Tuesday, July 2, 2013

በናይል/በአባይ ላይ የተፈፀሙ ስምምነቶች(8)

የናይል በከፊል በኛ አጠራር የአባይ ወንዝን በተመለከተ የተደረጉ የቅኝ ግዛት ውሎች ሲነሱ ለሁላችን በቅርብ የሚታወሱን በ1929 እና በ1959 የተደረጉት ናቸው፡፡ ይሁንና ሌሎች በርካታ ውሎችም በተለያዩ ወቅቶች ተፈርመዋል፡፡ ቢያንስ ሰባቱን አሁን መጥቀስ እችላለሁ፡፡ እነዚህ ስምምነቶች በተለያዩ ወቅቶች በተለያዩ ሀገራት መካከል የተፈረሙ ቢሆንም ከመጨረሻው በስተቀር ፍፁም ኢፍትሃዊነቻው ግን ያመሳስላቸዋል፡፡
በመሆኑም እነዚህ ስምምነቶች ባለፈው የአባይ ፖለቲካ በሚል ካወጣሁት ፅሁፍ ጋር ተደጋግፈው ይሄዳሉ በሚል ይህን የትርጉም ስራዬን /lol/ እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ፡፡

ስምምነት አንድ፤ ይህ ስምምነት በሚያዚያ 1891 በእንግሊዝና በጣሊያን መካከል የተደረገ ነው፡፡ /Anglo-Italian Protocol/ በመባል ይጠራል፡፡ የዚህ ስምምነት አንቀፅ ሶስት የጣሊያን መንግስት ከመስኖ ልማት ውጭ ካልሆነ በስተቀር ማንኛውንም አይነት ወደ ናይል በሚፈሰው የውሃ መጠን ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር ግድብ በአትባራ ወንዝ ላይ መገንባት አይችልም ይላል፡፡ ዊክ ፒዲያ ይህን ስምምነት የቋንቋ አጠቃቀሙ ግራ የሚያጋባና የወንዙ ውሃ ባለቤት ማን እንደሆን ወይም ደግሞ ማን የተጠቃሚነት መብት እንዳለው በግልፅ የማያሳይ ነው ይለዋል፡፡


ስምምነት ሁለት፤ ይህ ስምምነት በግንቦት 1902 በጣሊያን፤ በብሪታኒያና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገ ነው፡፡ የዚህ ስምምነት አንቀፅ ሶስት የኢትዮጵያው ንጉስ አፄ ሚኒሊክ ከብሪታኒያ ንጉሳዊ አስተዳደርና ከሱዳን መንግስት ስምምነት ሳያገኙ በአባይ ወንዝ፤ በጣና ሃይቅ ወይም በሶባት ላይ በውሃው ፍሰት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር ምንም አይነት ስራ ላለመስራት ከብሪታኒያ ንጉሳዊ አስተዳደር ጋር ተስማምተዋል ይላል፡፡ያም ሆኖ የዚህ አንቀፅ የአማርኛ ትርጓሜ ለሌላ አንደምታ የሚያጋልጥ ስለነበር ኢትዮጵያ አልፈረመችም፡፡ በመሆኑም ስምምነቱ በኢትዮጵያ በኩል አልፀደቀም፡፡


በዚህ አንቀፅ የሱዳን መንግስት የሚል ሃረግ ይግባ እንጅ ሱዳን ማለት በኮንዶሚኒየም ስምምነት /condominium agreement - CA/ መሰረት ሱዳን የብሪታኒያና ግብፅ የጋራ ግዛት እንደሆነች ነው የምትቆጠረው፡፡


ስምምነት ሶስት፤ ይህ ስምምነት በግንቦት 1906 በብሪታኒያና በኮንጎ መካከል የተደረገ ነው፡፡ የዚህ ስምምነት አንቀፅ ሶስት የኮንጎ መንግስት ከሱዳን መንግስት ስምምነት ካላገኘ በስተቀር በሴምሊኪ ወይም ኢሳንጎ ወንዞችም ሆነ በአቅራቢያቸው ወደ አልበርት ሃይቅ በሚገባው ውሃ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር ምንም አይነት ግንባታ ላለማድረግ ወይም እንዲደረግ ላለመፍቀድ ተስማምቷል ይላል፡፡ 


ከላይ በተጠቀሰው ኮንዶሚኒየም ስምምነት መሰረት ሱዳን የሚባለው ሀገር በብሪታኒያና በግብፅ የጋራ ቁጥጥር ስር ያለችውን ተገዥ ሀገር የሚያመለክት ነው፡፡ ይህን ስምምነት ኮንጎ የውሃ ሃብቷን እንዳትጠቀም ከመከልከሉ ባለፈ ይበልጥ ኢፍትሃዊ የሚያደርገው በኮንጎ ስም የተዋዋለችው ቤልጂየም መሆኗ ነው፡፡


