Thursday, November 8, 2012

RIP-ፈጣሪ ነፍሷን በገነት ያኑራት

በወ/ሮ ላቀች ደገፉ ሞት በጣም ነዉ ያዘንኩት፡፡ ፈጣሪ ነፍሷን በገነት እንዲያኖራትም ምኞቴ ነዉ፡፡ ወ/ሮ ላቀችን በተደጋጋሚ በስራ አጋጣሚ አገኛት ነበር፡፡ ለበርካታ ግዜዎች ተቀራርበን አዉርተናል፡፡ ምንም እንኳን ልትደርስበት ያሰበችዉ ቦታ የሚወስዳትን ትክክለኛ መንገድ መርጣለች ብዬ ባላምንም በጎ ነገሮችን የምትመኝና ችግሮቿ ሁሉ የተፈቱላትን ኢትዮጵያን ማየት የምትሻ ሴት ነበረች፡፡

በአንድነት/መድረክ ፓርቲ ዉስጥ ካሉ ጥቂት ሴት አባሎች ዉስጥ አንዷ ከሆነችዉ ወ/ሮ ላቀች ጋር ይበልጥ ተቀራርበን የነበረዉ በ2002 በተካሄደዉ ምርጫ ወቅት ነበር፡፡ መድረክ በወቅቱ በየክፍለ ከተሞቹ የምረጡኝ ቅስቀሳ ያካሂድ ነበር፡፡ ወ/ሮ ላቀች እንደሁሉም የአዲስ አበባ ዕጩዎች ሁሉ በተወዳደረችበት የምርጫ ክልል ለማሸነፍ የተቻላትን ሁሉ ታደርግ ነበር፡፡ አንድ እሁድ በአስኮ አካባቢ የመድረክ ዕጩ የነበሩ ተወዳዳሪ ቅስቀሳ ለማድረግ የሚያስችላቸዉን ትልቅ አዳራሽ ከነሙሉ ወንበሩ አዘጋጅተዉ ተሰብሳቢዎችን ይጠብቃሉ፡፡ እኔም ለኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የዜና ዘገባ በስፍራዉ ተገኝቻለሁ፡፡ ሆኖም የመጡት እጅግ በጣም ጥቂት ነዋሪዎች ብቻ ነበሩ፡፡ ወ/ሮ ላቀችን ጨምሮ እዛ የተገኙት የመድረክ አመራሮች በሙሉ በዚህ ነገር በጣም ተበሳጭተዉ ነበር፡፡

ወደ ወ/ሮ ላቀች ጠጋ ብዬ “ይህ ነገር ፓርቲው በህዝቡ ያለመፈለጉን /መጠላቱን/ አያሳይም ወይ?” ብዬ ጠየኳት፡፡ ወ/ሮ ላቀች “አያሳይም” ብላ ተከራከረችኝ፡፡ “በሚቀጥለዉ ሳምንት በኔ ምርጫ ክልል የሚወጣዉን ህዝብ ታያለህ” ብላ ፎከረች፡፡ በሳምንቱ የሷን የምርጫ ቅስቀሳ ለመዘገብ መርካቶ ሲኒማ ራስ አዳራሽ ተገኘሁ፡፡ ወ/ሮ ላቀች እንዳለችዉም ሲኒማ ራስ ጢም ብሎ ሞልቶ ነበር፡፡ እርሷም በጣም ተደስታ ነበር፡፡

ወ/ሮ ላቀች ደገፉ በአንድነት ዉስጥ ተሰሚነት ያላት ሴት ነበረች፡፡ በርግጥ በምርጫዉ መድረክ ከተሸነፈ በኋላ በተሳትፎ ረገድ መቀዛቀዝ ታይቶባታል፡፡ በምርጫዉ ማግስት መድረክ ራሱን እንደገና ሲያደራጅና የስራ አስፈፃሚዉን ኮሚቴ በአዲስ ቪዉ ሆቴል ሲመርጥ እዛዉ ተገኝቼ ነበር፡፡ ወ/ሮ ላቀች በኮሚቴ አባልነት አልተመረጠችም፡፡ ሌላ ማንም ሴትም በኮሚቴዉ አልተካተተችም፡፡

