Thursday, November 21, 2013

ያረረበት ያማስል
በጠዋት ተነስቼ ወሬ ስቃርም አንድ በኢትዮጵያ ነገረ ስራና በሀገሩ ተደራዳሪዎች የተበሳጨ ግብፃዊ ፕሮፌሰር ታላቁን የህዳሴ ግድብ አስመልክቶ የፃፈውን ረዘም ያለ ትንታኔ ተመለከትኩ፡፡ ይህ ምሁር የተሰማውን የብስጭት ስሜት ያሰፈራቸው ቃላት እንኳን በደንብ የገለፁለት አይመስሉም፡፡


በፅሁፉ <<እዚህ ሆነን በውሃ ጥም ከምናልቅ እዛው ኢትዮጵያ ሄደን እየተዋጋን ብንሞት ይሻለናል>> የሚለውን የዱሮውን መሪውን የሳዳትን ንግግር አስታውሷል፡፡ እኔማ <<እኛ እናንተን ውሃ የማስጠማት አጀንዳ የለንም፤ አይሆንም ካልክ ግን ና ና ሞክረን>> ብዬ እፅፍለታለሁ፡፡ችግሩማ የራሳችን መሪዎች ነው፡፡ አፄ ዮሃንስ በጉራና ጉንደት ጦርነቶች ወቅት ለወሬ ነጋሪ ቢያስተርፉላቸው ኖሮ መች እንዲህ ይመኙ ነበር፡፡


ሰውየው ቅናታም ቢጤ ነው፡፡ እስኪ ያሳያችሁ የሚቀናበት ቢያጣ በኢትዮጵያ ወተት ይቀናል፡፡ “ኢትዮጵያ ከግብፅ በተለየ መልኩ ከዝናብ በምታገኘው ውሃ አማካኝነት ሰፊ የእንስሳት ሃብት ልማት ስላላት በአፍሪካ ትልቋ የተፈጥሮ ወተት ላኪ ሀገር /exporter/ ሆናለች፡፡ ውሃዋ እንደ ግብፅ ያልተበከለ ስለሆነ ለአውሮፓ ሀገራት ምግብ ከሚያቀርቡ ቀዳሚ ሀገሮች ተርታ ተሰልፋለች” አለ፡፡ 

ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ ይላሉ ይህ ነው፡፡ ምግብና ወተት ከኤሌክትሪክ ሃይል ጋር ምን አገናኛቸው? ነው ወይስ <<ደሞ ከበሉና ወተት ከጠጡ ምን አነሳቸው>> ሊለን ነው? ብዬ ሽምቅቅ ማለት ስጀምር ሰውየው ለካ ሃሳቡ <<የዝናብ ውሃ ስላላችሁ የወንዙን ተውልን>> ለማለት ኖሯል፡፡ እፎይ፡፡


ፕሮፌሰሩ ግን ቅናት ብቻም ሳይሆን ውሸትም አለበት፡፡ “ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ 13 ያክል የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ሐይል ማመንጫዎችን ስትገነባ አንዲት የተቃውሞ ቃል አልተነፈስንም፡፡” ሲል የመሪዎቹን እኩይ ተግባር ሽምጥጥ አድርጎ ክዷል፡፡ ብድር እንዳናገኝ፤ ሰላማችን እንዲናጋና የፖለቲካ ጫናዎች እንዲበረቱብን በየአለም አቀፍ አበዳሪ ተቋሞች ቢሮ ደጅ ሲጠኑ የኖሩት፤ የአካባቢ ተቆርቋሪ ነን ባዮችን ሲያዘምቱብን የነበሩት እነማን ሆነው ነው?


ይህ የውሃና አፈር ሃብት ምሁር ችግሩ የሚፈታበት ያለውን አንድ የመፍትሄ ሃሳብ አመንጭቷል፡፡ ከምተረጉመው እንደወረደ አንብቡት፡፡


“One way out of the dilemma is for Egypt to allow Ethiopia to go back to the old specification of the dam — with a height of 90 metres and a lake of 14 billion m3. But this must be conditional on the Ethiopians not building future dams on the Blue Nile without prior consent from Egypt and Sudan.” ደፋር አላችሁ አይደል? ገና ጉድ ትሰማላችሁ፡፡


