Saturday, January 12, 2013

ምርጫ 2005

በመጪዉ ሚያዚያ የሚካሄደዉ የአካባቢ ም/ቤቶችና የአዲስ አበባና ድሬዳዋ አስተዳደር ም/ቤቶች ምርጫ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣዉ የግዜ ሰሌዳ መሰረት እየተፈፀመ ይገኛል፡፡ ለምርጫ ሂደቱ የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችና የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭት ከተጠናቀቀ በኋላ የዕጩዎችና መራጮች ምዝገባ በመካሔድ ላይ ነዉ፡፡ 29 የፖለቲካ ፓርቲዎችም የመወዳደሪያ ምልክታቸዉን ወስደዋል፡፡ 


የዚህ ፅሁፌ ትኩረት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለምርጫዉ የሰጡት የትኩረት መጠን ይሆናል፡፡ “ለምን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ብቻ?” ብላችሁ እንደማትጠይቁኝ አዉቃለሁ፡፡ ምክንያቱም ኢሕአዴግ ልክ እንደ 2002ቱ ሀገራዊ ምርጫ ዘንድሮም ተቀናቃኞቹን በዝረራ ለማሸነፍ እየተጣደፈ መሆኑን እናዉቃለንና፡፡ ጥያቄዉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በ1997ቱ ሀገራዊ ምርጫ ኢሕአዴግን አዲስ አበባ ላይ የመዘረራቸዉን ታሪክ በዚህ አመትም ለመድገም የሚያስችላቸዉን ትኩረትና ዝግጅት አድርገዋል ወይ? የሚለዉ ነዉ፡፡ እንደኔ ለምርጫዉ የሰጡት ትኩረትም ሆነ ዝግጅታቸዉ ምርጫዉን የሚመጥን አይደለም፡፡


አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ገና ከጅምሩ ሲቋቋም የደጋፊዎቹንና የአባላቶቹን አላማ በማንገብ፤ በጥቅሉም የማህበራዊ መሰረቱን ጥቅም በማቀንቀን በሰላማዊ የፖለቲካ ዉድድር ላይ ተሳትፎ ገዢ ፓርቲ ለመሆንና የራሱን አላማ በመንግስት ስልጣን ለማስፈፀም ነዉ፡፡ ስለሆነም በምርጫዎች ሁሉ መወዳደር የፖለቲካ ፓርቲዎች ተፈጥሯዊ ባህሪ ነዉ፡፡


እኛ ሀገር ግን ያለመታደል ሆኖ ፓርቲዎች በምርጫ ስለመወዳደራቸዉ የሚወስነዉ ወጥ የሆነዉ ተፈጥሯዊ ባህሪያቸዉ ሳይሆን ተለዋዋጩ ነባራዊ ሁኔታ ነዉ፡፡ እናም ማንም ደፍሮ ‘ይህ ፓርቲ  በምርጫ ይሳተፋል’ ብሎ መናገር አይችልም፡፡ ይልቁንም ምርጫ በተቃረበ ቁጥር ጋዜጠኞች ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን “በቀጣዩ ምርጫ ትወዳደራላችሁ ወይ?” ሲሉ መጠየቅ የተለመደ ነዉ፡፡ ፖለቲከኞችም “እሱን አሁን መናገር አንችልም፡፡ ግዜዉ ሲደርስ የምንወስነዉ ነዉ ይላሉ፡፡” ይች እንግዲህ የኛ ሀገር ፖለቲከኞች ብልጣብልጥነት መሆኗ ነዉ፡፡


በዘንድሮዉ ምርጫም እየታየ ያለዉም ይኸዉ ብልጣብልጥነት ነዉ፡፡ ፓርቲዎቻችንን ስንጠይቃቸዉ “በምርጫ ስለመሳተፋችን ገና አልወሰንም፡፡ ወደፊት እናየዋለን፡፡” ሲሉን ከርመዉ አሁን ደግሞ “የዉድድር ሜዳዉ እኩል ስላልሆነ ለመወዳደር እንቸገራለን፡፡” እያሉን ነዉ፡፡ የ33ቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብስብ የሚያራምደዉ “ምርጫ ቦርድ ጥያቄያችንን ካተቀበለ በምርጫዉ አንሳተፍም” አቋምም የዚህ ብልጣብልጥነት መገለጫ ነዉ፡፡ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ተቃዋሚ ፓርቲዎች የዘንድሮዉን ምርጫ ችላ እንዳሉት ገልፀዉ ፓርቲዎቹ ‘የሚርመሰመሱት’ በሀገራዊ ምርጫ  ወቅት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡


