Saturday, November 30, 2013

ብዙሃን ታታሪ… ጥቂት አሸባሪ… አንድ ፈሪ፤

 

(ቀልድ ቀመስ ትረካ ታገል ሠይፉ)
ሕንድ በአንድ ወቅት በድህነት በሽብርተኝነት የምትታመስ ሃገር ነበረች፡፡ ለዘመናት በሙስሊም በሒንዱ ሃይማኖቶች አመሃኝተው በዘር በጎሳ ተደራጅተው ቁም ስቅሉዋን ሲያሳዩዋት ኖረዋል ጭር ሲል ቅር ይለናል የሚሉ ጋጠወጥ ሽብርተኞች፡፡ ታዋቂ የቦሊውድ ተዋናዮች ዘፋኞች እራሳቸውን ከሽብርተኞች አደጋ ለመከላከል ሲሉ በጋርድ መንቀሳቀስ የጀመሩትም በዚያ አስቸጋሪ ወቅት ነበር፡፡
እዚህ ላይ ጋርድ ማለታችንን ተከትላችሁ ለምታሳድዱንና፡-
ካልታጣ አማርኛ
ያንተ እንግሊዘኛ
አይመቸን እኛ……..” በምትል ግጥምም ሆነ በስድ ንባብ ስድ ናችሁ ለምትሉን የቋንቋ ተቆርቋሪዎች ይቅርታችን ይድረሳችሁ፡፡
ይቅርታ የምንለው ለትሁትነቱ ያክል እንጂ ጋርድ የአማርኛ ቃል መሆኑን አጥተነው አይደለም፡፡ ጋርድ የተባለው ቃልጋረደከተባለው የአማርኛ ስርወ ቃል ይመዘዛል፡፡ ይህን ስንል ታዲያጋረደየሚለው ቃል ራሱጋርዳቸውከልላቸው፤ ሸፍናቸውከሚለው የግሪክ ቃል የሚመዘዝ መሆኑን መካዳችን አይደለም፡፡ ይሄማ አገር ያወቀው ጀንበር የሞቀው እውነት ነው፡፡
ግራም ነፈሰ ቀኝ ሽብርተኝነትንበጋራ ሕንድእንጂበጋርድ ክንድመከላከል እንደማይቻል ያስመሰከረው የጠቅላይ ሚኒስትር ኢንድራ ጋንዲ ግድያ ነበር፡፡ እርግጥ ከዚያም በኋላ ቢሆን ተተኪው መንግስት ይኼን ሃቅ ለመገንዘብ ጊዜ ወስዶበታል፡፡
በወቅቱ የጠቅላይ ሚኒስትሯን አሟሟት የሚያጠናው አጣሪ ኮሚቴ በደረሰበት መደምደሚያ ላይ የአደጋው መንስኤየጋርዶቹ እንዝህላልነትሆኖ ተገኘ፡፡ እንዝህላልነቱ የተገኘባቸው ጋርዶች ላይም ጠንካራ እርምጃ ተወሰደ፡፡
ይህን እርምጃ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር በሆኑት የወ/ ጋንዲ ልጅ ጠባቂዎች ላይ ትልቅ ጫና ፈጠረባቸው፡፡ እናም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ አደባባይ ብቅ ባሉ ቁጥር ዙሪያቸውን ከበው ይጯጯሃሉ፡፡ አንዱ በሌላው ጋርድ ላይ ጣቱን እየጠነቆለኧረ በደንብ አጅብ …….ኧረ አጅብ…….ኧረ አጅብ……” እያሉ እርስ በእርሳቸው ይጯጯሃሉ ……ይጮሃሉ …፡፡ አንድ ችግር ቢፈጠር በእኔ እንዳይሳበብ፤ እኔ የለሁበትም ለማለት፡፡
እሳቸው ብቅ ባሉ ቁጥር ይኼን መጯጯህ መስማት የለመደው ሕዝብም ጠቅላይ ሚኒስትሩንኧራጅብብሎ መጥራት የጀመረው ከዚያን ጊዜ ወዲህ ነበር፡፡ እናም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ብቅ ባሉ ቁጥርኧራጅብ ጋንዲ መጡይባላል፡፡ ሰውዬው እስከ እለተሞታቸው ድረስ የሚታወቁት በዚሁኧራጅብ ጋንዲበተባለ መጥሪያቸው ሆነ፡፡
