Saturday, June 22, 2013

የአባይ ፖለቲካኢትዮጵያ የአባይ ወንዝን የፍሰት አቅጣጫ በግዜያዊነት ማስቀየሯ በተፋሰሱ ሀገሮችና በቀጠናው የተለመደ ሙቀት ላይ የፖለቲካ ትኩሳት ጨምሮበታል፡፡
ኢትዮጵያ ገና የግድቡን መገንባት ጅማሮ ባበሰረችበት ወቅት የያዘችውን የጋራ ተጠቃሚነት መርህ በዚህ ወቅትም እየደጋገመች ስታነሳ ግብፅ ደግሞ “ምንም አዲስ የተፈጠረ ነገር የለም”፤ “ተራ የምህንድስና ስራ ነው” በሚል ትኩሳቱን ለማብረድ ሞክራለች፡፡ ያም ሆኖ የሶስትዮሽ አለም አቀፍ የአጥኝዎች ቡድኑ የጥናት ሪፖርቱን ለሶስቱም መንግስታት ማቅረቡን ተከትሎ በጭምብል ተሸፍኖ የነበረው የግብፅ አቋም እርቃኑን እየወጣ ነው፡፡
በብርሃን ፍጥነት የተቀየረው የግብፅ አቋምና የዲፕሎማሲ ውጤቶቹ፤ የናይል ተጠቃሚነት ሁኔታና ምቹ ሁኔታዎች የዚህ ፅሁፍ ትኩረቶች ናቸው፡፡
አባይ ለማን ነው?

ናይል የግብፅ ነው፤ ግብፅም የናይል ነች የሚለው ዘይቤ በግብፃውያን ደም ውስጥ የሰረፀ ብቻ ሳይሆን በኛ በኢትዮጵያውያንም ከሞላ ጎደል ቅቡል የሆነ አስተሳብ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ የመነጨው ከተራ ፕሮፓጋንዳ ብቻ ሳይሆን የግብፃውያን ነፍስያ በናይል ውሃ ላይ በመንጠልጠሏም የተነሳ ነው፡፡
ጥናቶች የሚያመለክቱት ግብፅ ለ100 አመት የሚበቃ የውሃ ሃብት ክምችት ከመሬት በታች እንዳላት ነው፡፡ ያም ሆኖ ሀገሪቱ በገፀ ምድር ውሃ ላይ ነው ጥገኛ የሆነችው፡፡ ግብፅ ከአጠቃላይ የውሃ ፍላጎቷ ከ90 በመቶ በላዩን የምታገኘው ከናይል ነው፡፡ የሃገሪቱ ኢኮኖሚም በተለይም የግብርና፤ የሃይል ማመንጫ፤ ትራንስፖርትና ቱሪዝም ዘርፎች በዚሁ በናይል ወንዝ ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡
በአንፃሩ 85 በመቶ የናይል ውሃ ምንጭ የሆነው አባይ በኢትዮጵያ ውስጥ 850 ኪሎሜትሮችን ቢጓዝም ይህ ነው የሚባል ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አልነበረውም፡፡ ሀገሪቱም ከአባይ ባለፈ ሌሎች በርካታ ወንዞችና የዝናብ ውሃ ምንጮችም አሏት፡፡ በአጭሩ አባይ የቁጭት ምንጭ ካልሆነ በስተቀር ለኢትዮጵያውያን የህይወት ምንጭ ሆኖ አያውቅም፡፡
ግብፅ የናይል ስጦታ ነች /Egypt is the gift of Nile/ የሚለው የግሪካዊው የታሪክ ሰው ሄሮድተስ አነጋገር በፅንሰ ሃሳብም በተግባርም የበላይነት የነበረው አመለካከት ነው፡፡ ናይል ከኢትዮጵያ ይልቅ ለግብፅ አስፈላጊ ነው የሚል እምነትም ከሞላ ጎደል አካባቢያዊና አለም አቀፋዊ ተቀባይነት ያለው ነው ማለት ይቻላል፡፡
የተናጠል ተጠቃሚነት
ግብፅ በናይል ላይ የተሰጣትን “እውቅና” በመጠቀም ስኬታማ የዲፕሎማሲና የልማት ስራዎችን በውስጥም በውጭም ሰርታለች፡፡ በሀገር ውስጥ የአስዋን ግድብን ጨምሮ በርካታ ናይልን መሰረት ያደረጉ የልማትና የምርምር ፕሮጀክቶችን በመገንባት ስኬታማ ነች፡፡ በዲፕሎማሲው ዘርፍም በናይል ላይ ያላትን ጥገኝነት በማስተዛዘኛነት በማቅረብ ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት በወንዛቸው ላይ ምንም አይነት የልማት ፕሮጀክቶችን እንዳይተገብሩ አድርጋለች፡፡ ሱዳንንም ቢሆን እንዳያማህ ጥራው አይነት እንጅ የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ አላደረገቻትም፡፡