ነባርና ታዋቂ የፓርቲዉ አባል የሆነችዉ ላቀች፤ ከብዙ ወንዶች መካከል የተገኘችዉ ላቀች፤ ሴቶችን ወደፊት በሚባልበት ዘመንና ምርጫ ቦርድም በርካታ ሴቶችን በዕጩነት ለሚያቀርብ ፓርቲ የተሻለ ገንዘብ በሚደጉምበት ወቅት የሷ በስራ አስፈፃሚነት ያለመመረጥ አስገርሞኝ ነበር፡፡ የስራ አስፈፃሚዉ አባል ሆነዉ የተመረጡትንና በ2002 ምርጫ ድል የቀናቸዉን አቶ ግርማ ሰይፉን እንዴት ነዉ ነገሩ አልኳቸዉ፡፡ “ልክ ነህ፤ግን ፈቃደኛ ስላልሆነች ነዉ” ነበር መልሳቸዉ፡፡

በርግጥ ይህና በፓርቲዉ ስብሰባ በተደጋጋሚ መቅረቷ በፓርቲዉ ዉስጠ ዴሞክራሲ ወይም ሌላ ጉዳይ ቅሬታ/ ያለመርካት/ ሳይሰማት እንዳልቀረ ያመላክታል፡፡ ሆኖም እስከ ሞቷ ድረስ በፓርቲዉ ዉስጥ ሚና የነበራትና ካሉት ጥቂት ሴቶችም ግንባር ቀድማ የምትታይ የመድረክ አባል ነበረች፡፡

የርሷን ሞት ተከትሎ በፌስቡክ በተለጠፈዉ ፎቶዋ ላይ “በክብር መሪያችን ሞት የተሳለቁ አረመኔዎች እጣዉ እየደረሳቸዉ ይገኛል” የሚል ፅሁፍ አንብቤአለሁ፡፡ በርግጥ እኔ በጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ሞት መሪር ሀዘን ከተሰማቸዉ እልፍ ሰዎች አንዱ ነኝ፡፡ በጠ/ሚ/ሩ ሞት የተደሰቱ ሰዎችንም አምርሬ ጠልቻቸዋለሁ፡፡ ይህንንም ከዚህ በፊት “ማንን እንመን” ወይም “Whom to Believe” በሚሉት ፅሁፎቼ ለማሳየት ሞክሬያለሁ፡፡ ነገር ግን በወ/ሮ ላቀች ላይ የቀረበዉን ይህን አስተያየት ቢያንስ በሁለት ምክንያቶች እቃወመዋለሁ፡፡

አንደኛዉ በጠ/ሚ/ሩ ሞት የተደሰቱ /አንዳንዶች ስሜታቸዉን በግልፅ በመገናኛ ብዙሃን የተናገሩ ሌሎቹ ዉስጥ ለዉስጥ የሚያወሩት/ እንዳሉ አዉቃለሁ፡፡ ወ/ሮ ላቀች ይህንን ስለመፈፀሟ ግን ምንም መረጃ የለኝም፡፡ ፖስት የተደረገዉም ይህንን አያረጋግጥም፡፡ ስለሆነም ስገምት ነገሩ ከኑግ የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ ይመስለኛል፡፡

ሁለተኛ በሀገራችን ባህል ሙት መዉቀስ ነዉር ነዉ፡፡ በጠ/ሚ/ር መለስ ሞት የተሳለቁትን ያዘንንባቸዉ በዚህ ነዉረኛ ተግባር ዉስጥ ዘቅጠዉ ስላገኘናቸዉም ጭምር ነዉ፡፡ ስለዚህ እዉነት እንኳን ቢሆን ክፉን በክፉ መመለስ አይገባም፡፡

ወ/ሮ ላቀችን ለመጨረሻ ግዜ ያገኘኋት በግምት ከወር በፊት ብሔራዊ ትያትር አካባቢ ነዉ፡፡ ከርቀት ጠራኋትና ሰላምታ አቀረብኩላት፡፡ ከተለመደዉ የተለየ አካላዊ ችግር አላየሁባትም ነበር፡፡ አጥብቃ ይዛ ሰላም አለችኝ፡፡ “አንተ ጥሩ ልጅ ነህ” አለችኝ የልጅ አባት መሆኔን ስለማታዉቅ፡፡ በሆዴ ‘አባቱን ልጅ አለችዉ’ እያልኩ ምስጋናዬን ገለፅኩላት፡፡ ወ/ሮ ላቀችን አከብራታለሁ፤ እወዳታለሁ፡፡ ግን የሞተችዉ እናቴ ስም ‘ላቀች’ መሆኑም ተፅዕኖ ሳያሳድርብኝ አይቀርም፡፡ ለማንኛዉም ዳግም ፈጣሪ ነፍሷን በገነት እንዲያኖራት እለምነዋለሁ፡፡ ለቤተሰቦቿ መፅናናትን ለአንድነት ደግሞ ማስተዋልን እመኛለሁ፡፡
Post a Comment