Friday, September 6, 2013

አንዳንድ ግዜ እኮ ‘አቶ’ም ይበዛል

ሳባዊ ደሳለኝ በፌስ ቡክ ገፁ አንድ አነጋጋሪ ጥያቄ አነሳ፡፡ <<በመስኖ ልማት ኢንጅነሪንግ የመጀመሪያ ድግሪ ብቻ ያለው የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ይልቃል ጌትነት ለምን ኢንጅነር ይልቃልተብሎ ይጠራል?>> የሚል፡፡
አንድ ምሁር ለሳባዊ ደሳለኝ እንደነገሩትና እሱም አንብቦ እንደተረዳው አንድ ባለሙያ ኢንጅነርየሚል ማዕረግ እንዲሰጠው ወይም ኢንጅነር ተብሎ እንዲጠራ ቢያንስ በሙያው ሁለት ዲግሪ ያለውና በተጨማሪም በሙያው ጥናትና ምርምር ያደረገ መሆን አለበት። እኔም መምህሬ ይህንኑ ነው ያስተማረኝ፡፡ ኧረ እሱ እንደውም በህክምና የመጀመሪያ ዲግሪ ያለውን ባለሙያ ዶክተር ማለትም አይገባም ሲል ይከራከራል፡፡
መቸም ካፈርኩ አይመልሰኝ በሚል ካልሆነ በስተቀር ኢንጅነሪንግ የተማረ ሁሉ ኢንጂነር የሚባል ማዕረግ ይኖረዋል ብሎ የሚከራከር አይኖርም፡፡ ራሱን ይልቃል ጌትነትን ጨምሮ ማለቴ ነው፡፡ መባል አለበት የሚል ከሆነም ራሱን መጀመሪያ መጠየቅ ያለበት በሰፈሩና በስራ ቦታው ያሉ በሲቪል ምህንድስና፤ በኤሌክትሪክ ምህንድስና፤ በእርሻ ምህንድስና፤ በውሃ ምህንድስና፤ በኮምፒውተር ምህንድስና፤ ወዘተ በዲግሪ የተመረቁ ወጣት ባለሙያዎችን ሁሉ "ኢንጂነር" እያለ መጥራቱን ነው፡፡
እኔ ግን 'ለሳባዊ ደሳለኝ ጥያቄ እንዲህ ስል ምላሼን ሰጠሁ፡፡
<<ምን እናድርግ፤ ኢንጅነር ብርቅ ሆኖብን እኮ ነው፡፡ አሁን አሁን እንጂ በፊትማ አንድ ዲግሪ ያለውስ ማግኘት ፈተና አልነበረም እንዴ? ያኔማ በአንድ ዲግሪ የሚሰበሰበው ኪራይም ነፍ ነበር፡፡ <<ትምህርት ዱሮ ቀረ>> የሚሉን እኮ እሱንም እያሰቡ ነው፡፡ አናውቅም እንዴ! 1997 <<የዶክተርና የኢንጅነር ስብስብ ነን>> እየተባለ ጥሩንባ ሲነፋብን አልነበር፡፡ አሁንም በዛው የኢንጅነሮችና የዶክተሮች ትዝታ ውስጥ የሚኖሩት ናቸው ይልቃል ጌትነትንኢንጂነርየሚሉትና እንዲባልላቸውም የሚፈልጉት፡፡>>
ሰሞኑን ቢቢሲን ጨምሮ አንዳንድ የውጭ ሀገር የመገናኛ ብዙሃን <<የኢትዮጵያ መንግስት የሰማያዊ ፓርቲን ሰልፍ አላሰናከልኩም ሲል አስተባበለ>> በሚል ባወጡት ዘገባ ላይ ይልቃል ጌትነትን ቃለ መጠይቅ እንዳረጉት ገልፀዋል፡፡ ግን ኢንጂነር ብለው ማዕረግ አላጎናፀፉትም፡፡
ይሄ ሰውኢንጅነርለመባል ገና መማር እንዳለበት ለነሱ አልጠፋቸውም፡፡ ግን ይህ ሰው የሚማር አይመስልም፡፡ ቢማር አይገባውም ማለቴ ግን አይደለም፡፡ ግዜውን አዳዲስ ሰልፍ በማቀድ፤ ክስ በማርቀቅና ኤምባሲዎች በመዞር የሚያሳልፍ ሰው የሚማርበትና የሚያጠናበት ግዜ እንደማይኖረው በማሰብ እንጂ፡፡
ያም ሆኖ እኔ ይልቃል የግድ ትምህት ቤት ገብቶ መማር አለበት ብዬ አላምንም፡፡ ከሰራበት የያዘው ድግሪም በቂ ነው፡፡ በተለይ በመስኖ ልማት የተገኘ ዲግሪ ራስን፤ አካባቢንና ሀገርንም መለወጥ ያስችላል፡፡ ያም አይሆንም ብሎ ፖለቲካውን ከመረጠ ስኬታማ የማይሆንበት ምክንያት የለም፡፡ እንዲህ እንዳሁኑ ቁስል እየፈለገ የማከክ ስልት የሚከተል ከሆነ ግን ለማንም አይበጅም፡፡
ይልቃል ጌትነት እንደፓርቲ መሪ ሀገርን ሊያሳድጉ ይችላሉ፤ የህዝቦችን ችግር ይፈታሉ የሚላቸውን አማራጮች ማቅረብ አለበት፡፡ ከልምድ ማነስ የተነሳ በሌሎች ዘርፎች ላይ ከኢሕአዴግ የተሻለ አማራጮችን ማቅረብ ሊሳነው ይችላል፡፡ ግን ሌላው ቢቀር በተማረበት የመስኖ ልማት ዘርፍ እንኳን አንድ ነገር ጣል አያደርግም እንዴ?