ከምርጥ የትምህርት ተቋሞቿ የሚወጡ የውሃና ተፋሰስ መሃንዲሶቿን በውሃ ልማት ላይ በተሰማሩ አለም አቀፍ ተቋሞች በማሰማራትና በአረቡ አለም ባላት ተቀባይነት አማካኝነት ሌሎች ሀገሮች ከለሙ እሷ እንደምትጎዳ አድርጋ ቀርፃለች፡፡ እንዲህ እንዳሁኑ በአደባባይ ባታውጀውም ጎረቤቶቿን የማዳከም ስልት ትከተል እንደነበርም ይታወቃል፡፡ እነዚህ ስልቶች ውጤት አስገኝተውላታል፡፡
እ.አ.አ. በ1929 እና በ1959 የተፈረሙት የቅኝ ግዛት ስምምነቶች እስካሁን ዘልቀው የኖሩት፤ በ1929 ስምምነት መሰረት የላይኛው ተፋሰስ ሀገሮች በናይል ወንዝ ላይ በሚያቅዷቸው ፕሮጀክቶች ውሳኔ ላይ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቷ ተከብሮ የቆየውና ማናቸውም ሀገሮች በናይል ላይ የሚተገብሩትን ፕሮጀክት የመከታተልና የመፈተሽ ስልጣን የጨበጠችው በዚሁ “ካልሆነ እጎዳለሁ” አመክንዮዋ የተነሳ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ግብፅ የ1929 እና 1959 ስምምነቶችን በመጥቀስ ድርሻዬ አይነካም የምትለው ቢያንስ በሶስት ምክንያቶች አለም አቀፍ ተቀባይነት የለውም፡፡ በመጀመሪያ ኢትዮጵያ የስምምነቱ አካል አይደለችም፡፡ ሁለተኛ በአለም አቀፍ ህግ መሰረት ሀገሮች ከቅኝ ግዛት በወጡ ማግስት መውረስ ያለባቸው ግዴታ ድንበር ብቻ ነው፡፡ በሌሎቹ አይገደዱም፡፡ ሶስተኛ ከግብፅና ከሱዳን በስተቀር የሌሎችን ተጠቃሚነት ያላካተተ /descriminatory/ ስለሆነ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቀባይነት የለውም፡፡
የጋራ ተጠቃሚነት እና የግብፅ ፍላጎት
አሁን ኢትዮጵያ በአባይ ላይ የምትገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ በኩል እንደተነገረለት ጠቀሜታው ለታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራትም ጭምር ነው፡፡ የመሰረት ድንጋይ በተጣለበት ወቅት የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ “ጥቅሙ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሀገሮች ሁሉ በተለይም ለሱዳንና ግብፅ ጭምር በመሆኑ ፍትህ የሰፈነበት ሁኔታ ቢኖር የግድቡን ወጪ ሶስቱም ሀገሮች ሊሸፍኑት በተገባ ነበር፡፡ እያንዳንዱ ሀገር በግድቡ በሚያገኘው ጥቅም ልክ ወጪውን ይሸፍኑ ቢባል ሱዳን ቢያንስ 30 በመቶ ግብፅ ደግሞ የወጪውን 20 በመቶ መሸፈን በተገባቸው ነበር፡፡” ብለው ነበር፡፡ የመንግስት ኮሚዩንኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊው አቶ በረከት ስምዖን በቅርቡ በአልጀዚራ ቴሌቪዥን በተደረገ ዉይይት ላይ በተግባርም የተቻችኛው ተፋሰስ ሀገራት ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ የሱዳን ሰሜን ምስራቅ አካባቢ አርሶ አደሮችን በተከዜ ግድብ ተጠቃሚነት በምሳሌ በማንሳት አብራርተዋል፡፡
