Saturday, December 22, 2012

ፆምና ፀሎት--ለእቅዱ ስኬትየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከታህሳስ 15 - ጥር 15/2005 ባሉት 30 ቀናት ዉስጥ እቀርፋቸዋለሁ ብሎ ባቀዳቸዉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ ከከተማዋ አመራሮችና ፈፃሚዎች ጋር ለሁለት ቀናት ዉይይት አድርጓል፡፡ ዉይይቱ ዉጥረት የነገሰበት ነበር፡፡

በአንድ ጫፍ ለዘመናት የተቆለሉ የአዲስ አበባ ችግሮችን እንዴት በወር ዉስጥ መፍታት ይቻላል?” የሚሉና በሌላዉ ጫፍ ስናንከባልላቸዉ የቆዩ ችግሮች አሁን ተራራ አክለዉ የስርዓታችን አደጋ ሆነዋልና የተፈለገዉን መስዋዕት ከፍለን በወሩ ዉስጥ መፍታት አለብን በሚሉ ጫፎች ላይ የተወጠረዉ የጭንቅ ገመድ ተሰብሳቢዎቹን ጠፍሮ ይዟቸዋል፡፡


በዚህ ሁኔታ ለምሳ እረፍት ሲወጣ ታዲያ በሁለት አመራሮች መካከል የነበረ ምልልስ ቀልቤን ሳበዉ፡፡ በቅርበት የሚተዋወቁ ይመስላሉ፡፡ አንደኛዉ ከቀረበዉ ብፌ ዉስጥ የፍስክ ምግቦችን ሲያፍስ ሌላኛዉ የፆም ምግቦችን ይለቃቅማል፡፡ እናም ጓደኛዉ “አንተ ደግሞ ከመቼ ወዲህ ነዉ መፆም የጀመርከዉ?” ሲል ጠየቀዉ፡፡ ሰዉየዉም ለመልሱ አልሰነፈም፡፡ “ታዲያ የዚህ ወር እቅድ በፆምና በፀሎት ካልታገዘ በስራ ብቻ ይሳካል ብለህ ነዉ?”  ሲል መልሶ በፌዝ ጠየቀዉ፡፡

ኋላ ታዲያ በወሩ ዉስጥ እንዲፈቱ የተያዙትና በ13 ዘርፎች የተከፋፈሉት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተተንትነዉ ሲታዩ የሚበዙቱ ችግሮች ቀላል፤ ነገር ግን አመራሩ በቸልተኝነት ስለተዋቸዉ እየገዘፉ የመጡ፤ ሆኖም ቁርጠኝነቱ ካለ አሁንም ቢሆን ባለዉ ግብዓት ሊፈቱ የሚችሉ መሆናቸዉ ተረጋጧል፡፡ በአጭር ግዜ ሊፈቱ የማይችሉትም ተለይተዉ በአመቱ መሪ እቅድ ዉስጥ ተካተዋል፡፡

በየገዳማት ያሉ አባቶችና እናቶች የሚበዛዉን ግዜያቸዉን ከቅባት እህሎች ርቀዉ በጥራጥሬና ቅጠላቅጠል ምግቦች  ራሳቸዉን ይገድባሉ፡፡  በቀን ሰባት ግዜም ይፀልያሉ፡፡ እነዚህ ቅዱሳን የቆሙለት አላማ የሚመኙት ሌላ አለምም አላቸዉ፡፡ አሱን ለማግኘት ሲሉም ይች ምድር ጀባ ያለቻቸዉን ፍሰሃና አዱኛ ይቃወማሉ፡፡ ይልቁንም መከራዋን ሁሉ በመሸከም ስጋቸዉን ያደክማሉ፡፡

እነዚህ የአዲስ አበባ ከተማ አመራሮችና ፈፃሚዎች ታዲያ እንደመነኮሳቱ ካሰቡት ለመድረስ ከስንፍና፤ ራስን ከመዉደድና በአድሎና ጉቦ ከመስራት ራሳቸዉን መገደብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከኔ በፊት የህዝብ ጥቅም ማለትን፤ የአላማ ፅናትንና ለሚመሩት ሰዉ መናገርን ብቻ ሳይሆን ማድመጥንም መልመድን ወቅቱ ግድ ይላቸዋል፡፡
Post a Comment