Thursday, September 27, 2012

ወዳጄ ሆይ፤ ካላገባህስ ቻይናዊት አግባ፡

Wendi with her aged billionaire husband-Rupert Murdoch.


                  ወዳጄ ሆይ፤ ካላገባህስ ቻይናዊት አግባ፡፡
በታላቋ ብሪታኒያ የመገናኛ ብዙሃን ታሪክ ትልቁ ቅሌት ተብሎለታል፡፡ የለንደን ፖሊስን፤ የሃገሪቱን ከፍተኛ ባለስልጣናትንና ኒዉስ ኦፍ ወርልድ ጋዜጣን ያስተሳሰረው የስልክ ጠለፋ ወንጀል፡፡ በብሪታኒያ  4 በላይ በሚሆኑ ግለሰቦች ላይ እንደተፈጸመ በሚገመተው የድምጽ መልዕክት ጠለፋ ተጠያቂ የሆነው የኒዉስ ኮርፖሬሽን የፍርድ ሂደት ገና ባይጠናቀቅም የቅሌቱ ባለድርሻዎች ግን የእጃቸዉን አግኘተዋል፡፡


ኒዉስ ኦፍ ወርልድ መታተም በጀመረ 168 አመቱ ተዘግቷል፡፡ 2003 እስከ 2007 የጋዜጣዉ አርታዒ የነበረዉን አንዲ ኮልሰንን ለፓርቲያቸዉ የኮሚዩኒኬሽን ሃላፊነት የሾሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮንም በሹመቱ እንደተጸጸቱ ገልጸዉ ህዝባቸዉን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ የጋዜጣዉን ወንጀል የመመርመር ሂደት በአግባቡ አልመሩም በሚል የተወቀሱት የለንደን ፖሊስ አዛዥ ፖል ስቴፈንሰን ስልጣናቸዉን በፈቃዳቸዉ ለቀዋል፡፡ ምክትላቸዉም እንዲሁ፡፡


በብሪታኒያ የኒዉስ ኦፍ ወርልድ፤ ሰንና ታይም በዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ የኒዮርክ ፖስት እንዲሁም በአዉስትራሊያ  ሔራልድና ዊክሊ ታይምስ የመሳሰሉ ግዙፍ ጋዜጦችን ያቀፈዉ የኒዉስ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚና ባለቤት በሆኑት ሩፐርት መርዶክ ስም የመርዶክ ቅሌት የሚል ስያሜ ያገኘዉ ወንጀል ለበርካታ ቀናት የአለምን አይንና ጆሮ ስቦ ቆይቷል፡፡ አሁንም የክስ መዝገቡ በተገለጠ ቁጥር አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል፡፡


ድርጊቱ በተደረሰበት ሰሞን መርዶክ በልጁ ጄምስ መርዶክ በባለቤቱና በቅርብ ሰዎቹ ታጅቦ ቅሌቱን እንዲመረምር በተሰየመዉ የፓርላማ ኮሚቴ ፊት በመቅረብ ሲጠየቅና ሲመልስ 3 ሰዓት በላይ ቆይቷል፡፡ ቢቢሲ የቀጥታ ሽፋን ያገኘዉ ይህ ችሎት ታዲያ አስገራሚ ክስተት አስተናግዶ ነበር፡፡ ስሜቱን መቆጣጠር ያልቻለ ግለሰብ በእጁ ላይ ባገኘዉ የፊት ክሬም መርዶክን ሊመታ ሲንደረደር የጸጥታ አካላት እንኳን አልጠረጠሩትም ነበር፡፡ ይልቁንም ለዌንዲ ዴንግ ባሏን በመታደግ ፍቅሯን የምትገልጽበት አጋጣሚ ፈጠረላት፡፡


ዌንዲ ዴንግ መርዶክ በፈረንጆቹ 1968 በቻይና የጠረፍ ግዛት ነዉ የተወለደችዉ፡፡ ዌንዲ የተወለደችበት ወቅት ቻይናዉያን በፈታኝ ችግር ዉስጥ ያሉበት ነበር፡፡ አሁን ሀገሪቱን የሚመራዉ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ታማኝ አባል የሆኑት ወላጆቿ የወቅቱን የፓርቲያቸዉን መሪ ሀሳብ ተከትለዉ ዌንጂ አሏት፡፡የባህል አብዮት ማለት ነዉ፡፡ኋላ ኋላ አብዮቱ መልክ መያዝ ሲጀምር ዌንዲ ብለዉ ጠሯት፤ የባህል መነቃቃት ለማለት፡፡ ዝቅተኛ ገቢ ካለዉ ቤተሰብ የተወለደችዉ ዌንዲ በእድሜዉ ከእጥፍ በላይ የሚበልጣትን ሩፐርት መርዶክን አግብታ አሁን ቢሊየነር ሆናለች፡፡ ይህች ሴት ታዲያ አሁን በታላቁ ቅሌት ዉስጥ ታላቅነቷን ያሳየች ሴት እንደሆነች አለም ተረድቷታል፡፡ በዚህ አጋጣሚም ቻይናዉያን ስለሷ የነበራቸዉን የተዛባ አመለካከት በመልካም ተግባሯ መቀየር ችላለች፡፡


