Monday, December 31, 2012

አፍ እላፊ

ከአዲስ አበባ በድቅድቅ ጨለማ ተነስተን ወደ ጅግጅጋ በቲዮታ ፒክአፕ እየከነፍን ነዉ፡፡ ሶስት የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ሰራተኞችና እኔ በማግስቱ በጅግጅጋ ከተማ ለሚካሄደዉ የልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎች የመልካም አስተዳደር ንቅናቄ መድረክ ለመድረስ ተጣድፈናል፡፡

በለሊት እየተላለፈ ያለዉ ኤፍ ኤም 97.1 ሬዲዮ ዝግጅት የጉዟችን ማጀቢያ ነበር፡፡ በእንግድነት የተጋበዙት አንድ ታዋቂ አርቲስት በቀደመዉ ዘመን ለኢትዮጵያ የጥበብ ዘርፍ እድገት ከፍተኛ አስተዋፆ ስላበረከተዉ ኦስትሪታዊ አርቲስት ፍራንሴስ ዞልቤከር ምስክርነታቸዉን እየሰጡ ነዉ፡፡ የኛዉ አርቲስት ታዲያ ዞልቤከርን የተዋንያንና የድምፃዉያን ወርሃዊ ክፍያ ማነስ ያበሳጫዉ እንደነበር ከነገሩን በኋላ ይህንኑ ተጨባጭ ለማድረግ ሲሉ ንፅፅር ያቀርባሉ፡፡ “ኢትዮጵያ ዉስጥ ለአንድ ሹፌር የሚከፈል ደሞዝ እንኳን ለአንድ አክተር ወይም ሙዚቀኛ አይከፈልም፡፡” ሲሉ ትችታቸዉን ሰነዘሩ፡፡

Saturday, December 22, 2012

ፆምና ፀሎት--ለእቅዱ ስኬትየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከታህሳስ 15 - ጥር 15/2005 ባሉት 30 ቀናት ዉስጥ እቀርፋቸዋለሁ ብሎ ባቀዳቸዉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ ከከተማዋ አመራሮችና ፈፃሚዎች ጋር ለሁለት ቀናት ዉይይት አድርጓል፡፡ ዉይይቱ ዉጥረት የነገሰበት ነበር፡፡

በአንድ ጫፍ ለዘመናት የተቆለሉ የአዲስ አበባ ችግሮችን እንዴት በወር ዉስጥ መፍታት ይቻላል?” የሚሉና በሌላዉ ጫፍ ስናንከባልላቸዉ የቆዩ ችግሮች አሁን ተራራ አክለዉ የስርዓታችን አደጋ ሆነዋልና የተፈለገዉን መስዋዕት ከፍለን በወሩ ዉስጥ መፍታት አለብን በሚሉ ጫፎች ላይ የተወጠረዉ የጭንቅ ገመድ ተሰብሳቢዎቹን ጠፍሮ ይዟቸዋል፡፡

Monday, December 10, 2012

Bosses are Ugly

Today a guest came to our home. She is my sister in law. My wife and I left our bed and slept on a mattress laid on the floor. But, I could not sleep. Thinking of the relationship bosses and employees had, two hours passed. It is midnight. I could not resist; and begun to write what is lurking in my mind. Unfortunately there was no electricity and I used candlelight.

As for the meaning, I don’t care whether you said it 'boss' or 'leader'. I know some argue a boss is different from a leader. They claim a boss creates fear, a leader confidence; a boss fixes blame, a leader corrects mistakes; a boss knows all, a leader asks questions; a boss makes work drudgery, a leader makes it interesting. However for my purpose, I make use of the simple dictionary meaning of a boss as a person who is in charge of an employee or organization.