ጋርዶቻቸውም ተጯጩኸው ስማቸውን እንጂ ህይወታቸውን ማትረፍ አቃታቸው ራጅብ ጋንዲን ከሽብርተኛ ጅብ ማዳን አልሆነላቸውም፡፡ ልክ እንደ እናታቸው ከአጃቢዎች ጫጫታ በላይ ከፍ ብሎ ባስተጋባ የቦንብ ፍንዳታ በአጭር ተቀጩ፡፡
ከአንዳንድ ያልታመኑ ምንጮች እንዳረጋገጥነው አሸባሪዎች ይህን ጨካኝ ድርጊታቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ከራጅብ ጋንዲ ሞት በኋላ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጅምላ ጨራሽ ቦንብ አጥምዶ ህፃናትን መፍጀት ጀግንነት መስሎ ይታያቸው ጀመር፡፡ በአንድ ወቅት እንዲያውም ሕንዳውያን መቼም የማይረሱት አንድ አሸባሪ ተነስቶ ነበር፡፡ ለጊዜው ስሙን መጥቀስ ያልፈለግነው ይኼው አሸባሪ በአንድ ታዋቂ የሕንድ ከተማ ብዙ ንፁሃን ዜጎችን የጨረሰ ታላላቅ ሕንፃዎችን ያፈረሰ አረመኔ ነው፡፡ በዚህ አረመኔያዊ ተግባሩም ከመኩራራት አልፎ እስከ ማቅራራት የደረሰም ነበር፡፡
እናም ሁል ጊዜ በዚያች በጨከነባት ከተማ በኩል ባለፈ ባገደመ ቁጥርያቺያትና ቦንቤ ያፈራረሳት ከተማ …..ቦንቤ ያወደማት ከተማ…..” ብሎ ማቅራራት ልማዱ ሆነ፡፡ ባጭሩ ከተማዋን የሰሯት እና የቆረቆሯት መሃንዲሶች እንኳ የሱን ያክል አይኮሩም አያቅራሩም፡፡
እጁም አፉም እስከ ተያዘበት ቀን ድረስያቺያትና ቦንቤ ያፈረሳት …..ቦንቤ የደመሰሳት….” እያለ ከመኩራቱ ከማቅራራቱ የተነሳ የዛች ከተማ መጠሪያ እስከ ዛሬም ድረስ ቦንቤ ሆኖ ቀርቷል፡፡
በእርሱ ዓይነት ሽብርተኞች የተማረረው ጀግናው የሕንድ ህዝብምሽብር አሻፈረኝ ….ፍንዳታ መረረኝብሎ እንደ አንድ ሰው በመነሳት ሃገሩን ከቦንብ እሳት ታድጎ በሰላም ማደግም መበልፀግም ቻለ፡፡
ይህን በሕንድ ሽብርተኝነት ተጋድሎ ዙሪያ የሚያጠነጥን ትረካችንን የምናሳርገው ያን ጊዜ በቦንቤ ከተማ ውስጥ ይኖር በነበረ አንድ ፈሪ ወጣት የኑዛዜ ቃል ይሆናል፡፡ የዚህን ፈሪ ጉድ የሰማነው ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ብዙሃኑ ሕንዳዊ እንደ አንድ ሰው ተነሳ ብለን አንድነቱን በአራት ነጥብ ለመዝጋት ጥቂት ነጥቦች ሲቀሩን ነው፡፡
ከላይ እንደገለጽንላችሁ ይኼን ወጣትየቦንቤ ልጆች ጥቃቅኖቹ ይናደፋሉ አንደንቦቹከተባለላቸው የቦንቤ ጥቃቅን ልጆች ጎላ የሚያደርገው ቦቅቧቃነቱ ነው፡፡ በተደጋጋሚ የቦንብ ፍንዳታ የተማረሩት የቦንቤ ልጆች ግን ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ ተነስተው ዘምተዋል፡፡ ዘምተው ተዋግተዋል፡፡ ተዋግተው ድል አድርገዋል፤ የእድገታቸው ማነቆ የነበረውን ሽብርተኝነት፡፡