የሕዳሴው ግድብ ለግብፅና ለሱዳን ይሰጣቸዋል ተብሎ ከሚጠበቁበት ጥቅሞች ዋነኞቹ ወጥነት ያለውና የተመጠነ የውሃ ፍሰት መኖር፤ ከደለል ነፃ የሆነ ውሃ ፍሰትና በተመጣጣኝ ዋጋ የሃይል አቅርቦት ናቸው፡፡ የአባይ ወንዝን ዘለቄታዊ ደህንነት በማረጋገጥ ረገድም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ነው፡፡
የአንዳንድ ግብፃውያን ድብቅ ፍላጎት ግን ራስን ከጉዳት የመጠበቅ ሳይሆን ሌሎችን ከጥቅም መግታት መሆኑን በሕዳሴው ግድብ በያዙት አቋም ግልፅ ሆኗል፡፡ ይህን ፍላጎታቸውን ለማሟላት ደግሞ የሌላ ሀገርን ሉዓላዊነት እስከመዳፈር ሊሄዱ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ሙርሲ በመሩት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የገዥው ፍሪደም ኤንድ ጀስቲስ ፓርቲ ውይይት ላይ ኢትዮጵያን በእጅ አዙር ማተራመስ፤ ከየትኛውም ድጋፍ መነጠልና ይህም ካልተሳካ የቀጥታ ጦርነት መክፈት በአማራጭነት ቀርበዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱም ሁሉንም አይነት አማራጮች እንጠቀማለን /all options are open/ ብለዋል፡፡ አለም አቀፍ ህግ ደግሞ አንድ ሀገር ሌላውን ጦር በማዝመት መዋጋት የሚችለው ወታደራዊ ጥቃት ሲደርስበት ወይም ጥቃቱ እንደማይቀር እርግጠኛ ሲሆን ብቻ ነው ይላል፡፡
የግብፅና የመሪዎቿ ተቀባይነት
ግብፅ አሁን ደረቷን ለከፋ ትችት አጋልጣ ሰጥታለች፡፡ ይህ እርቃኑን የወጣ ሌሎችን አሳንሶ የማየትና የማጥቃት የግብፅ ፖለቲከኞች አባዜ አሁን የአለም መዘባበቻ ሆኗል፡፡
ከራሷ ከግብፅ ውስጥ ብንጀምር ሰፊ ተቀባይነት ያላቸውና በታዋቂ ግለሰቦች የሚመሩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የፕሬዝዳንቱን የድረሱልኝ ጥሪ አውግዘውታል፡፡ ገዥው ፓርቲ በህዝብ የተነሳበትን ቁጣ ለማረሳሳት የዘየደው መላ ነው በሚልም አጣጥለውታል፡፡ ይህ አቋም በተለይ ናሽናል ሳልቬሽን ፍሮንት የተሰኘው ዋናው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅንጅት በግልፅ ያራመደው ነው፡፡ ይልቁንም በመጪው ሰኔ 23/2005 ከሚካሄደው ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ በፊት ሙርሲን የመተማመኛ ድምፅ ለማሳጣት የድጋፍ ፊርማ /15 ሚሊዮን/ ማሰባሰባቸውን ቀጥለዋል፡፡
የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሶቮኒ አንዳንድ የግብፅ ባለስልጣናትና  ቡድኖች  የሚሰጡትን የትምክህትና ኢምክንያታዊ ንግግሮች እንዲያቆሙ ጠይቀዋል፡፡ “ግብፅ ጥቁር አፍሪካውያንንና አካባቢውን እየጎዳች እንድትኖር ማንም አይፈቅድላትም” ሲሉም ማስፈራሪያ አዘል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በተመሳሳይ ሱዳንም በረጅም ግዜ ወዳጇ /ምንም እንኳን ወዳጅነታቸው በእኩልነት ላይ ያልተመሰረተ ቢሆንም/ ላይ ፊቷን አዙራባታለች፡፡ “ሱዳን ራሷን ከግብፅ ነጠለች” ሲሉ ነው የመገናኛ ብዙሃን የዘገቡት፡፡ ይህ አስተያየት የተሰጠው የግብፅ ፖለቲከኞች ሱዳን በግድቡ ላይ የያዘቸውን አቋም መተቸታቸውን ተከትሎ ነው፡፡ ሱዳን የግድቡ እውን መሆን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝላት ይህንንም በቁሳቁስና በባለሙያዎችም ለመደገፍ ዝግጅቷን አረጋግጣለች፡፡ ለነገሩ ሱዳን ለሕዳሴው ግድብ ከታህሳስ 2004 ጀምራ ነው የቁሳቁስ ድጋፍ ጭምር የሰጠችው፡፡ ይህም ሱዳን ከግብፅ ጋር ካላት የጌታና ሎሌ ግንኙነት ይልቅ በእኩልነትና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ለተመሰረተው የኢትዮ- ሱዳን ግንኙነት ዋጋ መስጠቷን ያመላከተ ነው፡፡
በእድሜ ትንሻ ደቡብ ሱዳንም ለእድሜ ባለፀጋዋ ግብፅ ግልፅ መልዕክት አስተላልፋለች፡፡ "ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው ግድብ አሁን ላለውም ሆነ ለመጪው የየሀገራቱን ትውልዶች የሚጠቅም ነው" ብላለች በዋና ተደራዳሪዋ አማካኝነት፡፡ ደቡብ ሱዳን በኢንቴቤው ማዕቀፍ ላይ የስምምነት ፊሪማዋን ለማስፈር ፍላጎቷንም አሳይታለች፡፡ የዝግጅት ስራዎችን እያጠናቀቀች መሆኗንና የሃገሪቱ ፓርላማ ስምምነቱን እንዳፀደቀው ቀድመው የፈረሙትን ስድስት ሀገሮች እንደምትቀላቀል የመስኖና ውሃ ልማት ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
በዚሁ ወቅት ግብፅ የጦር አመራሮቿን የሶማሊያን ጦር ማጠናከርና ከተቻለም በሶማሊያ የጦር ሰፈር ለማቋቋም በሚቻልበት አግባብ ላይ ለመምከር በሚል ወደ ሞቃዲሾ ልካለች፡፡ የሶማሊያ መንግስት ልዑካኑን በፕሬዝዳንት ደረጃ ለማነጋገር ፈቃደኛ አለመሆኗን ዘገባዎች አስረድተዋል፡፡ ሆኖም በቋፍ ያለ ሰላም ይዛ እንዲህ አይነት ሃላፊነት የጎደለው እርምጃ ልትወስድ አትችልም ከሚል መፅናኛ በስተቀር ሶማሊያ የግብፅን አቋም አትደግፍም ብሎ መደምደም ይከብዳል፡፡
ከሶማሊያ ይልቅ የሶማሊላንድ ግዛት አቋም አስተማማኝ የሆነ ይመስላል፡፡ አንዳንድ የግዛቷ ድረ ገፆች በርዕሰ አንቀፃቸው ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር ጦርነት ከገጠመች እኛም ከጎኗ እንሰለፋለን እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ሶማሊላንዶች ከሲያድ ባሬ የግፍ አገዛዝ ጋር ሲዋጉ ግብፅ የፈፀመችባቸውን በደል የረሱ አይመስሉም፡፡ ግብፅ ሲያድ ባሬን በወታደራዊ ቁሳቁስ ከመደገፏም ባለፈ ነፃነታችንን ካገኘንም በኋላ በአረቡ አለም ተደማጭነቷን ተጠቅማ እንደሀገር እንዳንቆጠር እንቅፋት ሆናብናለች ይሏታል፡፡ የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ እንዲሉ ሆኖ አሁን “ለግብፅ መሳሪያ አንሆንም፤ ዘላቂ ጥቅማችን ከኢትዮጵያ ጋር ነው” ብለዋል፡፡
ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ጎረቤት ሀገሮች ውስጥ እስከዛሬ አቋሟ በግልፅ ያልታወቀው ሌላዋ ሀገር ኤርትራ ነች፡፡ በርግጥ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አማካሪ የማነ ገብረኣብ ከሰሞኑ ወደ ካይሮ ተጉዞ በዚህ ጉዳይ ላይ መክሯል፡፡ በሚያዚያ ወር መጀመሪያም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኦስማን ሳላህ ጋር በመሆን የፕሬዝዳንታቸውን መልዕክት የያዘ ፓስታ ለሙርሲ ሰጥተዋል፡፡ መልዕክቱም ኤርትራ የግብፅን የቅኝ ግዛት ውሎች መሰረት ያደረገውን የውሃ አጠቃቀም ትደግፋለች የሚል ነው፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ካላት ወቅታዊ ግንኙነት አንፃር ሲመዘን በወንዙ አጠቃቀም ላይ ፍትሃዊ አቋም ትይዛለች ተብላ አትጠበቅም፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ እስካሁን አንድም ሀገር የግብፅን አቋም ደግፎ አልቆመም፡፡ በአንድ ወቅት የሕዳሴው ግድብ የግብፅን ደህንነት አደጋ ላይ ይጥላል ያሉት የሳውዲ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትርም እንኳን ምንም እንኳን ምክንያቱ በግልፅ ባይታወቅም ከሃላፊነታቸው ተነስተዋል፡፡ በቅርቡም በቁም እስር እንዲቆዮ መወሰኑ ተሰምቷል፡፡ ያም ድጋፍ ቢሆን በግለሰብ እንጅ በሀገር ደረጃ የተሰጠ አልነበረም፡፡ ሁሉም ሲደማመር የሚያሳየው ግብፅ የያዘችው አቋም አለም አቀፍ ድጋፍ ማጣቱን ነው፡፡
የሁሉም ሀገሮች ድጋፍ ያለመስጠት ብቻውን ግን ግብፅ በተሳሳተ መንገድ ላይ መቆሟን አያረጋግጥም፡፡ ከሁሉ በላይ ማረጋገጫ የሚሆነው የራሷ የግብፅ መከራከሪያ አመክንዮ ሚዛናዊነት ነው፡፡ አየር ላንዳዊው የአለም አቀፍ ጉዳዮች ባለሙያ ፊናን ከኒንግሃም እንደሚሉት በዚህ ረገድም ዉሃ የሚቋጥር የመከራከሪያ ነጥብ የላትም፡፡ “አለም አቀፍ የጥናት ቡድኑ በግድቡ የተነሳ በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገሮች ላይ ይህ ነው የሚባል ዘላቂ የውሃ ቅናሽ አያሳይም ብሏል፡፡ ይሁንና የግብፁ ፕሬዝዳንት ይህን የሚያጣጥል ምንም አይነት መረጃ ሳያቀርቡ የሀገራቸው የውሃ መጠን በ20 በመቶ እንደሚቀንስ እየተናገሩ ነው፡፡ ጥያቄው እውን ግድቡ የውሃውን ፍሰት ይቀንሰዋልን የሚለው ነው? እስካሁን ያሉ ሳይንሳዊ ጥናቶች ግን ይህን አያሳዩም፡፡ ይህ ጉዳይ ይልቅ የሚያስነሳው ሌላ ጥያቄ አለ፡፡ ፕሬዝዳንት ሙርሲ ለምንድን ነው እንዲህ ጉዳዩን ያከረሩት? መልሱ ደግሞ ከወንዙ የፍሰት አቅጣጫ መቀየር ይልቅ ወደ የውስጥ ፖለቲካ አቅጣጫ ማስቀየር ይቀርባል፡፡” ብለዋል፡፡
