Wednesday, August 21, 2013

የልጅነት ህልሜ


ነሃሴ ወር ነው 1991.ም፡፡ ቢጫ ወባ የምትባል ክፉ በሽታ ጥላኝ ራሴን ስቼ ነበር፡፡ እናም አዲነብሪድ ከምትባል አንዲትትግራይ ክልል የገጠር መንደር ለህክምና አንከብክበው ጎንደር ወሰዱኝ፡፡

እንደነገሩኝ ከሆነ የተጓጓዝኩት በወታደራዊ ሄሊኮፕተር ነበር፡፡ እየቀለዱብኝ ካልሆነ በቀር ያን ችምችም ያለ ጎፈሬዬን እየነካካሁ (የዛሬውን አያድርገውና) እስኪ ተመልከቱ ፀጉሬ እኮ ሙሉ በሙሉ ነጭ ሽበት ሆኗል” እያልኩ እቃዥ ነበር አሉ፡፡ እንኳን ማረኝ እንጅ በዛው አብጄ ብቀር ኖሮ እኮ እስካሁን 14 አመት ልምድ ያለኝ ታዋቂ’ እብድ ነበር የምሆነው፡፡

ለማንኛውም ያኔ በነሃሴ ወር ራሴን ስቼ ለትንሽ ደቂቃዎች በአየር ላይ የተጓዝኩትን ታሪክ እነሆ 14 አመት በኋላ በዚህኛው ነሃሴ በውኔ ልደግመው ከጫፍ የደረስኩበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡

ከበጣም ጥቂት ሰዓቶች በኋላ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ጅግጅጋ እጓዛለሁ፡፡ እግረ መንገዴንም (አየር መንገዴንም ብል ሳይሻል አይቀርም) የምወዳትን ድሬዳዋ ከተማን ለመጀመሪያ ግዜ አድርጌያት ብቻ አልፋለሁ፡፡

ገና ልጅ ሳለሁ ሁለት የኢትዮጵያ ከተሞችን አጥብቄ እወዳቸው ነበር፡፡ ያኔ ራዕዬ ቶሎ ማደግና ሁለቱን ከተሞች መጎብኘት ነበር፡፡ ራዕዬ ሳይሳካ በፊት አንዷ የኢትዮጵያ ከተማ መሆኗ አከተመላት፤ አስመራ፡፡ ሌላዋ ድሬዳዋ ነች፡፡

ከሰሜኗ ሽራሮ እስከ ደቡቧ ይርጋ ጨፌ፤ ከሞላ ጎደል ሙሉውን የአማራ ክልል፤ ምዕራብ እስከ መንዲ በስራና በግል ጉዳይ ሳካልል የምናፍቃትን ድሬዳዋን ሳላያት ቀረሁ፡፡ ባለፈው ታህሳስ ወር ጅግጅጋ ከተማ ድረስ ሄጄ ነበር፡፡ ሆኖም የተጓዝኩት በሌላ መስሪያ ቤት መኪና ነበርና የሰው ወርቅ አያደምቅ እንዲሉ ድሬዳዋን እንኳን ሳያሳዩ መለሱኝ፡፡ ዛሬም ይሄው አሞራ በሰማይ ሲያይሽ ዋለ’ እያልኩ ላልፋት ነው፡፡

አሁንስ በድሬዳዋ ተስፋ እየቆረጥኩ ነው፡፡ እንደውም ሳስበው ከድሬዳዋ በፊት አስመራን የማያት ይመስለኛል፡፡ በዚህ ተስፋ በሌለው ግዜ ውስጥ ሆኜ እንኳን አስመራ ከተማን ላይ የምችልባቸው ሶስት ጭላንጭሎች ይታዩኛል፡፡

አንደኛው የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች እንደቀድሟቸው በመረብ ወንዝ ማዶና ማዶ ሆነው ለቡና እንደሚጠራሩት አይነት ልቅ የድንበር ላይ ግንኙነት ከፈጠሩ ነው፡፡ ያኔ በዛላንበሳ በኩል የሁለቱ ሀገር ህዝቦች ደም የተፋሰሱባቸውን የፆረናና አሊቴና ተራሮችን እየቃኘሁ አልፌ አስመራው የኮምቢሽታቶ መንገድ እንደማንኛውም የውጭ ሃገር ጎብኚ ላይ ታች እል ይሆናል፡፡