ቻይናዉያን ኩሩ ዜጎች ናቸዉ፡፡ ለኩሩ ባህላቸዉ ፈተና የሆነዉን ድህነትና ኋላቀርነት ለማስወገድ በመሪያቸዉ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ዙሪያ ተደራጅተዉ ሌት ከቀን ሰርተዋል፡፡ በዚህም በአለም በግዙፍነቱ ሁለተኛዉን ኢኮኖሚ ገንብተዋል፡፡ ቻይና በህዝቦቿና በመሪዎቿ ጥረት አሁን በወጭ ንግድ በአለም አንደኛ ስትሆን በገቢ ንግድም ሁለተኛ ነች፡፡ በዉጭ ምንዛሬ ክምችት መጠንም የሚስተካከላት ሀገር የለም፡፡ ረጅሙን የፈጣን ባቡር ሀዲድ በመዘርጋትና ከታዳሽ ምንጮች በየአመቱ ከፍተኛ ሀይል በማመንጨትም ቀዳሚ ነች፡፡ በጦር ሰራዊት/active troops/ ቁጥርም እንዲሁ፡፡


ቻይናዉያን ታዲያ ዌንዲን የሚገነዘቧት ለገንዘብ ስትል ራሷን አሳልፋ የሰጠች ሴት አድርገዉ ነበር፡፡ አንዳንድ ፀሃፊዎች እንደሚሉት በሃገሯ ዜጎች ዘንድ ስሟ እንደ ቅናት፤ጥላቻና ምቀኝነት ካሉ ቃላት ተርታ የሚሰለፍ ነበር፡፡ በዚህ አለም በቴሌቪዥን መስኮት በተከታተለዉ ትዕይንት በፈፀመችዉ አኩሪ ተግባር ግን በርግጥም መርዶክን ከልብ እንደምትወደዉ በተግባር አሳይታለች፡፡


በፓርላማ ኮሚቴዉ የሚቀርብበት የጥያቄ ዶፍ ያደነዘዘዉ ሩፐርት መርዶክ ሊመታዉ የተንደረደረዉን ጆናታን ሜይ ቦዉለስን ተመልክቶ ራሱን የሚከላከልበት አቅምም ሆነ ዝግጁነት አልነበረዉም፡፡ ከጎኑ የተቀመጡት ልጁ ጄምስም ሆነ አጋሮቹ ከጩኸት ባለፈ ሊታደጉት አልቻሉም፡፡ ይልቁንም ከኋለኛዉ ረድፍ በጽሞና ተቀምጣ የነበረችዉ ዌንዲ ከአይን ጥቅሻ ፈጥና በመነሳት የግለሰቡን ክሬም አየር ላይ አስቀርታዋለች፡፡ በልጅነቷ በመረብ ኳስ ጨዋታ በጠነከረዉ እጇ ጭንቅላቱን በመምታት አጥቂዉን ተከላካይ አድርጋዋለች፡፡ ዘግይተዉ የደረሱት ፖሊሶች ግለሰቡን ከያዙት በኋላም ያልበረደዉን ንዴቷን በኩርኩም እንደተወጣችበት ትዕይንቱን በአካል የተከታተሉ ጋዜጠኞች ዘግበዋል፡፡ ዌንዲ በዚህ ብቻ ሳትወሰን ለባሏ ያላትን ፍቅር በልብሱ ላይ ያረፉ የክሬም ንጣቦችን በእጆቿ በመጥረግና አቅፋ በማጽናናት ገልፃለታለች፡፡


ለአመታት በተሳሳተ እይታ የሚመለከቷት ቻይናዉያን ዌንዲ በሀገሯ በተለይ በኢንተርኔት ዘርፍ በምታፈሰዉ መዋዕለ ንዋይ የተነሳና በእናቶች ጤና ላይ በምታደርገዉ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ ለርሷ ያላቸዉ አሉታዊ አመለካከት መሸርሸር ጀምሮ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በርሷ መኩራት ጀምረዋል፡፡ ዌቦ በተሰኘዉ ማህበራዊ ድህረ ገጽ ላይ ሉላን የተባለ ቻይናዊ ካገባህስ ቻይናዊት አግባ፤ በመከራህ ግዜ ከፊትህ ትቆማለችና ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡


በነገራችን ላይ ዌንዲ ምንም እንኳን ከድሀ ቤተሰብ ብትወለድም በትምህርቷ በመጠንከር ሁለተኛ ድግሪዋን የያዘች፤ የባለቤቷን ያልተገባ ባህሪ በማረም የደስታዉ ምንጭ የሆነችና በምትመራቸዉ የቢዝነስ ተቋሞችም ዉጤታማ መሪ እንደሆነች ብዙዎች መስክረዉላታል፡፡


የሀገሬ ላጤ ሆይ እኔ እንኳን ሀሳቤ ቤጅንግ ሄደህ ዉሃ አጣጭህን ፈልግ ለማለት ወይንም ኢትዮጵያን ሁለተኛ ሀገራቸዉ አድርገዉ ከሚኖሩ ቻይናዉያን አንዷን ጥበስ ልልህ አይደለም፡፡ ግን ማግባትህ ካልቀረ ቀሪ ሂወትህን አብራህ የምትገፋዉ ሴት ዌንዲን የምትመስል ካልሆነች ባታገባስ ምን አባቱ ልልህ ነዉ፡፡ በርግጥ ከያንዳንዱ ስኬታማ ወንድ ጀርባ ጠንካራ ሴት አለች ይባላል፡፡ ይህም ስኬታማ ለመሆን ግራ ጎንን መፈለግ ግድ መሆኑን ያመለክታል፡፡ታዲያ የስኬትህ ምንጭ የምትሆነዉን የትዳር አጋርህን ስትመርጥ እንደ ዌንዲ በአስተዳደጓ፤ በስራዋና በትዳሯ በመልካም ምግባር የታነፀች መሆን እንዳለባት እንዳትዘነጋ ብዬ ነዉ፡፡
 
Post a Comment