Tuesday, June 4, 2013

ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት Vs ሼክ ሻኪር

እየተገፋሁ፤ እየተሰደብኩ ስኳትን ለዋልኩለት ለሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍማ አንዲት ቁራጭ ዜና ብቻ ፅፌ አልቆምም፡፡ ከጠዋቱ 300 ሰዓት እስከ ቀትር 800 ሰዓት የነበረው ሂደት እኮ በሚገርሙ፤ በሚያዝናኑና በሚያበሳጩ ትዕይንቶች የተሞላ ነበር፡፡ እናም ላሁኑ አንዱን መዘዝኩ፡፡
ወደ ኋላ ሶስት ወር ልመልሳችሁ፡፡ በየካቲት ወር በዋሽንግተን ዲሲ የታሰሩት የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት’ እንዲፈቱ የሚጠይቅ አንድ መድረክ ተዘጋጀ፡፡ ግብፃዊ አሜሪካዊው ሼክ ሻኪር በዚህ መድረክ ተገኝተው እንዲህ አሉ፡፡
“መልካሙን ዜና ልንገራችሁ፡፡ በቃ አሸባሪ ብለው ፈርጀውናል፡፡ ቤታችሁ ብትቀመጡም፤ ቴሌቪዥን እያያችሁ ብትሆኑም፤ ቡና እየጠጣችሁ ብትሆኑም፤ ተኝታችሁ ብትሆኑም ወይም ደግሞ ከልጆቻችሁ ጋር እየተጫወታችሁ ብትሆኑ አሸባሪ ናችሁ፡፡ ምክንያቱም እናንተ ሙስሊም ናችሁና፡፡”
ተጨበጨበላቸው፡፡
ወደ ኋላ ሶስት ቀናት ልመልሳችሁ፡፡ በአዲስ አበባ የታሰሩት የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት’ እንዲፈቱ የሚጠይቅ አንድ የተቃውሞ ሰልፍ ተዘጋጀ፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢትዮጵያዊው ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት በዚህ መድረክ ተገኝተው ቃል በቃል እንዲህ አሉ፡፡
“እዚህ የተሰባሰባችሁት ብዙዎቻችሁ ወጣቶችና ጋዜጠኞች ናችሁ፡፡ እዚህ ሀገር ደግሞ ለናንተ የተሰጣችሁን ስም ታውቁታላችሁ፡፡ በሱ ስም ሰላምታ አቀርብላችኋለሁ፡፡ አሸባሪዎች እንደምን ዋላችሁ፡፡”
ተጨበጨበላቸው፡፡
መንግስትን ከፌስ ቡክ በስተቀር ሰልፉን በማውገዝ ማንም የቀደመው የለም፡፡ የመንግስት ቃል አቀባዩ አቶ ሽመልስ ከማል እንዲህ አሉ፡፡
“ሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ሰልፍ የተንፀባረቁት መፈክሮችና ቅሬታዎች ህገ መንግስቱ በፖለቲካና በሃይማኖት መካከል ያስቀመውን የልዩነት መስመር የጣሱ ናቸው፡፡”
በሰማያዊ ፓርቲ የተቃዉሞ ሰልፍ እስኪበቃው ድረስ የተሰደበው ኢሕአዴግ ደግሞ በፓርቲው /ቤት ሃላፊ በአቶ ሬድዋን ሁሴን በኩል ተከታዩን አለ፡፡
“የሃይማኖት አክራሪነትን አጀንዳው አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረው የሰማያዊ ፓርቲ ጸረ-ህገ መንግስታዊ እንቅስቃሴው ዛሬ በጠራው ሰልፍ ተጋልጧል ብዬ አምናለሁ።”
የሰማያዊ ፓርቲ ሰልፈኞች ፒያሳን አልፈው በቸርችል ጎዳና ቁልቁል ሲንደረደሩ ግዙፉን ባለ 13 ፎቅ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት /ኢሬቴድ/ ህንፃ አዩት፡፡ ይሄኔ ደማቸው ፈላ፡፡ ከዛ ጀምረው “ኢቲቪ ሌባ፤ ውሸት ሰለቸን” እያሉ ኢትዮ-ኩባ አደባባይ ደረሱ፡፡
ኢሬቴድ ግን ነገር ላብርድ ብሎ በሆደ ሰፊነት ስድቡን ችሎ አለፈው፡፡ ለምን ተሰደብኩ ብሎ ቃልም አልተነፈሰ፡፡ ቂም ይዞ እንደሁ ግን እንጃ፡፡
ለማንኛዉም ሰማያዊ ፓርቲ እንኳን ደስ አለህ፡፡ የዘራኸውን ልታጭድ ነው፡፡ የለፋህበትን ሰሞኑን የምትከፈል ይመስለኛል፡፡ የግብ ፓርቲዎች ኢትዮጵያን ለማተራመስ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን እያሰባሰቡ ነው፡፡ አንዱ አቅጣጫቸውም ደግሞ ያደሩላቸውን በገንዘብ መደገፍ ነው፡፡

Post a Comment