ሁለተኛው ይሄ ድንበራችን ቀይ ባህር ነው” የሚለውወደብ አፍቃሪ ሃይል ዳንዔል ብርሃነ እንደሚለው በቴክኒክ ችግር’ ድል ቀንቶት 'አስመራዬን' ከመለሰልኝ ነው፡፡ ያኔ ካምቦቦሎ ሰፈር ሰዎች በክፉ አይን ቢያዩኝም ትራቦሎ ሰንበል ሰፈሮች እየተዘዋወርኩ የናፍቆት ጥሜን መቁረጤ አይቀርም፡፡ ካሻኝም አባ ሻውል ጎራ እላለሁ፡፡ እኔ ፍላጎቴ አስመራን ማየት እንጅ ከቀይ ባህር ውሃ የመጎንጨት’ የእልክም ሆነ የትምክህት አመለካከት እንደሌለኝ ግን ከወዲሁ እወቁልኝ፡፡

ሶስተኛውኢፌዲሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 39 ንዑስ አንቀፅ 1 የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል’ የሚለው ሃረግ በአንድ ቃል ተሻሽሎ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠልና መልሶ መዋሀድ’ ወይም ‘unconditional right to self-determination including the right to succession and normalization’ ከሆነና ይህም የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች በውዴታ መልሶ የሚያቀላቅላቸው ከሆነ ነው፡፡

እንዲህ ከሆነ ቢያንስ በቀድሞው የሳዋ ወታደራዊ ማሰልጠኛ አካባቢ የሚኖሩ 5ሺ ነዋሪዎች በመስኖ ልማት ተጠቃሚ የሆኑበት ሁኔታ ነው ያለው፤ የቀድሞው ወታደራዊ አሰልጣኞችም አዲሱ የግብርና ስራችን በምግብ ራሳችንን እንድንችል አድርጎናል ብለዋል’ የሚል ዜና ለመስራት መሄዴ ስለማይቀር አስመራን ሳላያት አልመለስም፡፡

ለማንኛውም ዛሬ በአውሮፕላን ለመጀመሪያ ግዜ፤ በአየር ላይ ደግሞ ለሁለተኛ ግዜ ልጓዝ ነው፡፡ በአውሮፕላን የመጓዝ አጋጣሚውን ካገኘሁ ሁለት ተግባሮችን ለመፈፀም ለራሴ ገና በልጅነቴ ቃል ገብቼ ነበር፡፡ አንደኛው አውሮፕላኑ እየበረረ ሳለ መስኮት ከፈት አድርጌ ውጭው ምን እንደሚመስል መመልከት ነው፡፡ በቅርብ ቀን ውስጥ አዋቂዎች እንደነገሩኝ ከሆነ ግን ለካ አውሮፕላን የሚከፈት መስኮት የለውም፡፡

ሁለተኛው ፍላጎቴ ግን ልጅነቴ ሞኝነቴ አይነት ነገር ነው፡፡ ነውርም ነው፡፡ ለማንኛውም ይህም የሚሳካው መስኮት መክፈት ከተቻለ ብቻ ስለሆነ የማይሳካ ፍላጎት ሆኖ መቅረቱ ከወዲሁ ተረጋግጧል ማለት ነው፡፡

ባለቤቴ ከመሰነባበታችን በፊት “ተናዘዝና ሂድ” አለችኝ፡፡ እያሾፈች መሆኗ ነው እንጅ አውሮፕላን አስተማማኝ የመጓጓዣ መንገድ መሆኑ ጠፍቷት አይመስለኝም፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አንድ ተጓዥ ከቤቱ ተነስቶ ወደ አየር መንገድ ለመሳፈር የሚያደርገው የመኪና ጉዞ በአውሮፕላን እየበረረ ሳለ ከሚያጋጥመው አደጋ በአስር እጥፍ በለጠ ተጋላጭ ነው፡፡ በሌላ አገላለፅ ለአንድ ሰዓት በመኪና የሚደረግ ጉዞ ለአንድ ሰዓት በአየር ላይ ከሚደረግ ጉዞ በአስር እጥፍ ለአደጋ የተጋለጠ ነው ይሉታል፡፡

በኢትዮጵያ አየር መንገድና በኢትዮጵያ መኪና መንገድ መካከል ያለውን የደህንነት ልዩነት የምታውቅ ሚስት በየቀኑ በሃይገር ባስ የሚጓዘውን ባሏን ሁሌ ጠዋት ጠዋት ማናዘዝ ይጠበቅባት እንደሁ እንጅ በአስተማማኙ የአየር መንገዳችን መዳፍ ላይ ያረፈ እለት ጠብቃ እንዲህ አትለውም ነበር፡፡

ለማንኛውም እናንተ ራሳችሁን ከአደገኛ አሽከርካሪዎች ጠብቁ፡፡ እኔ እንኳን ይብላኝ ለናንተ እንጅ በአንድ ደረጃ ወደ ላይ ከፍ ብያለሁ፡፡ lol

Post a Comment