Monday, February 25, 2013

ዉሸታሞችስ ኢቲቪን ዉሸታም የሚሉቱዉሸታሞችስ ኢቲቪን ዉሸታም የሚሉቱ ናቸዉ፡፡ 

ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ አላደገም ብለው ሽምጥጥ አድርገው የካዱ የኢቲቪ የልማት ዘገባ እንዴት እውነት ይሆንላቸዋል?

በባሌም በቦሌም ብለዉ የመንግስትን ስልጣን መያዝ ሲፈልጉና ይህም የጥፋት በር ክርችም ተደርጎ የተቆለፈባቸው ሃይሎች የኢቲቪ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዜናዎች እንዴት እውነት ይሆኑላቸዋል?

ፅንፈኛ አሸባሪዎች በየጓዳዉ የሚያቦኩትን በአደባባይ የሚያጋልጠው የኢቲቪ ዘገባና የመንግስት የፀረ-ሽብር ዘመቻ እንዴት እውነት ይሆንላቸዋል? 

ፍሬ ነገር ሳይዙ በነፈሰበት የሚነፍሱ፤ እዛና እዚህ የሚላጉ የውሃ ላይ ኩበቶችም ይህንን ሲያራግቡት ይስተዋላሉ፡፡ አብነት አንሱ ሲባሉ ማጣፊያ የሚያጥራቸዉ በጅምላ የሚነዱ ሰዎችስ እንደ ገደል ማሚቱ ከማስተጋባት ሌላ ምን አማራጭ አላቸው?

ዉሸታም “እዚህ ቤት ዉስጥ ዘንዶ አለ” ቢል “አለ እንዴ? እስኪ ገብተን እንየዉ” ብለህ አጥብቀህ ትይዘዋለህ እንጅ የነገረህን እንዳለ አትቀበለውም ይላሉ አባቶች ሲመክሩ፡፡ እንግዲህ ከኋላ ያለው ፍልስፍና እንዲህ ስትለው አንድም “እዚሁ ግደለኝ እንጅ አልሔድም” ይልሃል፤ ያኔ እውነትም ዘንዶ እንዳለ ትረዳለህ አለዛም “እሺ እንሂድ” ብሎህ ይነሳል፤ በዚህም ሰው ወደ ዘንዶ ስለማይሄድ ዉሸቱን መሆኑን ታረጋግጣለህ የሚል ነው፡፡ 

“ኢቲቪ ዉሸታም” የሚሉቱ እስኪ አብነት አንሱና ምክንያት ደርድሩ ሲባሉ አንድም በቆሙበት ይቀራሉ አለያም ግራና ቀኝ ይላጋሉ፡፡ <<ዉሸታም>> ለማለትማ ማንም ሊል ይችላል፡፡ ግን ዉሸት ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ ቅንጣት ታክል እዉነት ያለማቅረብ በራሱ ዉሸታምነት ነዉ፡፡

ከሰሞኑ ከአንዷ ጋር ቻት ስናደርግ “በኢቲቪ የቀረበ ጅሃዳዊ ሓረካት ዉሸት ነዉ” አለችኝ፡፡ ምክንያት ስላት ለሊት ላይ የተላለፈዉን ፊልም አነሳችልኝ፡፡ “እሱን ታዲያ ምን ዉሸት አገኘሽበት?” አልኳት፡፡ 

“አይ እኔማ አላየሁትም፤ ኔትወርክ እንቢ ብሎኝ” አለችኝ፡፡

“ታዲያ ሳታይ እንዴት ዉሸት ብለሽ ትደመድሚያለሽ?” አልኳት፡፡

“እንዴ የኢቲቪን ሸት አላህ አጋለጠ ተብሎ ፖስት ተደርጎ የለም እንዴ?” አለችኝ፡፡ አልሳቅሁባም፡፡ በስንቱ ተስቆ ይቻላል፡፡ በንዲህ አይነቶቹ ሁሉ ከተሳቀማ ለሀዘን የሚሆን ግዜም አይኖርም፡፡ ለማንኛውም ከሷ ጋር ፊልሙን አይታው ዋናውን የጂሃዳዊ ሓረካት ዘጋቢ ፊልም ሃቅነት የሚያፋልስ አብነት እንድታመጣልኝ ተግባብተን ተለያየን፡፡ እስካሁን አልተመለሰችም፡፡

ኢቲቪ ያልታረሰውን ታረሰ፤ ያልተገነባውን ተገነባ ወይም በጥቅሉ ያልለማውን ለማ ብሎ አልዘገበም፡፡ ወይም ደግሞ ሻኪር ኤልሳይድ እንዳሉት “ቤታቸዉ ቁጭ ብለ ቡና የሚጠጡትን፤ ቴሌቪዥን እያዩ ያሉትን ወይም ከልጆቻቸዉ ጋር እየተጫወቱ ያሉትን” አሸባሪ አላለም፡፡ 

ይህ አስተያየቴ ግን ኢቲቪ ያለበትን የሚዛናዊ ዘገባ ችግር የሚደፍቅ አይደለም፡፡ ኢቲቪ ለሚዘግባቸው ሃቀኛ የህዝብና የመንግስት የልማት ስኬቶች የሚሰጠውን ትኩረት ያክል ፋይዳቸዉ አዎንታዊ ሊሆኑ ለሚችሉ ዉድቀቶችም ሚዛናዊ ሽፋን ሊሰጥ ይገባዋል፡፡ 

ህዝብ፤ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ሃገራዊ ተቋሞቻችን ለስኬት ሲታትሩ ያጋጠሟቸዉን ችግሮች በማራገብ የፖለቲካ ትርፍ ማግኘት የምትፈልጉ ግን ከንብ ቆሻሻ አትጠብቁ፡፡ አፍንጫችሁን ላሱ፡፡
Post a Comment