Tuesday, October 9, 2012

የሟርት ዉርጅብኞች


ከነሐሴ 27/2004 -- መስከረም 27/2005፤ 
ነሃሴ 27/ 2004፤ ኢትዮጵያዉያን ለ21 አመታት ያለመታከት ያገለገላቸዉን ታላቅ መሪ የሚገባዉን ክብር በመስጠት የተሰናበቱበት ዕለት፡፡ በሃገሪቱ ታሪክ ዉስጥ ቀድሞ ባልታየ መልኩ ለተከታታይ ዘጠኝ አመታት ፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገት እንዲመዘገብ ያስቻለዉ፤ ብዙህነትን ያስተናገደ ስርዓት በመዘርጋት ሰላምና መረጋጋት ያሰፈነዉ፤ በአለም አቀፍ መድረኮች የሃገሩንና የዜጎቹን ጥቅም ለማስከበር የታገለዉ መሪ ዜና ህልፈት ከተሰማ በኋላ መላ ኢትዮጵያዉያን ከጫፍ ጫፍ ተነቃንቀዉ በ13 ብሔራዊ የሃዘን ቀናት መሪር ሀዘናቸዉን ገለፁ፡፡
አንዳንዶች ለ38 አመታት ያለእረፍት መዉጣት መዉረዱ፤ ታሞ በአልጋ ላይ ሳለ እንኳን ከራሱ ጤና በላይ ሃገሬ ማለቱ አንገበገባቸዉ፡፡ እናም ለዛ ጀግና ላልተኖረ ግላዊ ሂወት አዘኑለት፡፡ “ምናለ እንደተመኘዉ ትንሽ አርፎ ቢሞት” ሲሉ አለቀሱለት፡፡ ሌሎችም ጥቅሜ ተነካ ብለዉ አነቡለት፡፡ “ተዉኝ አለቅሳለሁ፤ ንፁህ ዉሃ ያጠጣኝ፤ ደጄ ላይ ትምህርት ቤት የከፈተልኝ፤ ጓሮዬን ባለማሁ ጀግና ብሎ የሸለመኝ፤ ቤቴ ገብቶ ቆሎዬን የበላ፤ የእግር መንገዴን የተጓዘ፤ ተስፋዬን አለምልሞ ባለራዕይ ያደረገኝን መሪዬን ሳጣ ለምን አላለቅስ” አሉ ፊታቸዉ በእንባ እየታጠበ፡፡ “ጭቃ ሳልጠፈጥፍ ባለ ቤት ያረገኝ፤ እኔስ የማለቅሰዉ ለራሴ ነዉ” አሉ አዛዉንቷ ደረታቸዉን እየመቱ ፡፡ ምንም እንኳን አቤ ቶኪቻዉ ከሰሞኑ ከወደ እንግሊዝ በብሎጉ ባስነበበዉ ፅሁፉ “ዴቪድ ካሜሮን ገና እንግሊዝ እንደገባሁ ኮንዶሚኒየም ቤት ሰጥቶኛል፡፡ እና እሱ ሲሞት ከ10ኛ ፎቅ ላይ መፈጥፈጥ አለብኝ ማለት ነዉን?” ብሎ ቢሳለቅባቸዉም፡፡
ኢትዮጵያዉያን በመሪር ሀዘናቸዉ ዉስጥም የአይበገሬነትና ተስፋ ያለመቁረጥ ስብዕናቸዉ ጎልቶ የወጣባቸዉ፤ ይልቁንም ለላቀ ስኬት በአንድነት እንተማለን ሲሉ የተማማሉባቸዉ እኒያ 13 መሪር የሀዘን ቀናት አልፈዉ ነሃሴ 27/2004 የታላቁን መሪያቸዉን ግብዓተ መሬት አለምን ባስደመመ ስርዓት ፈፀሙት፡፡
ማንም ማንምን ማፅናናት ያልቻለበት ሁሉም በእንባ የተራጨበት አዲስ ታሪክ፡፡ አዎን መሪዎቻኞን እርስ በርስ ተጋለዉልናል፤ አዎን መሪዎቻችን “አንድ ጥይት እስኪቀር…” ብለዉ ከድተዉናል፡፡ ሲሞቱም አላዘንን፤ ሲሰደዱም አልከፋን፡፡ በርግጥ አንድነታችን እንዳይሸራረፍ ታግለዉልናል፤ መሬታችንም እንዳይቆረስ ጥይት ጠጥተዉልናል፡፡ ግና ያልበላንን ስላከኩልን ሞታቸዉ ሰቀቀን አልሆነብንም፡፡
የድሆች ጠበቃ፤ የዘመኑ ሰዉ ሞት ግን ጎዳና አዳሪዎችን፤ የቀን ሰራተኞችን፤ ዱር አደር ወታደሮችን በእንባ አራጨ፡፡ በቀብር ስነስርዓቱ ላይ የተገኙ የሀገራት መሪዎችና ተወካዮችም ሀዘኑ የኢትዮጵያዉያን ብቻ ሳይሆን የመላዉ አፍሪካዉያንና የአለም ድሆች መሆኑን በአንድነት መሰከሩ፡፡ ታግሎ ያታገለዉ፤ የድህነት ዘበኛን የጣለዉ፤ ድህነትን ያቆሰለዉ ወታደር፤ የሰላም መሪ የድሆች ጠበቃ በሁሉም መሪዎች አንደበት በባለራዕይነቱ፤ በብሩህ አዕምሮዉ፤ በትጉህ መሪነቱ፤ በፅኑ አቋሙ፤ በአመራር ብቃቱ ተሞካሸ፡፡ 
የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት ግን እኒያ አጋጣሚዎችን በመጠቀም ወደ ስልጣን የሚሮጡ ሀይሎች አጀንዳቸዉን ዳግም  እንዲከፍቱ ያረገም ነበር፡፡ የግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ “ይህን መልካም አጋጣሚ ኢትዮጵያዉያን ለለዉጥ ሊጠቀሙበት ይገባል” በማለት በኢትዮጵያዉያንና በገዥዉ ፓርቲ ላይ ያነጣጠረዉን የስነልቦና ዘመቻ ባርከዉ አስጀመሩ፡፡ ከሂዉማን ራይትስ ወች እስከ ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ፤ ከኢሳት ቴሌቪዥን እስከ ኢትዮጵያን ሪቪዉ  ያሉ ተቋማት ኢትዮጵያ አበቃላት፤ በብሔርና በሀይማኖት ልትበታተን ነዉ፤ ኢሕአዴግም በዉስጥ ክፍፍሉ መናቆር ጀምሯል አሉ፡፡ መለስ ዜናዊ በኋላቀር የአመራር ዘይቤዉ ሀገሪቱን አዘቅጥ ዉስጥ ከቷታል፤ እናም ለታሪክ የቀረ በጎ ግብር /ሌጋሲ/ የለዉም ሲሉ ደመደሙ፡፡
ኢሕአዴግ ግን ምክር ቤቱን ሰብስቦ የጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊን ራዕይ ማሳካት በሚቻልበት አግባብ ላይ መከረ፤ በመሪዉ ሞት የተነሳ የተፈጠረዉን የአመራር ክፍተትም ጥቂቶች እንደቋመጡለት ሳይሆን መላ ኢትዮጵያዉያን በሚሹት መልኩ ደፈነ፡፡ የግንባሩ ሊቀመንበር ምርጫ የዉስጠ ፓርቲ ሽኩቻ ምንጭ እንደሆነና አባል ፓርቲዎቹ መግባባት እንደተሳናቸዉ አሉባልታ ቢናፈስም የመተካካት ሂደቱ በሰላማዊ ሽግግር ተጠናቀቀ፡፡
ማንም በቴሌቪዥን እንደተከታለዉ የምርጫዉ ሂደት ፍፁም ሰላማዊ ድባብ የሰፈነበት፤ በሁሉም የምክር ቤቱ አባላት ፊት ላይ ብሩህ ገፅታ የታየበት ነበር፡፡ እናም የኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አስቀድሞ እንዳለዉ አመራር የመምረጡ ሂደት አንድን ጓድ ለሌላ ተጨማሪ ሃላፊነት ከመመደብ የዘለለ ፋይዳ በሌለዉ እሳቤ ተጠናቀቀ፡፡ አባል ፓርቲዎቹ በተናጠል በሰጡት መግለጫም ምርጫዉ የተጀመረዉን የህዳሴ ጉዞ የሚያስቀጥል፤ ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ እንደሆነ አረጋገጡ፡፡
የግንባሩን ዉሳኔ ተከትሎም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰየመ፡፡ እነሆ በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥም አዲስ ታሪክ ተፃፈ፡፡ ለዘመናት በግፍ ተበድሎ፤ በብሔራዊ ጭቆና ስር ከኖረዉ የወላይታ ብሔር አብራክ የተገኙት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ብቻ ታጥሮ የነበረዉን በትረ ሙሴ ተረከቡ፡፡ በዚህም ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸዉን በራሳቸዉ ማስተዳደር ብቻ ሳይሆን በብቃት ላይ ተመስርቶ ሀገር የመምራት ሃላፊነትን የሚሸከም ትከሻ እንዳላቸዉ በተግባር አሳዩ፡፡ ኢሕአዴግን እንደ ፓርቲ ካቆሙት ምሰሶዎች አንዱ የሆነዉ የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት መርህም ፍንትዉ ብሎ ታዬ፡፡ “ኢሕአዴግ ለይስሙላ ይህን መርህ ፃፈዉ እንጅ አይተገብረዉም፤ የጠቅላይ ሚንስትርነት ስልጣን ከትግሬዎች ከወጣ ከምላሴ ፀጉር” ያሉት መሲሆችም ዳግም አጀንዳቸዉን ተነጠቁ፡፡
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በፓርላማ ፊት ቀርበዉ ባደረጉት ንግግር “የኔ ድርሻ የመለስን ሌጋሲ ማስቀጠል ነዉ” በማለት ለለዉጥ በተነሳሳዉ የተስፈኞች ስሜት ላይ ቀዝቃዛ ዉሃ ቸለሱበት፡፡ “የኢትዮጵያን ህዝብ እንባ ማበስ የሚቻለዉ የመለስን ራዕይ በማሳካት ነዉ፤ የኢትዮጵያ ህዝቦችና ኢሕአዴግ ደግሞ ይህን የመፈፀም ብቃት አላቸዉ” በማለት በአንድ በኩል ለተሰዋዉ ጓዳቸዉ ያላቸዉን ታማኝነት በሌላ በኩል የአሁኑ ትዉልድ ሃላፊነትን የመወጣት አቅም አረጋገጡ፡፡
ወሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የአቶ መለስን ሌጋሲ በተግባር ያስቀጠሉበትና የራሳቸዉን አዲስ አሻራም ማስፈር የጀመሩበት ነዉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተባበሩት መንግስታት 67ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ አቋማቸዉን ለአለም መሪዎች ይፋ አድርገዋል፡፡ በጎንዮሽ ዉይይቶችም በሃገራቸዉ ጥቅም ዙሪያ መክረዋል፡፡ በአቶ መለስ ዜናዊ የተጀመረዉን ሱዳንንና ደቡብ ሱዳንን የማግባባት ሂደት ከዳር ለማድረስ ያደረጉት ጥረትም ሁለቱ ሀገሮች መስከረም 17/2004 እዚሁ አዲስ አበባ ዉስጥ በፈረሙት የሰላም ስምምነት መቋጫ አግኝቷል፡፡ የሁለቱ ሃገራት መሪዎችም ሆኑ ዋና አደራዳሪዉ ታቦን እምቤኪ “ያለ መለስ ዜናዊ ጥረት እዚች ቀን ላይ አንደርስም ነበር” ሲሉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም በሂደቱ ለነበራቸዉ ተሳትፎ ምስጋና ተችሯቸዋል፡፡
የመለስ ዜናዊ አስተዳደር የዉጭ ግንኙነት ፖሊሲ ትኩረት የሆነችዉ የሶማሊያ ጉዳይም አመርቂ መሻሻል የታየበት፤ ሀገሪቱም የተሳካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫና የስልጣን ሽግግር ያደረገችበት ነበር ወሩ፡፡ በሼህ ሀሰን መሃመድ በአለ ሲመት ላይ የተገኙት አቶ ኃይለማርያም ሶማሊያ ቀድሞ ወደነበረችበት ታሪካዊ ስፍራ እንድትመለስ ሃገራቸዉ አስፈላጊዉን ድጋፍ  እንደምታደርግ አረጋግጠዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተካሄደዉ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርና የአመራር መተካካት ልማቱና ሰላሙ ሳይንገጫገጭ እንዲቀጥልም አስችሏል፡፡ ወደ ሀገሪቱ የሚመጣዉ የዉጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና የልማት አጋሮች ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በዚህ ወር ብቻ የእንግሊዝ፤ የሲንጋፖርና የማሊዥያ ባለሀብቶች የልዑካን ቡድኖች በሀገሪቱ ዉስጥ መዋዕለ ንዋያቸዉን ለማፍሰስ የሚያስችላቸዉን ዉይይት ከመንግስትና ከአቻዎቻቸዉ ጋር አድርገዋል፡፡ የቻይናዉ ኤግዚም ባንክ ለስኳር ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብድር ሲሰጥ የአለም ባንክ በበኩሉ ለመሰረታዊ አገልግሎቶችና ለመንገድ ልማት የ1.15 ቢሊዮን ዶላር ከወለድ ነፃ ብድር ሰጥቷል፡፡ ይህ ገንዘብ የተፈቀደዉ ሟርተኞቹ ብድር እንዳይሰጥ ያለ የሌለ ሀይላቸዉን ባስተባበሩበት ወቅት መሆኑን አስታዉሱ፡፡ 
በ765 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ወደ ትግበራ የገባዉ የጦሳ ብረታብረት ማቅለጫ ፋብሪካና የመከላከያ እንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ያስመረቃቸዉ ሶስት የኤሌክትሪክ ኬብል ማምረቻና የከባድ መኪና መገጣጠሚያ ኢንዱስትሪዎች በዚህ ረገድ የሚጠቀሱ የወሩ ክስተቶች ናቸዉ፡፡
እናም ኢትዮጵያ ዛሬም እንደትናንቷ በህዝቦቿ፤ በመንግስትና በመሪ ድርጅቷ ቅንጅታዊ ሀይል ወደፊት መጓዟን ቀጥላለች፡፡ የጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊንና የመለስን ራዕይ በመተግበር ህልማቸዉን እንደሚያሳኩ በመተማመን ሶስቱ ሀይሎች ተቀናጅተዉ ጉዟቸዉን ቀጥለዋል፡፡ አረቦች እንደሚሉት ግመሎች ይጓዛሉ፤ ዉሾቹም መጮሃቸዉን ቀጥለዋል፡፡
Post a Comment