የዚህ ታሪካዊ ገድል አካል ያልነበረው ቦቅቧቃ በበኩሉ የቦንቤ ወጣቶች በስሙ የላኩለትን የዝመት ጥሪ ሰምቶ ቀርቷል፡፡ ቀርቶ ፈርቷል፤ ፈርቶም ጽፏል የሚከተለውን ፍርሀታዊ ኑዛዜ፡፡
<<ይድረስ ለቦንቤ ከተማ ወጣቶች
ቦንቤ
ለምን ወታደር አትሆንም?” ለሚል ጥሪያችሁ ምላሼ እንደሚከተለው ነው፡-
ወታደር ብሆን ሁለት ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ወይ ጦርነት ይነሳል፡ ወይ ጦርነት አይኖርም፡፡ ጦርነት ካልኖረ አረፍኩ፡፡ ጦርነት ካለ ግን አሁንም ሁለት ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ወይ ቆስዬ እማረካለሁ፡ አልያም እዚያው እሞታለሁ፡፡
ቆስዬ ከተማረኩ መልካም፡፡ ተመትቼ ከሞትኩ ግን አሁንም ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ ወይ በእሳት እቃጠላለሁ፤ ወይ ከመሬት እቀበራለሁ፡፡ በእሳት ከተቃጠልኩ ጥሩ፡፡ መሬት ከተቀበርኩ ግን አሁንም ሁለት ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ወይ አፈር ውስጥ በስብሼ እቀራለሁ፡፡ አልያም ሳር ሆኜ እበቅላለሁ፡፡
አፈር ውስጥ ከበሰበስኩ ግልግል፡፡ ሳር ሆኜ ከበቀልኩ ግን አሁንም ሁለት ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ወይ ሰዎች ይረጋግጡኛል፤ አልያም ከብቶች ይግጡኛል፡፡ ሰዎች ከረጋገጡኝ ደህና፡፡ ከብቶች ከጋጡኝ ግን አሁንም ሁለት ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ወይ ስጋቸውን ሆኜ አጥንታቸው ላይ እገኛለሁ፤ አልያም ሞራ ሆኜ ከቆዳቸው ላይ እቀራለሁ፡፡
ስጋቸውን ሆኜ ቢበሉኝ ግድ የለኝም፡፡ ሞራ ሆኜ ቆዳቸው ላይ ከተገኘሁ ግን አሁንም ሁለት ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ወይ ከቆዳው ገፈው ይጥሉኛል፤ አልያም ከቆዳው ፍቀው ሳሙና ይሰሩብኛል፡፡ ገፈው ከጣሉኝ አረፍኩ፡፡ ሳሙና ከሰሩብኝ ግን አሁንም ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ ወይ የልብስ ሳሙና ያደርጉኛል፤ አልያም የገላ ሳሙና እሆናለሁ፡፡
የልብስ ሳሙና ካደረጉኝ ጥሩ፡፡ የገላ ሳሙና ከሆንኩ ግን አሁንም ሁለት ነገሮች ይኖራሉ፡፡ የሚታጠብብኝ ወይ ወንድ ሊሆን ይችላል፤ አልያም ሴት ናት፡፡ ወንድ ከሆነ መልካም፡፡ ሴት ከሆነች ግን በጣም ስለማፍር ወታደር መሆን አልሻም፡፡>>
Post a Comment