Wednesday, December 5, 2012

አዲስ ራዕይ

እዉነቱን ለመናገር የኢሕአዴግ የንድፈ ሃሳብ መፅሄት የሆነችዉ አዲስ ራዕይ መፅሄት ዋና አዘጋጅ ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ እንደነበር አላዉቅም ነበር፡፡ በርግጥ መለስ ዜናዊ በተለያዩ መድረኮች ከሚያራምዳቸዉ አቋሞች ጋር የሚመሳሰሉ ፅሁፎችን በመፅሄቷ ስመለከትና በይዘቷና በአቀራረቧ ካላት ብስለት አንጻር በመመዘን ‘ሰዉየዉ’ ፅፏት ይሆንን ብዬ መጠርጠሬ አልቀረም፡፡ ዋና አዘጋጇ መለስ መሆኑን ርግጠኛ መሆን የጀመርኩት ግን የዚህ አመት የመጀመሪያዋ ልዩ እትም የገበያ ማስታወቂያ/commercial ad/ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲነገር ነዉ፡፡ አሁን ደግሞ መፅሄቷ ገበያ ላይ ስትዉል አግኝቸ ሳነባት ይህንኑ በድጋሜ የሚያረጋግጡ በርካታ አረፍተ ነገሮችን በዉስጧ አግኝቻለሁ፡፡ እንዲያዉም የዚች እትም ማስታወሻነት ለቀድሞዉ ዋና አዘጋጇ ለመለስ ዜናዊ መሆኑን አዘጋጆቿ እንደወሰኑ ነግረዉናል- በመፅሄቷ ርዕሰ አንቀፅ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት በድርጅትም ሆነ በመንግስት የአመራነት ሚና ላይ በሚያሳርፈዉ ተፅዕኖ ዙሪያ ብዙ ተብሏል፡፡ ብዙ ተስፋ መቁረጦች፤ ብዙ ሟርቶችንና ብዙ መፅናናቶችን ሰምተናል፤ አንበናል፡፡ ኢሕአዴግም ታላቁን መሪ በግለሰብ ደረጃ መተካት እንደማይቻል በማመን ይመስላል ጅምር የልማት ስራዎችን በጋራ አመራር/collective leadership/ የማስቀጠል ስልትን ተከትሏል፡፡

