Sunday, June 16, 2013

ለምን ጋሪውን ከፈረሱ እናስቀድማለን?አንዳንድ ሰዎች የኢቲቪን የኃላ ታሪክ በመዘከር የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ሲያስተላልፍ ያሉበትን ድክመቶች በማህበራዊ ድረ-ገፆች ሲተቹ ተመለከትኩ፡፡ ዛሬ ዋልያዎቹ ከባፋና ባፋና ጋር ያደረጉትን ጨዋታ የደቡብ አፍሪካ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ባለሙያዎች ሙሉ በሙሉ የስርጭቱ ባለቤት ሆነው ስለሰሩት እንዲህ ያማረ ጨዋታ በቴሌቪዥን መስኮት አየንም ተባለ፡፡ እውነታውን በኋላ እመለስበታለሁ፡፡
እኔ የምለው ግን ካሁን በፊት ራሱን እግር ኳሱንስ እንጫወተው ነበር እንዴ? አናውቅም እንዴ የእግር ኳስ ታሪካችንን? ርግጥ ነው ቀረፃውንና ስርጭቱን አንችልበትም፡፡ ግን ጨዋታውንም አንችልበትም ነበር እኮ፡፡ ታዲያ ከፈረሱ በፊት ለምን ጋሪውን እናስቀድማለን? አሁን እግር ኳሳችን እያደገ ነው፡፡ ኢቲቪም አቀራረቡን አብሮ ያሳድጋል ብለን ተስፋ ማድረግ አይሻልም ትላላችሁ?
የዛሬውን ቀረፃ ያካሄደው ደግሞ የሳውዝ አፍሪካ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አይደለም፡፡ የስርጭቱ ባለቤት ከሆነዉ ፊፋ ኮንትራቱን አሸንፎ ይህን ጨዋታ ያሰራጨዉ በዘርፉ እውቅና ያለዉ አውሮፓዊ ኩባንያ ስፖርት ፋይፍ ነው፡፡ ይህ ኩባንያ ቀረፃውን ያካሄደው በስምንት ካሜራ ነው፡፡ ኢቲቪ ስምንት ካሜራ እንኳን ለእግር ኳስ ለብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ቀንም መድቦ አያውቅም፡፡ ብዙዎቹን የአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታዎች በአንድ ካሜራ ነው የሚቀርፀው፡፡ ታዲያ ባለሙያው ከወዲያ ወዲህ ሲንከራተት ጎል የሆነች ኳስ ብታመልጠው እንኳን ይገርማል እንዴ?

የዛሬውን እግር ኳስ ቀረፃ በተመለከተ እውነታው ከተባለው እጅጉን የተለየ ነው፡፡ ስፖርት ፋይፍና የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ቀረፃቸውን በተናጠል ነው ያካሄዱት፡፡ ስፖርት ፋይፍ በስምንት ካሜራ ኢቲቪ ደግሞ በስድስት ካሜራ፡፡ ኢቲቪ አንድም የስፖርት ፋይፍ ካሜራማን ወይም ዳይሬክተር አልተጠቀመም፡፡ በመሆኑም በኢቲቪ የታየዉ ምስል በኢሬቴድ ባለሙያዎችና መሳሪያዎች የተቀረፀዉን ብቻ ነው፡፡ በርግጥ ለምልሰተ ጨዋታ /replay/ የነሱን ምስል ተጠቅሟል፡፡ ይህንም ያደረገው እነሱ ለምልሰተ ጨዋታ የሚጠቀሙበት መሳሪያ አይነት ስለሌለው ነው፡፡
ባለማወቅ ወይንም እያወቃችሁ የትችት ጥማታችሁን ለማርካት በኢቲቪ ላይ የዘመታችሁትን አሁንም ደግሜ ተሳስታችኋል አልያም ዋሽታችኋል እላችኋለሁ፡፡ የሳውዝ አፍሪካ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን /SABC/ እናንተ እንዳላችሁት ሳይሆን በኢሬቴድ ድጋፍ ነው የሃገሩን ተመልካችና አድማጭ ማገልገል የቻለው፡፡ ኮርፖሬሽኑ አንድ ካሜራ ማን፤ የተወሰኑ ሪፖርተሮችና አንድ የስፖርት ክፍል ሃላፊን ይዞ በመምጣት በአምስት የሬዲዮና በሁለት የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ ለተመልካችና አድማጮቹ ጨዋታዉን በቀጥታ አስተላልፏል፡፡ አንድ የካሜራ ባለሙያ ያመጡትም የተናጠል ቀረፃዎችንና ቃለመጠይቆችን ለመስራት እንጅ ሙሉ ጨዋታዉን ለማሰራጨት አይደለም፡፡
የሳውዝ አፍሪካ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሪፖርተሮች ስራቸዉን በአግባቡ እንዲያከናውኑ ማለትም የሌሎች ጋዜጠኞች /commentators/ ድምፅ ሳይቀላቀልና በስክሪን ላይም የኢሬቴድ አርማም ሆነ ሌላ ፅሁፍ ሳይገባ ማስተላለፍ እንዲችሉ የዲኤስኤንጂ /digital satellite news gathering/ መሳሪያና አንድ ባለሙያ ከኢሬቴድ ተከራይተዋል፡፡
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ኢቲቪ ምስጋና ሳይሰጥ የእነሱን ምስል እንዳሰራጨ ተደርጎ ተወቅሷል፡፡ እንደው ኢቲቪን የመተቸት ልምድ ሆኖብን ወይም ከሱ የአቅም ማነስ ፍቅር ይዞን ካልሆነ በስተቀር ስለምን ብሎ ነው ምስጋና ለነሱ የሚቸረው? እንደውም እነሱ ናቸው አንጅ ነፃ ሲግናል /free signal/ የሰጣቸውን /ዶላር ከፍለውም ቢሆን/ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትን ማመስገን የነበረባቸዉ፡፡
እንዲህ የምለው ኢቲቪ በሃሰት መረጃ ጥላሸት መቀባት የለበትም ለማለት እንጅ በሙያዉ የተካነ ወይም ከደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙሃን የተሻለ ነው ለማለት አይደለም፡፡ ሀገራዊው የቴክኖሎጂ ዘርፍ ኋላቀርነታችን የዚህ ተቋምም መገለጫ ነው፡፡ ከሳውዝ አፍሪካ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንም ሆነ ከስፖርት ፋይፍ የሚማራቸዉ ጥበቦችና ሊያሟላቸው የሚገቡ መሳሪያዎች አሉት፡፡ እንዲህ እንደዛሬዉ ያሉ ትላልቅ መድረኮች አቅሙን የሚፈትሽባቸውና ጉድለቱን የሚለይባቸው መሆንም ይገባቸዋል፡፡
እናንተ ግን ተናግራችሁ ታናግራላችሁ፡፡ ለማንኛዉም እንኳን ደስ አለን፡፡
Post a Comment