ስምምነት አራት፤ ይህ ስምምነት በታህሳስ 1906 በጣሊያን፤ በብሪታኒያና በፈረንሳይ መካከል የተደረገ ነው፡፡ የዚህ ስምምነት አንቀፅ አራት በአንድነት ለመስራት…ደህንነታችንን ለማረጋገጥ … የብሪታኒያንና የግብፅን የናይል ወንዝ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ… በተለይም የውሃውን ፍሰትና የገባር ወንዞችን ለመቆጣጠር ሲባል… ለአካባቢው ህዝቦች ተገቢውን ቦታ በመስጠት… የጣሊያን ጥቅምም ሳይጎዳ የሚሉ ሃሳቦችን ያካተተ ነው፡፡


ይህ በተግባር የኢትዮጵያን የውሃ ሃብት የመጠቀም ሉዓላዊ መብት ያገደ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይህን ስምምነት አልተቀበለችውም፡፡ ነገር ግን ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ሃይሏ በቂ ስላልነበረ በውሃ ሃብቷ የመጠቀም መብቷን ማስመለስ አልቻለችም፡፡


ስምምነት አምስት፤ ይህ እንኳን ስምምነት ተብሎ ሊወሰድ ባይችልም በብሪታኒያና በጣሊያን መካከል የተደረገ የስምምነት ማስታወሻ /exchange of notes/ ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይህ ማስታወሻ የጣሊያን መንግስት ግብፅና ሱዳን ከናይል ወንዝ የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት መብት እንዳላቸው እውቅና ይሰጣል፡፡ … በጥቁር አባይም ሆነ በነጭ ናይል መነሻዎችና ራስጌ ላይ እንዲሁም በገባሮቻቸው ላይ ወደታችኘው ተፋሰስ በሚፈሰው ውሃ ላይ አንዳችም ተፅዕኖ የሚያሳድር ስራ ላለመስራት የሚሉ ስምምነቶችን ይዟል፡፡


ኢትዮጵያ ይህን ውል እንዳልተቀበለችው በወቅቱ ለሁለቱም ሀገሮች በሚከተለው መልኩ በፅሁፍ አሳውቃለች፡፡


ለጣሊያን መንግስት፤ እናንተና ብሪታኒያ ከዚህ ስምምነት ላይ መድረሳችሁና ይህንንም ለኛ በጋራ ማሳወቃችሁ በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ የማሳደር ፍላጎታችሁን የሚያሳይ ነው፡፡ እኛ እንደምናምነው ይሄ ሌላም ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ጉዳዩ ለሊግ ኦፍ ኔሽን መቅረብ አለበት፡፡


ለብሪታኒያ መንግስት፤ የብሪታንያ መንግስት በዚህ ሃሳብ ላይ ከእኛ ጋር ድርድር ጀምሯል፡፡ እኛም አሁን ይህን ሃሳብ እንቀበለው ወይስ ይቅር እያልን እያሰብንበት ነው፡፡ ድርደሩ ፍፃሜ ላይ መድረስ ያለበት ከኛ ጋር ነው፡፡ የብሪታኒያ መንግስት በኛ ሃይቅ ላይ ከሌላ ሀገር መንግስት ጋር ይደራደራል ብለን አስበንውም አናውቅም፡፡


ሊግ ኦፍ ኔሽን በዚህ ጉዳይ ላይ ብሪታኒያንና ጣሊያንን እንዲከራከሩ ቢጠይቅም ኢትዮጵያ በጣና ሃይቅ ላይ ያላትን መብት መገዳደር አልቻሉም፡፡ በዚህም የተነሳ ይህን ስምምነት ተግባር ላይ እንዲውል የሚያስገድድ የህግ ማዕቀፍ አልተበጀለትም፡፡


ስምምነት ስድስት፤ ይህ ስምምነት በሚያዚያ 1929 በግብፅና በእንግሊዝና ግብፅ የጋራ ቁጥጥር ስር ባለችው ሱዳን መካከል የተደረገ ነው፡፡ በዚህ ስምምነት ውስጥ የሚከተሉት ዋና ዋና ነጥቦች ተካተዋል፡፡
v  ግብፅና ሱዳን እንደቅደም ተከተላቸው 48 እና 4 ቢሊዮን ሜትር ኪውብ የናይል ውሃ በየአመቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ፤
v  ከጥር 12 እስከ ሐምሌ 8 ባለው የበጋ ወቅት የሚኖረው የናይል ፍሰት ለግብፅ ብቻ የተፈቀደ ይሆናል፤
v  ግብፅ የማናቸውም የላይኛው ተፋሰስ ሀገሮች ፈቃድ ሳያስፈልጋት በናይል ወንዝ ላይ ፕሮጀክቶችን መተግበር ትችላለች፤
v  ግብፅ ጥቅሟን ሊጎዳ በሚችል ማንኛውም የላይኛው ተፋሰስ ሀገሮች ፕሮጀክት ግንባታ ውሳኔ ላይ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቷ የተጠበቀ ነው፡፡


