Sunday, February 10, 2013

ሶስት የጭካኔ ግድያዎች

ከአስራ ስምንት አመት በታች ያሉ እንዲያነቡት አይፈቀድም፡፡ በተለይ ወላጆች ግን እንድታነቡት ትበረታታላችሁ፡፡

ሻሸመኔ ከተማ የምትኖር በጣም የምወዳት ግን ከኔ በላይ እሷ የምትወደኝ አክስት አለችኝ፡፡ አንዲት ልጅ፤ ስምንት የልጅ ልጅና አንድ የልጅ ልጅ ልጅ አላት፡፡ እድሜዋ እየገፋ ነዉ፤ ህመምም በየግዜው እየተመላለሰ ይጎበኛታል፡፡

ከሶስት ወራት በፊት በስራ ምክንያት ሃዋሳ ስሄድ እግረመንገዴን ጠይቄያት ነበር፡፡ ሰሞኑን ታዲያ ደውላ “አንድ ግዜ እንኳን ናና አይንህን ልየ፤ በጣም እያመመኝ ነ አለችኝ፡፡ እኔም የሶስት ቀን ፈቃድ ጠይቄ ሄድኩላት፡፡ ፈጣሪ ይመስገን ስሄድ ግን ተሸሏት አገኘኋት፡፡

ከልጇ ቤት ሄጄ ሳለ ቡና ተፈልቶ ወሬው ደራ፡፡ አንድ ጥያቄ አነሳሁ፡፡ “ከወር በፊት እዚህ ከተማ ከነልጆቿ ስለተገደለችሴት እስኪ ንገሩኝ” አልኳቸው፡፡

ማን ያውራ የነበረ እንደሚባለው ወይም ፈረንጆቹ from the horse’s mouth እንደሚሉት ብዬ ነው እንጅ ዜናውን በፊትም ሰምቸዋለሁ፡፡ እየተቀባበሉ ያብራሩልኝ ጀመሩ፡፡ 

የጭካኔ ግድያ አንድ

ሰራተኛዋ ጠዋት ላይ ሟችን ፈቃድ ጠይቃ ነበር አሉ፡፡ ሟችም ትከለክላታለች፡፡ እናም አኩርፋ ነዉ የዋለችው፡፡ “አኩርፋ ላ ማታ እኮ ነው ሰይጣኗ ሲነሳባት በተኙበት የጨፈጨፈቻቸ አለችኝ የአክስቴ የልጅ ልጅ፡፡ አፌን ከፍቼ ማዳመጤን ቀጠልኩ፡፡

ሰራተኛይቱ ቀጣሪዋን በተኛችበት በመጥረቢያ መታ ትገድላታለች፡፡ ወንዱ ህፃን ልጅ ይህን ሲያይ ያለቅሳል፡፡ እሱን ደግማው መጥረቢያዋን ጥላ ልትወጣ ስትል ሴቷ ህፃን ከአንገቷ ቀና ብላ ስታያት አየቻት፡፡ “አሃ አንችም አይተሸኛል ብላ እሷንም ገደለቻት” አለች፡፡

ገዳይ በሟቾች ላይ ቤቱን ቆልፋባቸው ትሰወርና እዛ ቤት ላስቀጠራት ደላላ ስልክ በመደወል ቤት ዉስጥ አደጋ ተፈጥሯል ሂድ ትለዋለች፡፡ እሱ ደግሞ ለፖሊስ ደውሎ ያሳዉቃል፡፡ “ፖሊስ ደርሶ ቤቱ ተሰብሮ ሲገባ ሶስት አስከሬን ባንድ ላይ” አለች ስቅጥጥ እያላት፡፡

የአክስቴ ልጅ ቀበል አድርጋ ቀጠለች፡፡ “በጣም የሚያሳዝነዉ ደግሞ የሽሉ ነ፡፡ ለስድስት ሰዓት ያክል በሟቿ ሆድ ስጥ ሆኖ ይንቀሳቀስ ነበር አሉ” አለች፡፡

“ግን ቦታዉ ድረስ ሄዳችሁ ነበር?” ስል ጠየቅሁ፡፡

“እንዴ የሻሸመኔ ህዝብ ግልብጥ ብሎ አይደል እንዴ የወጣ፡፡ እኔ ራሴ ደማቸ ከቤት ስጥ ሲጠረግ ደርሻለሁ፡፡አቤት የሰ ደም” ብላ ጭንቅላትዋን ያዘች፡፡ 

ገዳይ ወደመጣችበት የገጠር መንደር ተደብቃ ልትሄድ ስትል ፖሊስ ይዟታል፡፡ ህዝቡ በሙሉ “ትገደል” በሚል ሰልፍ ወጥቶ ነበር አሉኝ፡፡

“ባሏስ?” አልኩ፡፡ “ባልየማ አሁን ደህና ነዉ” አለችኝ፡፡

“እሱ ደሞ ምን ሆኖ ነበር?”

