Friday, July 12, 2013

“ሼክ ኑርሃዊ ሃረካት”?
የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የአሸባሪዎችን ሴራ ፍንትዉ አድርጎ ያሳየዉን የጅሃዳዊ ሃረካት ዘጋቢ ፊልም ጥር 28 ምሽት ለማስተላለፍ ማስታወቂያ /spot/ እንደለቀቀ አንዳንድ ፅንፈኛ ድረ-ገፆች ኢቲቪ በሃሰት የተቀነባበረ ድራማ ሊያሳይ አስቧልና እንዳታምኑት፤ ቴሌቪዥናችሁንም እንዳትከፍቱ ሲሉ ለፈፉ፡፡

የኢቲቪ እዉነት ነዉ እና የዛኛዉ ጫፍ ዉሸት ነዉ እንካ ሰላንቲያ  በዝግጅቱ ተመልካቾች መጠን ላይ ምን አይነት ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችል በወቅቱ ለመገመት ሞክሬ ነበር፡፡ በብሎጌ ጅሃዳዊ ሃረካት፤እውነታ ወይስድራማ? በሚል ባወጣሁት ፅሁፍ የሁለቱ ሽኩቻ የተመልካቹን ቁጥር በከፍተኛ መጠን ሊጨምረው እንደሚችል ገምቻለሁ፡፡ በርግጥም ሁለቱም ወገኖች ለዝግጅቱማስታወቂያእየሰሩለት ስለነበር እድሜው ለአቅመ ዶክመንታሪ የደረሰ ሁሉ እንደተመለከተው ከተዘገበበት እለት ጀምሮ በተሰጡ የድጋፍና የተቃውሞ አስተያየቶች ማወቅ ይቻላል፡፡

ለነገሩ አሁን ይህን መነሻ አደረግሁት እንጅ ላወራ የፈለኩት ሰሞኑን በደሴ ከተማ በአዛውንቱ የሃይማኖት ምሁር ሼክ ኑር ኢማም ላይ ከተፈፀመው አሰቃቂ ግድያ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በሽማግሌው ላይ የተፈጠረው ግድያ ማንንም ሰብዓዊ ፍጡር የሚያሳዝን ነው፡፡ ያም ሆኖ ይገባዋል የጁን ነው ያገኘው ከሚለው ጫፍ የወጣ ኢሰብዓዊነት አንስቶ ገዳያቸው መንግስት ነው የሚሉ እርባና ቢስ ክሶች ተሰምተዋል፡፡

ፅንፈኞቹ የወንጀሉ ፈፃሚዎች ከብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎትና የፌዴራል ፖሊስ የጋራ የፀረ-ሽብር ግብረሃይል እጅ እንደማያመልጡ ያወቁ በሚመስል መልኩ አስቀድመው ገዳዩ ራሱ መንግስት ስለሆነ ንፁሃን ሙስሊሞችን ይዞ ገዳዮቹን በቁጥጥር ስር አዋልኩ ቢላችሁ እንዳታምኑት ሲሉን ሰነበቱ፡፡ ግብረ ሃይሉም እንደሚጠበቅበት ሃላፊነት ገዳይና ተባባሪ ያላቸውን ዘርዝሮ ነገረን፡፡ እኛም ያመንነውን አመንን፡፡

አሁን ደግሞ እነዚሁ ፅንፈኞች ኢቲቪ ደሴ አካባቢ ለዘገባ የሚሆን በቂ መረጃ እንዳገኘ ያወቁ ይመስላል፡፡ እናም አስቀድመው በተለመዱት ማህበራዊ ገፆቻቸው እንዲህ አይነት መረጃዎችን ይዘው ብቅ ብለዋል፡፡
<<በደሴ ከተማ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጋዜጠኞች በየቦታው በመዘዋወር ቃለመጠየቅ ለማድረግ እየሞከሩ ነው፡፡ ቃለ መጠይቅ ለማድረግ የጠየቁት አብዛኛው የደሴ ከተማ ነዋሪ ፈቃደኝነቱን የነፈጋቸው ሲሆን የገጠር ከተማ ነዋሪዎችን ብቻ ቃለ መጠየቅ እያደረጉ መሆኑ ታውቋል፡፡>>
<<በደሴ ከተማ መንግስት ከየቤታቸውና ከመንገድ ላይ ባሰራቸው ንፁሃን ሙስሊሞች ቤት ውስጥ ፖሊስ የጦር መሳሪያ ካስገባ በኋላ የቪዲዬ ቀራጮችን በማስመጣት የጦር ማሳሪያ በማስያዝና ከመኖሪያ ቤታቸው የጦር መሳሪያዎችን እንዲያወጡ በማድረግ ቀረፃ ማካሄዱን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡>>
<<ይህንንም የተቀረፀውን ቪዲዬ ማታ በኢቲቪ ዜና ላይ ለማቅረብ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተሰምቷል፡፡>>
<<ይህ አሳዛኝና አስከፊ ድራማ ሰሞኑን በኢቲቪ ለማቅረብ ዝግጅት እያደረጉ ሲሆን ይህን ሴራ በማጋለጥ መረጃው ላልሰሙት በማሰማት ሁሉም ሙስሊሙ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ እንጠይቃለን፡፡>>ወዘተ
የነዚህ ፅሁፎች ማጠቃለያ መልዕክት <<ኢቲቪ የሚለውን አትስሙት፤ ከሰማችሁትም አትመኑት>> ነው፡፡ ግን ይህ የአትስሙት ጭቅጨቃ የሚኖረው ውጤት የተገላቢጦሹ እንደሚሆን ከልምድ ይጠበቃል፡፡

እስካሁን ኢቲቪ በዚህ ጉዳይ ላይ ስለሚሰራው ዘገባ ምንነት ምንም አላለም፡፡ እነሱ ግን ሼክ ኑርሃዊ ሃረካትብለውታል፡፡ ዘገባው በዘጋቢ ፊልምም ይሁን በዜና መልክ፤ ርዕሱ ሼክ ኑርሃዊ ሃረካትም ይሁን ሌላ ሃረካት እኛ የዘገባዎቹን ድራማነት ወይም እዉነታነት የምንፈርደዉ ካየን በኋላ ስለሆነ በተዘዋዋሪ ለተደረገልን ግብዣ ግን ከወዲሁ ማመስገን ይገባናል፡፡

Post a Comment