ይህን አመለካከት ጥቂት የማይባሉ የሀገሪቱ ምሁራንና ፖለቲከኞችም የተጋሩት ነው፡፡ የኖቤል ተሸላሚውና የግብፁ ናሽናል ሳልቬሽን ፍሮንት ፓርቲ አመራር ኤል ባራዲ "አለም አቀፉ ህግ ከኛ ጎን አይደለም፤ እኛ በተከተልነው የተሳሳተ ፖሊሲ የተነሳ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ለኛ የሚያዝንልን አይደለም” ብለዋል፡፡ ኤል ባራዲ በቲውተር ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ ችግሩን ለመፍታት በሁለቱ ሀገሮች መካከል ምክንያታዊ ውይይትና ትብብር ያስፈልጋል ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
ልዩነትን በውይይት መፍታት
ከከባቢው ባሻገር ስንመለከት በቅርበት የሚታየው የአፍሪካ ህብረት ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የ53 ሀገሮችን ድምፅ የመወከል ሃላፊነት የተሸከመው ይህ ተቋም በኮሚሽኑ አማካኝነት ያስተላለፈው መልዕክት ግብፅን የሚያሳጣ ነው፡፡ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ድላሚኑ ዙማ ግብፅና ኢትዮጵያ ወደ ውይይት መግባት እንዳለባቸውና ውይይቱም በአዲስ አፍሪካዊ መንፈስ ላይ መመስረት እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡
ከቅኝ ግዛት ዉሎች ጋር ራሷን አቆራኝታ ያለችው ግብፅ እንጅ ኢትዮጵያ ባለመሆኗ የርሳቸው ንግግር ከዲፕሎማሲያዊ ንግግር በዘለለ ሲታይ ግብፅ የምትመራበት ያረጀ መንፈስ ከዘመኑ የአፍሪካ ህዳሴና ዳግም ዉልደት ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም የሚል ነው፡፡ ዙማ ኢትዮጵያ ወንዟን መጠቀም ያስፈልጋታል፤ ይገባታልም ብለዋል፡፡
ግብፅ በአፍሪካ ብቻም ሳይሆን በሌላው የዓለም ክፍልም በናይል ዲፕሎማሲ የበላይነቷን እያጣች ነው፡፡ በአሜሪካና ብሪታኒያ ባሉ መልዕክተኞቿ አማካኝነት እነዚህ ሃያላን ሀገራት በጉዳዩ ውስጥ እጃቸውን እንዲያስገቡ ጠይቃለች፡፡ ከሁለቱም ሀገሮች የተሰጣት ምላሽ ግን ችግሩን ሁለታችሁ በድርድር /amicably/ ፍቱት የሚል ነው፡፡ ይህም የራሱ ትርጓሜ ያለው ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህንን ጉዳይ የግብፅ መገናኛ ብዙሃን የዘገቡት "ግብፅ ፊት ተነሳች" በሚል ነው፡፡
የቀድሞው በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ዴቪድ ሺን “ግብፅ በግድቡ ላይ ያላትን ተቃርኖ አቁማ ከኢትዮጵያ ጋር ካልተባበረች ዘላቂ የውሃ ፍላጎቷን ለማግኘት ትቸገራለች” ሲሉ መላ ምታቸውን አስፍረዋል፡፡ አምባሳደሩ ግድቡ የምስራቅ አፍሪካን የኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን የሚያፋጥን እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ ባንኪ ሙን ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝና ለፕሬዝዳንት ሙርሲ ደውለው የነገሯቸውም በድርድር የመፍታት ግድነትን ነው፡፡
