Monday, March 11, 2013

ዉሸትና ስንቅ እያደር ይቀላልኢቲቪ ባለፈዉ ሰኞ ያስተላለፈዉን “የኛ ጉዳይ” ዉይይት ተከትሎ በአንድ የፌስቡክ ገፅ ላይ የወጣ ፅሁፍ ዉይይቱን ለማጣጣል ሙከራ ሲያደርግ በማስረጃነት ያቀረበዉ አሁን በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረዉ ማረሚያ ቤት የሚገኙ ግለሰቦችን የቡድን ስም አጠራር ነዉ፡፡

ፅሁፉ ከአልሞት ባይ ተጋዳይነት ጥቂት ፈቀቅ ያለ ባይሆንም ቢያንስ የግል እምነቴን ለማንፀባረቅ ፈለግሁ፡፡

ፅሁፉ በዚህ ጉዳይ ላይ ቃል በቃል  እንዲህ ነዉ የሚለዉ፡፡ “ሕዝብ የወከላቸውን መንግስትም እውቅና ሰጥቶ ቀርቦ ያነጋገራቸውን ሕጋዊ ወኪሎች መንግስት እውቅና እንዳልሰጣቸው ዛሬ በይፋ ነግረውናል አቶ ሽመልስ {የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ምክትል ሃላፊ}፡፡ በህግ አግባብ ስላለው ትንታኔ ረቺ የሆነ መረጃ ትንታኔ መስጠት የሚቻል መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ መንግስት በራሱ አንደበት የህዝብ ወኪል እያለ ያስጠራበትን ዜና ከዚህ ሊንክ ስሙት http://www.bilaltube.com/awoliya-news-etv-news-about-awoliya-meeting video_68a8d90c5.html#sthash.AQw0Lure.iSy5OPkW.dpbs፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በሌላ የፌስቡክ ገፅ የወጣ ፅሁፍም ተከታዩን ይላል፡፡ “አስገራሚው ነገር ‹‹በሙስሊሙ ህብረተሰብ የተወከሉ የኮሚቴ አባላት›› ብሎ ልክ የዛሬ አመት ዜና የሰራውና ድርድራቸውንም በዜና ያሰራጨው ኢቴቪ አሁን ልክ በአመቱ ተመራጭ ኮሚቴዎቹን ‹‹አሸባሪ›› እንዲሁም በህዝብ ያልተመረጡ እንደሆነ ሲገልጽ ተመልክተነዋል፡፡ በመንግስት የተወከሉት ግለሰብም መንግስት ከእነዚህ ሰዎች ጋር ተደራድሮ አያውቅም ሲሉ በአደባባይ ክደዋል፡፡
 
ሁለቱም ፅሁፎች ማስተላለፍ የፈለጉት መልዕክት መንግስትና ኢቲቪ በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ሆነዋል የሚል ነዉ፡፡

በአንድ ወቅት ሰላም ወዳድነቱ የተመሰከረለት በሌላ ወቅት በአሸባሪነት ሊጠረጠር ይችላል፡፡ ተገላቢጦሹም እንዲሁ፡፡ በአንድ ወቅት ሰላማዊዉንና ህጋዊዉን የሙስሊሞች ጥያቄ እንዲያቀርቡ የተወከሉ ግለሰቦች በሌላ ወቅት ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳቸዉን ማስፈፀም የሚፈልጉ አክራሪ ሃይሎች ጉዳይ ፈፃሚ ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ መከራከር ይቻላል፡፡ ጉዳዩ የስታተስ ሳይሆን በበቂ መረጃ የማሳመን ነዉ፡፡

ሆኖም ይህ ጉዳይ እንዲህ አይነትም ክርክር ዉስጥም የሚያስገባ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ቀድሞም ቢሆን እነዚህ ሰዎች በመንግስትም ሆነ መንግስት በሚደጉመዉ ሚዲያ “የሙስሊም ተወካዮች” ተብለዋል የሚባለዉ ዉሸት ስለሆነ፡፡

ይህንንም አሁን ራሳቸዉ ማስረጃ ብለዉ ባቀረቡት ዜና ብቻ ማሳየት ይቻላል፡፡ የዜና መሪዉ ያቀረበዉ መሪ አንቀፅ እንዲህ ይላል፡፡ “በአወሊያ የሙስሊም ማዕከል የተሰባሰቡ ሙስሊሞች የወከሉት ኮሚቴ ከመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር ተወያየ፡፡”


ሪፖርተሩ ከበደ ካሳም ዜናዉን ሲጀምር “በአወሊያ የሙስሊም ማዕከል የተሰባሰቡ ሙስሊሞች የወከሉት ኮሚቴ በአማኞቹ የተነሱ ጥያቄዎችን ለመንግስት አቅርቧል” ይላል፡፡

