Monday, April 15, 2013

የመለስ ዜናዊ ንግግር-የሕዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ በተጣለበት ወቅት

የተከበራችሁ የበአሉ ተሳታፊዎች፤
ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች፤
የሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ሃላፊዎች፤
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፤

ከሁሉ በማስቀደም በሀገራችን አዲስ ምዕራፍ በር ከፋች የሆነውንና በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው የሚሊኒየም ግድብ ስራ በይፋ በሚጀመርበት በአል ላይ ለመገኘት በመቻሌ የተሰማኝን ልዩ ክብርና ደስታ በራሴና በኢትዮጵያ መንግስት ስም ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ 

በተጨማሪም ፕሮጀክቱ በተሟላ ዝግጅት እንዲጀመር ሌት ተቀን በመረባረብ እዚህ ያደረሱትን ወገኖች ሁሉ በዚህ አጋጣሚ ለማመስገን እፈልጋለሁ፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፤
ክቡራንና ክቡራት፤

በታላቁ  የአባይ ወንዛችን ላይ በዛሬው እለት በይፋ መገንባት የሚጀምረው ግድብ የሚሊኒየም ግድብ መባሉ በብዙ ምክንያቶች ተመራጭ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

የመጀመሪያው ምክንያት ግድቡ በአባይ ወንዝም ሆነ በሌሎች ወንዞቻችን ላይ ሊገነቡ ከሚችሉ ግድቦች ሁሉ የላቀውና ከፍተኛው ግድብ  በመሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪም በሚቀጥሉት አምስት አመታት ከፍተኛ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በመገንባት የራሳችንን የሃይል ፍላጎት በአስተማማኝ መልኩ ከማሟላት አልፈን ለጎረቤት ሀገሮች ሃይል በመሸጥ እድገታችንን ለማፋጠን የያዝነውን እቅድ ለማሳካት አይነተኛ ድርሻ ያለው ፕሮጀክት ስለሆነ ነው፡፡ በእቅዳችን መሰረት በሚቀጥሉት አምስት አመታት ከ 6 እስከ 8 ሺህ  ሜጋ ዋት ተጨማሪ ሃይል ለማመንጨት የተዘጋጀን ሲሆን የሚሊኒየም ግድብ ብቻ 5250 ሜጋ ዋት  በማመንጨት እቅዳችንን ለማሳካት ወሳኝ ድርሻ ይይዛል፡፡

የግድቡ ስራ ተጠናቆ በውሃ ሲሞላ ከ63 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ያላነሰ ውሃ እንደሚይዝ ይጠበቃል፡፡ ይህም በመሆኑ የጣና ሃይቅ ሲሞላ ከሚይዘው 32 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ የበለጠ የውሃ መጠን በማከማቸት ሰው ሰራሹ የሚሊኒየም ግድብ ከተፈጥሮአዊ ሃይቃችን በልጦ ትልቁ የሀገራችን ሃይቅ ይሆናል፡፡ በመሆኑም በሃይቁ አካባቢ ሰፊ የአሳ እርባታና ምርት ስራ ለመስራት የሚያስችለን ይሆናል፡፡
 
ይህ ፕሮጀክት የአምስት አመቱ የልማትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ለማሳካትና ድህነትን ለማስወገድ ያለው ወሳኝ ድርሻ ግልጽ ነው፡፡ በሚቀጥሉት አመታት ልናመርት ካሰብነው ተጨማሪ ሃይል ውስጥ ከ65.6 እስከ ከ87.5 በመቶ የሚሆነው ከዚህ ግድብ ብቻ የሚገኝ መሆኑ ሲታሰብ የፕሮጀክቱን ወሳኝነት ለመረዳት ቀላል ይሆናል፡፡ 

ይሁንና የዚህ ታላቅ ፕሮጀክት ጥቅም በኢትዮጵያ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ሁሉንም ጎረቤቶቻችንን  በተለይም የታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች የሆኑትን ሱዳንና ግብጽን በእጅጉ የሚጠቅም ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ወንዙ ተሸክሞት ይሄድ የነበረው ደለል ስለሚቀር በግብጽና በሱዳን ያሉ ግድቦች በተለይም በደለል እየተሞላ የሚሰጠው ጥቅም በከፍተኛ መጠን የቀነሰው የሱዳን የሮሳሪስ ግድብ ከዚህ አደጋ ነጻ ይሆናል፡፡ 

ለዘመናት በአባይ ውሃ ሙላት በጎርፍ ሲጥለቀለቅ የነበሩ አካባቢዎች በተለይም የሱዳን አካባቢዎች ይህ ግድብ ሲጠናቀቅ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከአደጋው ነጻ ይሆናሉ፡፡

ከግድቡ የሚመነጨው ሃይል ከራሳችንም አልፎ ለጎረቤት ሃገሮች በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብ ስለሆነ ግብጽና ሱዳንም ከዚህ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ፡፡ 