የድርድር ጉዳይ ከተነሳ የላይኞቹ የተፋሰሱ ሀገሮች በተለይም ኢትዮጵያ ላለፉት /10/ አመታት ሲያቀነቅኑት የነበረ የመፍትሄ ሃሳብ ነው፡፡ ፍላጎት ያላሳየችው ግብፅና በውስኑም ሱዳን በመሆናቸው የነዚህ ሃያላን ሀገሮች ምላሽ ግብፅን ያለሽ አማራጭ ወደገፋሽው ድርድር መመለስ ነው የሚል ነው፡፡ በሌላ በኩል ድርድር ማጠንጠኛው ሰጥቶ የመቀበል መርህ ነው፡፡ ምንም ላለማግኘት ማንም አይደራደርም፡፡ ስለሆነም የግብፅ አንዲት ጠብታ ውሃ አንሰጥም አቋም ተቀባይነት መሸርሸሩን ያሳያል፡፡
ምቹ ሁኔታ
የግድቡ የፍሰት አቅጣጫ በግዜያዊነት መቀየርና የሶስትዮሽ አጥኚ ቡድኑ ሪፖርት ይፋ መሆን ኋላ ቀሩ የግብፅ አቋምና ተራማጁ የተፋሰሱ ሀገሮች አቋም በይፋ የሚፋለሙበትን አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡ ሆድ ያባውን እንዲሉ ግድቡ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገሮች ላይ ይህ ነው የሚባል ጉዳት አያስከትልም የሚለው የአጥኚ ቡድኑ ሪፖርት መውጣት የግብፅን እኩይ ተግባር በማሳየት ለከፋ የዲፕሎማሲ ክስረት ዳርጓታል፡፡
ይህ ሁነት ሁሉንም ወገኖች ተጠቃሚ ለሚያደርጉ ድርድሮች በሯን መዝጋቷን ያረጋገጠችበት ነው፡፡ የናይልን ውሃ እሷ እንዳሻት እንድትጠቀም ሌሎቹ የተፋሰሱ ሀገሮች ግን ወንዛቸውን ተጠቅመው ሲበለፅጉ ማየት እንደማትሻ አረጋግጣለች፡፡ እስካሁን በድብቅ የነበረውን ኢትዮጵያን የማተራመስ ስልት አሁን በአደባባይ ያወጀችበት፤ ጥቅሟ ቅንጣት ታክል ከተነካ ሉዓላዊ ሃገርን ለመውጋት የማትመለስ መሆኗን አለም የተረዳበት ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም እስካሁን ሲያካሂድ የነበረውን የዲፕሎማሲ ጥረት አጠናክሮ ማስቀጠል ይኖርበታል፡፡ ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ አለም አቀፍ ጫና የሚያሳድር የተፅዕኖ ፈጣሪ ቡድን ማቋቋም ላይ እንደተጠመደችው ሁሉ ኢትዮጵያም የትኩረት አቅጣጫዋን ለይታ ሰፊ የዲፕሎማሲ ዘመቻ ማካሄድ አለባት፡፡
ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸው ደግሞ የተፋሰሱ አባል ሀገሮች ናቸው፡፡ የሚበዙት ሀገሮች /ስድስቱ/ የኢንቴቤውን የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ ፈርመዋል፡፡ ቀሪዎች ሁለቱ ሱዳኖችና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፊርማቸውን እንዲያኖሩ የማግባባት ቀዳሚ ሚናዋን ኢትዮጵያ መጫወት አለባት፡፡  ስምምነቱ ፀድቆ  የአለም አቀፍ ህግ አካል እስኪሆንና በተግባር እስኪውል ድረስ ማለት ነው፡፡
“ግብፅ ከንግዲህ እንድትጎዳን አንፈቅድላትም” ያለችው ኡጋንዳ ያሳየችውን ያክል ጠንካራ ድጋፍ ከሌሎቹም ለማግኘት ኢትዮጵያ ሳታሰልስ መስራት ይጠበቅባታል፡፡