አቶ ሽመልስም ቃል በቃል ያሉት “መንግስት እዉቅና የሰጠዉ ላለፉት 40 እና ከዛ በላይ አመታት መላዉ ሙስሊም ህብረተሰብ ሲወክል ለነበረዉ መጅሊስ ነዉ፡፡ ከዚህ ዉጭ እዉቅና የሰጠዉ የለም፡፡ … ባለፉት ግዜያት በእስልምና ጉዳዮች ዙሪያ አንዳንድ ጥያቄዎች አለን ብለዉ ጥያቄዎችን ያነገቡ ሰዎችን መንግስት ያስተናገደዉ ወኪሎች ናቸዉ በሚል ሳይሆን ማንኛዉም ቅሬታ አቅራቢ ዜጋ በግልም ይሁን በቡድን ቅሬታዉን ለመስማትና አግባብነት ካለዉ መፍትሄ ለመስጠት የሚፈልግና ይህም ግዴታ ያለበት መንግስት በመሆኑ ነዉ፡፡ ስለዚህ ባለፈዉ ከተለያዩ የመንግስት አካላት ጋር ቁጭ ብለን ተነጋግረናል ማለታቸዉ ህዝበ ሙስሊሙን ለመወከል የእዉቅና ማረጋገጫ እንደተሰጣቸዉ አድርገዉ የሚወራዉ ስህተት መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ግልፅ ሊሆን ይገባዋል፡፡” ነዉ፡፡ 

ሪፖርተሩ በዜናዉ ላይ በአወሊያ የሙስሊም ማዕከል የተሰባሰቡ ሙስሊሞች የወከሉት ኮሚቴ … ነዉ ያለዉ፡፡ ፀሃፊዎቹ ግን “በአወሊያ መስጊድ አካባቢ የተሰባበሱ” የምትለዉን ሀረግ አንባቢ ለማጭበርበር ሲሉ በመዝለል ሙስሊሞች የወከሉት ኮሚቴ የሚለዉን ሃረግ ብቻ ተጠቅመዋል፡፡

በሃገሪቱ ያለዉ መስጊድ አወሊያ ብቻ ነዉ ካልተባለ በስተቀር ወይም በሃገሪቱ ያሉት ሙስሊሞች እነ ኡስታዝ አቡበከርን የመረጡት ጥቅት ሺህ ብቻ ናቸዉ ካልተባለ በስተቀር በየትኛዉም መመዘኛ አሁን በማረሚያ ቤት ያሉት ግለሰቦች ኢትዮጵያዉያንን ሙስሊሞችን ሊወክሉ አይችሉም፡፡ የዜና ዘገባዉም በዛ የጥንቃቄ ደረጃ የተሰራ ነዉ፡፡

በአጠቃላይ በፀሃፊዎቹ የቀረበዉ ማስረጃ እነዚህ ግለሰቦች የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተወካዮች መሆናቸዉን አያሳይም፡፡ ይልቁንም መንግስት ያኔም ሆነ አሁን አቋሙ ተመሳሳይ መሆኑን ነዉ የሚያረጋግጠዉ፡፡ 

ፀሃፊዎቹ ማስረጃዉ አሳማኝ እንዳልሆነ ይስቱታል ብየም አልጠራጠርም፡፡ ነገር ግን በርካታ የድረ-ገፅ ተጠቃሚዎች ልብ ብለዎ መረጃዎችን አያመሳክሩም (በግዜና በመረጃ እጥረት የተነሳ) ከሚል እሳቤ በመነሳት አንባቢን ለማደናገር ከመሞከር የዘለለ ሚና የለዉም፡፡ ባለፉት ቀናት ዉስጥ ታዋቂዉ ብሎገር ዳንኤል ብርሃኔ ያጋለጠዉ ጉዳቸዉም ይህንኑ አይን ያፈጠጠ እኩይ ተግባራቸዉን የሚያሳይ ነዉ፡፡

ለነገሩ እነዚህ የኮሚቴዉ አባላት ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትርና ከሚኒስትር ዲኤታዉ ጋር ዉይይት ከመጀመራቸዉ በፊት ‘እናንተን በሙስሊሙ ህብረተሰብ ወኪልነት አናዉቃችሁም፡፡ ግን በአወሊያ መስጊድ አካባቢ የተሰባሰቡ ቅሬታ ያላቸዉን ሙስሊሞች ወክላችሁ ስለመጣችሁ እኝም እናንተን የማናገር ሃላፊነት አለብን’ ተብለዋል፡ እነሱም ማን መሆናቸዉን ስለሚያዉቁ በዚህ ጉዳይ ቅሬታ አላቀረቡም ነበር፡፡
Post a Comment