Friday, March 22, 2013

ኢትዮጵያም በተራዋ


ከሰሞኑ ከአመት በፊት በሌላ ሃገር ጥቅም ላይ የዋለን የአንዲት ፊቷ ላይ ጥቃት የደረሰባት ወጣት ሙስሊም ፎቶ የኢትዮጵያዊት በማስመሰልና የኢትዮጵያ ወታደሮች የደበደቧት ነች በማለት በሃሰት የተሰራጨ ዘገባ ነበር፡፡

ጤናና ብርታትን ለዳንኤል ብርሃኔ  ይስጠውና ይኽኑ የሀሰት ጉድ አጋልጦ በማሳየት ውሸታሞቹን አንገት አስደፍቷቸዋል፡፡ ዳንኤል ምስሉን አይተው ያመኑትንና ጥርጣሬ የገባቸውንም ሆነ ውሸት እንደሆነ ቀድመው ያወቁትን ሁሉ በዚሁ ፖስት ትክክለኛ ግንዛቤ ማስያዝ ችሏል፡፡
በዚህ ሳምንት የተፈበረከዉ አሉባልታ ደግሞ ግማሽ አካሏ የሰው፤ ግማሽ አካሏ የዘንዶ የሆነች ፍጡር የህዳሴው ግድብ በሚገነባበት አቅራቢያ በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር ላይ ተገኘች የሚል ነው፡፡ ለዚህም ተያይዞ የቀረበ ቪዲዮ አለ፡፡
ይህ ቪዲዮ የተጫነበት ምክንያት የኢትዮጵያ ህዝቦች በአንድ ልብ ቆርጠው የተነሱለትን የግንባታ ሂደት በአፍራሽ ወሬዎች ማደናቀፍ ነው፡፡ ህዝቡ ይህንን “ከፈጣሪ የመጣ ቁጣ” አድርጎ እንዲያስብ በማድረግ የስነ ልቦና ጭንቀት ውስጥ መክተትን ያለመ ነው፡፡