ግድቡ በወንዙ በተለይም በግብጽና በሱዳን በየሚያልፈው የወንዙ ክልልና ግድቦች ዙሪያ የሚታየው ከፍተኛ የውሃ ትነት ቀንሶ አመቱን ሙሉ የተስተካከለ የውሃ ፍሰት እንዲኖር ስለሚያደርግ በወንዙ ተጋሪ ሀገሮች መካከል በውሃ አጠቃቀም ዙሪያ የሚታዩ ልዩነቶችን የሁሉም ሀገሮች ጥቅም በሚያስጠብቅ አኳኋን ለመፍታት ያስችላል፡፡ 

ጥቅሙ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሀገሮች ሁሉ በተለይም ለሱዳንና ግብጽን ጭምር በመሆኑ ፍትህ የሰፈነበት ሁኔታ ቢኖር የግድቡን ወጪ ሶስቱም ሀገሮች ሊሸፍኑት በተገባ ነበር፡፡ እያንዳንዱ ሀገር በግድቡ  በሚያገኘው ጥቅም ልክ ወጪውን ይሸፍኑ ቢባል ሱዳን ቢያንስ 30 ከመቶ ግብጽ ደግሞ የወጪውን 20 በመቶ መሸፈን በተገባቸው ነበር ፡፡ ይሁንና በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ እንዲህ አይነቱ ገንቢና ፍትሃዊ አሰራር እስካሁን ድረስ ሊሰፍን አልቻለም፡፡ በመሆኑም ወጪውን በሙሉ ኢትዮጵያ ለመሸፈን የተገደደችበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይባስ ብሎም ግድቡን ለመስራት ብድርና እርዳታ እንዳናገኝ የተለያዩ ሃይሎች ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ ምክንያት የፕሮጀክቱን ወጪ ለመሸፈን የሚተባበረን ሀገር ወይም ተቋም ማግኘት አልቻልንም፡፡ ስለሆነም ወጪውን ብቻችን ከመሸፈን አልፈን በራሳችን ቁጠባ ለመሸፈን የምንገደድበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ 

የፕሮጀክቱ የገንዘብ ወጪ ከ3.3 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ወይም ከ78 ቢሊዮን ብር በላይ በመሆኑ እና ከዚህ ፕሮጀክት ባሻገርም ሌሎች በራሳችን ወጪ ልንሸፍናቸው የሚገቡ በርካታ ፕሮጀክቶች በመኖራቸው ወጪውን መሸፈን በእጅጉ እንደሚከብደን ጥርጥር የለውም፡፡

ሸክሙን ለማቃለል ያደረግነው ጥረትም ስላልተሳካና ያለፉት ሃምሳ አመታት ታሪካችን እንደማይሳካ ያረጋገጠልን በመሆኑ የሚኖረን አማራጭ አንድም ግድቡን አለመስራት ነው፤ አለበለዚያም እንደምንም ወጪውን በራሳችን መሸፈን ነው፡፡ 

ከነዚህ ሁለት አማራጮች መካከል የኢትዮጵያ ህዝብ ምርጫ የትኛው እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡ በተለመደው ወኔው ምንም ያህል ድሃ ብንሆንም ድህነታችንን ለማስወገድ ማንኛውንም መስዋእትነት ለመቀበል ዝግጁ ነን፤ ስለዚህ ፕሮጀክቱ መሰራት አለበት እንደሚል ለአፍታም ያህል አልጠራጠርም፡፡

እንዲህ አይነቱ ቁርጠኝነት ተኪ የሌለው ሃይላችን ቢሆንም ብቻውን ግን በቂ አይደለም፡፡ ቁርጠኝነት ወደ ተጨባጭ የልማት ፋይናንስነት እንዲሸጋገር ከተፈለገ የቁጠባ ባህላችን በእጅጉ በማዳበር የፋይናንስ አቅማችንን ማጠናከር ይገባናል፡፡

መንግስት ገቢውን በማሻሻልና ወጪውን በመቆጠብ ፕሮጀክቶቹን ለማስፈጸም የበኩሉን ድርሻ ይጫወታል፡፡ የሀገራችን ባንኮች የህዝቡን ቁጠባ በማሰባሰብ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚጫወቱም ይጠበቃል፡፡

ከዚህም ባሻገር መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን ታሪካዊ ግድብ ለማሰራት የበኩሉን ቀጥተኛ ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ መንግስት ለዚሁ የተመቻቸ ሁኔታ ለመፍጠር አስፈላጊዉን ሁሉ ለማድረግ ተዘጋጅቷል፡፡ 5 በመቶ አመታዊ ወለድ የሚከፈልበት የሚሊኒየም ግድብ ቦንድ ለመሸጥ አዘጋጅቶ ለመሸጥ አቅዷል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቦንዱን እንደ አቅሙ ለመግዛት በአንድ በኩል ገቢዉን ለማሻሻልና በወለዱ ተጠቃሚ ለመሆን በሌላ በኩል ደግሞ ይህን ታላቅ ግድቡን ከዳር ለማድረስ የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ 