Friday, November 30, 2012

እዉነትም ደረቅ ነኝ

እይይእንግዲህ ድርቅናህን ጀመርክ ይሉኛል ሰዎች ክርክር ስንጀምር፡፡ ደረቅ አይደለሁም፡፡ ግትር ነህ ብትሉኝ ይሻላል እላቸዋለሁ፡፡ አንዳንዶቹ በል በቃህ ካንተ ጋር መነታረክ ብለው ይተዉታል፡፡ አንዳንዶቹ ተከራክረው ያሸንፉኛል፤ እኔም የማሸንፋቸው አሉ፡፡ ታዲያ አንድም ቀን እንኳን ራሴን ደረቅ ነህ ብየው አላውቅም፤ ከዛን እለት በቀር፡፡
ያን እለት ያው እንደተለመደው ልጄን ቁርሷን አብልቼ፤ የሷ ትራፊ ላይ ትንሽ ጨምረን ባለቤቴና እኔ እየተጎራረስን ከበላን በኋላ ልጄን ግንባሯን፤ ሚስቴን ደግሞ ከንፈሯን ስሜ ለስራ ወጣሁ፡፡
የምኖረው ሳሪስ አቦ አካባቢ ነው፡፡ የምሄደው ደግሞ ብሔራዊ ቲያትር አጠገብ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት፡፡ ከመነሻዬ እስከ መድረሻዬ ያለውን መንገድ የምታዉቁ አዲስ አበቤዎች ገጠመኜ በአዕምሯችሁ እንደሚሳል ርግጠኛ ነኝ፡፡
ወደ ታክሲ ተራ አመራሁ፡፡ በአቦ ቤተክርስቲያን በር ሳልፍ ሁልግዜ እሳለማለሁ፡፡ በሰላም ያሳደርከኝ አምላኬ በሰላም አዉለኝ፤ ቤቴን ቤተሰቤን ጠብቅልኝ፤ ከመኪና አደጋ ሰዉረኝ ማለት ልማዴ ነዉ፡፡ እንደሁኔታው አንዳንድ ቀን የምጨምራቸው ጥያቄዎችም አሉኝ፡፡ ታዲያ አምላኬም ልመናዬን ሰምቶ እኔንና ቤተሰቤን በሰላም ሲያውል ነዉ የኖረው፡፡ አምላኬን ሰላም አውለኝ ስል ታዲያ ነገር ላለማርዘም ብዬ እንጅ በውስጡ ገንዘቤን ለብክነት አትዳርግብኝ፤ አለቆቼን ስለኔ በጎ አሳስባቸው፤ የሰው ፍቅር ስጠኝ የሚሉና ሌሎች ንዑስ ልመናዎቼንም አካትቼ ነዉ፡፡ ዛሬ ታዲያ ከንዑስ ልመናዎቼ አንዱ የተፈፀመልኝ አይመስልም፡፡ 
ታክሲ ተራ ደርሼ በሃይገር ተሳፈርኩ፡፡ ሳሪስ፤ አደይ አበባ፤ ዮሴፍ፤ ጎተራ፤ ላንቻ፤ ግሎባል፤ ሪቼ፤ መሻለኪያ፤ ስቴዲየም፡፡ ሰው ይወርዳል፤ ሰው ይወጣል፡፡ ለገሃር ስንደርስ ባለሁለት ብሮች መጨረሻ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ሶስት ብር ነው ሲል ረዳቱ ለፈለፈ፡፡ እኔም ያው የተለመደ የማይገፉበት ጭቅጭቅ ነዉ ብዬ ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡ 
ለገሃር ብወርድ መስሪያ ቤቴ ለመድረስ የሚቀረኝ 650ሜትር ግድም ነው፡፡ ብሔራዊ ጋር ከወረድኩ ግን በእግሬ የምጓዘው 200ሜትር ብቻ ይሆናል፡፡ ብሔራዊ ቲያትር ጋር ስወርድ ታዲያ ረዳቱ ሶስት ብር እንድከፍል ጠየቀኝ፡፡ እኔ ደግሞ ሁለት ብር ነው ብዬ ግትር አልኩ፡፡ ታሪፉን አዉቀዋለሁ፤ አታውቀውም ክርክር ገጠምን፡፡ ነገሩ ወደ ሹፌሩም ተዛመተና ዋጋው ሶስት ብር ነው፡፡ ግን እኔ ለአንድ ብር ብዬ ጭቅጭቅ ስለማልፈልግ ይጥቀምህ ይዘኸው ሂድ አለኝ፡፡ እኔ ታዲያ ከታሪፍ በላይ እያስከፈላችሁ ነው፡፡ ብሩን እከፍላለሁ ግን እከሳችኋለሁ ስል ድርቅናዬን ቀጠልኩ፡፡ ሹፌሩም እንዲያ ካልክስ ብሩን ክፈልና የፈለክበት ክሰስ፤ ከታሪፍ በላይ አላስከፈልንም አለ፡፡
ሶስት ብር የከፈለ ተሳፋሪ እስከ ፒያሳ ድረስ መሄድ ይችላል፡፡ እኔም ሶስት ብሬን ከፍዬ ትራፊክ ፖሊስ እስከማገኝበት ድረስ እንደገና መጓዜን ቀጠልኩ፡፡ ጥቁር አንበሳ ስንደርስ /ስራ ቦታዬንም አልፌ/ ትራፊክ ፖሊስ አገኘሁና መኪናው እንዲቆም ሆነ፡፡