የታችኛው ተፋሰስ አካል የሆነችው ሱዳን ከግብፅ አቋም በተቃራኒ እንደቆመች በከፍተኛ ባለስልጣኖቿ አማካኝነት ያስተላለፈችው መልዕክት ያስረዳል፡፡ ይሁንና ሱዳን አሁንም የቤት ስራዋን ገና አልጨረሰችም፡፡ የኢንቴቤው የትብብር ስምምነት እስከመፈረም መዝለቅ አለባት፡፡ ግብፅን ለማግባባትም ቢሆን ከሱዳን የሚቀርብ አይኖርም፡፡ በተጨማሪም በሶስትዮሽ የባለሙያዎች ቡድኑ ሪፖርት ላይ ግልፅ አቋም መያዝ ይጠበቅባታል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ኢትዮጵያ የስካሁኑን የሱዳን ተነሳሽነት ማድነቅና ቀሪዎቹን እንድትፈፅም ማግባባት ይኖርባታል፡፡ በደቡብ ሱዳን በኩል የሚሰነዘሩ በጎ አስተያየቶችም አስተማማኝ የሚሆኑት ሀገሪቱ የስምምነቱ አካል መሆኗን በፊርማዋ ስታረጋግጥ ነው፡፡
ኢትዮጵያ እስካሁን ከሁሉም ጎረቤት ሀገሮች ጋር በትብብር ለመስራትና የጋራ ችግሮችን በጋራ ጥረት ለመፍታት ያሳየችውን ቁርጠኝነት አሁንም አጠናክራ ማሰቀጠል አለባት፡፡ ለዚህም መልካም አጋጣሚ የሚፈጥረው ደግሞ የተጀመረው የመሰረተ ልማትና የሃይል ትስስር ነው፡፡
ኢትዮጵያን አሁንም በተዛባ እይታቸው የሚመዝኗትን ግብፆች ማሳያ በሆነው ንግግራቸው ዶክተር ሆሳም ኤል ሻዝሊ የተባሉ የግብፅ የኢኮኖሚ፤ ፖለቲካና አለም አቀፍ ጉዳዮች አማካሪ “እስራዔል አይዞሽ ባትላት ኖሮ ኢትዮጵያ ግድቡን እንኳን ልትገነባ አታስበውም ነበር” ብለዋል ከናይል ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ፡፡
በርግጥ ኢትዮጵያ በድህነቷ የተነሳ በአባይ ላይ እንዲህ አይነት ታላቅ ግድብ መስራት ይቅርና አሳ ማጥመድ እንኳን ሳትችል ቆይታለች፡፡ አሁን ግን የእስራዔልንም ሆነ የማንንም ሀገር የገንዘብ ድጋፍ ሳያሻት ነው የግድቡን ግንባታ አንድ አምስተኛ ያጠናቀቀቸው፡፡ ለዚህም በሀገሪቱ የተመዘገበው ፈጣንና ተከታታይ እድገት ዋናው ምክንያት ነው፡፡ የግድቡን ቀሪ ስራ የማጠናቀቅ ጉዳይም ይህንኑ ፈጣን እድገት ከማስቀጠልና ድህነትን ከማጥፋት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ የግድቡን ደህንነት አስተማማኝ የማድረግና ሌት ተቀን በግንባታ ስራው የተጠመዱ የኩራት ምንጮች የሆኑ ሰራተኞችን ሰላም ማረጋገጥም ለነገ የሚባል ስራ መሆን የለበትም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዳሉት የግብፅ መንግስት “ካላበደ በስተቀር” ወደ ጦርነት ይገባል ተብሎ  አይታሰብም፡፡ ነገር ግን በውስጥም በውጭም ተፅዕኖ ውስጥ የወደቀ መንግስት አያብድም ለማለትም ያስቸግራል፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ አስቀድሞ ያበደ ጎረቤትም አላት፡፡ እናም የግብፅ መንግስት ማናቸውንም የፀረ- ሰላም ሃይሎች ተጠቅሞ መፍጨርጨሩ የማይቀር ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ዘርፍም አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡
Post a Comment