Monday, December 31, 2012

አፍ እላፊ

ከአዲስ አበባ በድቅድቅ ጨለማ ተነስተን ወደ ጅግጅጋ በቲዮታ ፒክአፕ እየከነፍን ነዉ፡፡ ሶስት የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ሰራተኞችና እኔ በማግስቱ በጅግጅጋ ከተማ ለሚካሄደዉ የልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎች የመልካም አስተዳደር ንቅናቄ መድረክ ለመድረስ ተጣድፈናል፡፡

በለሊት እየተላለፈ ያለዉ ኤፍ ኤም 97.1 ሬዲዮ ዝግጅት የጉዟችን ማጀቢያ ነበር፡፡ በእንግድነት የተጋበዙት አንድ ታዋቂ አርቲስት በቀደመዉ ዘመን ለኢትዮጵያ የጥበብ ዘርፍ እድገት ከፍተኛ አስተዋፆ ስላበረከተዉ ኦስትሪታዊ አርቲስት ፍራንሴስ ዞልቤከር ምስክርነታቸዉን እየሰጡ ነዉ፡፡ የኛዉ አርቲስት ታዲያ ዞልቤከርን የተዋንያንና የድምፃዉያን ወርሃዊ ክፍያ ማነስ ያበሳጫዉ እንደነበር ከነገሩን በኋላ ይህንኑ ተጨባጭ ለማድረግ ሲሉ ንፅፅር ያቀርባሉ፡፡ “ኢትዮጵያ ዉስጥ ለአንድ ሹፌር የሚከፈል ደሞዝ እንኳን ለአንድ አክተር ወይም ሙዚቀኛ አይከፈልም፡፡” ሲሉ ትችታቸዉን ሰነዘሩ፡፡

ይህን ንግግር ስሰማ ደነገጥኩ፡፡ ንግግራቸዉ አርቲስትን ከላይ ሹፌሩን ከታች የሚያስቀምጥ ነዉ፡፡ ሌሎቹም የእኔን ስሜት የተጋሩ ይመስለኛል፡፡ ፀጥታ በጣም ነግሶ ስለነበር ሁሉም ሰዎች /ሹፌሩን ጨምሮ/ እንደሰሙት እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ ሹፌሩ በፍፁም ፀጥታ መኪናዉን ማሽከርከሩን ሲቀጥል ግን መስማቱን ተጠራጠርኩ፡፡ ለካስ እሱ ነገሩን በሆዱ እያብሰለሰለዉ ኖሯል፡፡ 

ትንሽ ቆይቶ በንግግሩ መበሳጨቱን ይነግረን ጀመር፡፡ “ለእሱ ሹፌር ሰዉ አይደለም፡፡ ባያዉቀዉ ነዉ አንጅ አንድ አርቲስትና አንድ ሹፌር ወደ ሀገር ቢሄዱ ቀድሞ ስራ የሚያገኘዉ  ሹፌሩ ነዉ፡፡” ሲል ብሶቱን ገለፀልን፡፡ እኛም ትንሽ ተነጋገርንበትና ጉዳዩን በአጭሩ ዘጋንዉ፡፡

እኔ ከሹፌርና ከአርቲስት የቱ ይበልጣል የሚል አጀንዳ አልከፍትም፡፡ ተገቢም አይደለም፡፡ ግን ሁኔታዉ ሁለት ጥያቄዎችን አጭሮብኛል፡፡ በመጀመሪያ እንግዳዉ ሰዉ /አርቲስቱ/ አርቲስትን ከሹፌር ጋር ሳያነፃፅሩ የአርቲስቶችን በደል መዘርዘር አይችሉም ነበርን? የሚለዉ ጥያቄ ነዉ፡፡ እንደኔ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም የአርቲስቶች ጥቅም የሚገኘዉ ከሹፌሮች ተቀንሶ ስላልሆነ፡፡

አርቲስቶች በሙያቸዉ ሊያገኙት የሚገባ ጥቅም፤ ክብርና ዝና አላቸዉ፡፡ ይኽ ከተጓደለ ራሱን ችሎ የትችት ርእስ ሊሆን ይችላል፡፡ ማንም ሳያስከፉ የማንም ድጋፍ ማግኘት ይቻላል ማለቴ ነዉ፡፡ እናም በንግግራችን አንዱን ስናወድስ ያለበቂ ምክንያት ሌላዉን ወገን እንዳናንኳስስ ልንጠነቀቅ ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡ 

ሁለተኛዉ ጥያቄዬ የጋዜጠኝነት ሚና ነዉ፡፡ ሰዉዬዉ ተሳስተዋል ብዬ በግሌ አምኛለሁ፡፡ ተናጋሪዉ ቢሳሳቱስ መገናኛ ብዙሃኑ ወይም አዘጋጁ ጋዜጠኛ  ይህን ነገር እንደወረደ ማስተላለፍ ነበረበትን? እንደኔ ማስተላለፍ አልነበረበትም፡፡ ምክንያቱም መገናኛ ብዙሃንና ባለሙያዎቹ ማህበራዊ ሃላፊነት አለባቸዉ፡፡ በርግጥ ዘገባዉ ምርጥ የሚባልና አቀራረቡም ማራኪ ነበር፡፡ ስለሆነም ዝግጅቱ መተላለፉ ተገቢ ነዉ፡፡ ሆኖም በአርትዖት ተገቢ ያልሆኑ ንግግሮችን ማስወገድ የአዘጋጁም የአርታዒዉም መብትና ሃላፊነት ነዉ፡፡

ስለሆነም በመገናኛ ብዙሃን መልዕክት ለማስተላለፍ አድሉን ያገኘን ሰዎች ከመናገራችን በፊት የምንለዉን ነገር አንደምታ ቀድመን እንመርምር፤ ጋዜጠኞችም ካፋችን የወጣዉ አፋፍ ሳይደርስ ቀድማችሁ አፈፍ አድርጉልን፡፡
Post a Comment