Saturday, September 15, 2012

ማንን እንመን?


የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት የብዙዎችን እልህ አስጨርሷል፡፡ ያለመናገር እልህ፤ ያለመፃፍ እልህ፤ ያለማንበብ እልህ፤ ወዘተ…:: ለወትሮዉ ዝምታን የሚመርጡ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋሞች አሁን ከዚህ በላይ ላለመታገስ የወሰኑ ይመስላሉ፡፡ “ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በፓርላማዉ አዳራሽ ወይም በአፍሪካ ህብረት አለዛም በድርጅታቸዉ ጉባዔ ተገኝተዉ እንዲህ አሉ፤ ለዚህ ጥያቄ ማብራሪያ ሠጡ ወይም ደግሞ የእገሌ ሀገር ልዑካንን በፅህፈት ቤታቸዉ ተቀብለዉ አነጋገሩ” ከሚል ዘገባ የማይዘለዉ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሞት ተከትሎ በግለሰባዊ ባህሪያቸዉ ላይ ሳይቀር ለቁጥር የሚያታክቱ ዜናዎችንና ፕሮግራሞችን ለአየር አብቅቷል፡፡
 
ራሱ ድርጅታቸዉ ኢሕአዴግም ቢሆን 'በግለሰቦች ስብዕና ላይ ሳይሆን በድርጅት ህልዉና ላይ ነዉ' የማተኩረዉ የሚለዉን የቆየ ዘይቤዉን ለግዜዉም ቢሆን ችላ ያለዉ ይመስላል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስብዕና ከማንኛዉም የድርጅቱ አባልም ሆነ አመራር የላቀ እንደነበር ፓርቲዉ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ የቀድሞዉ ም/ል ጠ/ሚ/ር አቶ አዲሱ ለገሰ በቀብር ስነስርዓቱ ላይ ያነበቡት ባለ 25 ገፅ ‘ምስለ መለስ የማንነቱ ገፅታ’ ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነዉ፡፡
 
በተለይ ሁለቱ ተቋሞች/ኢሬቴድ እና ኢሕአዴግ/ በትብብር የሰሯቸዉ ፕሮግራሞች አቶ መለስ ምን ያህል ለህዝባቸዉ በተለይም ለአርሶአደሩ ቅርብ እንደነበሩ፤ ምን ያህል እረፍት የለሽና ባለራዕይ እንደነበሩና ለሀገራቸዉና ለህዝባቸዉ ፍላጎት ሲሉ ዉድ ሂወታቸዉን ስለመክፈላቸዉ የሚያወሱ ናቸዉ፡፡ ታዲያ እነዚህን ከምናዉቃቸዉ በላይ የሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩን በጎ ስራዎች የተረዱ ዜጎች “ምነዋ እስከዛሬ?” የሚል ጥያቄ ለተቋሞቹ ማንሳታቸዉ አልቀረም፡፡
 
በጋዜጦችና በማህበራዊ ድረ-ገፆችም መለስን የተመለከቱ ፖስቶች ቁጥር በብዙ እጥፍ ጨምሯል፡፡ለወትሮዉ በዋዛ ፈዛዛ ግዜያቸዉን የሚያሳልፉ የድረ-ገፅ ተጠቃሚዎች አሁን መረጃዎችን እያጣቀሱ ፅፈዋል፤ ለተፃፉትም ሰፊ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ያኔ ያኔ በመለስና በመንግስታቸዉ ላይ የሚሰነዘር ነቀፋ የበላይነቱን የያዘበት ፌስቡክ አሁን አሁን አዲሱን ማዕበል እያስተናገደ ነዉ፡፡ 
 
ይህን ስል ታዲያ በጠቅላይ ሚኒስትሩና ይመሩት በነበረዉ መንግስት ላይ የሚሰነዘሩ ትችቶች ቆመዋል ማለቴ አይደለም፡፡ ይልቁንም በዚህኛዉም ወገን ቢሆን እልህ መያያዙ አልቀረም፡፡ በዚህኛዉ ወገን የሚነሱት ያዉ የለመድናቸዉና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲያጣጥሏቸዉ የነበሩ የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ናቸዉ፡፡ በነዚህ ጉዳዮች ላይ በተለያዩ ግዜያት የመከርንባቸዉና የዘከርናቸዉ ስለሆኑና እንደምገምተዉ የየራሳችንን አቋም የያዝንባቸዉ በመሆኑ በዚህ ፅሁፌ ጠለቅ ብዬ ላያቸዉ አልፈለኩም፡፡ ይልቁንም የጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ሂወት ማለፉን ተከትሎ የግንቦት 7 ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ለአዉራምባ ታይምስ ድረ-ገፅ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ ማተኮር ፈለግሁ፡፡ ዶ/ር ብርሃኑ በቅርብ የሚያዉቋቸዉን ወይም በቅርብ የሚያዉቋቸዉ የመሰላቸዉን የአቶ መለስ ዜናዊን ስብዕናና አቅም ተችተዋል፡፡
 
