Monday, July 22, 2013

“ጋኖች አለቁና ምንቸቶች ጋን ሆኑ”

ፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክንም ሆነ ሞሀመድ ሙርሲን ከስልጣናቸው ለማንሳት በግብፅ የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ በሃገሪቱ ሰንደቅ አላማ የታጀበ ነበር፡፡ መፈክር ያላነገቡቱ በሙሉ ሰንደቅ አላማቸውን ከፍ አርገው ሲያውለበልቡ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በቅርቡ በቱርክ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍም እንዲሁ፡፡ በብራዚል ትንሽ የሳሳ ቢሆንም ሰንደቅ አላማ አልባ ተቃውሞ አልነበረም፡፡ እነሱ ድንጋይና ርችት በእጃቸው ቢይዙም እንኳን ፊታቸውን በሀገራቸው ባንዲራ ቀለም አስውበው አይተናል፡፡
በአዲስ አበባ የተካሄደውን የሰማያዊ ፓርቲ የተቃውሞ ሰልፍ ጨምሮ በደሴና በጎንደር በተካሄዱ ሰልፎች ላይ ግን ይህን አላየንም፡፡ ይልቁንም በኛ ሰልፍ ላይ ሰንደቅ አላማ የያዙ ተሰላፊዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ ሰንደቅ አላማዋም ስትጎሳቆል መላው ህዝብ በቴሌቪዥን መስኮት ተመልክቶቷል፡፡
አንዳንዶች በሰንደቅ አላማዋ መካከል ያለው አርማ እኛን አይወክልም እንደሚሉ አውቃለሁ፡፡ ግን ለምን ታዲያ እነሱን የሚወክላቸውን አርማ ለጥፈውባት በሰልፉ ብቅ አይሉም? ስለሚያፍሩበት ነው ወይስ የፖለቲካ ዋጋ ስለሚያስከፍላቸው? /በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ይህ ባንዲራ የኛ እንዳልሆነ አታውቁምን በሚለው ፅሁፌ ገልጨው ነበር፡፡/
“ይህ ባንዲራ አይወክለንም” ከሚሉት ውስጥ አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ አንዱ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ፓርቲው በደሴና በጎንደር ባካሄዳቸው ሰልፎች ላይም ይህንኑ በተግባር አሳይቷል፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያቱ ሃይማኖትና ፖለቲካን ደባልቆ የማስኬድ የቆየ አባዜው ነው፡፡
ጅብ ከማያውቁት ሀገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ እንዳለው ሁሉ አንድነትም አሁን አክራሪ ሙስሊሞችን ተጠግቶ ራሱን የእስልምና ጠበቃ አድርጎ ያቅርብ እንጅ እውነተኛ ምንነቱ የቀደመውን የአንድ ሃይማኖት ስርዓት የሚናፍቅ ነው፡፡ በኔ እምነት አንድነት ይህን አርማ ሲያይ የሚያቅለሸልሸውም የአንድ እምነት የበላይነትን የሚወክለውን የአንበሳውን ምስል የቀየረ በመሆኑ ነው፡፡
በመስከረም ወር 2004 የፓርቲው አፈ ቀላጤ በሆነችው ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ላይ “ጋኖች አለቁና ምንቸቶች ጋን ሆኑ” በሚል ርዕስ የወጣ ፅሁፍ እንዲህ ይላል፡፡ /ፍኖተ ነፃነት በአንድነት ለዴሞክሲና ለፍትህ ፓርቲ የምትታተም ጋዜጣ ነች፡፡/