በታሪፉ ሁለት ብር መሆን እንዴት ርግጠኛ ሆንኩ? 
እንግዲህ በዚህ መስመር ላለፉት ሶስት አመታት ገደማ በሃይገርና በታክሲ ተመላልሸበታለሁ፡፡ የደመወዝ ሰሞን በታክሲ፤ ከወሩ አጋማሽ ጀምሮ ደግሞ በሃይገር ማለቴ ነዉ፡፡ ታዲያ በፊት በፊት በሃይገር ስሳፈር ከቸኮልኩ የእግር መንገድ ለማስወገድ ስል ሶስት ብር ከፍዬ ብሔራዊ ቲያትር ጋር እወርዳለሁ፡፡ ስራ ካልረፈደብኝ ደግሞ በሁለት ብር ለገሃር ወርጄ ወክ እያደረግሁ መስሪያ ቤቴ እገባለሁ፡፡ በታሪፍ ላይ ያለኝ እውቀትም በዚሁ የተወሰነ ነበር፡፡
አንድ ቀን ከጎረቤት ጓደኛዬ ጋር ተሳፍረን ስንመጣ ለገሃር ጋር እንውረድ ስለው ብሔራዊ ድረስ በሁለት ብር መሔድ እየቻልን ለምን እዚህ እንወርዳለን?” ሲል ጠየቀኝ፡፡ ታሪፉ ነዋ አልኩት፡፡ እሱ ግን ታሪፉን በደንብ እንደሚያውቀውና ረዳቶቹ እያጭበረበሩ እንደሆነ ነገረኝ፡፡ ከዛ ቀን በኋላ አብረንም ሆነ በተናጠል ስንጓዝ እንዲሁ ማድረግ ጀመርን፤ ከሹፌሮችና ረዳቶች ጋር መዳረቅ፡፡ 
ረዳቶቹ ሶስት ብር ክፈሉ ማለታቸዉን አልተውም፡፡ አንዳንዶቹ አይ ተሳስታችኋል ሁለት ብር ነዉ ስንላቸዉ እየተነጫነጩም ቢሆን ከነቃህ ይቀራል በሚል እሳቤ ተቀብለውን ይከንፋሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ አልተሳሳትንም ለአንድ ብር ብለን ግን ግዜያችንን አናቃጥልም ብለው ሁለት ብራቸውን ተቀብለው ይበራሉ፡፡ በዚህ ሂደት ዉስጥ ታዲያ ለክስ የተዳረስንባቸው አጋጣሚዎችም ነበሩ፡፡ ጓደኛዬ ኋላ እንደነገረኝ ከሰባት የማያንሱ ሹፌሮችን ሶስት ብር ስለተቀበሉት አስቀጥቷቸዋል፡፡ እኔ እንኳን እንዲህ አይነት ነገር ሲያጋጥመኝ እዛው አደባባይ ጋር ለማይጠፉት ትራፊክ ፖሊሶች እናገራለሁ፡፡ እነሱም እኔ ያልኳቸዉን ብቻ ያዳምጡና ውሳኔ ያስተላልፋሉ፡፡
ረዳቶችና ሹፌሮች በትራፊክ ፖሊሶች ፊት እንደተከሳሽ የመደመጥ መብት የላቸውም፡፡ በዛ ዘመነኛ ዘይቤያቸዉ ገና መናገር ሲጀምሩ ዝም በል አንተ፤ እነሱን እንድታገለግል ነው እኮ ፈቃድ የተሰጠህ፡፡ ጋጠ ወጥ፤ ወዘተ…” ይባሉና አፋቸውን ይይዛሉ፡፡ ከዛ ከሳሽ ያለ ተከራካሪ ይረታና ወደ ውሳኔ ይኬዳል፡፡ በዚህ ግዜ ረዳትና ሹፌር ቁርጣቸውን አውቀው ከሳሻቸውን መለመን ይጀምራሉ፡፡ 
በተለመደው አሰራር ትራፊክ ፖሊሱ ከሳሹን ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ ልቅጣው? ወይስ ትምረዋለህ?” ብሎ ነው የሚጠይቀው፡፡ ከሳሹ ከጨከነ ይቀጣሉ/160ብር/፡፡ ከሳሹ ከራራ ይምራቸዋል፡፡ የቅጣት ማቅለያ ምናምን ብሎ ነገር የለም፡፡ እንዳልኳችሁ የኔ ጓደኛ ሰባት ያክል ሰዎችን አስቀጥቷል፡፡ እኔ እንኳን ይቅርታ እየተጠየቅሁ፤ 'ይቅር እያልኩ' ብዙ ግዜ ተመስግኜ ተለያይቻለሁ፡፡ እናም ልበ ሙሉ ያደረገኝ ይኸው የእዉቀቴ ዳራ ነው፡፡
ታዲያ የዛሬዉን ምን ልዩ አደረገዉ?
