Tuesday, August 13, 2013

ደብዳቤ
ለዳንኤል ብርሃነ፤

አዲስ አበባ

ዳንኤልን በውፍረቱ ለተቻችሁቱ፤

በያላችሁበት

ዳንኤል ብርሃነን በኢሬቴድ ሚዲያ ዳሰሳ ዝግጅት ላይ ለመጀመሪያ ግዜ ተሳትፎ ያዩቱ የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡ ብዙዎቹ ያነሷቸው ግን ሁለት ነጥቦች ላይ ያተኩራሉ፡፡

አንደኛው “ዳንኤል የምትፅፈውን ያክል መናገር አትችልም” የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ “ዳንኤል ለካ እንዲህ ወፍራም ነህ እንዴ” የሚል አግራሞት የታከለበት አስተያየት ነው፡፡

ለመጀመሪያው አስተያየት ራሱ ዳንኤል ምላሽ ይሰጥበታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሁለተኛው ላይ ግን የራሴን ሃሳብ ማንፀባረቅ ፈለግሁ፡፡ እንደ ብዙዎቹ እኔም ዳንኤልን የሳልኩት ቀጠን ሸንቀጥ ያለ አድርጌ ነው፡፡ ለቀረፃ ሲመጣ ሳየው ትንሽ ወፈር ብሎብኛል፡፡ ያም ሆኖ በቴሌቪዥን ያየሁት ዳንኤል አብሬው ተቀምጬ ያወጋሁት ዳንኤል መሆኑን እስከምጠራጠር ድረስ ገርሞኛል፡፡ አንዳንዶቻችሁ ኢቲቪ ያጋንናል የምትሉት እዚች ላይ እውነትነት ሳይኖረው አይቀርም፡፡ ሎል ብያለሁ፡፡
የዳንኤል ወፍራምነት (ቦርጫምነት) ያሳሰባቸው ወገኖች ጂም እንዲገባ መክረውታል፡፡ ይህ በጎ አስተያየት ነው፡፡ ሁላችንም አቅሙና ግዜው ካለን ብንሞክረው ጥሩ ነው፡፡ ስለሆነም ዳኒ በጦማሩ የሚያመሰግናቸው ይመስለኛል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የዳኒን ወፍራምነት (ቦርጫምነት) ከያዘው ፖለቲካዊ አቋም ጋር ለማስተሳሰር ፈልገዋል፡፡ ይሄ ያመነበትን ለተናገረ ሰው ሁሉ “ለሆዱ ያደረ” የሚል ታርጋ መለጠፍ እንኳን እንደ ዳንኤል ልምድ ላለው ቀርቶ ለኛም ለጀማሪዎቹ የተለመደ ስለሆነ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርትን በገለፀበት አግባብ “ክብደት አልሰጠውም” ብሎ እንደሚያልፈው አስባለሁ፡፡

እኔ በዋናነት የማምነው ዳንኤልም ሆነ ማንኛውም ተናጋሪ መመዘን ያለበት በመልዕክቱ ይዘት እንጅ በሰውነቱ ግዝፈት መሆን የለበትም ብዬ ነው፡፡

እስኪ ወደ አንዳንዶቻችሁ ቤት እንግባና መሪዎቻችሁን እንመልከት፡፡ ኢንጅነር ግዛቸው ከሰማይ ስባሪ ትንሽ መለስ የሚሉ የጥንት ዘመን ፖለቲከኛ ናቸው፡፡ አንዱአለም አራጌ ደግሞ ቀጭን የዘመኑ ፖለቲከኛ ነው፡፡ ታዲያ የአንድነት አባላት እነዚህን መሪዎቻቸውን በክብደታቸው ነው እንዴ የሚመዝኗቸው?

ከሀገር ከመውጣታቸው በፊት አበበ ገላው ዋሽንት ነፊ፤ አበበ በለውም ፉጨት አስተማሪ ይመስሉ እንደነበር ሁለቱንም በአካል የሚያውቃቸው ጓደኛዬ ነግሮኛል፡፡ ታማኝ በየነንም ቢሆን ያኔ በቴሌቪዥን ከእንግዳዘር ነጋ ጋር (አፈሩን ገለባ ያድርግላትና) ብቅ ሲሉ ዞራ ስትተነፍስበት እንዳይወድቅ እንፈራለት ነበር፡፡ አሁን እነዚህ ሰዎች እንዲህ የወፈሩት ለአሜሪካ መንግስት አድረው ነው ሊባል ነው? እኔ አልቀበለውም፡፡ ካልጠፋ ሰው አሜሪካ ለነኝህ ሰዎች የምትሰጠው አደራ ይኖራታል ብዬ አልገምትም፡፡
እነ አቤ ቶክቻው እንዳሉት ለሆድ ማደር የሚለካው በሰውነት ግዝፈት ከሆነ እነሱ መንምነው ጅማት መስለው ባየናቸው ነበር፡፡ ይልቁንም አንዳንዶቹ (በተለይ ውጭ ሀገር ያሉቱ) የኛን ወዘና ሁሉ አሟጠው የወሰዱ እስኪመስሉ ድረስ እንደ ቅቤ ቅል ሲያብረቀርቁ እያየናቸው ነው፡፡ እነሱ ምን ያድርጉ፤ ሰው ለፍቶ በለወጠው ሀገር ባሟረቱት መጠን እየተመፀወቱ ይኖራሏ፡፡ እኛ ምን እናድርግ፤ ችግር በከበባት ድሃ ሀገር ውስጥ ሆነን ችግርን ለማባረር እየጣርን ነዋ፡፡

ዳንኤል ለነገሩ አንተ የግር እሳት ሆነህ አላስቆም አላስቀምጥ (አላስዋሽ አላስሸብር) ስላልካቸው በዚህም መጡብህ እንጅ በኛ ሀገር ባህል ገዘፍ ሲሉ ነበር ተሰሚነትም የሚመጣው፡፡ ለቀጭን ቦታ የሚሰጥ ባህል አልነበረንም፡፡ ከአራት አመታት በፊት መንዝ ጌራ ምድር ማስታወቂያ ፅ/ቤት ስሰራ የምቀመጥበት ወንበር ከኔ ሰውነት ይገዝፍ ነበር፡፡ እናም ባለጉዳይ አርሶ አደሮች እኔን ፈልገው ቢሮዬ ይመጡና በር ላይ ደርሰው ይመለሳሉ፡፡ “ኧረ ግቡ፤ ምን ፈልጋችሁ ነው?” ስል “አይ አቶ ከበደን ፈልገን ነው፤ በኋላ ሲመጡ እንመለሳለን” ብለውኝ ይሄዱ ነበር፡፡

እናም ዳኒ ብትፈልግ ወፍር፤ ብትፈልግ ቅጠን፡፡ እሱ ያንተ ምርጫ ነው፡፡ ከአንተ አዕምሮ የሚፈልቁ ሃሳቦች ግን እኛን ያስጨንቁናል፡፡ ጣፋጭ መረጃዎችህ፤ የሰሉ ሂሶችህ፤ ለእውነት ያለህ ጥብቅናና የአላማ ፅናትህን ሁሌም እንፈልገዋለን፡፡

ውሾቹ አምርረው የሚጮሁት ይበልጥ ስትራመድ ነው ዝም እንዳይሉ አድርጋቸው፡፡

Post a Comment