“የድሮው የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማና አርማው ምስጢር የእግዚአብሔርንና የኢትዮጵያን ግንኙነትና አንድነት የሚያስረዳ ታሪክ ነው፡፡ አንበሳው እስከ ዘውዱና መስቀሉ የራሱ የባለቤቱ የኢየሱስ ክርስቶስ ምልክትና ሥዕል ነው፡፡ ከዚህ የተለየ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም፡፡ ይሁን እንጂ የእግዚአብሔርን አምላካዊነትና ጠባቂነት አምና ለተቀበለችው ጥንታዊት የአዳም መገኛ ምድረ ኤዶም ወይም ምድረ ገነት ለተባለችው ለኢትዮጵያ የተሰጣትን በረከት ምንነቱንና ምሥጢሩን ሳይረዳ ይህ መንግሥት የአንበሳውን ዓርማ አንስቶ ትርጉም በሌለው ዓርማ መተካቱ ታሪክ የማይረሳው ከፍተኛ ስህተት ነው፡፡ ስለዚህ መስተካከል አለበት እላለሁ፡፡”
ለመሆኑ ለኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ኢየሱስ ክርስቶስ ምናቸው ነው? መስቀሉስ ቢሆን የእስልምና እምነትን ይገልፃል እንዴ? ለነገሩ አሁን አንድነት የእስልምና ጠበቃ ሆኖ መቅረቡ ተገቢ ያለመሆኑን ለማሳየት ብዬ እንጅ ይህ አርማ እኮ ለፕሮቴስታንቱም ምኑም አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎችም ሀገር ነች፡፡ እና የዚህ ባንዲራ መመለስ በሩቅ እንደ ህልም የሚታየው ፓርቲ እንዴት ብሎ ለእስልምና እምነት ነፃነት ሊቆም ይችላል? በየትኛው ሞራሉስ ነው “መንግስት በሃይማኖቶች መካከል ጣልቃ መግባቱን ያቁም” የሚል መፈክር አንግቦ አደባባይ የሚወጣው?
የኢፌዴሪ ሰንደቅ አላማ ፀሃፊው እንዳስቀመጡት የአንድ እምነት መገለጫ የሆነውን ‘አንበሳ ታቅፎ መኖር ነበረበት’ ካልተባለ በስተቀር የሚገባውን ትርጉም የተሰጠውን አርማ የያዘ ነው፡፡ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 3 ንዑስ አንቀፅ 2 መሰረት አርማው የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦች፤ ሕዝቦች እና ሃይማኖቶች በእኩልነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ ይወክላል፡፡ ከዚህ የዘለለ ሌላ ትርጓሜ አልተሰጠውም፡፡ የፓርቲ አርማ አይደለም፤ የትኛውንም ሃይማኖትም አይወክልም፡፡
“የኢየሱስን የትንቢት ስምና መግለጫ የሆነውን ምልክት ወይም የአንበሳ ዓርማ ምንነት በተለይ ለወጣት አንባቢያን ለማሳወቅ ይቻል ዘንድ”
ሲሉ ፀሃፊው ይቀጥላሉ፡፡ ታሪክ የጣለባቸው ሃላፊነት ሆነባቸውና ለተተኪው ትውልድ ያን በጎደሎ ቀለም የተፃፈ ታሪካቸውን ማስተላለፋቸውን ቀጠሉ፡፡ አንድነትም የልብ የልቡን የሚተነፍስባትን ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣን ጀባ አላቸው፡፡
“ይህ ዘውድ ደፍቶ ሠንደቅ ዓላማውን በባለመስቀል ዘንግ ላይ ሰቅሎ ዘንጉን በቀኝ እጁ ይዞ ከሰንደቅ ዓላማው መካከል የተቀረጸው ወይም የተነደፈው የአንበሳ ምስል ወይም ዓርማ በጣም ከፍተኛ ምሥጢር ያለው በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ መለያ ወይም መታወቂና የማንነታችን መገለጫ ሁኖ መኖሩን ታሪክ ያስረዳል፡፡” ሲሉ ቀጠሉና አርማውን ስናይ ምን አይነት ስሜት ሊሰማን እንደሚገባ ሊያስታውሱን ሞከሩ፡፡
