Wednesday, December 5, 2012

አዲስ ራዕይ

እዉነቱን ለመናገር የኢሕአዴግ የንድፈ ሃሳብ መፅሄት የሆነችዉ አዲስ ራዕይ መፅሄት ዋና አዘጋጅ ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ እንደነበር አላዉቅም ነበር፡፡ በርግጥ መለስ ዜናዊ በተለያዩ መድረኮች ከሚያራምዳቸዉ አቋሞች ጋር የሚመሳሰሉ ፅሁፎችን በመፅሄቷ ስመለከትና በይዘቷና በአቀራረቧ ካላት ብስለት አንጻር በመመዘን ‘ሰዉየዉ’ ፅፏት ይሆንን ብዬ መጠርጠሬ አልቀረም፡፡ ዋና አዘጋጇ መለስ መሆኑን ርግጠኛ መሆን የጀመርኩት ግን የዚህ አመት የመጀመሪያዋ ልዩ እትም የገበያ ማስታወቂያ/commercial ad/ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲነገር ነዉ፡፡ አሁን ደግሞ መፅሄቷ ገበያ ላይ ስትዉል አግኝቸ ሳነባት ይህንኑ በድጋሜ የሚያረጋግጡ በርካታ አረፍተ ነገሮችን በዉስጧ አግኝቻለሁ፡፡ እንዲያዉም የዚች እትም ማስታወሻነት ለቀድሞዉ ዋና አዘጋጇ ለመለስ ዜናዊ መሆኑን አዘጋጆቿ እንደወሰኑ ነግረዉናል- በመፅሄቷ ርዕሰ አንቀፅ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት በድርጅትም ሆነ በመንግስት የአመራነት ሚና ላይ በሚያሳርፈዉ ተፅዕኖ ዙሪያ ብዙ ተብሏል፡፡ ብዙ ተስፋ መቁረጦች፤ ብዙ ሟርቶችንና ብዙ መፅናናቶችን ሰምተናል፤ አንበናል፡፡ ኢሕአዴግም ታላቁን መሪ በግለሰብ ደረጃ መተካት እንደማይቻል በማመን ይመስላል ጅምር የልማት ስራዎችን በጋራ አመራር/collective leadership/ የማስቀጠል ስልትን ተከትሏል፡፡


ሀገሪቱም ሆነ ፓርቲዉ ታላቅ ስብዕና ያለዉን መሪ ቢያጡም፤ መላዉ ህዝብ በመሪር ሀዘን ቢዋጥም፤ ምክንያቶች ተዘርዝረዉ በቃ አለቀልን/አለቀላቸዉ ቢባልም እስካሁን ከግምት ያለፈ ተጨባጭ አደጋ ግን አልታየም፡፡ ይሄ ከመለስ ዜናዊ የአመራር ስብዕና ጋር የተያያዘዉ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ በስነ-ፅሁፉ/በተለይ በአዲስ ራዕይ/ ዘርፍ ያለዉ ክፍተትም አሳሳቢነቱ አያጠራጥርም፡፡ ዋና አዘጋጇን ሌላ ይተካዋል? በጋራ ፀሃፊዎች ትዘጋጃለች? የጥራ ደረጃዋ ይወርዳል? እስከነአካቴዉ ትጠፋስ ይሆን? የሚሉ ጥያቄዎችን ለራሴ አነሳሁ፡፡ ይህን የማነሳዉ ግን የመለስ ዜናዊ ሞት የፈጠራቸዉን ክፍተቶች ለመቁጠር ብየ ሳይሆን ለእኔም ጭምር የሚጎልብኝን በማሰብ ነዉ፡፡

የጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ አስከሬን ቦሌ አለምአቀፍ አዉሮፕላን ማረፊያ በመግባት ላይ ሳለ የእንጀራ ጉዳይ ሆኖብኝ ሌሎች ሲያለቅሱ እኔ “ምን ሆናችሁ ነዉ” እያልኩ ቃለመጠይቅ አደርግ ነበር፡፡ አንድ አሮጊት ታዲያ “እኔስ የማለቅሰዉ ለሱ አይደለም፡፡ ኑሮዬ ጎደለብኝ ብዬ ነዉ” ብለዉኝ ነበር፡፡ በርግጥ የሳቸዉን ምላሽ በቀጥታ የሚቃረን ሌላ ምላሽ የሰጠችኝ ሴትም አለች /ሴት ብቻ ነዉ እንዴ የሚጠይቀዉ እንዳትሉኝ እንጅ/፡፡ ይች ሴት ታዲያ “እኔስ የማለቅሰዉ ለሱ ነዉ፡፡ ማረፍ እፈልጋለሁ እያለ ሳያርፍ በመሞቱ” ብላኛለች፡፡ ዞሮ ዞሮ ሁለቱም በመሪያቸዉ ሞት በጣም አዝነዋል፡፡ እኔም የአዲስ ራዕይ እጣ ፈንታ ላይ ጥያቄ ያነሳሁት እንዳትጎድልብኝ ስለሰጋሁ ነዉ፡፡ መፅሄቷ ለንባብ መብቃት ከጀመረች አንስቶ ሳላነበዉ ያለፍኩት እትም ያለ አይመስለኝም፡፡ በወቅታዊ አለማዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከሚያተኩረዉ የትንታኔ አምዷ በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ብዙ ቁምነገሮችን አግኝቸበታለሁ፤ ተምሬበታለሁ፡፡

የሻዕቢያን የአፍሪካ ቀንድ የትርምስ ስትራቴጂ የተነተነችዉ የግንቦት/1998 እትምና የሷዉ ተከታይ የሆነችዉ የሻዕቢያ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ስልት በሚል ርዕስ ህዳር/1999 የታተመችዉ መፅሄት ሻዕቢያን ከስር መሰረቱ ፍንትዉ አድርገዉ የሚያሳዩ፤ አሁን ያለዉ የኤርትራ ገዥ መደብ ያሉትን አማራጮችና የመረጠዉን ስልት እንደዚሁም ከመካከለኛ ግዜ አንጻር  የሚከተለዉን አቅጣጫ ተንትነዉ ያቀረቡ ነበሩ፡፡ ትንቢቱ የተነገረለት ሻዕቢያም በተግባር ይህንኑ ስልት ሳያዛባ እየተገበረዉ እንደሆነ አለም በግልጽ እያወቀዉ መጥቷል፡፡

አዲሱ ሚሊኒየምና የኢትዮጵያ ህዳሴ በሚል ልዩ እትም መስከረም/2000 ብቅ ያለችዉ አዲስ ራዕይ መፅሄት ደግሞ ኢትዮጵያ ከስልጣኔ ማማ ተንሸራታ የወደቀችበትን አዘቅት፤ አሁን የለመለመዉን ተስፋዋንና ፈተናዎቿን ትተርክ ነበር፡፡ የአሁኑ ጠ/ሚ/ር ኃ/ማርያም ደሳለኝ በአንድ ወቅት በዚች መፅሄት ላይ ተንተርሰዉ የሰጡትን ማብራሪያም በአንድ አጋጣሚ መከታተል ችዬ ነበር፡፡

ከጥንቆላ የማይተናነስ ሆኖ ያገኘሁት በዚሁ አመት ጥቅምት ወር በወጣችዉ መፅሄት ስር የግሎባላይዜሽን ቆሞ ቀሮች በሚል ንዑስ ርዕስ የወጣዉ ፅሁፍ ነዉ፡፡ በዚህ ፅሁፍ ስለአረቡ አለም እጣ ፈንታ የቀረበዉን ትንታኔ ብዙ መላምቶች ስለነበሩት ለማመን ከባድ ነበር፡፡ ሆኖም መፅሄቷ ከታተመች ከአንድ አመት በኋላ የተጀመረዉ የአረቡ አለም ፀደይና አሁን ድረስ ያለዉ የቀጠናዉ ሁኔታ የመፅሄቷ ‘የትንቢት ቃል’ ሳይጓደል መፈፀሙን አረጋግጧል፡፡