ሰውየው ቅናተኛና ውሸታም ብቻ ሳይሆን ድፍረቱም ወሰን የለውም፡፡ ፅሁፉን ሊያጠቃልል ሲል “ኢትዮጵያ በታችኞቹ ሀገራት ላይ ይህን አይነት ደባ ልትፈፅም በማሰቧ ብቻ ይቅርታ ልትጠይቀን ይገባል” ብሏል፡፡ እዚች ላይ ግን ምሁሩ የመረጃ ክፍተትም እንዳለበት ተረዳሁ፡፡ ከሁለቱ የታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት አንዷ ሱዳን እኮ አስቀድማ <<እስከዛሬ የተቃወምኩት ግብፅን ፈርቼና ሳይገባኝ ቀርቶ ነው፡፡ አሁን እንደሚጠቅመኝ ተረድቻለሁ፤ ግድቡንም አልቃወምም፤ እንደውም እደግፋለሁ፡፡>> ማለቷን የሰ አልመሰለኝም፡፡


ይች መዳፈር ግን ምንጯ ከየት እንደሆነ አልገባኝም እንጅ በአንድ ቀን ለሁለተኛ ግዜ ነው የተደገመችው፡፡ ከአልጀዚራ ድረ ገፅ ዛሬ ጠዋት እንዳነበብኩት ከሆነ የግብፁ ግዜያዊ ፕሬዝዳንት አድሊ ማንሱር ጠቅላይ ሚኒስትራችንን አስቀይመዋቸው ነበር አሉ፡፡ 


ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ አድሊ ማንሱር ኩዌት ላይ በሚደረገው የአፍሪካ አረብ ጉባዔ የአባይ /Nile/ ጉዳይ መነጋገሪያ እንዲሆን አጀንዳ ይያዝልኝ ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ የኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ታዲያ ይህን ጥያቄ ውድቅ ያደርጉታል፡፡ እንግዲህ <<መስራት ነው እንጅ ማውራት ምን ያደርጋል>> ብለው ሊሆን ይችላል፡፡ ለነገሩ እውነታቸውን ነው፡፡ 


የአድሊ ጋሻ ጃግሬዎች ታዲያ ሃይለማርያምን ወደ አድሊ ማንሱር ሄደው እንዲመካከሩ ለማዘዝ /ለማግባባት/ ይሞክራሉ አሉ፡፡ አሉ ነው እንግዲህ /እውነታውን አሸብር ጌትነት ሲመለስ ይነግረናል/፡ አቶ ኃይለማርያም በዚህ ድፍረት በጣም በመበሳጨታቸው ውይይቱ ሁሉ ሊቋረጥ ነበር አሉ፡፡ ግን ለመሆኑ ያረረበት ካለ ራሱ ያማስላል እንጅ መጥታችሁ አማስሉልኝ ይላል እንዴ?  እንደውም <<እንዲህ ከሆነ ካሁን በኋላ ማንኛውም አይነት በአባይ ላይ የሚደረግ ድርድር በካርቱም ወይም በአዲስ አበባ ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያ አትሳተፍም>> የሚል የእልኸኝነት ውሳኔ ሊያስወስኑን ነው መሰል፡፡


በዚህ የተነሳ ሁለቱ መሪዎች ቁጭ ብለው በዚህ ጉዳይ ላይ አልመከሩበትም፡፡ በምስል እንደታየው ግን ኮሪደር ላይ አውርተዋል፡፡ ውይይቱም ያለመስማማት መቋጨቱን አልጀዚራ ዘግቦታል፡፡ ሁለቱ መሪዎች ግን ውይይቱ ፍሬያማ እንደነበር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ ተከድኖ ይብሰል ብለው እንዳይሆን ስጋት አለኝ፡፡


ይህን ፕሮፌሰር ቀላል ሰው አድርጋችሁ እንዳታዩት፡፡ ፅሁፉ ራሱ የወጣው እኮ አህራም ላይ ነው፡፡ በአህራም ድረ ገፅ የወጣውን የዚህን ፕሮፌሰር ፅሁፍ አያይዠላችኋለሁ፡፡ አንብቡት፡፡ እንግሊዘኛ ወይም አረብኛ የምትችሉ ደግሞ ፃፉለት፡፡ አስተያየትም ስጡበት፡፡ እኔም በአማርኛ እፅፍለታለሁ፡፡
Post a Comment