“ከሰንደቅ ዓላማችን ላይ ይህን የአንበሳ ዓርማ ስንመለከት ወይም ስናይ ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባትና መረዳት ያለብን ዓርማው በሱ በራሱ በኢየሱስ አምሳል ተመስሎ የተቀረጸ/ የተቀመጠ መሆኑን ነው፡፡ ይህን በማድረጋችንም ሰንደቅ ዓላማችንን እናከብረዋለን፡፡ በተጨማሪም ሰንደቅ ዓላማችንና ዓርማው ለኛ ለኢትዮጵያውያን ድላችን ወይም በሌላ አነጋገር ታቦታችን ነው፡፡”
ይህን ሰንደቅ አላማ የተመለከተ አንድ ዜጋ በምናቡ የቱንም ነገር ሊቀርፅ ይችላል፡፡ ድል አድራጊነቱን፤ እምነቱን፤ ወዘተ… ከምንም ነገር በላይ ደግሞ ኢትዮጵያዊነቱን በሰንደቅ አላማው ውስጥ ሊያየው ይገባል፡፡ ነገር ግን ይህን ባንዲራ ሲያይ ድል ተደራጊነቱ፤ እምነቱ ቦታ ማጣቱ፤ በሀገሩ ሰንደቅ አላማ ያለመወከሉ ሊሰማው አይገባም፡፡ እንዲህ ከሆነ ያ ሰንደቅ አላማ በግድ የተጫነበት እንጅ አምኖ የተቀበለው ሊሆን አይችልም፡፡
“በአንበሳ ተመስሎ ከድሮው ሰንደቅ ዓላማችን ላይ የነበረው የአንበሳ ዓርማ የሚወክለው መሲህ ኢየሱስንና ኢትዮጵያን እንጂ ማንኛዎቹንም ምድራዊ ነገሥታትን ከቶ አይወክልም፡፡”
ሲልም ያትታል ፅሁፉ፡፡ ኢትዮጵያንና ኢየሱስ ክርስቶስን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ አድርጎ የሚያሳይ አርማ በሀገሪቱ ሰንደቅ አላማ ላይ አንዲለጠፍ የሚሻው አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ታዲያ ለሃይማኖቶች እኩልነት ብሎም መንግስት በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ አይግባ ብሎ ለመለፈፍ አንደበቱ እንዴት ሊፈታለት ቻለ?
ፀሃፊው ትረካቸውን ሲያጠቃልሉ ይችን ምክር ጣል አድርገዋል፡፡ 
“ጋኖቹ አልቀው ምንቸቶቹ ጋን እንዳይሆኑ ለማንኛውም አርቆ የሚያስብ አእምሮ እግዚአብሔር እንዲሰጠን መልካሙን ሁሉ እመኛለሁ፡፡”
ጋኖቹ እነማን ነበሩ? ምንቸቶቹስ እነማን ናቸው?
እንግዲህ “ጋኖች” የተባሉት በቀደሙት ንጉሳውያን ስርዓቶች እምነታቸው ህገ መንግስታዊ ጥባቆት ያገኘላቸው፤ መንግስታዊ ሃይማኖት መሆን የሚያስገኛቸው ትሩፋቶች የተበረከቱላቸው ናቸው፡፡ በአንፃሩ “ምንቸቶች” የተባሉት ደግሞ ይህን መብት ተነፍገው የነበሩቱ ይልቁንም “መጤ” ተብለው የተፈረጁት ናቸው፡፡

የበርካታ እምነት ተከታዮች ከዛም አለፍ ሲል እምነት የሌላቸው ዜጎች ባለቤት በሆነች ሀገር በሰላም ለመኖር ያለው አማራጭ ለሁሉም እምነቶች የእኩልነት መብት እውቅና መስጠት ነው፡፡ ሃይማኖት በመንግስት፤ መንግስትም በሃይማኖት ጣልቃ እንዳይገባ ማድረግ፤ ሁለቱን የሚለያይ ቀይ መስመር ማበጀት ይገባል፡፡ በአፈፃፀም ረገድ ችግሮች ከተፈጠሩም እግር በእግር ተከታትሎ መፍታት ያስፈልጋል፡፡ ይህን ማድረግ ሲቻል ነው “ጋኖቹንም” “ምንቸቶቹንም” ሳያልቁ/ሳይሰባበሩ ማኖር የሚቻለው፡፡ ካልሆነ ግን አጋጣሚዎችን ሁሉ ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረግ እንቅስቃሴ “ጋኖቹን” አይጠብቃቸውም፤ “ምንቸቶቹንም” ዘላቂ ዋስትና አይሰጣቸውም፡፡

በመስከረም ወር 2004 የወጣውን የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ከፈለጋችሁ በዚህ ሊንክ ታገኙታላችሁ፡፡
Post a Comment