ዶ/ር ብርሃኑ በአስተያየታቸዉ “መለስ ይህን ስልጣን ባገኘበት ግዜ ያለዉን የአለም ሁኔታ በቅጡ ባለመገንዘብ ኢትዮጵያን ልክ በ60ዎቹና በ70ዎቹ የነበሩ የአፍሪካ መሪዎች ያስተዳድሩ በነበረበት ዘይቤ ትንሽ ብልጥነት ጨምሮበት ለመግዛት የሞከረ ከግዜዉ ጋር መሄድ ያቃተዉ መሪ አድርጌ ነዉ የማየዉ፡፡ … ታሪክ ሁልግዜ መለስን ያየዋል ብየ የማስበዉ ግዜዉን መሆን ያልቻለ ግዜዉ የፈጠረዉን አመለካከት መቀበል አቅቶት ፍፁም ኋላቀር የሆነ የአምባገነንነትን ግርሻ ተሸክሞ ያንን የአስተሳሰብ ዘመናዊነት ሳይቀበል የሞተ አሳዛኝ መሪ አድርጌ ነዉ የማየዉ” ብለዋል፡፡
 
እንደምናዉቀዉ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በድህረ ምርጫ 97 በተነሳዉ ግጭት ጥፋተኛ ተብለዉ የእድሜ ልክ እስራት ከተፈረደባቸዉ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ይቅርታ ጠይቀዉ ከእስር የተፈቱ፤ ኋላም በሽብርተኝነት የተፈረጀዉን ግንቦት 7ን ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድ በመምራታቸዉ በሌሉበት የሞት ዉሳኔ የተላለፈባቸዉ ናቸዉ፡፡ ስለዚህ እኝህ ሰዉ እንደሰዉ ህሊና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ለመጥላት የሚያስችል ከበቂ በላይ ምክንያት አላቸዉ፡፡ ስለሆነም የሳቸዉን አስተያየት የሀገራችን እጣ ፈንታ የሆነዉ የጥላቻ ፖለቲካ አንድ አካል በማድረግ ገሸሽ ልናደርገዉ እንችላለን፡፡ግን ይህም በራሱ ጥላቻና አጉል ፍረጃ እንዳይሆን እሰጋለሁ፡፡ ማን ያዉቃል ከሳቸዉ የበለጠ ‘ዉስጥ አዋቂ’ መጥቶም የዶ/ር ብርሃኑን ትክክለኛነት ሊያስረዳኝ ይችላል፡፡
 
ወደተነሳሁበት ነጥብ ልመለስና እኔ ዶ/ር ብርሃኑንና መሰሎቻቸዉን ልሞግታቸዉ የፈለግሁት በእኔና በመሰሎቼ ያልበሰለ እዉቀት ሳይሆን ልክ እንደርሳቸዉ ድርጅትና ሀገር በሚመሩ ሰዎች ምስክርነት ነዉ፡፡ ለዚህም ስል በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀብር ስነስርዓት ላይ ተገኝተዉ ንግግር ካደረጉት ዉስጥ የተወሰኑትን ወስጃለሁ፡፡ በርግጥ እነ ፕሬዝዳንት ሰርሊፍ ጆንሰን፤ ዶ/ር ጃን ፒንግ፤ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ፤ ጠ/ሚ/ር ሁጂን ታኦ፤ ጠ/ሚ/ር ዴቪድ ካሜሮን፤ ጎርደን ብራዉን፤ ቢል ክሊንተንና ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቃት ብዙ ተናግረዋል፡፡ እነሱን ትቸ እነዚህን የመረጥኩት በቀብሩ ወቅት በነበረዉ የቀጥታ ስርጭት በአይናችን በብረቱ ሲናገሩ ስላየናቸዉና የማንጠረጥረዉ ጆሯችን ስለሰማቸዉ ነዉ፡፡
 