ህዳር/2003 ላይ የወጣዉ ትንታኔ ደግሞ በግንባሩ የተሃድሶ መስመርና በኢትዮጵያ ሕዳሴ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ በዚህ እትም ኢትዮጵያ ሕዳሴዋን ለማረጋገጥ ያሏት አማራጮች ተፈትሸዋል፡፡ የኒዮ ሊበራሊዝምና የልማታዊ ዲሞክራሲ አማራጮች በስፋት ተተንትነዉበታል፡፡ የተሃድሶዉ መስመር ግልፅ ትልሞች እንዳሉት፤ ትልሞቹም በፍጥነት በማደግ ላይ ባሉ የኤስያ ሀገሮች ተተግብረዉ አዋጭነታቸዉ የተረጋገጠ መሆኑን ይተነትናል ፅሁፉ፡፡ ይህ ፅሁፍ የተጠናቀቀዉ በተከታዩ አንቀፅ ነበር፡፡
“ኮሪያዉያን ከድህነት ወደ ብልፅግና ያደረጉትን ረጅም ጉዞ የሚቃኙበት አንድ ቀላል አባባል ነበራቸዉ፡፡ “ጃፓናዉያን ወንዙን ለመሻገር እየረገጧቸዉ ያለፏቸዉን ድንጋዮች እየረጋገጥን እናልፋለን” የሚል፡፡ … ይሁንና ማንም ሀገር ከሌሎች ልምድ ከመማር አልፎ የሌሎች አገሮች ታሪክን መድገም አይችልምና ኮሪያዉያን ጃፓናዉያን የቀየሱትን መንገድ ከሁኔታቸዉ ጋር አጣጥመዉ ማስተካከል ነበረባቸዉ፡፡ እናም ኮሪያዉያኑ ወንዙን የተሻገሩት ጃፓኖች የረገጧቸዉን ድንጋዮች ራሳቸዉን እየረገጡ ሳይሆን ወንዙን ለመሻገር የቀለለዉ መንገድ የቱ እንደሆነ ከጃፓናዉያን ተምረዉ የራሳቸዉን ማስተካከያ በማድረግ ነበር፡፡ እኛ የሕዳሴ ጉዟችንን ስንቀይስ የሁሉንም ልማታዊ መንግስታት ልምድ ቀምረናል፡፡ ከስኬታቸዉና ከጉድለታቸዉ ለመማር እድል አግኝተናል፡፡ ከራሳችን አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ባህሪና ከሃገራችን ልዩ ሁኔታ በመነሳት ከልምዳቸዉ የማይሆነንን ጥለን የራሳችንን አክለን የኛ የምንለዉ አቅጣጫ ቀይሰናል፡፡ እኛ ቀደምት ልማታዊ መንግስታት ረግጠዉ የተሸገሩባቸዉን ድንጋዮች በመርገጥ ሳይሆን የራሳችንን ድልድይ በተመሳሳይ ቦታና አቅጣጫ በመገንባት ነዉ የምንሻገረዉ፡፡” አዲስ ራዕይ ህዳር/2003፤ ገጽ 123-125፡፡
አዲስ ራዕይ መፅሄት ባለፈዉ አመት እትሟ ደግሞ ሶስት የዉጭ ሀገር መፅሃፍትን ዳስሳለች፡፡ ከነዚህ ዉስጥ በመጀመሪያ የቀረበዉ የ The Shock Doctrine ዳሰሳ/book review/ ለኔ ልዩ ነበር፡፡ እነዚህን ለአብነት አነሳሁ እንጅ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ትንታኔ ሰጥታለች አዲስ ራዕይ፡፡

የአሁኗ እትም አዘጋጆች ካሁን በኋላ የጋራ ዋና አዘጋጅነት ስልትን እንደሚከተሉ በርዕሰ አንቀፃቸዉ ጠቁመዋል፡፡ “መፅሄታችን አዲስ ራዕይ ካፕቴኗን ብታጣም ሁሉም አዘጋጆቿና አንባቢዎቿ በመተጋገዝ በዚህ ታላቅ መሪ መስዋዕትነት በመፅሄታችን ላይ ሊደርስ የሚችለዉን ክፍተት እያሟላን እንደምንጓዝ … እንገልፃለን፡፡” ብለዋል፡፡