በመሆኑም የዘመናት የልማት ህልማችንን እውን ለማድረግ መላው የሀገራችን አርሶ አደሮች፤ የከተማ ነዋሪዎች፤ ባለሃብቶችና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በቦንድ ግዢው ዘመቻ እንደሚሳተፉ  እምነቴ የጸና ነው፡፡

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች፤
ክቡራንና ክቡራት፤

ታላቁን የሚሊኒየም ግድብ በራሳችን ወጪ ለመሸፈን በመዘጋጀታችን ከሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባሻገር እኛ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁለት መሰረታዊ መልዕክቶችን በዚሁ አጋጣሚ ማስተላለፍ እንፈልጋለን፡፡

እንደሚታወቀው ሁሉ ሀገራችን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በማካሄድ ላይ ባለቸው የተሳካ የልማት ትግል ድህነትን በአፋጣኝ ለማስወገድ ቆርጠን ተነስተናል፡፡ በዚሁ ጸረ ድህነት ትግላችን  በተግባር ከጎናችን የተሰለፉ በርካታ ወዳጅ ሀገሮች እንዳሉን እናውቃለን፡፡ የልማት አጋሮቻችን ለሚያደርጉልን ትብብርና ድጋፍም ምስጋናችን ወደር የለውም፡፡

ኢትዮጵያ በራሷ ጥረትና በልማት አጋሮቿ ድጋፍም ድህነትን በአፋጣኝ እያሸነፈች በእድገት ጎዳና መረማመድ ከመጀመሯ በፊት በቆየው ድህነታችን ምክንያት በወንዞቻችን የመጠቀም መብታችን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአጅጉ ተገድቦ ቆይቷል፡፡

ይሁንና እድሜ ለታታሪው ህዝባችን ያን ዘመን በአስተማማኝ ሁኔታ ተሻግረን ታላቁን የልማት ህልማችንን በሚሊኒየም ግድባችን አማካኝነት እውን የምናደርግበት አዲስ ዘመን ተፈጥሯል፡፡

ስለሆነም ከእንግዲህ ወዲያ በወንዙ የመጠቀም መብታችንን እንዳንገለገል የሚገታን ምንም ነገር አይኖርም፡፡ ዛሬ የአባይ ወንዝ ላይ ሊገነባ የሚችለውን ትልቁን የሚሊኒየም ግድብ ግንባታ በማስጀመር የቆየውን ማነቆ ስንሰብር የምናስተላለፈውን መልዕክት ሌሎቹ ግድቦቻችን ሁሉ ከዚህ ያነሱ ናቸውና በመብታችን ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ ለመሆን ፍላጎቱ ብቻ ሳይሆን አቅሙ እንዳለን ነው፡፡

በዛሬው እለት ለማስተላለፍ የምንፈልገው ሁለተኛው መልዕክት በወንዞቻችን ለመጠቀምና ድህነትን ለማስወገድ የምናደርገው ጥረት ሁሉ እራሳችንን፣ ጎረቤቶቻችን ጭምር ለመጥቀም እንጂ ማንንም ለመጎዳት አለመሆኑን ነው ታላቁን የሚሊኒየም ግድብ በራሳችን ለመስራት ስናስብ ታሳቢ ካደረግናቸው ቁልፍ ጉዳዩች አንዱ በግድቡ በጎረቤቶቻችን ላይ በተለይም በግብጽና በሱዳን ላይ አንዳች አይነት ጉዳት የማያስከትል ይልቁኑም ጠቃሚ እንዲሆን ማድረግን ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ፕሮጀክት በጎረቤቶቻችን ላይ አንዳችም አይነት ጉዳት የማያስከትል ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚያስገኝላቸው እንዲሆን ተደርጎ ተቀርጿል፡፡

በራሳችን አቅም እንራመዳለን ስንል ከጎረቤቶቻችን ጋር በመደጋገፍ የጋራ ጥቅማችንን ለማስፋት እንጂ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚል ፈሊጥ እንዳልሆነ ከዚህ የጋራ መጠቀሚያ ግድብ በላይ ምስክር ሊኖር አይችልም፡፡ እናም ይህ ግድብ በአባይ ተፋሰስ ሀገሮች መካከል እንዲኖር ለምንፈልገውና የሁሉንም ሀገሮች ጥቅም ለሚያስጠብቀው ትብብር መታሰቢያ ሀውልት እንዲሆን በሌለ አቅማችን ያበረከትነው አስተዋጽኦ መሆኑ እንዲታወቅልን እንፈልጋለን፡፡

በዚሁ አጋጣሚ የወንዙ ልጆች የሆኑ ህዝቦች ሁሉ አዲስ የትብብር ምዕራፍ እንድንጀምር እኛ የኢትዮጵያ ህዝቦች የከበረ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን፡፡

ይህ የሚሊኒየም ግድብ ያለንን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ሁሉ የተፋሰሱን ሀገሮች የጋራ ጥቅም የሚያስከብር ትብብር ለመፍጠር ያለንን ቁርጠኝነት በተግባር የሚያረጋግጥልን ፕሮጀክት እንደሆነም  እንዲታወቅልን እንፈልጋለን፡፡

አመሰግናለሁ

Post a Comment