በርግጥ የግንቦት 7 ልሳን የሆነዉ ኢሳት ቴሌቪዝን መሪዎቹ በህወሃት ወታደሮች አፈሙዝ ተገደዉ ምስክርነታቸዉን እንደሰጡ ተናግሯል፡፡ /ይህን ዜና ብዙዎች በማህበራዊ ድረ-ገፆች እየተቀባበሉ ሲያነቡት ተመልክቸ እኔም በፌስቡክ አድራሻዬ ላይ ሼር ስላደረግሁት ማየት ይቻላል፡፡/ ይሁንና ይህ ዉሃ የማይቋጥር ተራ ፌዝ በመሆኑ የዋሆችን ከማወናበድ በዘለለ ለመከራከሪያ ነጥብነት ይቀርባል ብየ ስለማልገምት እንዳላየ አልፌዋለሁ፡፡
 
እዚህ ላይ ከላይ የቀረበዉን የዶ/ር ብርሃኑ ነጋን አስተያየት ከሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ ጠ/ሚ/ር መለስ በዘመን እይታና የታሪክ ትዉስታቸዉ፡፡
 
                ጠ/ሚ/ር መለስና የመሩበት ዘመን
ዶ/ር ብርሃኑ አቶ መለስ አሁን ያለዉን አለማቀፋዊ ሁኔታ በአግባቡ ባለመረዳታቸዉ ሀገሪቱን በግማሽ ምዕተ አመት ወደ ኋላ በቀረ ዘይቤ እንደመሯት ሲናገሩ እነኝህ የየራሳቸዉን ሃገርና ተቋም በዘመኑ እየመሩ ያሉ ሰዎች ደግሞ መለስ ግዜ ያለፈባቸዉ መሪ ሳይሆኑ የአሁኗና የወደፊቷ አፍሪካ መሪ ናቸዉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
 
የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሶቮኒ “የአፍሪካ ችግር የተፈጥሮ ሀብት ሆኖ አያዉቅም፡፡ ችግሯ ራዕይ ያለዉ መሪ የሌላት መሆኗ ነዉ” ብለዋል፡፡ መለስ ዜናዊን “ባለራዕዩ መሪ” ያሉት ሙሶቨኒ መለስን የዛሬና የወደፊቷ ኢትዮጵያና አፍሪካ መሪ ሲሉ ነዉ የገለፁት፡፡ የአፍሪካን ክፍተት የሞላ መሪ ሲሉም አሞግሰዋል፡፡ የሩዋንዳ መሪ ፖል ካጋሜም ይህንኑ በማጠናከር “አሁን መለስ በመሞቱ የተፈጠረዉ ክፍተት ስፋቱ ይሰማናል” ብለዋል፡፡
 
በቀብር ስነስርዓቱ ላይ የመናገር እድሉን ያገኙ መሪዎች በሙሉ በአንድ ድምፅ ጠ/ሚ/ር መለስ ባለራዕይ መሪ እንደሆኑ መስክረዋል፡፡ የሳቸዉ ራዕይ ለሚመሩት ሀገርና ዜጋ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካና ለመላዉ አለም ድሆች እንደሆነም አረጋግጠዋል፡፡
 
ታቦ እምቤኪ /የቀድሞዉ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት/ መለስ አሁን ያለዉን አለምአቀፍ የዲፕሎማሲ ጨዋታ እንዴት መጫወት እንደሚገባ የተረዱ መሪ መሆናቸዉን በማያሻሙ አረፍተነገሮች አብራርተዋል፡፡ እሳቸዉ “መለስ ሁልግዜ የሚማር፤ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካንም ጭምር ያጋጠሟትን ተግዳሮቶች በሚገባ የሚረዳና አሁን በምንኖርበትና በምንሰራበት አለምአቀፋዊ ሁኔታ ዉስጥ እንዴት መለወጥ እንደሚቻል ጠንቅቆ የሚያዉቅ ነዉ፡፡” ብለዋል፡፡
 
