Thursday, March 28, 2013

ፀብ አጫሪ ስሞች(ክፍል አንድ)


ከጥቂት አመታት በፊት የወረዳ ፖሊስ ፅ/ቤት የሰራዉ ጥናት እንደሚያለክተዉ በመንዝ ጌራ-ምድር ወረዳ ውስጥ ካሉ የወንዶች ስሞች መካከል 30 ከመቶ ያክሉ ሃይል የተቀላቀለባቸዉ፤ ፀብ አጫሪ ወይም ሰላም የሚነሱ አይነት ናቸዉ፡፡

ጥቂት የመንዝ አካባቢ ስሞችን እነሆ

በላቸው፤   ሽናባቸው፤   ድፋባቸው፤  ኩራባቸው፤  ቀማቸው፤   አጋጨው፤  ደምሰው፤ ዳምጠዉ፤  አምታታው፤  ጣሰው፤  ናደ፤  ዘርጋው፤  ቅጣው፤  ዳጨው፤  ጣልአርጌ፤  ሰጥአርጌ፤  ናቅአርጌ፤  ተምትሜ፤  እርገጤ፤  ደባልቄ፤ ገስጥ፤  አደፍርስ፤  አንበርብር፤   አስደግድግ፤  አሸብር፤   አደናግር፤  ደምመላሽ፤   ደፋር፤  አስጨናቂ፤   ሽብሩ...

በነገራችን ላይ ቁጥራቸ ቢያንስም መሰል የሴቶችን ስም ማግኘትም አይከብድም፡፡ ለምሳሌ በለጠች፤ አታለል፤ የሺመቤት፤ ላቀች፡ ወዘተ…፡፡ በነገራችን ላይ የኔም እናት ስሟ ላቀች ደፋር ነዉ፡፡ መንዜዎች ሌላም ካላችሁ ጨምሩበት፡፡

ከጎጃም በተለየ መልኩ በመንዝ አካባቢ የሚወጣ ስም ቤት እንዲመታ ወይም አረፍተ ነገር እንዲሰራ አይጠበቅበትም እንጅ ለጆሮ የሚሰቀጥጡ ስሞችን መስማታችን አይቀርም ነበር፡፡

እንደ በላይ ዘለቀ፤ ፍሬ ዘሪሁን፤ ለ ምሳሌ፤ በልእስኪ ወዳጄና ፍቅር ይልቃል አይነት ስሞች በጎጃም የተለመዱ ናቸዉ፡፡ ይህን አይነት ልማድ በመንዝ ቢኖር ኖሮ እንደ ቀምተህ በላቸዉ፤ ልአርገህ ሽናባቸዉ፤ ዘርጋና አጋጨዉ ያሉ ስሞችን በሰማን ቁጥር ስንደነግጥ መኖራችን አይቀርም ነበር፡፡

አሁን አሁን ግን እነዚህ አይነት ስሞች እየቀነሱ በአንፃሩ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ስሞች እየተስፋፉ ናቸዉ፡፡ እንደዉም እኔ ሳስበዉ እነዚህ ስሞች ባለፉት 10 አመታት ባለሁለት አሃዝ ፈጣን እድገት ሳያስመዘግቡ አይቀሩም /lol/፡፡

እነዚህ ስሞች በጥሬ ትርጉማቸዉ አመጽን፣ ውንብድናን፣ ዝርፊያን፣ ሰው መግደልን በጥቅሉም ወንጀልን የሚያበረታቱ ናቸ፡፡ በስሞቹ መጠን በአካባቢዉ የወንጀል ድርጊት የተስፋፋ ነ ለማለት ባይቻልም የአሸናፊነትና የጀግንነት ፅንሰ ሃሳብን አረዳድ ላይ ግን አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸዉ አልቀረም፡፡

በርግጥ ለዚህ ችግር ምክንያቱ ስሞች ብቻ ሳይሆኑ በአካባቢዉ የሚነገሩ ስነ ቃሎችም ናቸዉ፡፡ በክፍል ሁለት ፅሁፌ በአካባቢዉ ለወንጀል የሚያነሳሱ ስነቃሎችንና ማጠቃለያ ሀሳቤን ይዣለሁ፡፡

ምስጋና፤ የጥናቱን መሰረታዊ ነጥቦች እንዳስታስ ያገዘኝን ኢንስፔክተር እሸቱ ጌታቸን በዚህ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡
Post a Comment