክብር ዲግሪ ለዜናነት ብቁ መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡
  • ታዋቂነት /prominence/፤  ደመቀ መኮንን የኢፌዲሪ ም/ል ጠቅላይ ሚኒስትር ነው፡፡ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ አባል ያለው ፓርቲ ሊቀመንበር ነው፡፡ በ4ቢሊየን ዶላር የሚገነባው የህዳሴ ግድብ ም/ቤት ሰብሳቢ ነው፡፡ ስለዚህ ታዋቂ ነው፡፡
  • ጠቀሜታ /significance/impact/፤ ይህ ፅንሰ ሃሳብ ድርጊቱ በሌሎች ዜጎች ላይ የሚያመጣውን አወንታዊ አስተዋፆ የሚመለከት ነው፡፡ ብራድፎርድ ዩንቨርስቲ ያወጣው መግለጫ የደመቀን ስም ከኢትዮጵያ ጋር አያይዞ ነው ያቀረበው፡፡ በዜግነቱ፤  በሃላፊነቱና በቀደመ ታሪኩ፡፡ ስለዚህ ድርጊቱ ከ85ሚሊዮን ዜጎች ጋር የተሳሰረ ነው፡፡
  • ድግግሞሽ /frequency/፤ በጣም በተራራቀ ግዜ የሚከሰቱ ድርጊቶች ከእለታዊና በሂደት ከሚከሰቱ ድርጊቶች የተሻለ ለዜና ተመራጭ ናቸው፡፡ የአውሮፕላን አደጋ ከመኪና አደጋ በተሻለ ሽፋን ያገኛል፡፡ ካልተሳሳትኩ ካሉን ሚኒስትሮች የክብር ዶክትሬት ያለው ደመቀ ብቻ ነው፡፡
  • ወቅታዊነት /timeliness/፤ይህ ድርጊት የተዘገበው ድርጊቱ እንደተፈፀመ ወዲያውኑ ነው፤ በአዲስነቱ፡፡ ዜና ማለት ደግሞ አዲስ ማለት ነው፡፡
  • ሰዋዊነት /human interest/ personalization/፤ ሰዎች ስለ ሰው ድርጊት የሚተርክን ዘገባ ስለመሬትና ዉሃ ከሚተርከው ይልቅ ይወዱታል፡፡ የዚህ ድርጊት ባለቤቱ ደግሞ ሰው ነው፡፡
እርግጥ ነው ይህ ዜና የማያሟላቸው ሌሎች መስፈርቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያክል ግጭት /conflict/ የለበትም፤ ከተለምዶ የወጣ /bizarre/ ክስተት አይደለም፡፡ ሆኖም እያንዳንዱ ዜና ሁሉንም መስፈርቶች እንዲያሟላም አይገደድም፡፡ ዋናው ነገር ሃቅ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነው፡፡

ስለ ሃቅ ጉዳይ ሳነሳ ፀሃፊው ባለማወቅ የፈፀሙትን አንድ ትልቅ የሃቅ /Fact/ ግድፈት አስታወስኩ፡፡ አቶ ደመቀ የዶክትሬት ዲግሪ ያገኙት ፀሃፊው እንዳስቀመጡት “ስለ ሰላም አጥንተው” አይደለም፡፡ በርግጥ መረጃው ላይ <<The Deputy PM earned his post-graduate degree in Peace Studies from Bradford where he read inter alia philosophy, history, sociology and politics, which informed his leadership career in various capacities and portfolios.>> ይላል፡፡ ሆኖም ይህ የሚያስረዳው ስለ ሁለተኛ ዲግሪያቸው ነው፡፡ እናም አሁን የተሰጣቸው ዶክትሬት ዲግሪ የክብር ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ <<will be made a Doctor of Education, receiving an honorary degree for improving access to education in Ethiopia over the last five years.>> በሚል ተገልጧል፡፡

ይህን ዜና እየተቀባበሉ የዘገቡት ሀገር በቀሎቹ አውራምባ ታይምስ፤ ሃሁ ዴይሊ፤ ድሬ ቲዩብ፤ ኢትዮ ቲዩብ፤ ሶደሬ ቲዩብ፤ ኢሬቴድ፤ የኢሕአዴግ ደጋፊ ግለሰቦች፤ ወዘተ ብቻ አይደሉም፡፡ ከውጭ መገናኛ ብዙኃንም ቴሌግራፍ አርጉስ፤ ስትሪሚካ ድረ ገፆችም አውጥተውታል፡፡ ታዲያ እነዚህም መገናኛ ብዙኃን ስንተች ቢያንስ አንድ ሳይንሳዊ ጥቅስ እንኳን መጥቀስ አይገባንም ትላላችሁ?

እንደኔ እንደኔ ግን አቶ ፍቅሩ የሚያዋጣቸው መፃፍ ሳይሆን ለፀሃፊዎች አጀንዳ ማቀበል ነው፡፡ አለ አይደል፤ <<በእንትን ማዕረግ የፀሃፊዎች አጀንዳ አቅራቢና አማካሪ>> የሚል ስልጣን ብንሰጣቸውስ?

በዚህ ፅሁፌ ያስከፋሁት አንዳች ሰው ካለ ይቅርታ፡፡
Post a Comment