Monday, July 22, 2013

“ጋኖች አለቁና ምንቸቶች ጋን ሆኑ”

ፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክንም ሆነ ሞሀመድ ሙርሲን ከስልጣናቸው ለማንሳት በግብፅ የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ በሃገሪቱ ሰንደቅ አላማ የታጀበ ነበር፡፡ መፈክር ያላነገቡቱ በሙሉ ሰንደቅ አላማቸውን ከፍ አርገው ሲያውለበልቡ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በቅርቡ በቱርክ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍም እንዲሁ፡፡ በብራዚል ትንሽ የሳሳ ቢሆንም ሰንደቅ አላማ አልባ ተቃውሞ አልነበረም፡፡ እነሱ ድንጋይና ርችት በእጃቸው ቢይዙም እንኳን ፊታቸውን በሀገራቸው ባንዲራ ቀለም አስውበው አይተናል፡፡
በአዲስ አበባ የተካሄደውን የሰማያዊ ፓርቲ የተቃውሞ ሰልፍ ጨምሮ በደሴና በጎንደር በተካሄዱ ሰልፎች ላይ ግን ይህን አላየንም፡፡ ይልቁንም በኛ ሰልፍ ላይ ሰንደቅ አላማ የያዙ ተሰላፊዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ ሰንደቅ አላማዋም ስትጎሳቆል መላው ህዝብ በቴሌቪዥን መስኮት ተመልክቶቷል፡፡
አንዳንዶች በሰንደቅ አላማዋ መካከል ያለው አርማ እኛን አይወክልም እንደሚሉ አውቃለሁ፡፡ ግን ለምን ታዲያ እነሱን የሚወክላቸውን አርማ ለጥፈውባት በሰልፉ ብቅ አይሉም? ስለሚያፍሩበት ነው ወይስ የፖለቲካ ዋጋ ስለሚያስከፍላቸው? /በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ይህ ባንዲራ የኛ እንዳልሆነ አታውቁምን በሚለው ፅሁፌ ገልጨው ነበር፡፡/
“ይህ ባንዲራ አይወክለንም” ከሚሉት ውስጥ አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ አንዱ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ፓርቲው በደሴና በጎንደር ባካሄዳቸው ሰልፎች ላይም ይህንኑ በተግባር አሳይቷል፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያቱ ሃይማኖትና ፖለቲካን ደባልቆ የማስኬድ የቆየ አባዜው ነው፡፡

Thursday, July 18, 2013

መንዜ ስነ-ቃሎች(ክፍል ሁለት)


ፀብ አጫሪ ስሞች በሚል በፃፍኩት ሀተታ ከጥቂት አመታት በፊት የተሰራ ጥናትን መሰረት በማድረግ የመንዝ ጌራ ምድር ወረዳን የስም አወጣጥ ሁኔታ ለመቃኘት ሞክሬያሁ፡፡

በፅሁፉ ማጠቃለያም በክፍል ሁለት ፅሁፌ በአካባቢ ለወንጀል የሚያነሳሱ ስነ-ቃሎችንና ማጠቃለያ ሀሳቤን ይዤላችሁ እመለሳለሁ ብዬ ነበር፡፡ ይኸ በቃሌ ተገኝቻለሁ፤ በመጀመሪያ እነዚህን ስነ-ቃሎች ያንቧቸዉ፡፡

‹‹ባትገድል እንኳ በል እንገፍ እንገፍ
የአባትህ ጋሻ ትኋኑ ይርገፍ››፡፡

‹‹ገዳይ ገዳይ ያልሽው አባትሽ አይገድል
ገዳይ ገዳይ ያልሽው ወንድምሽ አይገድል
አርሶ ያብላሽ እንጂ ሆድሽ እንዳይጐድል››፡፡

Friday, July 12, 2013

“ሼክ ኑርሃዊ ሃረካት”?
የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የአሸባሪዎችን ሴራ ፍንትዉ አድርጎ ያሳየዉን የጅሃዳዊ ሃረካት ዘጋቢ ፊልም ጥር 28 ምሽት ለማስተላለፍ ማስታወቂያ /spot/ እንደለቀቀ አንዳንድ ፅንፈኛ ድረ-ገፆች ኢቲቪ በሃሰት የተቀነባበረ ድራማ ሊያሳይ አስቧልና እንዳታምኑት፤ ቴሌቪዥናችሁንም እንዳትከፍቱ ሲሉ ለፈፉ፡፡