“ቀዉሶ ነበር እኮ፡፡ አዲስ አበባ አማኑኤል ሆስፒታል ሁሉ ሄዶ ነበር፡፡ አሁን ግን ተሽሎት በቀደም እዚህ ዮሃንስ ቤተስኪያን ቆሞ ህዝቡን ሲያመሰግን አይቸዋለሁ፡፡” 

“ምን ብሎ ነ ደሞ ህዝቡን የሚያመሰግነዉ?” አልኩ፡፡ ታሪኩ መስጦኝ ይሁን ወይስ ጋዜጠኝነቱ ተጠናውቶኝ መጠየቅ አብዝቻለሁ፡፡

“እንዴ ህዝቡ እኮ ነ ፅናት የሆነ፡፡” 

ሻሸመኔ ሁሉም ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በአንድነት የሚኖሩባት ከተማ ነች፡፡ ስለህዝብ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ግን አላስጨረሱኝም፡፡ “ኧረ የነሱማ ጭካኔ” አለች የአክስቴ ልጅ፡፡ “የነሱ” ስትል የቤት ሰራተኞችን ማለቷ እንደሆነ አልጠፋኝም፡፡ ሌላ የጭካኔ ወሬ እንዳላት ተረድቶኛል፡፡ አንገቴን አሰገግኩ፡፡

የጭካኔ ግድያ ሁለት 

“እዚህ እኮ ነ ባለፈአለች የቦታውን አቅጣጫ እያመላከትች፡፡ ሰራተኛዋ “በቃኝ እሄዳለሁ፤ ከንግዲህ ካንቺ ጋር አልኖርም፡፡ ደመወዜን ስጭኝና ሸኚኝ” ትላለች ቀጣሪዋን፡፡ ቀጣሪዋ ደግሞ የወለደችዉ ህፃን ክርስትና ደርሶ ስለነበር “ይሄ ጣጣ ሳይወጣ አትሄጅም ባይሆን ልክ በክርስትና ማግስት ትሄጃለሽ” ትላለች፡ ሰራተኛዋም በዚህ ትከፋለች፡፡

ጎረቤቱ ተሰባስቦ የድግሱን ሽር ጉድ ተያይዞታል፡፡ ገብስ በትልቅ በርሜል ውስጥ እየተጨመረ በእሳት ይቀቀላል፡፡ ለኪኒቶ መስሪያ ማለት ነው፡፡ አንዷ የተጣደውን ስታማስል ከበድ ያለ ነገር ያጋጥማታል፡፡ በሃይል ስትገፋዉ የህፃን ልጅ አስከሬን ወደላይ ወጣ፡፡ “ዞር ብለ ቢያዩ ሰራተኛዋ በአካባቢ የለችም” አለች፡፡

በርግጥ የቤት ሰራተኞች ከአስገድዶ መደፈር ጀምሮ በርካታ በደሎች ይፈፀሙባቸዋል፡፡ ግን ለምን ቁጭታቸውን ምንም በማያውቁ ጨቅላ ህፃናት ላይ ይወጣሉ? ትተዉ መሄድስ አይችሉም? እያልኩ መብከንከኔን ቀጠልኩ፡፡ 

“ያችን ግን እግዜር አጋለጣት” አለች የአክስቴ የልጅ ልጅ ወደ እናቷ እያየች፡፡ እናትየዋን እስኪ አንች ንገሪው ብላ እየጋበዘች እንደሆነ ከአስተያየቷ ያስታዉቃል፡፡ እናትየዋም ተረዳቻትና ቀጠለች፡፡

በቀጣዩ ክፍል ይህን ያልተሳካዉን የጭካኔ ግድያ ሙከራና ሌሎች በዚሁ የተሲያት ቡና ላይ የተዘከሩ በጥንቃቅ ጉድለት የተከሰቱ ግድያዎችን ይዠላችሁ እቀርባለሁ፡፡ እስከዛዉ ራሳችሁንና ቤተሰባችሁን ጠብቁ፡፡ እባካችሁ ሰራተኞቻችሁን አታስኮርፉ፡፡ ካስኮረፋችሁ ደግሞ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርጉ፡፡
Post a Comment