ይህ ስምምነት ግብፅ ለእርሻ ስራ የመስኖ ውሃ በጣም አስፈላጊ በሆነበት በበጋ ወቅት የናይልን ውሃ ሙሉ በሙሉ እንድትጠቀም መብት ያጎናፀፈ ነው፡፡ ለሱዳን ሊደርሳት የሚገባትን የውሃ መጠን በእጅጉ የቀነሰና ሌሎቹ የላይኛቸው ተፋሰስ ሀገሮች ምንም ያህል ውሃ እንዳያገኙ የከለከለ ነው፡፡


ስምምነት ሰባት፤ ይህ ስምምነት በ1959 በሱዳንና በግብፅ መካከል የተደረገ ነው፡፡ ሁለቱ ሀገሮች የናይል ውሃን እነሱ ብቻ እንዲቆጣጠሩ በማሰብ የተዋዋሉበት ነው፡፡ በዚህ ስምምነት ከተካተቱት ነጥቦች ዋነኞቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡


ü  አመታዊው የናይል ወንዝ ውሃ አማካኝ የፍሰት መጠን አስዋን ግድብ ውስጥ በተለካው መሰረት 84 ቢሊዮን  ሜትር ኪውብ እንደሆነ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፤
ü  ግብፅና ሱዳን  ሁሉንም የውሃ መጠን ለብቻቸው እያንዳንዳቸው እንደ ቅደም ተከተላቸው 55.5 እና 18.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ እንዲከፋፈሉ ተፈቅዶላቸዋል፤
ü  በትነትና ሌሎች ምክንያቶች የሚባክን አመታዊ የውሃ መጠን 10 ቢሊዮን  ሜትር ኪውብ እንደሚሆን ከስምምነት ተደርሷል፡፡ በመሆኑም ይህ መጠን የውሃ ክፍፍል ከመደረጉ በፊት ታሳቢ ተደርጎ ይቀነሳል፤
ü  ሱዳን የውሃውን ትነት በመቀነስ የውሃ አቅርቦቱን ያሻሽላል ብላ ካሰበች ከግብፅ ጋር ተማክራ በነጭ አባይ ረግረጋማ ቦታዎች ላይ ፕሮጀክቶችን ልትገነባ ትችላለች፡፡ ወጪውም ሆነ በውሃ መጨመር የሚገኘው ጥቅም ለሁለቱ ሀገሮች እኩል ይካፈላል፤
ü  ከላይኞቹ የተፋሰስ ሀገሮች የይገባኛል ጥያቄ ቢነሳ ሁለቱ ሀገሮች በጋራ በመሆን ለጉዳዩ ምላሽ ይሰጣሉ፤
ü  በላይኞቹ ተፋሰስ ሀገሮች የቀረበው ጥያቄ ምንአልባት ተቀባይነት ካገኘና ለሌላ ሀገር ውሃ ማካፈልን ካስከተለ ያኑ ያህል የውሃ መጠን በእኩል መጠን ከሁለቱ ሀገሮች ይቀነሳል፤
ü  ግብፅ የአንድ አመት የናይል ወንዝን የውሃ ፍሰት በሙሉ ሊይዝ የሚችል የአስዋን ታላቁን ግድብ እንድትገነባ ተፈቅዶላታል፤
ü  ሱዳን የሮሰሪስ ግድብን እንድትገነባና የውሃ ፍጆታዋን እስካላለፈች ድረስ ሌሎች የመስኖና የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን እንድትገነባ ተፈቅዶላታል፤
ü  በሁለቱ መካከል የተደረሰውን ቴክኒካዊ ስምምነት ተግባራዊነት ለማረጋገጥ ቋሚ የጋራ የቴክኒክ ኮሚሽን እንዲቋቋም ተወስኗል፡፡


ስምምነት ስምንት፤ ይህኛው ስምምነት የናይል ተፋሰስ ሀገሮች ኢንሼቲቭ /Nile Basin Initiative/ የሚባለው ነው፡፡ በናይል ተፋሰስ ሀገሮች መካከል የተደረገ ስምምነት ሲሆን ወንዙን በጋራ ለማልማት፤  ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞቹን ለመጋራትና አካባቢያዊ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ታስቦ የተከናወነ ነው፡፡ በጥር 1999 ናይልን በሚጋሩ 9 ሀገሮች የውሃ ሚኒስትሮች አማካኝነት የተመሰረተም ነው፡፡ 

Post a Comment