ሳባዊ ደሳለኝ ወርወር ያደረጋት ምክር ለይልቃል የምታዋጣው ትመስለኛለች፡፡ <<ኢንጅነር ነኝ በማለት ያልተሳካለት ፖለቲከኛ ከሚሆን በሙያው እየሰራ የሀገሩ ገበሬ ምርታማ እንዲሆን ሞያዊ እገዛ ቢያደርግ የተሻለ ስኬታማ ይሆናል እላለሁ፣ ካልተጠበቀ ኪሳራም ይድናል>> ሲል ነው ምክሩን የለገሰው። እኔም እደግፋለሁ፡፡ እናም ደግሜ እመክራለሁ፡፡
ይሄ የመስኖ ልማት እኮ በታሪክ ትምህርት የተመረቀውን የኢዴፓውን ልደቱ አያሌውን እንኳን ያንገበግበው ነበር፡፡ <<ኢሕአዴግ በዘርፉ ለመጠቀም ካለን እምቅ ሃብት አንፃር ተመጣጣኝ እቅድ የለውም>> እያለ በተደጋጋሚ ይተች ነበር፡፡ ባለፉት ጥቂት አመታት በሀገሪቱ በመስኖ ልማት ላይ የሚደረገው ርብርብ ከኢዴፓ የተኮረጀ ሀሳብ እንዳይሆን እጠራጠራለሁ፡፡ ታዲያ ይልቃል ጌትነት ይችን የልደቱ አያሌውን ሌጋሲ እንኳን ማስቀጠል እንዴት ያቅተዋል? ይሄ እንደውም ሰውየው የመጀመሪያ ዲግሪውንም በደንብ አልተማረውም እንዴ? የሚል ጥያቄ አጭሮብኛል፡፡
ኧረ ጎበዝ! አንዳንድ ግዜ እኮአቶ ይበዛል፡፡ እኔ ይልቃልን ብሆን ማዕረጌን በመቀየር ረገድ ተነሳሽነቱን የምወስደው ራሴ ነበርኩ እንጅ ይሄ ያንተ አይደለም እስከምባል አልጠብቅም፡፡አቶዬ ይሻለኛልብዬ በአደባባይ ነበር የማውጀው፡፡ ይሄው ፕሮፋይሌን ያልቀየርኩትና ከባለ አንድ ዲግሪዎች ጋር የምጋፋው አንዲት ቁራጭ ፅሁፍ ለመምህሬ ማስረከብ አቅቶኝ አይደል እንዴ፡፡
አሁንም ግዜው አልረፈደም፡፡ እናም ለአቶ ይልቃል አንድ በአንድ የሚከተሉትን አቋሞች ወስደው ወይ በኢሳት ወይ በኢካዴፍ አለዛም በሃበሻ ቲዩብ አማካኝነት ይፋ እንዲያደርጉ እጠይቃለሁ፡፡
1.  እስካሁን ኢንጂነር ስባል መቆየቴ ተገቢ እንዳልሆነ ተረድቻለሁ
2.  ካሁን በኋላ ራሴንም ሆነ መሰሎቼን ኢንጂነር ብዬ አልጠራም
3.  ካሁን በኋላ ኢንጂነር ብሎ የሚያሞግሰኝን ግለሰብም ሆነ የመገናኛ ብዙኋን እከሳለሁ
4.  ራሴ በፈጠርኩት ስህተት የተነሳ ስራዬን ሳይሆን ማዕረጌን አይተው የተጠጉኝ የዋሆች በሙሉ ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱ እጠይቃለሁ፡፡
Post a Comment