ያለእረፍት ሙሉ ግዜያቸውን በስራ ላይ የሚያሳልፉትን ሰራተኞች የደህንነት ስጋት ዉስጥ በመክተት ከተቻለ ስራውን እንዲያቋርጡ ካልሆነም በአሉባልታው እንዲዘናጉ ማድረግም ነበር ፍላጎታቸው፡፡
ይህን ፍላጎታቸውን ለማሳካት እያገዛቸው ያለዉ ደግሞ በሀገራችን ያለው የኢንተርኔት ፍጥነት ዘገምተኛ መሆንና አገልግሎቱም በሁሉም ቦታዎች ተደራሽ ያለመሆኑ ነው፡፡ እነርሱ ያገኟትን ቁራጭ መረጃ ለሚጠቅማቸው አላማ ለማዋል ይጠቀሙበታል፡፡ ብዙዎቻችንም በጠቀስኩትና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ሳናጣራ እንወስደዋለን፡፡
ወደዋናው ጉዳይ ልመለስና ከላይ በሊንክ አያይዤ ያቀረብኩት ቪዲዮ እነርሱ /ጸረ-ልማት ሃይሎች/ እንዳሉት በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የተገኘች ፍጥረት ቀረፃ ሳይሆን እ.ኤ.አ ከታህሳስ 2009 ጀምሮ በተለያዩ አጋጣሚዎች ለተለያዩ ጥቅሞች ሲውል የነበረ የማሳሳቻ ቪዲዮ ነው፡፡
መረጃዎቹን ከዚህ በታች በቪዲዮ ሊንኮች አስደግፌ እዘረዝራለሁ፡፡
እኔ ያየኋቸው ድረ-ገጾች የዚህ ቪዲዮ መነሻው ኢንዶኔዥያ እንደሆነ ያስማማሉ፡፡ ለምሳሌ በ2009 ዩቲዩብ ላይ Half human half snake በሚል ርዕስ የተጫነውን ይህን ቪዲዮ እስካሁን 145 ሺህ ያክል ሰዎች አይተውታል፡፡ በዚሁ ግዜ በሌላ ርዕስ የተጫነ ቪዲዮም 145,000 ያክል ሰዎች ተመልክተውታል፡፡  
ከሶሰት አመት በኋላ ይኸው ቪዲዮ half human half snake creature caught in the Congo River በሚል ርእስ ተጭኖ እስካሁን 12 ሺህ ያህል ሰዎች አይተውታል፡፡ ቻይናውያን በኮንጎ ወንዝ ውስጥ ያገኙት ፍጡር የሚል ማስፈራሪያም ተጨምሮለታል፡፡
ይኸው ከ3 አመት በፊት በሌላ አካባቢ ጥቅም ላይ የዋለው ቪዲዮ ፍጆታዉ /1 ደቂቃ ከ48 ሰኮንድ/ እንኳን ሳይቀየር የስም ለውጥ ብቻ ተደርጎለት ‘ለኛ ሰዎች’ አላማ ማስፈጸሚያ ወደ ኢትዮጵያ መጥቷል፡፡ 
በመጨረሻ ስለኢትዮጵያዉ ትንሽ ከማለቴ በፊት ይህ ቪዲዮ በታሪኩ ለምን ለምን ጥቅም እንደዋለ ላመልክት፡፡
በአንድ ወቅት ሲጫን አንዲት የኡጋንዳ “ገንዘብ የሰረቀች ሴት ወደ ግማሽ እባብነት ተቀየረች” በሚል ርእስ  ነበር፡፡ በ61 ሺህ 834 ጎብኚዎችም ታይቷል፡፡ 
በሌላ ግዜ ደግሞ አንዲት “ቁራንን የወረወረች /የቀደደች/ ሴት ወደእንሽላሊትነት ተቀየረች” ተብሎ ተጭኗል፡፡ ይህን እንደውም 1.5 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች አይተውታል፡፡ 
ጄስትማጊያ የተሰኘ ታዋቂ የናይጀሪያ ድረ-ገጽ ደግሞ “በኤክሴል ሆቴል ውስጥ ዛሬ አንዲት ሴት ወደ እንሽላሊትነት ተቀየረች” ብሎ ይህንኑ ቪዲዮ ተጠቅሞበታል፡፡
ቪዲዮው ለተለያዩ ጥቅሞች መዋሉን ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡ አንዱ መገናኛ ብዙሃን ዝናን ለማትረፍ ወይም ለርካሽ ተሰሚነት ሲሉ የሚያደርጉት ነዉ፡፡ ሌላው የራስን እምነት በሐሰት መረጃ አስደግፎ በሌሎች ላይ ለመጫን ነው፡፡ ለምሳሌ በኮንጎ የተደረገው ቻይናውያን ወደ ሀገሪቱ መግባታቸው እንደ እሬት የሚመራቸው ሃይሎች ቻይናውያንን ከርኩስ መንፈስ ጋር በማስተሳሰር ከህዝቡ ለመነጠል ያደረጉት ነው፡፡
ይህን ቪዲዮ በጋና የተጠቀሙበትና አሁን ኢትዮጵያ የመጣበት መሰረታዊ ምክንያት ግን ተመሳሳይ ነው፡፡ ጋና በቅርቡ ታስመርቀዋለች ተብሎ የሚጠበቀውን ባለ 400 ሜጋ ዋት የሃድሮ ኤሌክትሪክ ሃይል ማንጫ ግድብ ስራ ስትጀምር ነው ይሄ ቪዲዮ ፖስት ተደርጎባት የነበረው፡፡ ያኔ ታዲያ ይች ፍጡር ግድቡ ባለበት ቦታ እንደተገኘችና ለግድቡ መጓተትና በተደጋገሚ ለመናዱ ምክንያት /ከላይ የመጣ ቁጣ/ እንደሆነች ተገልጾ ነበር፡፡
አሁን በተመሳሳይ ኢትዮጵያ እየሰራች ባለችው ግድብ አጠገብ ተገኘች መባሉ የሐሰት ውዥንብር በመንዛት ስራውን ለማደናቀፍ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህንንም ስል ያለምክንያት አይደለም፡፡
ዛሬ ጠዋት ስራ እንደገባሁ አንዱ ጓደኛዬ “ይገርማል እንትና /ስሙን መጥቀስ ያልፈለኩትን ባለስልጣን/ <<ሁሉም ነገር ውሸት ነው፤ ምንም የተገኘ ፍጥረት የለም፤ ግንባታው በአግባቡ እየተሰራ ነው>> ብሎ ካደ  አሉ”  አለኝ፡፡
“አንተ ስለ ቪዲዮዉ ምን ያህል እርግጠኛ ነህ?” አልኩት፡፡ “እንዴ በሞባይል የተቀረጸውን እኮ አየሁት” አለኝ፡፡ በወቅቱ መረጃው ስላልነበረኝ በዚሁ ተለያየን፡፡
ከሰዓታት በኋላ ሌላ የስራ ባልደረባዬ ደግሞ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ቆሟል አሉ” አለኝ ለምን ስለው እንዲህ አይነት ፍጡር ስለተገኘች አለኝ፡፡ ተው! አሉባልታ አትሰማ ሰሞኑን ለዘገባ በአካል ቦታዉ ሄደው የተመለሱትን ባልደረቦችህን ለምን አትጠይቃቸውም?” ብዬው ተለያየን፡፡
በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው የጥላቻ ዘመቻ አካል ሆኖ የመጣው ይህ እድሜ ጠገብ ቪዲዮ አዲሱ ኢትዮጵያዊ የዩቲዩብ ስሙ Half human half reptile being is found around Ethio Sudan border ነዉ፡፡ ከተጫነ ጀምሮ ይህን ጽሁፍ አስከማዘጋጅ ድረስ 3500 ያህል ጎብኝዎችን አግኝቷል፡፡ በጣም ይገርማል፤ አመናችሁም አላመናችሁም ይህች ፍጡር በአባይ ግድብ አቅራቢያ ተገኝታለች፡፡ የሚል ማብራሪያም ተመርቆለታል፡፡
በተመልካቾች የተሰጡት አስተያየቶች ቪዲዮው እውነት መሆኑን ያመኑት መብዛታቸውን ያሳያሉ፡፡ በርግጥ የሀሰት/Fake/ ነው ያሉም አልጠፉም፡፡ ብዙዎቹ ግን በሚወዷት ሀገራቸው ላይ የመጣባት መአት አስደንግጧቸዋል፡፡ አይዞን፤ ለፈጠራ ወሬ እጅ አንሰጥም፡፡  ግድባችንን እንደጀመርን እንጨርሰዋለን፡፡ እስከዛዉ ግን ራሳችንን ከቆሻሻ መረጃዎች እንጠብቅ፡፡
Post a Comment