Monday, September 16, 2013

ራሳችሁን ከአደገኛ ሹፌሮች ጠብቁ


ቅርብ ግዜ ነው፡፡ በመስሪያ ቤታችን መኪና ተሳፍረን ወደየቤታችን እየተጓዝን ነው፡፡ ሳሪስ ሃና ማሪያም አካባቢ ስንደርስ አንድ ውሻ ወደ መንገዱ ሲገባ አየነው፡፡ መኪናው በፍጥነት ነበር የሚጓዘው፤ ለዛውም በቁልቁለት፡፡ በዛ ፍጥነት ሁላችንም ሹፌሩ Andualem Mekonnen Andu Kiya መኪናውን ለማቆም ቢሞክር እንደምንገለበጥ፤ በዛው ፍጥነት ከቀጠለ ደግሞ ውሻውን እንደሚገጨው እያሰብን ነበር፡፡ በድንጋጤ ተውጠን ባለንበትገጭየሚል ድምፅ ሰማን፡፡
ከመካከላችን አንደኛው አዳንከው?” ሲል ሹፌሩን ጠየቀው፡፡ አዳንኩት አለ ትንሽ ቆይቶም ከዚህ አለም ኑሮ አዳንኩት ሲል ቀለደ፡፡ እኛም ሳቅንለት፡፡
በቀደም ደግሞ ምሽት 300 ሰዓት ላይ በሌላ መኪና ተሳፍረን እንደተለመደው ጎናችንን ልናሳርፍ ወደየቤታችን እየሄድን ነው፡፡ መሻለኪያ አካባቢ ስንደርስ አስፋልቱን የሚመስል ጥቁር ውሻ መንገዱ መሃል ተኝቶ አጋጠመን፡፡ መኪናው ሲደርስበት ለማምለጥ ቀና አለ፡፡ ግን ዘግይቶ ነበር፡፡ ባለበት ድፍት ብሎ ህይወቱ አለፈች፡፡
ሁላችንም ደንግጠን በሃዘን ተዋጥን፡፡ የተናገረ የለም፡፡ ትንሽ ቆይቼ ሹፌሩን ውሻ ስትገድል ይሄ ስንተኛህ ነው?” አልኩት፡፡ ዝም አለኝ፡፡ እኔስ የገደላቸውን ውሾች ብዛት በህሊናው እየቆጠረ መስሎኝ ነበር፡፡ ለካስ ጥያቄዬ አስኮርፎት ኖሯል፡፡ ቤቴ ደርሼ እስከምወርድ ድረስ አንድም ቃል አልተለዋወጥንም፡፡
በመስሪያ ቤታችን ድመትን አምርሮ የሚጠላ አንድ ሹፌር አለ፡፡ እያሽከረከረ ሳለ ድመት ካየ በተለይም ጥቁር ከሆነ/ ከመኪና መንገድ ወጥቶም ቢሆን አባሮ ለመግጨት ይሞክራል፡፡ መንገዱ ላይ ካገኛትማ የሞት ሲሳይ ነው የሚያደርጋት፡፡
ድመት በመጥላቱ እኔ ቅር አልሰኝበትም፡፡ የራሱ ምክንያት ይኖረዋል፡፡ ያለ ምክንያት ሰው የሚጠላስ አለ አይደል፡፡ ነገር ግን የጠላውን መግደሉ ተገቢ አይደለም፡፡ እኔም ጥሎብኝ እባብ አልወድም፡፡ ግን እኮ ምንም አላደረገኝም፡፡ እኔ ታዲያ ሳየው እሸሻለሁ እንጂ ልገለው አልሞክርም፡፡ ፈርቸው እንዳይመስላችሁ፡፡
ድንገት ከነመኪናቸው መንገድ ዳር ካለ ቤት ጥልቅ እንደሚሉት የአይሱዙ ሹፌሮች ከዛፍ ጋር የሚጋጩ ሹፌሮችም አሉን፡፡ ምነው ሲሏቸው ደግሞ "ድንገት ገብቶብኝ ነው" ይላሉ አሉ፡፡ አርፎ የቆመውን ዛፉን እኮ ነው፡፡ የኛ ግቢ ሹፌሮች ግን 81በመቶ ለሚሆነው አደጋ መንስዔ ለሆኑት የሀገራችን ሹፌሮች መገለጫ ናቸው፡፡
ለመሆኑ ውሾች ወይም ድመቶች ተገጭተው ሲገደሉ ለማን ነው አቤት የሚባለው?
የመገናኛ ብዙሃን በየእለቱ በሚያቀርቡት የአደጋ ሪፖርት ላይ የቤት እንሰሶችን በህይወት አደጋም ሆነ በንብረት አደጋ ውስጥ የማያካትቷቸው ለምን ይሆን?
ለማንኛውም እባካችሁ ራሳችሁን ከአደገኛ ሹፌሮች ጠብቁ፡፡
Post a Comment