የኢቲቪ እዉነት ነዉ እና የዛኛዉ ጫፍ ዉሸት ነዉ እንካ ሰላንቲያ  በዝግጅቱ ተመልካቾች መጠን ላይ ምን አይነት ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችል በወቅቱ ለመገመት ሞክሬ ነበር፡፡ በብሎጌ ጅሃዳዊ ሃረካት፤እውነታ ወይስድራማ? በሚል ባወጣሁት ፅሁፍ የሁለቱ ሽኩቻ የተመልካቹን ቁጥር በከፍተኛ መጠን ሊጨምረው እንደሚችል ገምቻለሁ፡፡ በርግጥም ሁለቱም ወገኖች ለዝግጅቱማስታወቂያእየሰሩለት ስለነበር እድሜው ለአቅመ ዶክመንታሪ የደረሰ ሁሉ እንደተመለከተው ከተዘገበበት እለት ጀምሮ በተሰጡ የድጋፍና የተቃውሞ አስተያየቶች ማወቅ ይቻላል፡፡

ለነገሩ አሁን ይህን መነሻ አደረግሁት እንጅ ላወራ የፈለኩት ሰሞኑን በደሴ ከተማ በአዛውንቱ የሃይማኖት ምሁር ሼክ ኑር ኢማም ላይ ከተፈፀመው አሰቃቂ ግድያ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በሽማግሌው ላይ የተፈጠረው ግድያ ማንንም ሰብዓዊ ፍጡር የሚያሳዝን ነው፡፡ ያም ሆኖ ይገባዋል የጁን ነው ያገኘው ከሚለው ጫፍ የወጣ ኢሰብዓዊነት አንስቶ ገዳያቸው መንግስት ነው የሚሉ እርባና ቢስ ክሶች ተሰምተዋል፡፡

Tuesday, July 2, 2013

በናይል/በአባይ ላይ የተፈፀሙ ስምምነቶች(8)

የናይል በከፊል በኛ አጠራር የአባይ ወንዝን በተመለከተ የተደረጉ የቅኝ ግዛት ውሎች ሲነሱ ለሁላችን በቅርብ የሚታወሱን በ1929 እና በ1959 የተደረጉት ናቸው፡፡ ይሁንና ሌሎች በርካታ ውሎችም በተለያዩ ወቅቶች ተፈርመዋል፡፡ ቢያንስ ሰባቱን አሁን መጥቀስ እችላለሁ፡፡ እነዚህ ስምምነቶች በተለያዩ ወቅቶች በተለያዩ ሀገራት መካከል የተፈረሙ ቢሆንም ከመጨረሻው በስተቀር ፍፁም ኢፍትሃዊነቻው ግን ያመሳስላቸዋል፡፡
በመሆኑም እነዚህ ስምምነቶች ባለፈው የአባይ ፖለቲካ በሚል ካወጣሁት ፅሁፍ ጋር ተደጋግፈው ይሄዳሉ በሚል ይህን የትርጉም ስራዬን /lol/ እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ፡፡

ስምምነት አንድ፤ ይህ ስምምነት በሚያዚያ 1891 በእንግሊዝና በጣሊያን መካከል የተደረገ ነው፡፡ /Anglo-Italian Protocol/ በመባል ይጠራል፡፡ የዚህ ስምምነት አንቀፅ ሶስት የጣሊያን መንግስት ከመስኖ ልማት ውጭ ካልሆነ በስተቀር ማንኛውንም አይነት ወደ ናይል በሚፈሰው የውሃ መጠን ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር ግድብ በአትባራ ወንዝ ላይ መገንባት አይችልም ይላል፡፡ ዊክ ፒዲያ ይህን ስምምነት የቋንቋ አጠቃቀሙ ግራ የሚያጋባና የወንዙ ውሃ ባለቤት ማን እንደሆን ወይም ደግሞ ማን የተጠቃሚነት መብት እንዳለው በግልፅ የማያሳይ ነው ይለዋል፡፡


ስምምነት ሁለት፤ ይህ ስምምነት በግንቦት 1902 በጣሊያን፤ በብሪታኒያና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገ ነው፡፡ የዚህ ስምምነት አንቀፅ ሶስት የኢትዮጵያው ንጉስ አፄ ሚኒሊክ ከብሪታኒያ ንጉሳዊ አስተዳደርና ከሱዳን መንግስት ስምምነት ሳያገኙ በአባይ ወንዝ፤ በጣና ሃይቅ ወይም በሶባት ላይ በውሃው ፍሰት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር ምንም አይነት ስራ ላለመስራት ከብሪታኒያ ንጉሳዊ አስተዳደር ጋር ተስማምተዋል ይላል፡፡