Thursday, February 28, 2013

ህልም ፈርተን ሳንተኛ አናድርም“ለዘመናት በአባይ ውሃ ሙላት በጎርፍ ሲጥለቀለቁ የነበሩ አካባቢዎች በተለይም የሱዳን አካባቢዎች ይህ ግድብ ሲጠናቀቅ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከአደጋው ነጻ ይሆናሉ፡፡” ይህን ያሉት ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ነበሩ::

የሳዉዲ አረቢያ ም/ል መከላከያ ሚኒስትር ካሊድ ቢን ሱልጣን ደግሞ ከሰሞኑ ግብፅ ሄደዉ “የህዳሴዉ ግድብ ምናልባት ከፈረሰ የተገደበዉ ዉሃ ሲፈስ ካርቱምን ያጥለቀልቃታልእንዲያዉም ለአስዋን ግድብም ይተርፋል”  አሉ:: 

ይሄማ የፈሪ ትንቢት ነዉ:: “አንድ ቀን ቢፈርስስ?” ብላ ግብፅ አስዋንን ከመገደብ ወደኋላ አላለችም፤ ሱዳንም ሮሳሪስን እንዲሁ:: 

ቦሊቪያዉያን የሞት መንገድ ብለዉ በሰየሙትና በየአመቱ በአማካኝ 250 ያክል ሰዎችን በሚገድለዉ የገደል ላይ መንገድ መኪና ማሽከርከራቸዉን አልተዉም:: ወደ አማዞን ለመሄድ  እሱን ማለፍ የግድ ነዋ::

እኛም ፈሪ ብንሆን ኖሮ የጎተራ ማሳለጫን አንገነባም ነበር /ሰዉ ባለዉ ነዉ/:: በሊማሊሞ ገደል፤ በግራት ካሕሶ ዳገት ለዘመናት በዳፍ አዉቶቡስ ታጭቀን የተጓዝንዉ እንደማንሞት እርግጠኛ ሆነን አይደለም:: እሱን አልፈን የምናሳካዉ አላማ ስላለን እንጅ::

እንዴ! ሰዉ ሞትን ቢፈራ ኖሮ በ1ሚሊዮን 700 ዶላር ቡጋቲ ቬይሮን መኪና ገዝቶ በሰዓት 430ኪ/ሜ ያሽከረክር ነበር እንዴ?

ቻይና “ሲፈርስ ምን ይዉጠኛል?” ብትል ኖሮ ወገቧን አስራ በአለም ትልቁን ግድብ ባልገነባች ነበር:: ካልሆነማ 40ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ዉሃ ማሰሪያዉ ከተበጠሰ ቻይናን ቬትናምን አያጥለቀልቃትም እንዴ? ቻይና ለመገደብ አይኗን አላሸችም:: ቬትናምም ፈርታ አልባነነችም::

ለነገሩ ለግብፅም የፈሩላት የሳዉዲዉ ጄነራል እንጅ እሷ “ግድቡ ቢፈርስስ?” ብላ አልጠየቀችም:: ግን እኝህ ጄነራል ለዉሃ እንዲህ የሆኑ ሀገራችን ነዳጅ ብታወጣ ምን ሊሆኑ ነዉ? የአለም ግዙፍ ነዳጅ አምራች ሀገር ጄነራል እንዲህ ፈሪ መሆን አለባቸዉስ እንዴ? 

እንግዲህ እኛ ህልም ፈርተን ሳንተኛ አናድርም::

Post a Comment