የአካባቢ ም/ቤቶች ምርጫ ህብረተሰቡ በአቅራቢያዉ ሆነዉ የልቡን ትርታ የሚያዳምጡ፤ ለችግሩ መፍትሄ የሚያፈላልጉና አዳዲስ የልማት ሃሳቦችን የሚያፈልቁ የም/ቤት አባላትን የሚሰይምበት ነዉ፡፡ በተለይም በአስፈፃሚዉ አካል በታችኛዉ መዋቅር የሚፈጠሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማረምና ብልሹ ስነምግባር ያላቸዉን አስፈፃሚዎች በመቆጣጠር ረገድ የነዚህ ም/ቤቶች አባላት ሚና ከፍተኛ ነዉ፡፡


በመሆኑም ‘ለህዝብ ጥቅም ቆሜያለሁ፡፡’ የሚል የፖለቲካ ድርጅት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት አቅሙና ተነሳሽነቱ ያላቸዉን አባሎችና አመራሮች ማፍራት እንደዚሁም በምርጫ ተወዳድረዉ በም/ቤት አባልነት እንዲገቡ ማብቃት ይጠበቅበታል፡፡ ለነገሩ ይሄ ለህዝብ ጥቅም ከመስራት ባለፈ የፓርቲዎችን ህልዉና የመጠበቅም ጉዳይ ነዉ፡፡


የፖለቲካ ፓርቲዎች በተደጋጋሚ በታችኛዉ የአስተዳደር አካል በደል እንደሚፈፀምባቸዉ ይናገራሉ፡፡ ፓርቲዎቹ በነዚህ ም/ቤቶች የሚሳተፍ ተመራጭ ቢኖራቸዉ ‘አቤት’ የሚሉበት፤ ተወካዮቻቸዉ ከበዙም አጀንዳዎችን በማስያዝ አማራጮቻቸዉን የሚያቀርቡበት መድረክ አገኙ ማለት ነዉ፡፡ በም/ቤቱ በሚያራምዱት አቋም የመራጮችን ልብ ማሸፈትም ይቻላቸዋል፡፡ የመንግስትነት ስልጣን ባይይዙ እንኳን ህልዉና ማስቀጠል መቻል ማለት ይሄዉ ነዉ፡፡


ምርጫዉ ምንም የረባ ጥቅም ባይኖረዉም እንኳን /አንድም መራጭ አይኖረንም ብለዉ ቢያስቡም እንኳን ማለቴ ነዉ/ የዴሞክራሲ መገለጫ በሆነ ምርጫ መሳተፍ የፓርቲዎች ሃገራዊ ሃላፊነት ጭምር ነዉ፡፡ ዜጎች በመምረጥ የመሳተፍ የዜግነት ሃላፊነት እንዳለባቸዉ ሁሉ ፓርቲዎችም በምርጫ የመወዳደር ሃላፊነት አለባቸዉ፡፡ ምክንያቱም ሁላችንም የምንሻዉ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲኖር ከጅምሩ መራጮችና ተወዳዳሪ ተመራጮች መኖር አለባቸዉ፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ የዉድድር ምህዳሩ ቢጠብ፤ ህዝቡ በቂ አማራጮች በማጣቱ የመምረጥ ፍላጎቱ ቢላሽቅ አለያም ምርጫ የማስፈፀም ሀገራዊ አቅማችን እየዘቀጠ ቢሄድ ማናቸዉም ፓርቲዎች ከታሪክ ተጠያቂነት አይድኑም፡፡


