Wednesday, August 7, 2013

ኢሳት ሳላውቅና ሳያስፈቅደኝ ኢንተርቪው አደረገኝ

የቢሯችን ስልክ አንቃጨለ፡፡ ተንደርድሬ ሄጄ አነሳሁት፡፡ ከዛኛው ጫፍ ያለው ሰው <<ከዋሽንግተን ነው የምደውለው፤ ኢቲቪን በተመለከተ መረጃ ልትሰጠኝ ትችላለህን?>> አለኝ፡፡ ይህን አይነት ስልኮችን የክፍሉ ሰራተኞች በተደጋጋሚ የምናስተናግድ በመሆናችን አዲስ ነገር አልሆነብኝም፡፡
<<የማውቀው ጉዳይ ከሆነ እነግርሃለሁ፤ ካላወቅሁት ደግሞ ወደሚመለከተው ክፍል እመራሃለሁ>> አልኩት፡፡
ጥያቄውን ቀጠለ፡ <<የፀረ-ሽብር ህጉ ከወጣ ረጅም ግዜ ሆነው፡፡ አሁን ደግሞ ኢቲቪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በዚህ ጉዳይ ላይ አወያያለሁ እያለ ነው፡፡ ለምንድን ነው የቆየ ነገር የሚያነሳው?>> አለኝ፡፡ ‘ህጉ ለምን ተነካብኝ’ የሚል አይነት የመቆርቆር ስሜት እንዳለው ከድምፁ ያስታውቃል፡፡
እኔም እንዲህ ስል መለስኩለት፡፡ <<የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት የምትከታተል ከሆነ (ከዋሽንግተን ነኝ ብሎኝ ስለነበር) አሁን አንድነትና ሌሎች ፓርቲዎች የሽብር ህጉ ይነሳ እያሉ ተቃውሞ እያሰሙ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ግልፀኝነት መፍጠር ስላለበት ነው ተቋሙ ይህን ውይይት እያዘጋጀ ያለው>> አልኩ፡፡
ጠያቂው ግን በቀላሉ የሚለቅ አይነት አይደለም፡፡ <<እና አንድነት ስለጠየቀ ብቻ ነው ይህን ውይይት እያዘጋጀ ያለው?>>
<<ተቋሙ በሀገሪቱ በሚወጡ አዋጆችና መመሪያዎች ላይ ግልፀኝነት የመፍጠርና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሃላፊነት አለበት፡፡ ህዝቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች የማዳመጥ፤ ለመንግስትም የማስተላለፍ ሃላፊነት አለበት፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ደግሞ ይብዛም ይነስም በስራቸው ደጋፊ (የህዝብ ክፍል) አላቸው፡፡ ስለዚህ ውይይቱ የተዘጋጀበት ምክንያት ይህ ይመስለኛል::>> አልኩት፡፡
ይህን እያወራሁት ሳለ አጠያየቁ ለራሴ በማንነቱ ላይ ጥያቄ አጭሮብኝ ነበር፡፡
<<ለመሆኑ ይህ ውይይት በህጉ ይዘት ላይ ለውጥ ያመጣል?>> አለኝ
<<እሱንማ አብረን የምንከታተለው ይሆናል>> አልኩ ኮስተር ብዬ <<ለመሆኑ ማነህ? ምንስ ነው የፈለከው?>> ስልም ጠየኩት፡፡
<<እኔ የደወልኩልህ ከኢሳት ነው፡፡ መረጃ የማስተላለፍ ሃላፊነት ስላለብን ለዛ ነው>> ምናምን አለኝ፡፡ አስከትሎም የሰጠሁትን መረጃ መጠቀም ይችል እንደሆን ‘ፍቃድ’ ብጤ ጠየቀኝ፡፡ ኢሳት በሌሎች እንደለመደው እኔንም ሳላውቅና ሳያስፈቅደኝ ኢንተርቪው እንዳደረገኝ ተረዳሁ፡፡
<<እኔ ውክልና ስለሌለኝ በዚህ ጉዳይ ተቋሙን ወክዬ መግለጫ ልሰጥህ አልችልም ባትጠቀመው እመርጣለሁ>> አልኩት፡፡ እሱም <<እሺ እንግዳውስ እባክህ የሚመለከተው ሃላፊ ስልክ ስጠኝ>> አለኝ፡፡ እሺ ልሞክርልህ ከአምስት ደቂቃ በኋላ ደውል ብየው ተለያየን፡፡
በቀጠሮው ደወለ፡፡ እኔ ደግሞ ለኢሳት መግለጫ የሚሰጥ ሃላፊ አላገኘሁም፡፡ እውነቱን ለመናገር አላፈላለኩም፡፡
<<አገኘህልኝ?>>
<<አይ አላገኘሁልህም?>>
<<እንግዲያውስ አንተ የሰጠኸኝን መረጃ እጠቀማለሁ>> አለኝ፡፡ <<የኔን ባትጠቀም እመርጣለሁ፡፡ ምክንያቱም ያን መረጃ የመስጠት ሃላፊነት የለብኝም>> አልኩት፡፡ የሃላፊ ስልክ ካልሰተጠኽኝማ ‘የያዝኩትን’ እጠቀማለሁ አለኝ ጫን ባለ ድምፀት፡፡
እኔም ከረር ብዬ <<የሰረቅሁት መረጃ በል እንጅ ማንነትህንና መረጃውን ለምን እንደፈለከው ሳትጠይቀኝ ነው የቀረፅከኝ>> ስል ልከራከረው ሞከርኩ፡፡
<<ሌላ ሃላፊ ካገናኘኸኝ አንተን እተውሃለሁ>> አለኝ፡፡
<<እንዲህ ብለህማ እጄን ልትጠመዝዘኝ አትሞክር፡፡ ይህን ስላልክም ከሃላፊዬ አላገናኝህም፡፡ የነገርኩህ የማውቀውንና ትክለኛውን ነው፤ እንደፈለግህ ተጠቀምበት>> ብዬው ተለያየን፡፡

እባካችሁ ያላግባብ የጠፋውን ድምፄን ከሰማችሁ ቀርፃችሁ አስቀሩልኝ፡፡
Post a Comment