Wednesday, February 6, 2013

ጅሃዳዊ ሐረካት፡ ክፍል ሁለት

“ጅሃዳዊ ሓረካት” አየነዉ፡፡

ፊልሙ የጀመረዉ ሽብርተኝነት በአለም አቀፍ፤ በአህጉር አቀፍና በክፍለ-አህጉር ደረጃ ያለዉን አዝማሚያ፤ የሽብርተኝነት ምንጮችንና የሚከተላቸዉን ተለዋዋጭ ስልቶች በማስቃኘት ነዉ፡፡ ያለፉትን ሁለት አስርት አመታት በፅኑ እንቅልፍ /hibernation/ ዉስጥ ካላሳለፍን በቀር ይህን በ“እዉነት”ነት ለመቀበል የሚከብደን አይመስለኝም፡፡
መሃሉ ተከድኖ ይብሰልልን፤ ኋላ አንመለስበታለን፡፡

በፊልሙ መዉጫም “እዉነት” ነዉ ከሚል መደምደሚያ ላይ እንዳንደርስ የሚያግደን ነገር የለም፡፡ መዉጫዉ በእድገት አዙሪት ዉስጥ መግባቷ በሁሉም አፍ ስለተነገረላት ኢትዮጵያ ዳግም ከማዉራት ያለፈ ነገር አልነበረዉም፡፡ ትረካዉን ደግፎ የቀረበዉ ምስልም ቢሆን ቀድሞም በሃገራችን ያየንዉ የልማት ስራ ነዉ፡፡ የኢንዱስትሪ፤ የግብርና፤ የመሰረተ ልማት መስፋፋት፤ ወዘተ… እዚህ ያለነዉ ዜጎች በአይናችን ጭምር ያየነዉ ነዉ፡፡ በርግጥ ልዩነቱ ጥቂት እጆች የፈንጂ ጉድጓድ ሲቆፍሩ በፊልሙ ማየታችን እንጅ ሚሊዮን እጆች የችግኝ መትከያ ጉድጓዶችን ሲቆፍሩም በፊት አይተናል፡፡ 
         
እናም የፊልሙን ዳርናዳር ተቀብለን በመሃሉ ምንነት ላይ ለመወሰን የመመልከቻ መነፅራችንን እናስተካክል እላለሁ፡፡ በኔ እምነት የ ‘እዉነታ/ድራማ’ እንካሰላንቲያዉ መፍቻ በፊልሙ ላይ ምስክርነታቸዉን በሰጡ ተጠርጣሪዎች ላይ ባለን እይታ ብቻ ሊፈታ ችላል፡፡ የአክራሪዎች፤ የመንግስት ወይም የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የኋላ ታሪክ የፊልሙን ምንነት በመወሰን ረገድ ያላቸዉ ድርሻ ወደ ዜሮ ተጠግቷል፡፡

አሁን ከግምታዊ አስተሳሰብ ወጥተን በምክንያት ላይ በመመስረት ያለጥርጥር ሁለት አቋሞችን መያዝ እንችላለን፡፡ አንድም ፊልሙ መንግስት በእስልምና እምነት ላይ በደል እየፈፀመ ነዉ የሚሉ ወገኖች እንዳሉት “ድራማ” ነዉ የሚል አለዛም ኢሬቴድ እንዳለዉ የአሸባሪዎችን ሴራ ፍንትዉ አድርጎ የሚያሳይ “እዉነታ” ነዉ የሚል:: ሁለቱም አቋሞች ግድ የሚሉን እምነት ግን ይኖራል፡፡
ፊልሙ ድራማ ነዉ ካልን ምስክርነታቸዉን የሰጡ ተጠርጣሪ አሸባሪዎች በሙሉ የተዋጣላቸዉ ተዋንያኖች ናቸዉ ብለን ማመን አለብን፡፡ ያ ካልሆነ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ነዉ የሚሆዉ፡፡
ከነዚህ ግለሰቦች አንዳንዶቹን የምናዉቃቸዉ በሃይማኖት ሰባኪነታቸዉ እንጅ በትወና ስራ አይደለም፡፡ በዚች አጭር ግዜ ተለማምደዉ እንዲህ አይነት የተዋጣለት “ድራማ” ለመስራት ይቸገራሉ፡፡ የአንዱን ቃል አንዱ ሲደግመዉ፤ እርስ በርስ ሲመጋገቡና አንዱ የሌላዉን ሲያብራራዉ “ድራማ”ዉ በአማተሮች እንዳልተሰራ ያስታዉቃል፡፡ ስለሆነም ይህን ዝግጅት ድራማ ለማለት የነዚህን ተጠርጣሪዎች ፕሮፌሽናል አክተርነት አስቀድሞ መቀበልን ግድ ይላል፡፡ 
ፊልሙ “እዉነት” ነዉ ካልን ደግሞ ከአይናችንና ከጆሯችን ዉጭ ማንንም የማናምን ጅላጅሎች እንደነበርን ማመን አለብን፡፡ /ይሄኛዉ እንኳን ‘መንግስት ያለበቂ ምክንያት አሸባሪ አይላቸዉም’ ብለን ያመንነዉን አይመለከትም፡፡/ ስለዚህ አሁን የተጠርጣሪዎችን ማንነት፤ ትስስራቸዉንና የጋራ ግባቸዉን ተመልክተን ከአፍንጫችን ስር የሚፈፀምን እዉነታ አይናችን ማየት ተስኖት እንደነበረ እናምናለን ማለት ነዉ፡፡
በዚህ ፊልም ላይ ያለን አተያይ በሽብር ድርጊቶች ላይ ከአሁን በፊት በኢቲቪ በተሰሩ እንደ “አኬልዳማ” እና “የሽብር አባት” ባሉ ፊልሞች ላይ ባለን አተያይ ላይም ተፅዕኖ ያሳርፋል፡፡ ተደጋጋፊ ስለሆኑና ማዕከላዊ የስበት ነጥባቸዉ ተመሳሳይ (ግልፅ የሽብርኝነት አደጋ እንዳለብን ማሳየት) ስለሆነ የአሁኑን በእዉነታነት ስንቀበል ያለፈዉን ጥርጣሬያችንን ያስወግዳል ወይም በአንፃሩ ይህንን ስንክድ ቀድሞ የጨፈንነዉን አይናችንን ይበልጥ እየከደንነዉ እንደሆነ ያሳያል ማለቴ ነዉ፡፡
የድህረ “ጅሃዳዊ ሓረካት” ዉይይት በማህበራዊ ድረ-ገፆች ተጀምሯል፡፡ ኢቲቪም በግብረ-መልስ ያገኛቸዉን አስተያየቶች ጀባ እንደሚለን እንጠብቃለን፡፡ ከጠየቅነዉም ራሱን ፊልሙን ይደግምልናል፤ እንኳን ይሄን የመሰለ ዶክመንታሪ እነ እንትና ይደጋገሙልን የለ እንዴ፡፡ እስከዛዉ ግን እንወያይበት፡፡ እኔም አቋሜን  በአስተያየቶቼ አሰፍራለሁ፡፡ ልብ በሉ እንወያይበት ነዉ ያልኩት፤ እንሰዳደብበት አላልኩም፡፡
አይን ራንድ ዘ ቪርቹ ኦፍ ሰልፊሽነስ ባለችዉ መፅሃፏ “If, in any given set of circumstances, any victory is possible at all, it is only reason that can win it. And, in a free society, no matter how hard the struggle might be, it is reason that ultimately wins.” እንዳለችዉ ማለት ነዉ፡፡
Post a Comment