ሌላዉ ትኩረት የሚሻዉ ጉዳይ በኢሕአዴግ ስርዓት ተጠቃሚዎች የመኖራቸዉን ያክል በስርዓቱ ጥቅማቸዉ የተነካ ወገኖች የመኖራቸዉ ጉዳይ ነዉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ቢቻላቸዉ ለኛ ይጠቅመናል የሚሉት ፓርቲ ወደስልጣን  እንዲመጣ ይፈልጋሉ፡፡ ያን የሚያደርግ የድምፅ ብዛት ባይኖራቸዉ እንኳን ለገዥዉ ፓርቲ ያላቸዉን ቅሬታ/ጥላቻ/ የሚገልፁበት መድረክ ይሻሉ፡፡ የተቃዋሚዎች የመኖር አንዱ ፋይዳና በምርጫ የመወዳደር ሀላፊነት ምንጩም ይሄዉ ነዉ፡፡


በርግጥም ምርጫ ለማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ፖሊሲና ፕሮግራምን ለማስተዋወቅ ጭምር አጋጣሚን የሚፈጥር /once in a 4/5 year/ እድል ነዉ፡፡ በተለይ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች፡፡ ስለሆነም በየደረጃዉ ለሚካሄዱ ምርጫዎች የሚመጥን ዝግጅት ማድረግ፤ ለአሸናፊነት ካልሆነም ደግሞ ለምርጥ ሁለተኛነት የሚያበቃቸዉን ስልት መንደፍ ይኖርባቸዋል፡፡


ምርጫ ዕጩዎችን የማዘጋጀት፤ እነሱን በአባላት የማስገምገም፤ ወቅቱን የሚመጥኑ የክርክር አጀንዳዎችን የመምረጥና ሰፊ የፕሮፓጋንዳ ስራ መስራን ይጠይቃል፡፡ የተፎካካሪን ድክመት መተንተን፤ የራስን አማራጭ ማስተዋወቂያ ስልት መቅረፅና ዉስጣዊና ዉጫዊ ተግዳሮቶችን መለየት ሁሉ የምርጫ ዝግጅት ምዕራፍ ናቸዉ፡፡


የሃገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተጠመዱት ግን እነዚህን ዝግጅቶች በመፈፀም ላይ ሳይሆን  በዉስጥ ችግሮችና ከምርጫ ቦርድ ጋር ባላቸዉ ንትርክ ነዉ፡፡ አጀንዳዎቻቸዉም ከአስርት አመታት በፊት የተዘጉ እንደ የባህር በር፤ የክልሎች ድንበር አወሳሰን፤ የብሄር እኩልነት አይነት  እንጅ ተራማጅ አመለካከቶች አይደሉም፡፡ በርካታ ፓርቲዎች ለምርጫዉ ካለመመዝገባቸዉ ጋር ተያይዞም በምርጫ ቦርድ የግዜ ሰሌዳ እየተጓዙ አይደለም፡፡ እና ዝግጅታቸዉም የምርጫዉን ፋይዳ የሚመጥን አይደለም፡፡


በዘንድሮዉ ምርጫ 3.6 ሚሊዮን ያክል ሰዎች ይመረጣሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ ይህ በራሱ የዉክልና ዴሞክራሲ በተፈጥሮዉ ያለበትን ጉድለት በማከም የህዝብን ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያሳድግ ነዉ፡፡ በርግጥ ‘የዉክልና ዴሞክራሲ’ ወይስ ‘ቀጥተኛ ዴሞክራሲ’ የሚለዉ ጉዳይ በራሱ አከራካሪ ነዉ፡፡ ቢሆን ግን ያላደገ የዴሞክራሲ ስርዓት ባላቸዉ ሀገሮች የቀጥታ ዴሞክራሲ /ከተቻለ/ ተመራጭ መሆኑ ብዙዎችን ያስማማል፡፡ እናም በዚህ ምርጫ ላለመሳተፍ መወሰን ከሃገራዊዉ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ራስን ማግለልና የራስን ህልዉና ፈተና ዉስጥ ማስገባት ነዉ፡፡
Post a Comment