ይሄ እንግዲህ መንግስትና ግንባሩ በአመራር ዘርፍ የተከተሉት ስልት በስነ-ፅሁፉም ዘርፍ መታሰቡን የሚያሳይ ነዉ፡፡ ይችኛዋ እትምም በዚሁ ስልት እንደተዘጋጀች መገመት አያዳግትም፡፡ በርግጥ የዛሬዉ እትም በአንድ ሳይንሳዊ ጉዳይ ላይ ትንታኔ የቀረበበት አይደለም፡፡ ይልቁንም በታላቁ መሪ ህይወት ዙሪያ በሀገር ዉስጥም በዉጭም ሲባሉ ስለነበሩ ጉዳዮች በተለየ አተያይ ሰፊ ትንታኔ የቀረበበት ነዉ፡፡ በመፅሄቷ ላይ ይህ ነዉ የሚባል ችግር አላየሁም፡፡ ይልቁንም በተለመደዉ ማራኪ ፍሰት ያልተነኩ ርዕሶችን በመምረጥ ማራኪ ትንታኔ ይዛ ብቅ እንዳለች አይቻለሁ፡፡ ስለሆነም መፅሄቷ መታተም እንደማታቆም ብቻ ሳይሆን የጥራት ደረጃዋም እንደማይወርድ ፍንጭ ሰጥታለች፡፡ አሁንም በሃላፊነት ላይ ያሉ ነባር የግንባሩ አመራሮች ገና በረሃ ሳሉ በተባ ብዕራቸዉ ያሳዩትን የስነ-ፅሁፍ ብቃት ላይደግሙት፤ የአዲሱ ትዉልድ አመራሮችም ይህንኑ ላያግዙ ምን ያግዳቸዋል፡፡

ይች ልዩ እትም መለስ ስለተፈጠረበት ዘመን፤ መለስ በተፈጠረበት ዘመን የፈፀመዉ ነገር ግን ገና ላልተፈጠረዉም ዘመን ትቶት ያለፈዉ ትዉስታ/legacy/ እንደዚሁም ስለግል ስብዕናዉ ጭምር በርካታ መረጃዎችን ይዛለች፡፡ ከዚህ ባለፈም ከሽያጯ የሚገኘዉ ገቢ ጠ/ሚ/ሩ ከት/ቤት እድሜያቸዉ ጀምሮ እስከ ህልፈተ ህይወታቸዉ ድረስ ያለፉባቸዉን ሂደቶች ለአዲሱ ትዉልድ ለማስተላለፍ እንዲቻል ለንባብ፤ ለጥናትና ምርምር እንደዚሁም ለታሪክ መዘክር በሚሆን መንገድ ተደራጅቶ በአዲስ አበባ ለሚገነባዉ ማዕከል ግንባታ የሚዉል ነዉ፡፡ እናም መታሰቢያነቷ ለታላቁ መሪ የሆነችዉን መፅሄት ባለቤት መሆን ድርብርብ አላማዎችን ማሳካት ነዉ፡፡

ይህን ፅሁፌን የምቋጨዉ ከመፅሄቷ የወሰድኩትን አንድ አንቀፅ በማስነበብ ሲሆን በቀጣይም በተለይ በፌስቡክ ገፄ ላይ የአሳታሚዉን መብት ሳልጋፋ የተወሰኑ አንቀፆችን ፖስት ለማድረግ እሞክራለሁ፡፡
“ዛሬ በዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ስም ሲመፃደቁ የምናያቸዉ፤ ትላንት ከትላንት ወዲያ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ጭምር እኛን አፍሪካዉያንን ከእንስሳት ባልተለየ ሁኔታ ሲያንገላቱን የምንመለከታቸዉ፤ ዴሞክራሲን መጀመሪያ ለሃብታሞች፤ ከዚያ ከስንት አስር አመታት በኋላ ለሴቶች፤ ከዚያ እንደገና ከስንት አስር አመታት በኋላ ደግሞ ለጥቁሮች እየቀነጫጨቡ በማደል የተጓዙት የበለፀጉት ሃገሮች ከዴሞክራሲ በፊት ሊበራሊዝምን ማስቀደማቸዉና ለባለገንዘቦች ያደላ አካሄድ መከተላቸዉ በመሰረቱ ከኛ የሚለየዉ መለስ/ኢሕአዴግ የዴሞክራሲና ሰብዓዊ ክብርን ለመላ የአገራችን ህዝቦች ያለልዩነት ወለል አድርጎ በመክፈት ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነዉ፡፡” አዲስ ራዕይ ጥቅምት/2005፤ ገጽ 23፡፡
Post a Comment