እንደመሪዎቹ የጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ሳይንሳዊ እዉቀትም ጥያቄ ዉስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ እንዴት መምራት፤ ሀሳብ ማፍለቅና መተግበር እንደሚችሉ የሚያዉቁ መሪ ብለዋቸዋል፡፡ የናይጀሪያ ፕሬዝዳንት ጉድ ላክ ጆናታን መለስን እጅግ የተለየ ተሰጥዖ ያለዉ መሪ /extraordinarily dynamic/ ሲሉ ገልፀዋቸዋል፡፡ ታቦ እምቤኪ የመለስን አዋቂነት የገለፁበት ንግግርም የሚያስደምም ነበር፡፡ “የመለስ ጭንቅላት በተከታታይ ትምህርት የበለፀገ የልዩ ተሰጥዖ ባለቤት የሆነ አዕምሮ የያዘ ነዉ” ብለዋል፡፡ አሁን ደቡብ አፍሪካን የሚመሩት ጃኮብ ዙማም የኢትዮጰያ ታሪክ በጠ/ሚ/ር መለስ መታደሱን ባመለከቱበት ንግግራቸዉ “መለስ እንደ ቡድን 7 እና ቡድን 20 ባሉ የሀያላን ሀገሮች ስብስብ እንዲሳተፍ በተደጋጋሚ ይጋበዝ የነበረዉ የታላቅ ሀገር መሪ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን የትልቅ አላማ አመንጭ በመሆኑም ጭምር ነዉ” ብለዋል፡፡ 
 
ሁሉም መሪዎች በየራሳቸዉ አገላለፅ ለጠ/ሚ/ሩ ብሩህ አዕምሮ ያላቸዉን አድናቆት ይግለፁ እንጅ ለእኔ እንደ ሱዛን ራይስ ንግግር የመሰጠኝ የለም፡፡ ምንአልባትም ሴትየዋ የኒዎሊበራሊዝም ዋና አቀንቃኝ በመሆናቸዉ ይሁን ወይም የታላቋ አሜሪካ ተወካይ ስለሆኑ ባልተረዳኝ ስሜት ንግግራቸዉ የተለየ ስሜት ፈጥሮብኛል፡፡ እኝህ በልበሙሉነታቸዉና በንግግር አዋቂነታቸዉ በተባበሩት መንግስታት የስብሰባ አዳራሽ የአለም መሪዎችን አቋም ሲፈታተኑ የምናዉቃቸዉ ሴት ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊን/የኢትዮጵያሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትን ትርጓሜ ልዋስና/ የመጠቀ አለምአቀፍ እዉቀት ያለዉ አዕምሮ ባለቤት/world class mind/ ሲሉ ገልፀዋቸዋል፡፡
 
        የጠቅላይ ሚኒስትሩ የታሪክ ትዉስታ
ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ታሪክ መለስ ዜናዊን እንዴት ብሎ እንደሚዘክራቸዉ አስተያየት ለመስጠት ድፍረት አላነሳቸዉም፡፡ ጠ/ሚ/ሩ ለታሪክ ጥሎት ያለፈዉ በዙሪያዉና በአለምአቀፍ ደረጃ እየተፈፀመ ያለዉን የማይረዳ የኋላቀር መሪን ትዝታ ነዉ ሲሉ ነግረዉናል፡፡ ይህ በመሆኑም ለሟቹ ጠ/ሚ/ር ሀዘኔታ /sympathy/ እንደተሰማቸዉ አክለዋል፡፡
 
ጉድ ላክ ጆናታን ግን “ያለዉን እምቅ እዉቀት፤ የንግግር ችሎታና ራዕይ ሀገሩን ለመቀየር የተጠቀመ መሪ አድርጎ ታሪክ መለስን ይዘክረዋል” ሲሉ የተባበሩት መንግስታት ተወካይ ጀፍሪ ፌልትማን በበኩላቸዉ “መለስ የተለየ የአመራር ክህሎቱን በመጠቀም የአፍሪካን ድምፅ በአለም መድረክ ያሰማ መሪ ተደርጎ በታሪክ ይወሳል” ብለዋል፡፡
 
እንግዲህ ከላይ የተጠቀሱት መሪዎች ንግግር በሙሉ የዶ/ር ብርሃኑን አስተያየት የሚቃረኑ ናቸዉ፡፡ መቸም ቀና ብሎ ሊያያቸዉ በማይችለዉ አስከሬን ፊት የቆሙት እነዚህ መሪዎች መለስ ዜናዊ በዘመኑ የአመራርነት ጥበብ የተካኑ መጪዉንም መተንበይና መተንተን የሚችሉ እንደሆኑ መስክረዋል፡፡ የምስክርነት ቃላቸዉ ደግሞ ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር ሲነፃፀር ሀራምባና ቆቦ የሚሉት አይነት ነዉ፡፡ ከምንም በላይ ግን እኛ እዚሁ ሀገራችን የምንኖር ኢትዮጵያዉያን በየቀኑ የሚፈፀመዉን እናያለን እንሰማለን፡፡ ታዲያ አንዱ እዉነታ በሁለት መነፅር የሚታይበት ምክንያት ምን ይሆን? እኛስ ማንን አምነን እንቀበል?

Post a Comment