Thursday, January 17, 2013

ትኩስ ድንች

ከረፋዱ 5፡00 ሠዓት ላይ ነዉ፡፡ ከመስሪያ ቤቴ ፈቃድ አግኝቼ ለግል ጉዳይ ከዘገየሁበት መርካቶ እየተመለስኩኝ፡፡ ከመርካቶ ወደ ፍልዉሃ በሚጓዘዉ ታክሲ ዉስጥ ተሳፍሬ የግል ጉዳዬን አወጣለሁ፤ አወርዳለሁ፡፡ ከኋላ ወንበር ላይ ተቀምጣ በስልክ የምታወራዉ ሴትዮ ድምፅ እየጎላ መጥቶ ወደ ሁላችንም ጆሮ መድረስ ጀመረ፡፡ ሴትዮዋ ከምታናግራት ሌላ ሴት ላይ በብስጭት ትደነፋለች፡፡ 

“እንዴት እንዲህ ትያለሽ? ተሳስተሻል እኮ፡፡” እያለች ትጮህባታለች፡፡ በዛኛዉ የስልኩ ጫፍ ያለችዉ /በኋላ እንደተረዳሁት የደወለቸዉ ሴትዮ የቢሮ ፀሀፊ ነች/ ነገሩን ቀለል ለማድረግ የሞከረች መሰለኝ የሴትየዋ ቁጣ እየከረረ መጣ፡፡

“አይባልማ፡፡ ነዉር እኮ ነዉ፡፡ በዚህ ሰዓት ሁሉም ሰራተኛ በስራዉ ላይ መገኘት እንዳለበት እያወቅሽ እየመጣች ነዉ ይባላል እንዴ?” ብላ በድጋሚ ተቆጣቻት፡፡ ወቀሳዋ አልበረደም፡፡ “ቆይ አሁን ሰራተኞችን ማነዉ የሚቆጣጠራቸዉ ይባላል? የኛን ሰራተኞች ደግሞ ታዉቂያቸዋለሽ፤ ሃላፊ ከሌለ ስራ አይሰሩ፡፡”

ፀሃፊዋ ይሁን ሁሉ ወቀሳ የምትሰማዉ ከወንበሯ ብድግ ብላ እንደሆነ አሰብኩ፡፡ እንደሚመስለኝ ታዲያ “የታለች ሲለኝ ምን ልበለዉ?” ሳትል አትቀርም፡፡ የኔ አጎራባች ከቁጣዋ በረድ ብላ የቢሮ ስርዓት ማስተማር ቀጠለች፡፡

“አሁን ወጣ አለች፤ አሁን እዚህ ነበረች እኮ፤ ለሻይ ወጥታ ነዉ መሰል… ነዋ የሚባለዉ” አለቻት፡፡

ነገሩ ግልፅ እየሆነልኝ መጣ፡፡ የዚች አለቃ ተብዬ የበላይ ሃላፊ ወደሷ ቢሮ ሲገባ ያገኘዉ ፀሃፊዋን ብቻ ነዉ፡፡ ከዛም “የት ሄደች?” ብሎ ይጠይቃል፡፡ ፀሃፊቱም አርፋጇን አለቃዋን የሸፈነች መስሏት “እየመጣች ነዉ ደርሳለች፤ ታክሲ ዉስጥ ነች፤ ፍልዉሃ ጋር ደርሳለች፤ ወዘተ…” ብላ ትወሸክታለች፡፡ 

ሃላፊዉ ታዲያ እስከ 5፡00 ሠዓት ድረስ ቢሮ ያልገባችዉን የበታቹን በስልክ ይቆጣታል፡፡ እንግዲህ እሷም በተራዋ ከላይ የመጣዉን ትኩስ ድንች ወደ ፀሃፊ እየወረወረች ነዉ ማለት ነዉ፡፡ ታዲያ የዚች ሴትዮ የስልክ ንግግር ሁለት ነገሮችን አስገነዘበኝ፡፡ አንደኛ የሴትዮዋን አዋቂነት/አስተዋይነት ሲሆን ሁለተኛዉ ያወቀችዉን/ያመነችበትን የማትፈፅም መሆኗ ነዉ፡፡

ይች ሴት በስራ ሰዓት ቢሮ መግባት እንዳለባት፤ ቢረፍድ እንኳን እስከዛ ሰዓት ድረስ መቆየት ነዉር መሆኑን፤ በተለይ በሷ ስር ያሉ ሰራተኞችን አፈፃፀም ለመከታተል የሷ መኖር ቁልፍ መሆኑን ጠንቅቃ ታዉቃለች፡፡ ይህንን እያወቀች ግን በስራ ገበታዋ አልተገኘችም ወይም ፈቃድ አልጠየቀችም፡፡ ለህሊና ያለመታመን ማለት ይሄ ነዉ፡፡ የሷ ህሊና የማይቀበለዉን ድርጊት ፀሃፊዋ በመደገፍ እንድትተባበራትም ማዘዟ/ማግባባቷ ተገቢ አልነበረም፡፡//
Post a Comment