የዛሬው ልዩነቱ ሹፌሩም የኔ ቢጤ ደረቅ መሆኑ ነው፡፡ ሹፌሩ ታሪፉ ሶስት ብር እንደሆነ ቅንጣት ታክል አልጠራጠርም፡፡ የተፈለገበት ቦታ ሄጄ እከራከራለሁ እንጅ አትቀጣኝም አለው ለፖሊሱ፡፡ እኔም እንደሱ አውቃለሁ ባይ ነኝ፡፡ ፖሊሱ ደግሞ ታሪፉን አያውቀውም፡፡ በዚህ መሃል ተሳፋሪው ህዝብ እረፈደብን እያለ ይጮሃል፡፡ ፖሊሱ የአሽከርካሪውን መንጃ ፈቃድ ከተቀበለ በኋላ ተሳፋሪዎችን ፒያሳ አውርዶ እንዲመለስ ያዘዋል፡፡ ልብ በሉ እኔ ግን መታወቂያ እንኳን አልተጠየቅሁም፡፡ 
የድርቅና ጡዘት
ነገሩን እያሳጠርኩት ልሂድና ሹፌሩ፤ ረዳቱና እኔ በራሳቸው ሃይገር ተሳፍረን ጎማ ቁጠባ አካባቢ ወደሚገኘዉ ልደታ ፖሊስ ጣቢያ ትራፊክ /ቤት ሄድን፡፡ በጉዞዉ ላይ አንተ ማን ሆነህ ነዉ?” እያሉ ይደነፉብኛል፡፡ ቃልም ሳልተነፍስ ፖሊስ ጣቢያ ደረስንና መካሰስ ጀመርን፡፡ እዛ ያሉ የትራፊክ ፖሊሶች ብሔራዊ ቲያትር ድረስ ሶስት ብር ሳይሆን አይቀርም አሉኝ፡፡ እኔ ግን አይደለም ብዬ ሞገትኳቸዉ፡፡ ረጅም ግዜ በዘርፉ የሰራ ፖሊስም እኔ የማውቀዉ ሶስት ብር መሆኑን ነዉ ሲል መሰከረ፡፡ እኔ ግን እናንተ ታሪፉን ላታዉቁ ትችላላችሁ፤ ይህን ነገር በርግጠኝነት የሚያውቁትና ፍርድ መስጠት የሚችሉት የመንገድ ትራንስፖርት ሰራተኞች ናቸው ስል ተከራከርኩ፡፡ ስለሆነም መንገድ ትራንስፖርት እንድንሄድ ሃሳብ አቀረብኩ፡፡ በዚህ ሰዓት ግን በራሴ እውቀት ላይ ያለኝ እምነት መሸርሸር ጀምሮ ነበር፡፡ ሆኖም ወደፊት እንጅ ወደኋላ ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ሁሉ እንግልት በኋላ ተከሳሾቹም አይለቁኝማ፡፡
ሃይገሩን ፖሊስ ጣቢያ አቁመን መገናኛ ወደሚገኘው መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ሄድን፡፡ በመንገድ ላይ የታክሲ የምንከፍለዉ እየተረዳዳን ነበር /ለደርሶ መልስ ከሃያ ብር ያላነሰ ከፍለናል/፡፡ ጉዳዩን የሚመለከተዉ ሃላፊ ጋር ገብተን የሰጠን ምላሽ ግን እኔ መሳሳቴንና ትራፊክ ፖሊሶችንም ሳሳስት መኖሬን ያረጋገጠ ነበር፡፡ የስራ ሃላፊው መብቴን ለማስከበር ያደረግሁትን እንቅስቃሴ ሁሉ አድንቆ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ቢሆን መልካም እንደነበር መከረኝ፡፡
መከራ ሲመክር
ይህ ሁሉ ሂደት የተፈፀመው ከጠዋቱ 300 ሰዓት ጀምሮ እስከ 500 ሰዓት ድረስ ነበር፡፡ በዚህ ግዜ መኪናው ስራ ፈቶ ቆሟል፡፡ እኔም ከስራ ቀርቼ ማለት ነዉ፡፡ ደግነቱ ... የሰዓት ፊርማ የለውም፡፡ የታሰረውን መኪና ለማስፈታት ትራፊክ /ቤቱ ስንመለስ ሹፌሩ ለሁለት ሰዓት ያክል ያለስራ ቆሜያለሁና ካሳ ያስፈልገኛል ብሎ ከሰሰኝ፡፡ እዉነትነት አለው፡፡ ከብዙ ክርክርና ድርድር በኋላ ስራ ላስፈታሁበት ጊዜ 200ብር ተቀጥቸ ተለያየን፡፡ እንደውም እነሱ 400 ብር ካልሆነ ብለዉ በስንት ልመና ነዉ የተስማሙት፡፡
በርግጥ የተከራከርኩት ለአንድ ብር ብዬ አይደለም፡፡ ለመብቴ ነዉ፡፡ አሁንም ለመብቴ እቆማሁ፡፡ ይህ አጋጣሚ ግን ከመብት በፊት ግዴታን አዉቆ መፈፀም እንደሚገባ በደንብ አስተምሮኛል፡፡ ከሁሉ በላይ ግን ሳያጠፉ ለሚቀጡ ሹፌሮች መራራትን አስተምሮኛል፡፡ በርግጥ ተሳፋሪን የሚያስመርሩ፤ ያላግባብ የሚያስከፍሉና ስድብ የሚቃጣቸዉ ሹፌሮችና ረዳቶች አሉ፡፡ ግና በህግ ፊት ሁሉም ሰዉ እኩል ነውና እኩል የመደመጥ መብት ይገባቸዋል፡፡ ሲቀጡም ከጥርጣሬ ነፃ የሆነ ማስረጃ ሊቀርብባቸዉ ይገባል፡፡